Saturday, 23 May 2020 15:47

ፕ/ር በየነ - በሽግግር መንግስት፣ በህገመንግስቱና በመድረክ ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

    “መረራ ኦፌኮን ይዞ በጐን የሚፈጥረው ትብብር አሳስቦናል”

          የመድረክ አባል ድርጅቶች በአቋም እየተለያዩ ነው ለምን? የሕገ መንግሥት ትርጉምና አንደምታው እንዲሁም የሽግግር መንግሥት ጥያቄዎችና ሌሎች እንዴት ይታያሉ? በሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

              ሰሞኑን በሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ ሲሰጡ የነበሩትን ሙያዊ ማብራሪያዎች እንዴት አገኙት?
በጥቅሉ ሲታይ ከአገር አቀፍና አለማቀፍ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ምንነት በመነሳት ብዙ ማብራሪያዎች የተሰሙበት መድረክ ነው:: ሕገ መንግሥቱ በሁለንተናዊ መንገድ መታየት እንዳለበት፣ አንዱ አንቀፅ ብቻ በራሱ ቆሞ በቂ ምላሽ እንደማይሰጥ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ትንታኔ ቀርቧል፡፡ አንድ ወጥ አቅጣጫ ብቻም የተቀመጠበት ሂደት አይመስለኝም፡፡ አብዛኛው የሕግ ባለሙያ፤ መፍትሔ መምጣት ያለበት በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ነው እያለ ነው ይሄ ደግሞ እኛም የምንከተለውን አቅጣጫ ያጠናከረ ይመስለኛል፡፡
ከቀረቡት ሀሳቦች ተነስተው ሂደቱ ጥሩ መፍትሄ ይወጣዋል የሚል እምነት አለዎት?
አሁን ባለንበት አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ሕገ መንግሥቱ ይተርጎም የሚለው ቅቡል እስከሆነ ድረስ፣ ሕገ መንግሥታዊ ስልጣን የተሰጠው አካል፣ የሚሰጠውን ትርጉምና ችግሩ በዚህ መልክ ይፈታ ብሎ የሚያስቀምጠውን መፍትሄ ለመቀበል ዝግጁ መሆን፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የሚሰጠውን ውሳኔ ተቀብለን መሄድ እንዳለብን ነው የሚሰማን:: ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የፖለቲካ መፍትሄ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም ሕገ መንግሥታዊ መፍትሄ የሚለውን መንፈስ ይዞ የምንመኘው ምርጫ ላይ መድረሱ ነው የሚሻለው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ሀይሎች ይዘው የሚመጡት ትርጉም አገሪቱን ችግር ውስጥ ሊያስገባት ይችላል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ራሱ ውሳኔ ሰጪና፣ ራሱ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ ሆኖ ሥልጣኑን ለማራዘም የተሞከረበት ሂደት ነው የሚል ትችት የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል…?
ፕ/ር እንድሪያስ ለረዥም ጊዜ የማውቀውና በባለሙያነቱ የማከብረው ሰው ነው፡፡ አለቃዬም ሆኖ አብረን ሰርተናል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሱ አቋም ትንሽ የዋዠቀ  ይመስለኛል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በሰጠው አስተያየት ቀድሞ የተናገረውን አርሟል፡፡  እሱ እንዳለው ብንሄድ እንኳ ያነሳው ጉዳይ፣ የሕገ መንግሥቱ ችግር እንጂ አሁን ያለው መንግሥት ሊሆን አይችልም፡፡ “ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ብዙ ተቃውሞ ስናቀርብ የነበረው ለዚህ ነው፡፡ እኔ ያኔ የአማራጭ ሃይሎች ም/ቤት ሊቀ መንበር ነበርኩ፡፡ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሂደቱ አሳታፊ አይደለም፤ አያስማማም” እያልን ተቃውመናል። አንዱ የተቃወምነው ይሄንኑ የመተርጎም ሥልጣን ጉዳይ ነበር። ስለዚህ ችግሩ የሕገ መንግሥቱ ጉድለት ነው እንጂ መፍትሄ ፍለጋ ላይ የሚደረገው ሂደት ችግር አይደለም፡፡
ምርጫው የሚካሄድበት የጊዜ ገደብ ጉዳይም ተነስቷል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ምርጫው በቂ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልገዋል:: በቀድሞ አሰራር የሚካሄድ ከሆነ ትርጉም የለውም፡፡ አሁን የምርጫ አስፈፃሚ ምልመላ ላይ ከዚህ ቀደም ካድሬ የነበሩ ሰዎች እየመለመሉ ከወዲሁ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመራረጥ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የጊዜ ሰሌዳው ከመውጣቱ በፊት የምርጫ አስተዳደሩ የነጠረ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ምርጫ አስፈፃሚው እስከ ታችኛው ደረጃ ድረስ ነፃና ተአማኒ  መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው ምርጫው መደረግ ያለበት፡፡ ምርጫ ቦርድ እንከን የለሽ ዝግጅት አድርጎ በብቃት የማጠናቀቁ ጉዳይ ነው የምርጫውን ጊዜ ሊወስነው የሚገባው፡፡
‹‹መድረክ›› “የብሔራዊ አንድነት መንግስት እንዲቋቋም” የሚል የመፍትሄ ሀሳብ አቅርቧል:: የእናንተ ፓርቲ ደግሞ ‹‹ይሄ ከኔ ስምምነት ውጪ የሆነ ነው፤ ሰነዱን አላውቀውም›› የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በመድረክ አባላት መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?
ነገሩን ከስሩ ማስረዳት ይሻላል። ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ በጽ/ቤታቸው ሁላችንንም ጋብዘው በባለሙያዎች ተጠንቷል ባሉት ባለ 4 አማራጭ ሃሳቦች ላይ አስተያየት እንድንሰጥ ጠየቁን፡፡ የመድረክ አባላት በየግል ነበር የተጋበዝነው፡፡ እኔ ኢሶዴፓን፣ ፕ/ር መረራ ከኦፌኮ፣ ጎይቶም ከአረና፣ አቶ ደሳለኝ ሲዳማ አርነትን በመወከል ነበር በመድረኩ የተገኘነው። የእለቱን አጀንዳም ያየነው እዚያው ነበር፡፡ አራቱም አማራጮች በሕግ ባለሙያው ቀረቡልን፡፡ ከዚያም ጠ/ሚኒስትሩ በቀረቡት አማራጮች ላይ አስተያየት እንድትሰጡ እንፈልጋለን አሉን፡፡ በወቅቱ እኔ በኢሶዴፓ ስም የፓርቲያችንን አቋም በአራቱም አማራጮች ላይ አቀረብኩ፡፡ አራቱንም አማራጮች ዳስሼ ከጨረስኩ በኋላ እንግዲህ የምንቀሳቀሰው በሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፤ ያ እንደመሆኑ ሕገ መንግሥቱ የፌደሬሽን ም/ቤት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ይሰጣል የሚል ግምት ተጠቅሞ ስለሆነ፤ የሕገ መንግሥት ትርጉም አማራጭ ነው፡፡ በትርጉሙ ምን እንደሚሰጥ ባናውቅም፡፡ ለፌዴሬሽን ም/ቤት የተሰጠውን ሥልጣን አክብረን፣ ያንን ወሳኔ መጠበቅ ይሻላል የሚል አቋም የአረናም ተወካይ ይሄን አቋም ነው የወሰደው:: የሲዳማ አርነት ተወካይም ተመሳሳይ አቋም ነው የወሰደው፡፡ ዶ/ር መረራ ግን “በቂ ጊዜ ተሰጥቶን ባልተነጋገርንበት ሰነድ፣ የመድረክ አባላትም የተለያየ ነገር እየተነጋገርን ነው›› ብሎ እሱ በኛ ሀሳብ እንደማይስማማ አስተያየት ሰጠ:: እንደውም ጊዜ ይሰጠንና በድርጅታችን ውስጥ ተነጋግረን በጉዳዩ ላይ አስተያየታችንን ብናሳውቅ ይሻላል የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ነገር ግን ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን እንደማይቀበሉ በሚገልጽ መልኩ ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡ ከዚያ ቆይቶ የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ “በስብሰባው ላይ “እኛም የራሳችንን አማራጭ ማቅረብ አለብን” የሚል ሀሳብ ቀረበ፡፡ እኛ አካሄዱ ተገቢ አይደለም ብለን ተከራከርን፡፡ “አቋማችንን በመድረኩ ላይ ግልጽ አድርገናል፤ ሌላ ሁለተኛ አቋም መያዝ ጥሩ አይሆንም” አልናቸው፡፡ በመጨረሻም በየድርጅቶቻችን ተነጋግረን አቋም እንይዝበታለን ተብሎ ተለያየን፡፡ አንድ አርብ ቀን የኛ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ድንገት ቢሮ በሄደበት አጋጣሚ ስብሰባ ግባ ተባለ፡፡ ይሄን ደውሎ ነገረኝ፡፡ ስለስብሰባው የተነገረን ነገር አልነበረም፡፡ ‹‹ለማንኛውም ተሰብሰብና የሚባለውን ስማ፤ ነገር ግን አቋማችን አይቀየርም›› አልኩት፡፡ በሌላ በኩል፤ የአፋር ሕዝቦች የፍትህና የዴሞክራሲ ፓርቲ የሚባለው የመድረኩ አባልም በዕለቱ አልተወከለም ነበር:: እንግዲህ ሁለታችንም ባልተወከልንበት ሁኔታ ነው የተባለውን አማራጭ ሰነድ በመድረክ ስም ያወጡት፡፡ ይሄ ለኛ በጣም እንግዳ ነው የሆነብን፡፡ በወቅቱ ለአቶ ገብሩ አስራት ደውዬ ‹‹ምንድነው ነው” ብዬ ስጠይቀው›› ‹‹አይ ዝም ብሎ ደብዳቤ ነው፣ ለጠ/ሚኒስትሩ የሚገባ›› አለኝ፡፡ ለዶ/ር መረራ ደውዬ ‹‹ደብዳቤው ምንድን ነው፤ እኛም እንየው›› ስለው ‹‹አይ ደብዳቤው እኮ መሸኛ ነው እንጂ እያዘጋጀን ያለነው አማራጭ ሀሳብ የያዘ ሰነድ ነው›› አለኝ:: ‹‹እሱንም ቢሆን ላኩልንና እንየው›› አልኩት::  ሰነዱን ስናየው ከእኛ አቋም ውጭ የሆነ የብሄራዊ አንድነት መንግሥት ተቋቁሞ፣ ሌላ አገር አቀፍ ጉባኤ እንዲመሰረት የሚጠይቅ ሰነድ ነው፡፡ “ይሄንንማ እኛ አንቀበለውም” አልን፡፡ በኛ ስም እንዳይወጣም ለሶስቱ ድርጅቶች ማለትም ለኦፌኮ፣ ሲአንና አረና ማስታወሻ ልኬያለሁ፡፡ ግን ያንን ሰነድ በመድረክ ስም ነው ያሰራጩት፡፡ እኛ በመርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት ነው የምናንቀሳቅሰው፡፡ እኛን በጣም ያሳሰበን ሌላው ጉዳይ፣ ዶ/ር መረራ ኦፌኮን ይዞ ሌላ ትብብር የሚባል ቡድን ጋር አባል ሆኗል፡፡ ይሄ ‹‹ትብብር›› እነ ኦነግና ኦብነግን ጨምሮ ሌሎች 7 ድርጅቶች ያሉበት ነው፡፡ “አረና” በዚህ ትብብር አንዴ አለሁበት፤ ሌላ ጊዜ የለሁበትም ይላል፡፡
ዶ/ር መረራ በዚህ ‹‹ትብብር›› በሚል ስም ያወጣው መግለጫ ደግሞ አሁን በመድረክ ስም ካወጣው በይዘት የተለያየ ነው፡፡ በትብብሩ በኩል ያወጣው ሰነድ፤ ‹‹ጠ/ሚኒስትሩ የአንድ አመት ጊዜ ተሰጥቶት ይምራ፣ ውጭ ጉዳይና መከላከያን በሚመለከት ተቃዋሚዎች ሁሉ አባል የሆኑበት አመራር ይዋቀር›› የሚል ሰፊ አንደምታ ያለው መግለጫ ነው፡፡ ኦፌኮ  ሲፈልግ “የብሄራዊ አንድነት መንግሥት” የሚል በመድረክ ስም እያወጣ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ ነገር እያለ እንዴት አድርገን ነው የምንዘልቀው? ችግር ፈጥሮብናል፡፡ ይሄ አካሄድ እንዲታረም እንፈልጋለን፡፡ የኦፌኮ እዚህም እዚያም የማለት ነገር በጣም ስላሳሰበን ነው ራሳችንን የዚህ ሰነድ አካል አይደለንም ብለን መግለጫ ለማውጣት የተገደድነው፡፡
መድረክ ውስጥ ያለ ፓርቲ ሌላ ጥምረት በተናጠል እንዲቀላቀል ሕገ ደንባችሁ ይፈቅዳል?
በፊት እንዲህ ያለ ጥምረትን የመድረክ ሕገ ደንብ አይፈቅድም ነበር፡፡ በመድረክ ውስጥ ያለ ድርጅት ከሌላ ጋር ተዋህዶ ወደ መድረክ ያመጣዋል እንጂ ሌላ ቅንጅት ወይም ጥምረት በጎን መፍጠር አይቻልም ነበር በኋላ አዲሱ የለውጥ መንግሥት የሚባለው ከመጣ በኋላ ግን በየክልሉ ያለውን መቧደን መነሻ በማድረግ፣ ሕገ ደንቡ ተከልሶ ይሄን አይነቱን ጥምረት በክልል ደረጃ ማድረግ ይችላሉ የሚል ማሻሻያ ገባበት፤ በክልል ማለት ለምሳሌ የዶ/ር መረራ ፓርቲ በጎን ከኦሮሚያ ፓርቲዎች ጋር ትብብር መፍጠር ይችላል፡፡ አሁን ግን ከዚያም አልፎ አገር አቀፍ ትብብር ውስጥ ነው የገባው፡፡ ይሄ ሕገ ደንባችንን ይጥሳል፡፡ ሕዝቡንም ግራ ማጋባት ነው፡፡
ከዚህ በኋላ የመድረክ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
እስካሁን እኛ በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ነው ይሄን እንቅስቃሴ እያደረግን ያለነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በመድረክ ስለሚኖረን ዘላቂ አባልነትም ሆነ ራስን የማግለል ጉዳይ የሚወሰነው በፓርቲያችን ማዕከላዊ ም/ቤት ነው፡፡ አሁን መድረክ ሳንካ ውስጥ ገብቷል፡፡ በአንድ መንፈስ እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ አባል ድርጅቱ ከሌሎች ጋር በማናውቀው ሁኔታ እየተቧደነ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ ስለዚህ የወደፊቱን ሁኔታ የሚወስነው የኛ ፓርቲ ማዕከላዊ ም/ቤት ስብሰባ ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን እኛ ክርክራችንን ይዘን እንቆያለን፡፡ መድረክ ሲነሳ ብዙ ነገር ተስፋ አድርጎ ነው የተነሳው። ብዙ ዋጋ የተከፈለበት፤ የዕውቀት ልፋት የተደረገበት ነው፡። መድረኩን እዚህ ለማድረስ ብዙ ለፍተናል፤ በግልም በድርጅትም የለፋነውን ህሊናችን ያውቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ ሁኔታ አጋጥሞታል፡፡
በቀጣይ በአገሪቱ ምን አይነት የፖለቲካ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል? የቢሆን ግምቶችዎን ሊነግሩን ይችላሉ?
አንደኛ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትዕግስት ባያጡ ጥሩ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ሙሉ ለሙሉ ተአማኒነት ያለው መንግሥት ተቋቁሞ አያውቅም፡፡ ይህቺ አገር እጣዋ ሆኖ አንዱ ወደ ሌላ በሀይል እየተላለፈ እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁን ያለው ጥያቄ ደግሞ ከፊታችን ያለውን ምርጫ እንዴት አድርገን እናካሂድ የሚለው ነው፡፡ ከኢህአዴግ የበቀለው ብልፅግና ፓርቲ ደግሞ ‹‹እዚያ አደርሳችኋለሁ›› እያለ ነው፡፡ አሁን ያለው መንግሥት  ጠንካራ ነው፤ ዝም ብሎ ሊወድቅ እየተንገዳገደ ያለ መንግሥት አይደለም፡፡ አገራችን ደግሞ በዚህ ወቅት አለማቀፍ የወረርሽኝ ስጋት ተጋርጦባታል፡፡ ሌሎችም ተግዳሮቶች አሉ:: ስለዚህ የበለጠ ጠንካራ መንግሥት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነው ያለው፡። አሁን ያለው ኢትዮጵያም መልክ የያዘ መንግሥት በሥልጣን ላይ ቆይቶ ምርጫው በሰከነ መልኩ እንዲካሄድ አስፈላጊውን እገዛና ግፊት ማድረግ ነው ያለብን እንጂ ይሄ የአለም መጨረሻ ይመስል “መስከረም 30 ሲደርስ መንግሥት የለም፣ አገር የለም” የሚባል አይነት ጨለምተኛ አቋም የምንወስድበት ምክንያት አይገባኝም:: የሽግግር መንግሥት የሚባለውስ በየትኛው ተሞክሮ ነው? ይሄ ያላዩት አገር የማይናፍቃቸው ሰዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ ይመስለኛል፡፡ እኔ በሽግግር መንግሥት ውስጥ ያለፍኩ ሰው ነኝ፤ በሽግግር መንግሥትን ከተደራደሩት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ያኔም ብዙ ለፍተናል፤ ብዙ ጥንቃቄ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ የፖለቲካ ጽንፈኛ ፍላጎት ያላቸውን ለማግባባት ሞክረናል፤ ግን ውጤታማ አልሆነም፡፡ ያ የሽግግር መንግሥት ያልነው አንድ ወር እንኳ አልቆየም ችግሮች ሲከሰቱ:: ጉልበተኛው ኢህአዴግ ብትንትናችንን ነው ያወጣው፡፡ ግማሹ ተሰደደ፤ ግማሹ ከሃላፊነት ተባረረ፡፡ የሽግግር ም/ቤት ተሞክሯችን ውጤታማ አይደለም። አገራችንን ለዚህ አይነት ፈተናዎች ማጋለጥ ማለት ከታሪክ አለመማር ነው፡፡
ስለዚህ እንረጋጋ፡፡ ምርጫ ከምንለው አለፍ ብለን አገርንም እንይ፡፡ የምርጫ ምህዳሩ እንዲስተካከል እየታገልን ነው መቆየት ያለብን:: መፍትሄ በዚህ መንገድ ነው መፈለግ ያለብን:: ከዚህ ባለፈ ያሉ አማራጮች ግን አገሪቱን ችግር ውስጥ የሚከቱ ከቁጥጥር የወጡ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ትንሽ ሰከን ማለት መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ የምርጫ ምህዳር ይስተካከል የሚለውን ግፊት እየፈጠርን ነው ተረጋግተን መጠበቅ ያለብን፡፡ ከዚህ በላይ አልፈን ፖለቲካውን ከነቀነቅን ውጤቱን መተንበይ ያስቸግረኛል፡፡ የኛ ፓርቲ ትዕግስት አያጣም፤ ሌሎችም በዚህ መጠን ቢታገሱ ውጤቱ ጥሩ ይሆናል። አሁን አገር እየመሩ ያሉት በኢትዮጵያ ስም ነው፡፡ እኛም የምንቀሳቀሰው በኢትዮጵያ ስም ነው፡፡ ሁሉም ለኢትዮጵያ መልካም እሰራለሁ ነው የሚለው፡፡ ከዚህ ውጪ ራስን የተለየ አድርጎ መመጻደቅ አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ ተረጋግተን፣ ሁላችንም አብረን መፍትሄ እንፈልግ እላለሁ፡፡              



Read 2193 times