Saturday, 23 May 2020 14:44

"ዛሬም ለወገናችን ደማችንን እንሰጣለን!"

Written by  (በጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ)
Rate this item
(1 Vote)

 የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ወለድ ሠራዊት አባላት፤ ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም የሚችለውን የደም ዕጥረት ታሳቢ በማድረግ፣ በነገው ዕለት የደም መስጠት መርሐ ግብር እንደሚያካሂዱ ተገለፀ፡፡ የማሕበሩ ስራ አስፈጻሚ አባላት በተለይ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ገለጹ።  "ትናንት በጦር ግንባር፤ ዛሬ በሕዝባችንን መሐል ሆነን ደማችንን ለወገናችን እንሰጣለን!" በሚል መሪ ቃል ከመቶ በላይ የሚሆኑ የቀድሞው አየር ወለድ (በራሪው ነብር) ማሕበር አባላትና ወዳጆቻቸው፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ባመቻቸላቸው ፕሮግራም መሰረት ደም እንደሚሰጡ የማሕበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት መቶ አለቃ ብርሃኑ አጥላው አስታውቀዋል።  የቀድሞው አየር ወለድ 102ኛ ክፍለ ጦር ም/ዋና አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ካሳዬ ታደሰ ስለ ሁኔታው ሲገልጹ፤ "የቀድሞው አየር ወለድ ሠራዊት ለአገሩ ሉዓላዊነትና ክብር በጀግንነትና በአገር ፍቅር ስሜት ሲዋደቅ ኖሯል፤ ደሙን አፍስሷል። ዛሬ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱ አቅም በፈቀደ መጠን ከወገናችን ጎን ከመቆምም በላይ፤ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም የሚችለውን የደም እጥረት ታሳቢ በማድረግ ይህን መርሐግብር አዘጋጅተናል።" ብለዋል። መሰል ወገናዊ አጋርነታቸው እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ሌላው የማሕበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የቀድሞው አየር ወለድ ሠራዊት ባልደረባ የነበሩት ኢንጅነር ክፍሎም ኪዳኔ፤ "ይህ ወገናዊ አጋርነት ከየትኛውም ፖለቲካዊ ንክኪ የጸዳና ጀግናው የአየር ወለድ ክፍለ ጦር ለአገሩና ለወገኑ በተፈለገበት ጊዜ ሁሉ እንደሚደርስ የሚያሳይበት አይነተኛ መገለጫ ነው" ብለዋል።
   ኢንጂነር ክፍሎም አያይዘውም፤ "የክፍለ ጦራችን ባልደረባ የነበረው ገዛኸኝ ገ/መስቀል (ኢትዮጵያዊው ነብሮ) ለአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን በሰላማዊ መንገድ ሲታገል በደቡብ አፍሪካ በአልሞ ተኳሾች ደሙ እንደፈሰሰ ይታወቃል። እኛም በነገው ዕለት ደማችንን ስንሰጥ ለመስዋዕትነት ዋጋው ክብር ለመስጠት ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ በስነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው በተመሳሳይ መንገድ ደማቸውን እንዲሰጡ ሁኔታውን አመቻችተናል።" ብለዋል።
   ከሳምንት በፊት የቀድሞው አየር ወለድ ማሕበር አባላት፣ በመዲናችን የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ስለ ኮሮና ቫይረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ያካሄዱ ሲሆን አቅም ለሌላቸው ወገኖች የሳኒታይዘር፣ የፊት ጭምብልና የእጅ ጓንት እደላ አድርገዋል።
(በጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ)

Read 8056 times