Print this page
Saturday, 23 May 2020 14:52

የዓለም ስፖርት ከኮሮና በፊትና በኋላ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የኮሮና ቫይረስ በዓለም ዙሪያ ከ200  በላይ አገራትን በማዳረስ ከ5.01 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማጥቃት ከ328ሺ በላይ ሰዎችን ለሞት አብቅቷል፡፡ ወረርሽኙ ባለፉት 3 ወራትም የዓለም በተለይ  በስፖርት ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ነው፡፡ የዓለም ስፖርት የገባበት ቀውስ በሚቀጥሉት 5 ዓመታትም ከተፅእኖዎቹ የማይላቀቅበት ሲሆን፤ ዓለምአቀፍ ተወዳጅነት ያላቸውን  እግር ኳስና አትሌቲክስ ህልውና አደጋ ውስጥ ከቷል፡፡ ኮቪድ 19 በዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ያደረሰውን ኪሳራ በቻርት አስደግፎ ያቀረበው አልጀዚራ  ስፖርት እንዳመለከተው የቶኪዮ ኦሎምፒክ 6 ቢሊዮን ዶላር፤ በፕሮፌሽናል የቤዝቦል፤ ቅርጫት ኳስ፤ ሆኪ እና አሜሪካን ፉትቦል የተደራጀው የአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ፤ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 1.35 ቢሊዮን ዶላር፤የስፓኒሽ ላሊጋ 1 ቢሊዮን ዶላር፤ ክሪኬት፣ ራግቢና እግር ኳስን የሚያንቀሳቅሰው የዩናይትድ ኪንግደም ስፖርት ኢንዱስትሪ 850 ሚሊዮን ዶላር፤ የጣሊያን ሴሪኤ 703 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የፈረንሳይ ሊግ1 430 ሚሊዮን ዶላር ከዓመታዊ ገቢያቸው አጥተዋል፡፡
ኮሮና  በስፖርት ውድድሮች ላይ አዳዲስ ደንቦችና መመርያዎች እንዲወጡ የሚያስገድድ ሆኗል፡፡ ግዙፍ የስፖርት ውድድሮች የሚያዘጋጁ አገራትና ከተሞቻቸውን ለተጨማሪ የበጀት ወጪ ተዳርገዋል፡፡ ከዓለም ስፖርት አፍቃሪዎች የሚያገኙትንም ትኩረት አሳጥቷቸዋል፡፡ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን የስፖንሰርሺፕ ድጋፋቸውን እየቀለበሱና የደረሰባቸውን ኪሳራ እያስከፈሉ ሲሆን፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የማድረግ ፍላጎታቸውን አቀዛቅዞታል፡፡ በቴሌቭዥን የብሮድካስት መብት ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ ውሎች ውዝግብ እየፈጠሩ ናቸው፡፡ ከስታድዬሞች፤ ከውድድር ማካሄጃ ስፍራዎችና ከሌሎች የስፖርት መሰረተልማቶች ህዝቦን እያራቀ የስፖርቶችን ተወዳጅነት እየቀነሰ ነው፡፡  በተለያዩ ስፖርቶች እየታዩ የነበሩ የእድገት አቅጣጫዎችን ከማደናቀፉም በላይ   የውድድር ደንቦች እንዲቀየሩ የተለመዱ የስፖርቱ ባህርያት ለዘላለም እንዲቀየሩም ምክንያት ሆኗል፡፡ በሁሉም ስፖርቶች ያሉ ባለሙያዎች፤ ድጋፍ አቅራቢዎች እና አገልግሎት ሰጭዎችን ከስራ እያስወጣ ነው፡፡ የስፖርተኞች  ገቢና ደሞዝ እየቀነሰ ሲሆን በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ያለውን የዋጋ ተመን አሽቆልቁሎታል፡፡
ከኮሮና በፊት የዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ በ2019 እኤአ ላይ ከ129 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደነበረው ትዋይስ ሰርክል  በጥናታዊ ሪፖርቱ ሲያመለከት ፤ ከኮሮና በኋላ በ2020 እኤአ የሚኖረው ገቢ ከ73.7 ቢሊዮን ዶላር በታች እንደሆነና ወረርሽኙ ከ61.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሳጣቱን ገልጿል፡፡ ከኮሮና በፊት የዓለም ስፖርት ከስፖንሰርሺፕ የነበረው ዓመታዊ ገቢ ከ46.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን፤ ከኮሮና በኋላ ግን በ37 በመቶ ወርዷል:: ከስፖንሰርሺፕ ሰጭ ኩባንያዎች መካከል የመኪና አምራች፤ የኃይል አገልግሎት እና የአየር ትራንስፖርት ኩባንያዎች በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባታቸው ዋናው ምክንያት ነው፡፡ ስለሆነም የዓለም ስፖርት በ2020 እኤአ ከስፖንሰርሺፕ የሚጠብቀው ዓመታዊ ገቢ ከ28.9 ቢሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ ትዋይስ ሰርክል በሰራው ጥናት ኮሮና ከዓለም ስፖርት የስፖንሰርሺፕ ገቢ ከ17.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሳጣቱን ሲሆን በሚቀጥለው 1 ዓመት  ወረርሽኙ የማይገታ ከሆነ ዓመታዊ የስፖንሰርሺፕ ገቢው ወደ 6.9 ቢሊዮን ዶላር ሊወርድ ይችላል፡፡
ኮሮና በታሪክ ከፍተኛውን ኪሳራ እያስከተለ የሚገኘው በእግር ኳስ ላይ ነው፡፡ በተለይ በአውሮፓ የእግር ኳስ ታላላቅ ሊጎች ውድድሮች ያለፉት ሁለት ወራት ተቋርጠው በመቆየታቸው ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ እንደተመዘገበ፤ ከ200 በላይ ክለቦችም የመፍረስ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ቅርጫት ኳስ፤ ቤዝቦል፤ አሜሪካንፉትቦል ሌሎች ትልልቅ ውድድሮችን በሚያንቀሳቅሰው የአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ ከቴሌቭዥን የስርጭት መብት በተያያዘ ብቻ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኮቪድ -19 ወረርሽኝ በስፖርቱ ዓለም ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የሚዳስስ ሪፖርት የሰራው የተባበሩት መንግስታት  ለስፖርተኞች ጤንነትና ደህንነት ሲባል ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ ብሔራዊ ደረጃ ያላቸው ውድድሮች ተቋርጠው መቆየታቸውን የስፖርቱን ህልውና ተፈታትኖታል፡፡ ከኮሮና በፊት በዓመት እስከ 750 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የነበረው የስፖርት ኢንዱስትሪው በኮሮና ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩን የዓለም ህዝቦች ከስራ ውጭ አድርጓል፡፡
ሌሎች የተያያዙ ኢንዱስትሪዎችን ማቃወሱን የሚቀጥል ሲሆን በተለይ የጉዞና ቱሪዝም፤ የስታድዬሞችና ሌሎች የስፖርት መሰረተልማቶች፤ የሆቴልና የምግብ አገልግሎትን፤ የትራንስፖርት መስክን፤ የሚዲያና ብሮድካስቲንግ መብት ሽያጮችን … ገበያ እና ገቢ በማሳጣት ለተጨማሪ የኢኮኖሚ ድቀት አጋልጧቸዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት በጥናታዊ ሪፖርቱ የዓለም ስፖርት ኢንዱስትሪን ከኮሮና በፊት የነበረውን የዋጋ ተመን Sport Value ያቀረበውን መረጃ በመንተራስ ሲያሰፍር የተለያዩ ስፖርት ምርቶች ከ171 ቢሊዮን ዶላር በላይ፤ የስፖርት  ትጥቆችና ሌሎች ቁሳቁሶች ከ270 ቢሊዮን ዶላር በላይ፤ የስፖርት ክለቦችና ደሞዝ ክፍያ ከ115 ቢሊዮን ዶላር በላይ፣ የስፖርት መሠረት ልማቶች አገልግሎት፤ የምግብና መጠጥ አቅርቦትና ከውድድሮች 200 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋእለንዋይ ያንቀሳቅሱ ነበር፡፡
ለስፖርቶች ህልውና ሲባል ውድድሮችን በአዳዲስ መርሐግብሮች መቀጠል
የዓለም ስፖርትን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው ለመመለስ በየአቅጣጫው ጥረቱ  ቀጥሏል፡፡  የስፖርት አስተዳደር ተቋማት፤ የውድድር አዘጋጆች፤ ስፖርተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ውድድሮችን ያለ ተመልካች ለመቀጠል በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡ ዋንኛ ምክንያታቸው በውድድሮች መቋረጥ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ ለመግታት ነው፡፡ የውድድር ዘመኑን ቀሪ መርሃ ግብሮችን በመጨረስ የስፖርቶችን ህልውና ለመታደግ ብቸኛው አማራጭ ውድድር መሆኑን አምነውበታል፡፡ ስለዚህም በአዳዲስ ደንቦችና መመርያዎች፤ በጥብቅ የህክምና ምርመራ ሂደቶች የስፖርት ውድድሮችን ማስቀጠል ወሳኝና አስፋላጊ ሆኗል::
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ የምታስተናግደውን 32ኛው ኦሎምፒያድ በጁላይ 23 / 2021 እኤአ ላይ እንዲሁም  ፓራኦሎምፒያድን ኦገስት 24 /2021 እኤአ  ላይ ለማካሄድ ወስኗል፡፡ ከኮሮና በፊት ኦሎምፒኩን በማስተናገድ እስከ 25 ቢሊዮን ዶላር ለማትረፍ አቅዳ የነበረችው የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ ከኮሮና በኋላ ጭራሹኑ 6 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶባታል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ኦሎምፒኩን ከ2021 እኤአ ውጭ አናስተናግድም ብለዋል፡፡
ከአውሮፓ አምስት ታላቅ ሊጎች መካከል የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ የቆመውን ውድድር ባለፈው ሰሞን ሜይ 16 ላይ በመጀመር ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ተመክሮውም በሌሎች የእግር ኳስ ሊጎች አጀማመር ላይ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋን በጁን ወር ካቆመበት ለመቀጠል የተወሰነ ሲሆን፤ ጨዋታዎችን በሁሉም የሳምንቱ ቀናት ለማካሄድና አንድ ክለብ በ72 ሰዓታት ውስጥ አንድ ጨዋታ እንዲኖሩ የተያዙ እቅዶች አሉ፡፡ አንዳንድ የጨዋታ ምርሃ ግብሮች ባልተለመደ ሰዓት በተለይ ሞቃታማ አየር ላይ እንዲከናወኑ መታሰቡ አንዳንዶችን አሳስቧቸዋል፡፡ በጣሊያን ሴሪኤ የውድድር ዘመኑን ካቆመበት ለመቀጠል ቁርጥ ቀን የተወሰነ ባይሆንም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ቡድኖች በእያንዳንዱ የልምምድ መርሃ ግብር 10 ተጨዋቾችን በመያዝ እንዲሰሩ ፈቅደው ከትናንት በስቲያ  ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን በጁን 12 ለመጀመር የሊጉ አስተዳደር የወሰነ ሲሆን፤ ‹‹ፕሮጀክት ሪስታርት›› በሚል መመርያ ዙርያ የሊጉ ባለቤቶች ምክክራቸውን ቀጥለዋል፡፡
በአውሮፓ የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ በ12 ወራት ሲሸጋሸግ፤ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና ዩሮፓ ሊግ በፌብርዋሪ እና ማርች ላይ በዝግ ስታድዬሞች እንዲቀጥሉ ቢደረግም ከዚያ በኋላ እንደተቋረጡ ናቸው፡፡  የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሁለቱን አህጉራዊ ውድድሮችን ቀጣይነት ከየሊጎቹ የተሳካ አጀማመር  በኋላ ያሳውቃል:: በፊፋ ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል በፓናማና ኮስታሪካ በጣምራ የሚያዘጋጁት ሀ20 የሴቶች አለም ዋንጫ በኦገስት ላይ እንዲሁም በህንድ የሚካሄደው ሀ17 የሴቶች ዓለም ዋንጫ  እስከ ኖቬምበር ባለው ጊዜ ለማካሄድ ፕሮግራም ቢወጣም ሙሉ ለሙሉ ሊሰረዙም ይችላሉ፡፡ በአፍሪካ አህጉር በርካታ የእግር ኳስ ሊጎች፤ እና በተለያዩ ስፖርቶች የሚካሄዱ ውድድሮች እጣ ፋንታ ላይ የተዘበራረቁ ውሳኔዎች እያጋጠሙ ሲሆን፤የ2020 የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ውድድር ሊሰረዝ እንደሚችል ግን ተገልጿል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሰሞኑን በኦፊሴላዊ ድረገፁ ይፋ ባደረገው መግለጫ  አዳዲስና የተሸጋሸጉ የውድድሮች መርሃግብሮችን በዝርዝር አስታውቋል፡፡ የዳይመንድ ሊግ ውድድር በጁላይ መግቢያ ላይ መጀመር ቢኖርበትም ይህን ለማድረግ አልተቻለም፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ተቋም ዳይመንድ ሊጉ በለንደን እና ራባት ከተሞች የሚደረጉትን መርሃ ግብሮች በመሰረዝ በሴፕቴምበር እንደሚጀምር ነው የገለፀው፡፡ በቻይና ናይጂንግ ከተማ ሊካሄድ የነበረው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአንድ አመት ተሸጋሽጎ ማርች 21 2021 ኤኤ ላይ እንዲደረግ ሲወሰን፤ በሌላ በኩል ፖላንድ የምታስተናግደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮንሺፕ ወደ ኦክቶበር 2021 እኤአ ተራዝሟል፡፡ ከታዋቂዎቹ የማራቶን ውድድሮች መካከል በሴፕቴምበር የሚደረገው የበርሊን ማራቶን ቢስተጓጎልም ሌሎች ማራቶኖች ከመደበኛው  ወቅታቸው ከ5 እና 6 ወራት በላይ ተሸጋሽገው እንደሚካሄዱ ተገልጿል::  በ2020 እኤአ ለመካሄድ የበቃው  ብቸኛው ማራቶን ከ2 ወራት በፊት የቶኪዮ ማራቶን ነው፡፡ የበርሊን ማራቶን ሴፕቴምበር 24 ላይ ሊካሄድ ፕሮግራም ወጥሎት፤  የጀርመን መንግስት ከ5000 በላይ ህዝብን የሚሰበሰቡ ውድድሮችና ዝግጅቶችን እስከ ኦክቶበር 24 በመከልከሉ ነው የተሰረዘው፡፡ አስቀድሞ አፕሪል 25 ላይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የለንደን ማራቶን ለኦክቶበር 4 ሲተላለፍ፤  የቦስተን ማራቶን ለሴፕቴምበር 14፣ የቺካጐ ማራቶን ለኦክቶበር 11፤ የአምስተርዳም ማራቶን ለኦክቶበር 18 ፤ የፍራንፈርት ማራቶን ለኦክቶበር 25 እንዲሁም የኒውዮርክ ማራቶን ለኖቬምበር 1 ተቀጥረዋል፡፡
የአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ ትልልቅና ፕሮፌሽናል ሊጎችን መልሶ ለመጀመር በተለያዩ አቅጣጫዎች እየሰራ ይገኛል፡፡ የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ማህበር ከ2 ወራት በፊት ፕሮፌሽናል የሊግ ውድድሩን ያቋረጠው ተወዳዳሪ ክለቦች እያንዳንዳቸው ከ63 እስከ 67 ጨዋታዎችን ተደርገው ነበር፡፡ ከዓለም ስፖርቶች ከፍተኛው ገቢ፤ የስፖርተኞች ደሞዝ ክፍያ ፤ የስታድዬም ተመልካች እና የቲቪ ተከታታይ ያለውን ፕሮፌሽናል የቅርጫት ኳስ ሊጉ መቼ እንደሚጀመር የተገለፀ ቀን ባይኖርም ለ30 የቅርጫት ኳስ ቡድኖች ሰሞኑን ጥሪ አድርጓል፡፡ የቅርጫት ኳስ ሊጉን ለመቀጠል ቡድኖቹ በኦርላንዶ ከተማ ካምፕ አድርገው እንዲቆዩ ውድድሮችንም የዋልት ዲዝኒ ንብረት በሆነው የስፖርት ማዕከል ለማካሄድ በምክክር ላይ ነው:: ለቅርጫት ኳስ ቀሪ ውድድሮች የላስቬጋስና ሂውሰተን ከተሞችም በአማራጭነት ቀርበዋል፡፡ በሌላ በኩል የሜጀር ሶከር ሊግ ቀሪ ኳስ ጨዋታዎችን በተመሳሳይ በኦርላንዶ ለማካሄድ የታቀደ ሲሆን፤ የአሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በ26 ክለቦች የሚገኙ ከ1000 በላይ ተጨዋቾች፤ አሰልጣኞችና ሌሎች የቡድን አባላትን በካምፕ በማቆየት ውድድሮቹን ለመምራት ነው ያሰበው፡፡ የአሜሪካን ፉትቦል የኤንኤፍኤል ውድድሮችን በሴፕቴምበር ለመጀመር እቅድ ቢኖርም  ግጥሚያዎችን በዝግ ስታድዬም ማካሄድ ከ5.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያከስረኛል በሚል ምክንያት ሙግት ውስጥ ገብቷል፡፡   እና የሜጀርሶከር ሊግ መልሶ አጀማመር የተሰሙ ውሳኔዎች የሉም፡፡
ከኮሮና በኋላ እግር ኳስ መልኩን ይቀይራል
በመላው ዓለም ከ3 ቢሊዮን በላይ ተከታታይ ያለው እግር ኳስ ያለጨዋታዎች ከ10 ሳምንታት በላይ መቋረጡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያጋጠመ ነው፡፡ የእግር ኳስ ስፖርትን ወደ ውድድር የሚመልስ ውሳኔ ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች መነሳቱ የሚጠበቅ ነበር፡፡  በሳምንቱ መግቢያ ላይም የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ካቆመበት መቀጠል ከፍተኛ መነቃቃት ከመፍጠሩም በላይ ዓለምን የሚጠቅም ተመክሮዎችም ተገኝተውበታል::  በቦንደስ ሊጋው በተካሄደ ጨዋታ  ሌላው ዓለም እንደተመክሮ የሚመለከታቸውና የስፖርቱን የነበረ ገፅታና የሚቀይሩ ደንቦችና ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በቦንደስ ሊጋው የዝግ ስታድዬም ጨዋታው ላይ የተሳተፉት ለ2 ለሳምንት ያህል በለይቶ ማቆያ የነበሩ፤ በጥብቅ የህክምና ክትትልና ምርመራ ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ ለጨዋታው በስታድዬም አካባቢ ውስጥና ሜዳ ላይ እንዲገኙ ፍቃድ የተሰጣቸው በድምሩ 213 ሰዎች ሲሆኑ፤ የሁለቱ ክለብ ተጨዋቾች እና የቡድን አባላት፤ ሚዲያ፤ የህክምና ባለሙያዎች፤ የፀጥታ እና ጥበቃ ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጭዎች ናቸው፡፡ ወደ ጨዋታው የመጡትም ርቀትን ለመጠበቅ በበርካታ አውቶብሶች ነበር፡፡  በጨዋታው ላይ የቀረቡት 30 ኳሶች ፀረ ተዋህስያን የተረጨባቸውና ኳስ አቀባይ ሳይኖራቸው በተመረጡ ቦታዎች ላይ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ የየቡድኑ ቅያሪ ተጨዋቾች ብዛት አስቀድሞ እንደነበረው 3 ብቻ ሳይሆን ወደ 5 አድጓል፡፡ ከሜዳ ውጭ ያሉ ተጨዋቾች፤ ሌሎች የቡድን አባላትና አገልግሎት ሰጭዎች ርቀታቸውን በመጠበቅ ስታድዬም ውስጥ ሲገኙ ሁሉም ጭምብል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተጨዋቾች ከሜዳ ሲወጡ አዲስ ጭምብል የሚሰጣቸው ሲሆን ጭምብል የማያደርጉት በጨዋታ ላይ ያሉት ብቻ ናቸው፡፡ በየጨዋታው የጎል ደስታ አገላለፅና የሰላምታ ልውውጥ ከንክኪ እንዲርቅ ታስቦ ለየት ያሉ ተግባራት ተስተውለዋል፡፡  ክንድን በማጋጨት፤ በታኬታ እግሮችን በማነካካት እና ክርኖችን ወደራስ በማቀፍ የጎል ደስታ እና ሰላምታ የሚገለፅ ሆኗል፡፡
ዝግ ስታድዬሞች  ባለሜዳን ድል ያሳጣሉ፤ የፉክክር ደረጃ ይቀንሳሉ፤ ያከስራሉ
ከሳምንት በፊት ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም በጡመራ ገፁ ላይ ባቀረበው ልዩና ጥናታዊ ዘገባ የስፖርት ውድድሮች ያለደጋፊዎችና ያለተመልካቾች  በዝግ ስታድዬሞች መደረጋቸው ለስፖርቶች ህልውና ወሳኝ ርምጃ ቢሆንም፤ በውጤቶች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚፈጥር አመልክቷል፡፡ በተለይ የእግር ኳስ ጨዋታዎች በዝግ ስታድዬሞች ሲካሄዱ ባለሜዳ የሆኑትን ቡድኖች ውጤታማነት እንደሚቀንስ እና አጠቃላይ ድባቡ የፉክክር ደረጃን እንደሚቀንስ ነው የተገለፀው:: ኳስ ጨዋታዎችን  በዝግ ስታድዬሞች ያለተመልካች ማካሄድ ስፖርት አፍቃሪዎችና ደጋፊዎች ለየቡድኖቻቸው አበረታች ሆነው የሚጫወቱትን ሚና የሚገድብ መሆኑ የሚያሳስብ ነው ብሏል ጥናቱ፡፡ ከኮሮና በፊት ጨዋታዎች በዝግ ስታድዬሞች እንዲካሄዱ የሚደረገው  በተመልካቾች ረብሻ፤ በዘረኝነት ጥፋቶች፤ በሙስና ሌሎች ችግሮች ቡድኖችና ደጋፊዎቻቸው በሚጣልባቸው ቅጣቶች ነበር:: ይህም ውጤት ቢያሳጣቸው በጥፋታቸው የገጠማቸው ጣጣ መሆኑ ነበር የሚታወቀው፡፡ በኮሮና ላይ ውድድሮች እንዲቀጥሉ ሲደረግ ግን የበሽታዎችን ስርጭት ለመከላከል ነው ዝግ ስታድዬሞች ላይ ውድድሮች እንዲካሄዱ የተወሰነው፡፡ በዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ የቀረበው ጥናታዊ ዘገባ እንዳመለከተው የስፖርት ውድድሮች በዝግ ስታድዬሞች መከናወናቸው መጭውን ጊዜ ፈታኝ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ በኳስ ጨዋታዎች እና በሌሎች የስፖርት ውድድሮች ደጋፊዎች አለመኖራቸው ባለሜዳ የሆኑ ቡድኖችን ለደካማ ውጤት የሚዳርጋቸው፤ በዳኞች ውሳኔዎችና የባካኑ ሰዓቶች ጭማሪ ላይ የሚያሳድሯቸውን ተፅእኖዎች ይቀንሳቸዋል፡፡
ኳስ ጨዋታዎች በዝግ ስታድዬም ሲካሄዱ የባለሜዳውን  ክለብ ውጤታማነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ደጋፊዎች ስታድዬም ባለመግባታቸው ስለሚያስቀረው ውጤቶችን ማበላሸቱ የማይቀር ይሆናል፡፡ በዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ጥናታዊ ዘገባ መሰረት በኳስ ጨዋታዎች ላይ  በሜዳቸው የሚጫወቱ ክለቦች  ደጋፊዎች ባሉበት ስታድዬም ሲጫወቱ የማሸነፍ እድላቸው 46 በመቶ ሲሆን ያለደጋፊ ደግሞ 43 በመቶ ነው፡፡ በአንፃሩ ከሜዳቸው ውጭ የሚጫወቱት ደግሞ የማሸነፍ እድላቸው ከደጋፊዎቻቸው ጋር 26 በመቶ እንዲሁም ያለደጋፊዎቻቸው 34 በመቶ ነው፡፡
የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በመቋረጣቸው፤ በመስተጓጎላቸው ብቻ ባለፉት 10 ሳምንታት  ትልልቆቹን የአውሮፓ ክለቦች ከ3.5 እስከ 6.2 ቢሊዮን ፓውንድ ገቢ እንዳሳጣቸው የሚያመለክተው ቢቢሲ ስፖርት ዋናው ገቢ ከስታድዬም የትኬት ሽያጭ የሚገባው መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡  የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለብ የሆነው ቦርስያ ዶርትመንድ ግጥሚያዎችን በዝግ ስታድዬም ሲያካሂድ በያንዳንዱ ጨዋታ 2.6 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያከስረው ያስታወቀ ሲሆን፤ ዴይሊሜል ባቀረበው ሃተታ ደግሞ የእንግሊዝ ክለቦች የውድድር ዘመኑ በቀረው ጊዜ በአግባቡ ለመጨረስ ቢችሉም፤ ጨዋታዎች በዝግ ስታድዬሞች በመካሄዳቸው ከ878 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ በማስቀረት ሊሳራ ይዳርጋቸዋል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ እስከ 140 ሚሊየን ፓውንድ፤ አርሰናል እስከ 122 ሚሊየን ፓውንድ እንዲሁም በርን ማውዝ እስከ 6.7 ሚሊዮን ፓውንድ በዝግ ስታድዬሞች ጨዋታዎችን በማድረግ ኪሳራ ይገጥማቸዋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ  ህልውናውን ለመጠበቅ
ውድድሮችን ተስፋ ያደርጋል
በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ  ከእግር ኳስ ቀጥሎ በኮሮና ቫይረስ የተቃወሰውና በርካታ አሳሳቢ ሁኔታዎች የተጋረጡበት የዓለም አትሌቲክስ ላይ ነው:: ሰሞኑን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፕሬዝዳንት እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮው በሰጡት መግለጫ፤ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በተሸጋሸጉ መርሃግበሮቻቸው ወደ መደበኛ ሁኔታቸው ለመመለስ የምናስብበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብለዋል:: ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት፤ ከየአገራቱ መንግስታት እና ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስንሰራ ቆይተናል ያሉት ሴባስቲያን ኮው፤ በኮቪድ 19 ዙርያ የሚደርሱንን መረጃዎች እና መመርያዎችን በማክበር ቆይተናል ብለው፤ የዓለም አትሌቲክስን ህልውና ለመጠበቅ ውድድሮችን ማካሄድ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡  ከገደቡ ጋር ሊፃረሩ የሚችሉ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እየተዘጋጀንም ነው ብለዋል፡፡ በመላው ዓለም የአትሌቲክስ ውድድሮችን በሚያመቹ ሁኔታዎች ካቆሙበት ለመቀጠልና በአዳዲስ መርሃግብሮቻቸው ለመፈፀም ነው የታሰበው፡፡   የዓለም ስፖርት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የስፖርቱን ህልውና ከመጠበቅ አንፃር ያለባቸው ሃላፊነት ለመወጣት በራሳቸው ስትራቴጂ እና ውሳኔ መንቀሳቀስ ይኖርባቸውል ሲሉም ሴባስቲያን ኮው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች ባሻገር የኮሮና ወረርሽኝ  አሳሳቢ ፈተናዎችን የፈጠረው በመላው ዓለም በሚካሄዱ ትልልቅ ማራቶኖችና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ላይ ነው፡፡ አሁን ያለንበት ወር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚካሄዱ ትልልቅ ማራቶኖች የሚካሄዱበት መደበኛ ጊዜያቸው ቢሆንም በ5 እና በ6 ወራት መራዘማቸውና አንዳንዶቹም ሙሉ ለሙሉ በመሰረዛቸው ኪሳራ አጋጥሟል፤ በስፖርቱ እድገት ላይ መስተጓጎል አምጥቷል:: በጎዳና ላይ ሩጫዎችና በማራቶኖች አለመከናወን የውድድሮቹ አስተናጋጅ ከተሞች እና አዘጋጆቻቸው ለበጀት ብክነት የሚዳርጋቸውና ገቢ የሚያሳጣቸው ሲሆን በየውድድሮቹ የሚሳተፉ አትሌቶችም በአንድ የውድድር ዘመን የሚያገኙትን ገቢ በማስቀረጥ፤ ጥሩ እና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሰሯቸውን ልምምዶች ዋጋ ያሳጣባችዋል፡፡ ከትልልቅ የማራቶን ውድድሮች መካከል የመሰረዝ እጣ የገጠማቸው በሴፕተምበር ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የበርሊን ማራቶን እንዲሁም የፓሪስ እና ባርሴሎና ማራቶኖች ዋናዎቹ ተጠቃሾች ሲሆኑ በኒውዮርክ የሚካሄደው የግማሽ ማራቶንም ሌላው ነው፡፡
ማርኬትዎች የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ሰሞኑን በድረገፁ ባሰራጨው የጎዳና ላይ ሩጫዎች በተለይም የማራቶን ህልውና ለመታደግ አዲስ ሃሳብ አቅርቧል::  በዓለም ዙርያ ከሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች በተለይ በማራቶን ሊግ የተመዘገቡ 6 ማራቶኖች ተባብረው በመስራት የስፖርቱን ህልውና መጠበቅ እንደሚኖርባቸው  ማርኬትዎች መክሯል፡፡ በማራቶን ሊግ ስር የሚካሄዱት 6 ትልልቅ ማራቶኖች በቦስተን፤ ኒውዮርክ፤ ችካጎ፤፤ ለንደን፤ በርሊንና ቶኪዮ ከተሞች እንደሚያስተናግዷቸው ይታወቃል፡፡ ማርኬትዎች በዘገባው በ2020 የሚከበረውን የዓለም ማራቶንን ቀን ምክንያት በማድረግ ስድስቱ ማራቶኖች በልዩ መንገድ የጋራ ውድድር ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ በየከተሞቹ የዓለም ማራቶን ቀንን ምክንያት አድርጎ የሚዘጋጀው ልዩ ማራቶን የስፖርቱን ህልውና የሚታደግ ወሳኝ ርምጃ እነደሚሆን የገለፀው ማርኬትዎች፤ የማራቶኑን መታሰቢያነት  ኮቪድ 19ን ከምድረገፅ ለማጥፋት ለሚዋጉ የህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭዎች ማዋል እንደሚቻልም ጠቁሟል፡፡ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮንሺፕ፤ 6 ማራቶኖችን የሚያካትተው የማራቶን ሊግ፤ ዳይመንድ ሊግና ሌሎች ውድድሮች ወቅታቸው ቢያልፍም እስካሁን አልተጀረም፡፡ ስለሆነም ስፖንሰር የሌላቸው የአፍሪካ አትሌቶች በመላው ዓለም ውድድሮች በመቋረጣቸው ለችግር ይጋለጣሉ ብሎ የዘገበው ቢቢሲ ስፖርት ነው፡፡ አትሌቶች በስፖርቱ ገቢያቸውን የሚያገኙት ከስፖንሰር፤ ከሽልማት ገንዘብ፤ ከቦነስ እና ከተሳትፎ ክፍያዎች ነው፡፡ ውድድሮ ካልተካሄዱ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በማራቶን ውድድሮች መስተጓጎልም የሚጉዱት ከፍተኛ ውጤታማነት ያላቸው የአፍሪካ አትሌቶች ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ከ1ሺ እስከ 100ሺ ዶላር የሽልማት ገንዘብ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት እስከ 800ሺ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለተቸገሩ አትሌቶች ለመስጠት ያለውን እቅድ አስታውቋል፡፡
ከኮረና በፊት ውድድሮችን ለማዘጋጀት ሽሚያ፤
ከኮሮና በኋላ ግን ሽሽት
ትልልቅ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች የማዘጋጀት እድል የተሰጣቸው የዓለማችን ታላላቅ ከተሞች ላይ ኮሮና ያልተጠበቁ ፈታኝ ሁኔታዎች በመፍጠር ለበጀት ጭማሪ፤ ለኪሳራ እና ከህዝብ የሚያገኙትን ድጋፍ በማሳጣት እየጎዳቸው በሚል ያጠናው bcw ስፖርት ኢቨንትስ ተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡ በስፖርት ውድድሮች ዓለምአቀፋዊ ግንኙነትን ለማጠናከር፤ አዘጋጅ ከተሞች በመርሃ ግብራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ በማገዝ እና ድምቀት እንዲኖራቸው በአማካሪነት የሚሰራ ነው bcw ስፖርት ኢቨንትስ፡፡ ከአዘጋጅ አገራት በተያያዘ የሰራውና ከ1 ወር በፊት ያደረገውን ጥናት ለማዘጋጀት በሳምንት ውስጥ ከመላው ዓለም ከ100 በላይ የስፖርት ውድድሮችን የሚያስተናግዱ ከተሞችን ልዩ መጠይቅ አድርጎላቸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን ለማስተናገድ ሃላፊነት ይዘው ሙሉ ዝግጅት ጨርሰው የነበሩ አገራትና ከተሞቻቸው በተለያዩ ሁኔታዎች ጉዳት እንደተፈጠረባቸው እና የሚዳርስባቸው ተፅእኖ እና ኪሳራ እስከ 2021 እኤአ የሚዘልቅ መሆኑን ጥናቱ ይገልጻል፡፡  ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የሚያዘጋጁ ከተሞች የተሰጣቸውን ሃላፊነት በቻሉት ሁሉ ለመወጣት ፍላጎት እንዳላቸው በጥናቱ ላይ በሰጡት ምላሾቻቸው ቢያረጋግጡም፤ በተፈጠሩ የግዜ መሸጋሸጎች እና መስተጓጎሎች ከስፖንሰሮች እና ከየህዝቦቻቸው የሚያገኙትን ድጋፍ ማቀዝቀዙ ረብሿቸዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ተቋም መጠይቅ ካቀረበላቸው ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች አዘጋጅ ከተሞች መካከል፤ 84 በመቶው በወረርሽኙ ከፍተኛ ተፅእኖ ደርሶብናል ያሉ ቢሆንም የቫይረሱ ጉዳት ከ2021 እኤአ በኋላ እንደማይዘልቅ ያደረጉት 58 በመቶው ተስፋ አድርገዋል:: በሌላ በኩል በጥናቱ ከተካፈሉት የስፖርት ውድድሮችን አዘጋጅ ከተሞች 56 በመቶው ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት በወረርሽኙ ዙሪያ የተሟላ መረጃዎችን ማግኘት መቻላቸውን በአድናቆት ሲገልፁ 78 በመቶው ደግሞ እናተርፍበታለን ካሉት መስተንግዶ ላልጠበቁት ኪሳራ  እንዳጋለጣቸው በምሬት ገልፀዋል፡፡ በሚቀጥሉት 2 ዓመታት በዝግጅት በጀታቸው ላይ የገጠማቸው ጭማሪ ፈተና እንደሚሆንባቸውም ተናግረዋል፡፡
የስፖርት ውድድር አዘጋጆች እና
ተወካዮቻቸው አስተያየት
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖርት ውድድሮችን የማዘጋጀት ሁኔታዎች ለዘላለሙ ተቀይረዋል›› የእንግሊዝ ተወካይ
‹‹የስፖርት ውድድሮች ህዝብን ያስደስታሉ፡፡  ያለንበት ወቅት ግን ለህዝባችን ጤንነት እና ደህንነት ትኩረት የምንሰጥበት ነው›› የሆላንድ ተወካይ
‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድደሮችን ማዘጋጀት ለስፖርት እድገት እንደማይጠቅም እየተስተዋለ መጥቷል፡፡ ለስፖርቶች ህልውና በአገር ውስጥ ውድድሮች ላይ መስራት ያስፈልጋል›› የዴንማርክ ተወካይ
‹‹የዓለምን ስፖርቶች ከህዝቡ የሚያርቅ እና የስፖንሰሮችን ድጋፍ የሚቀንስ ሁኔታ በሁሉም ወገን የታየ ነው፡፡ ኮቪድ 19 በዓለም ስፖርት ላይ በአጭረና በረጅም ጊዜ ተፅኖዎችን ያሳድራል:: ወደፊት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የትኛውም ህዝብ ድጋፍ የሚሰጥ አይመስልም›› የሰሜን አሜሪካ ተወካይ
Sources
UEFA, BBC sport, Newyork times, worldathletics.org, Runnersworld, worldmarthonmajors.com, athletics weekly, Marketwatch, bcw, Dw.com, Un.org, Business wire, Global legal Group limited, KPMG, Deliote, Global sports salar survey 2019, sportintelegence


Read 1297 times