Print this page
Saturday, 16 May 2020 12:48

አንጋፋው ጋዜጠኛና የመድረክ መሪ አባተ ማንደፍሮ በጠና ታሟል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   ለተሻለ ሕክምና የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልገዋል ተብሏል
                          
               በጋዜጣ በሬዲዮና በመጽሔት ጋዜጠኝነቱ፣ በዘፈን ግጥምና በተውኔት ጽሑፍ ደራሲነቱ እንዲሁም በድንቅ መድረክ መሪነቱ የሚታወቀው አንጋፋው ጋዜጠኛና መድረክ መሪ አባተ ማንደፍሮ ሀይሉ በጠና ታሞ የካቲት 12 ሆስፒታል መግባቱን ቤተሰቦቹና የቅርብ ጓደኞቹ አስታወቁ፡፡
አባተ ማንደፍሮ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በየካቲት 12 ሆስፒታል ከገባ በኋላ እስካሁን የጤናው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነና ከዚህ የተሻለ ሕክምና እንደሚያስፈልገው የገለፁት የጋዜጠኛው የቅርብ ጓደኛ ጋዜጠኛ ይጥና ደምሴ አስታማሚ መግባትና መጠየቅ ባለመቻሉ ምኑን እንደታመመና በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማየት አለመቻሉን ተናግረው ከዚህ የተሻለ ሕክምና ማግኘት እንዲችል ሁሉም ሊያግዘው እንደሚገባ አቶ ይጥና ተናግረዋል፡፡
በ1955 ዓ.ም የተወለደው ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ጦርነት ጊዜ (በ1970 እና 71 ዓ.ም) አካባቢ በውትድርናው ዓለም ውስጥ የነበረ ሲሆን በፓራ ኮማንዶ ውትድርና ሀረር እንደነበርና ከዚያ ከተመለሰ በኋላ እንደገና በብሄራዊ ውትድርና ዘምቶ በባሌ ክ/ሀገር የባሌ ፖሊስ ኦርኬስትራ መድረክ መሪና አስተዋዋቂ ሆኖም አገልግሏል፡፡
በ1983 ዓ.ም ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣና ሰራዊቱ ሲበተን ከተበተኑት ውስጥ አንዱ እንደነበር የሚገልፀው የጋዜጠኛው ታሪክ የላሊበላ የባህል ኪነት ቡድን አስተዋዋቂ ሆኖ ደሴ ከሰራ በኋላ በ1989 አካባቢ በግል ፕሬስ መስራት መጀመሩም ታውቋል፡፡ በጋዜጣ ደረጃ በኒሻን፣ ምኒልክ፣ አስኳል፣ ሳተናውና ታሪክ ጋዜጣ ላይ የሰራ ሲሆን ዕድሜ፣ ሮያል፣ ሮዳስና ምኒልክ መጽሔቶች ላይ መስራቱም ተጠቁሟል፡፡
ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ ሀይሉ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የራሱን ፕሮግራም ከጓደኛው ጋር አዘጋጅቶ ያቀርብ እንደነበር የሚናገሩት የቅርብ ጓደኛው ከዚያ በኋላም ‹‹አቢሲኒያ ኢንተርቴይመንት›› የተሰኘ ድርጅት ከፍቶ በቀድሞው ዛሚ 90.7 ኤፍኤም እና በኤፍኤም አዲስ 96.3 ላይ ለረጅም ጊዜ ኪነ ጥበባዊና የመረጃ ፕሮግራሞችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ጋዜጠኛው በ96.3 FM  ላይ በተለይም አዳዲስ ድምፃዊያንን በቀጥታ በሬዲዮ በማወዳደር ለአሸናፊ ድምፃዊያን የዘፈን ግጥምና ዜማ በመስጠት ነጠላ ዜማ እንዲሰሩ ሁኔታዎችን እስከ ማመቻቸት ድረስ ለኪነ ጥበብና ለኪነ ጥበብ ሰዎች ያለውን ድጋፍ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ጋዜጠኛ አባተ እስከ ቅርብ ጊዜ በጄቲቪ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሀላፊነት ከአራት ዓመት በላይ ሲሰራ ቆይቷል ዘርፈ ብዙ ከያኒ የሆነው አባተ ማንደፍሮ የቴአትር ድርሰት ፀሐፊ፣ የዘፈን ግጥምና የመጽሐፍ ደራሲ ሲሆን ‹‹የአባቴ ልጅ›› የተሰኘ ቴአትር ጽፎና አዘጋጅቶ ለመድረክ ማብቃቱን፣ ‹‹የደም ምድር›› የተሰኘ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱንና ሰማኸኝ በለውን ጨምሮ ለተለያዩ ድምፃዊያን የዘፈን ግጥሞችን መስጠቱን የቅርብ ጓደኛው ጋዜጠኛ ይጥና ደምሴ ተናግረዋል፡፡ የ3 ሴቶችና የ2 ወንዶች አባት የሆነው ታታሪውና ለታናናሾቹ የሙያ አጋሮቹ አርአያና መምህር የሆነው ይህ ከያኒ ዛሬ በጠና ታሞ በየካቲት 12 ሆስፒታል የተኛ ሲሆን ለተሻለ ሕክምና የሚረዳውን ድጋፍ ሁሉም በሚችለው አቅም እንዲደግፈው ጥሪ ቀርቧል፡፡ ጋዜጠኛውን ለማገዝ መርዳት ለምትፈልጉ በዳሽን ባንክ የሒሳብ ቁጥር 0148104461011 አባተ ማንደፍሮ ብላችሁ መላክ እንድትችሉ ጥሪ ቀርቧል፡፡


Read 1514 times