Saturday, 16 May 2020 11:44

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ላይ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የእስካሁን አፈፃፀም የገመገመ ሪፖርት ያወጣው የህዝብ እንባ ጠባቂ፤ ተቋም፣ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት አሁንም ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የጠየቀ ሲሆን፤ በአዋጁ አፈፃፀም ላይ ግን ሰብአዊ መብቶች እየተጣሱ በመሆኑ እርማት ያስፈልገዋል ብሏል፡፡
ተቋሙ ከህብረተሰቡ የመጡለትን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ በሁሉም ክልሎች የባለሙያዎች ቅኝት አድርጐ ሪፖርቱን ማዘጋጀቱን ጠቁሞ፤ ኮሮናን ለመከላከል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን መገምገሙንና በዚህም በርካታ ግድፈቶች መስተዋላቸውን ተቋሙ አስታውቋል፡፡
ህብረተሰቡ በተለያየ አግባብ ስለ ወረርሽኙ ግንዛቤ እንዲያገኝ የተደረገበትን መንገድ ያደነቀው ሪፖርቱ፤ ምርመራዎችና የሰዎች የድንበር ዝውውር ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብሏል፡፡
ከተወሰዱት አበረታች እርምጃዎች በመለስ ግን ቀሪ የቤት ስራዎች አሉ ያለው የህዝብ እንባ ጠባቂ፤ ከዘረዘራቸው ጉዳዮች መካከልም ህብረተሰቡ የእለት ጉርሱን ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት በትራንስፖርት ማጣት መንገላታቱን፣ በሁሉም የገበያ ቦታዎች ርቀትን የመጠበቅና ሌሎች በሽታውን የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ እየተደረጉ አለመሆናቸው፣ ለሠልፍና የተጨናነቀ ሁኔታ በሚጋብዝ መልኩ ግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ግብር እየሰበሰበ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በሚፈለገው መጠን አለመኖሩን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር እጥረት እየተፈጠረ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በሽታውን ለመከላከል ይረዳሉ ተብለው የሚታሰቡ እንደ የፊት መሸፈኛ ጭምብል ያሉ ቁሳቁሶች በትራንስፖርት መናሃሪያ አካባቢዎች ጥራታቸውንና ንጽህናቸውን ባልጠበቀ መልኩ እየተሸጡ መሆኑም በሪፖርቱ እንደ ችግር ከተጠቀሱት መካከል ሲሆን ለይቶ ማቆያ ሳይገቡ ከውጭ እንደመጡ ተደብቀው ቤተሰቦቻቸውን እየተቀላቀሉ ያሉ ሰዎች መኖራቸውም ስጋት መፍጠሩን አመልክቷል፡፡
በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት በአዲስ አበባ በተለይ ህገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ በእጅጉ መስፋፋቱን ጠቅሷል ሪፖርቱ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ብቻ 30 ሺህ ሄክታር ያህል ስፋት ያለው ህገወጥ ግንባታ መገንባቱን፣ በዚሁ ቦታ 8 መቶ የፕላስቲክ ቤቶች መሰራታቸውን አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን አድርጐ ቤቶችን አፍርሶ ዜጐችን ለችግር ዳርጓል የሚለውን ጉዳይ መመርመሩንና አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ ህገወጥ ቤቶች ላይ መሆኑን ማረጋገጡን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ ጠቁሟል፡፡
በአንፃሩ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ህገወጥ ቤቶችን ማፍረስ በሚል ለበርካታ አመታት የቆዩ ቤቶች መፍረሳቸውን እንዲሁም ከመንግስት የኪራይ ቤቶች ውስጥ ዜጐችን የማስወጣት ህገወጥ ተግባር መከናወኑን አስታውቋል - ተቋሙ፡፡
በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሚፈልጉትን መረጃ ከመንግስት ተቋማት ጠይቀው ለማግኘት መቸገራቸውን መረዳቱን እንዲሁም ለተመረጡ ሚዲያዎች ብቻ አድሎአዊ በሆነ መልኩ መረጃ እየተሰጠ መሆኑን በመግለጽም ድርጊቱ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ በተለይ ከአዋጁ መርህ ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ ዜጐችን የአፍ መሸፈኛ ጭንብል አላደረጋችሁም በሚል እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከአዋጁ መርህ ውጪ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምም ሆነ ኢሠመኮ፤ ህብረተሰቡ አሁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመሪያዎች በማክበር፣ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡  


Read 10625 times