Print this page
Saturday, 16 May 2020 11:21

ሀገሪቱ ለገጠሟት ፖለቲካዊና ህገ መንግስታዊ ችግሮች አስቸኳይ ድርድር እንዲካሄድ መድረክ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

በኮሮና ምክንያት የምርጫ ሂደት መቋረጥና ለሌላ ጊዜ መተላለፍ ህገ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል ያለው መድረክ፤ ሀገሪቱ የገጠማትን ቀውስ የገመገመበትንና የመውጫ መፍትሔ ያለውን የአስቸኳይ ድርድር መካሄድን ያመላከተበትን ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ በዚህ ባለ 17 ገጽ የግምገማና የመፍትሔ ሃሳብ ሰነዱ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከኮሮና በመለስ እየገጠሟት ያሉ ዋነኛ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ያላቸውን በዝርዝር አቅርቧል፡፡
ከእነዚህም ፖለቲካዊ ችግሮች መካከል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደተጠበቀው ገለልተኛ ሆኖ አለመገኘቱና የተቃዋሚዎችን ሃሳብና አስተያየት ተቀብሎ በሚያወጣቸው መመሪያዎችና አዋጆች ውስጥ ለማካተት ፈቃኛ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡ “የምርጫ ቦርድ እንደተጠበቀው ገለልተኛ ሆኖ አለመገኘቱ፣ ለወደፊቱ በምርጫ ሂደቱ ላይ የሚኖረንን ተስፋ አጨልሞታል” ብሏል መድረክ - በሰነዱ፡፡
አሁን ሀገሪቱ ለምትገኝበት የፖለቲካ ለውጥ መነሻ የሆነው የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግርም እየተባባሰ መሆኑን በተለይ የታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ጉበኛ፣ ዘራፊና ሰብአዊ መብት ረጋጭ መሆኑን መድረክ ጠቅሶ፤ ይህም ህብረተሰቡን በእጅጉ እያማረረ ነው ብሏል፡፡
“ፖለቲካን እንደ ወንጀል የመቁጠር ባህል  በለውጡ አመራር ይለወጣል የሚል ተስፋ ሰንቆ እንደነበር የጠቆመው መድረክ፤ ይህ አመለካከት ከመቀየር ይልቅ ይበልጥ ስር እየሰደደ ነው፤ ሰዎች ዛሬም በፖለቲካ አመለካከታቸው ለእስርና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ብሏል፡፡
በዚህ ወቅት ሀገሪቱ እየገጠሟት ካሉ ፈተናዎች ሙስናና የመሬት ዝርፊያ አንደኛው መሆኑን የጠቆመው መድረክ፤ ይህም የህዝብ ሃብትን ለህገወጥ ብዝበዛ ከመዳረጉ ባለፈ በማህበረሰቡ መካከል ኢ- ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን እየፈጠረ ነው ብሏል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተፈጠሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችንም መድረክ በዝርዝር አስረድቷል፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች ግን የላቀውና ዋነኛው አሁን ሃገሪቷ ያጋጠማት የፖለቲካና ህገመንግስት ቀውስ ነው ብሏል፡፡
መንግስት ይህን ቀውስ ለመፍታት ያቀረበው የህገመንግስት ትርጉም ሆነ ሌሎች ያቀረቡት ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ተገቢነት የሌለውና ህገመንግስቱን የሚጥስ ነው ያለው መድረክ፤ ሀገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ ብቸኛ መውጫው የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያካሂዱት አስቸኳይ የጋራ ድርድር ነው ብሏል፡፡
ድርድሩ በሚካሄድበት ወቅትም ባለድርሻዎች በጋራ የተግባቡባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ የሚያደርግ ተቋም ከወዲሁ እንዲቋቋም እንዲሁም ፓርቲዎች በድርድር ስምምነት ከደረሱ በኋላ ባሉት የ6 ወር ጊዜያት ውስጥ ምርጫ ማካሄድ የሚሉ ሃሳቦችንም መድረክ አቅርቧል፡፡



Read 941 times