Saturday, 30 May 2020 11:42

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የማሻሻያ ሀሳቦች አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት እንዳይገደብ ስጋት አለኝ ብሏል

                የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል እየተተገበረ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ከሰብዓዊ መብት አንፃር የማሻሻያ ሀሳቦች አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ በዋናነት ከቆመለትና አገሪቱ ከፈረመቻቸው አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ድንጋጌዎች ጋር በቀጥታ ይጋጫሉ ያላቸውን የአዋጁን ድንጋጌዎች ይፋ አድርጎ የሚስተካከሉበትን መንገድም ጠቁሟል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠንካራ ጎን ተብለው ከተጠቀሱት መካከልም፡- ለአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው የሕግ ማዕቀፍ መኖሩ፣ መርማሪ ቦርድ መቋቋሙ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው በሲቪል አስተዳደር እንዲመራ መደረጉ ይገኙበታል፡፡
በአዋጁ ዋነኛ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ስጋቶች ተብለው ከተዘረዘሩትና ማስተካከያ ቢደረግባቸው ከተባሉት ድንጋጌዎች መካከል ለተለጠጠ ትርጉም የተጋለጡ ድንጋጌዎች መቀመጣቸው፣ በአይነትና ክብደታቸው ሰፊ ልዩነት ያላቸው የጥፋት አይነቶች፣ አንድ አይነት ቅጣት እንዲፈፀምባቸው መደንገጉና ለሁሉም እስከ 3 ዓመት እስር ማስቀጣቱ እንዲሁም እስከ 2 መቶ ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት መደንገጉ የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡ የኮቪድ 19ን በሚመለከት የግላዊ ሕይወት  መብትን የሚጥሱ ሁኔታዎችን፡- ለምሳሌ የታማሚዎችን የግል ምስጢር አለመጠበቅ፣ ለአድልኦ ሊዳርጉ የሚችሉ የቅጣት ድንጋጌዎች መቀመጣቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡
የግል ንብረትን መውሰድን በተመለከተ ለመንግሥት በመመሪያው ሙሉ ስልጣን መሰጠቱም ተገቢ እንዳልሆነ ይገልጻል - ኮሚሽኑ፡፡ በመናገርና የሚዲያ ነፃነት ላይ ጥብቅና አላስፈላጊ ጫና የሚያሳድሩ ድንጋጌዎች በአዋጁ በመመሪያ መቀመጡ፣ የፍትሃብሄር ጉዳዮች ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ሊታገዱ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ፣ የእስረኞችን ጉብኝት በተመለከተ የተቀመጡ ጠቅላላ ክልከላዎች፣ የንግድ ነፃነት ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ጫና የሚጥሉ ድንጋጌዎች ከላይ ጉድለት ብሎ ለጠቀሳቸው ጉዳዮችም የማስተካከያ ምከረ ሀሳቦችን ኮሚሽኑ ያቀረበ ሲሆን ለእያንዳንዱ ጥፋት ተመጣጣኝ ቅጣት በዝርዝር ማዘጋጀት እንደሚገባ፣ አነስተኛ የደንብ መተላለፎችን አስተምሮና መክሮ ማለፍ ቢቻል፣ ኮቪድ 19 አለበት ተብሎ የተጠረጠረን ሰው መጠቆም ግዳጅ የመሆኑ ጉዳይ ሰዎችን ለበቀል ጥቃትና ማሳደድ የሚያጋልጥ በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግበት፣ ለኮቪድ መከላከል ስራ የግል ንብረትን መውሰድን በተመለከተ ለመንግሥት የተሰጠው የተለጠጠ ስልጣን እንዲሻር ወይም እንዲሻሻል፣ በሌሎች ድንጋጌዎች ላይም ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ኮሚሽኑ በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችም በከፊል በጥንቃቄ የሚጎበኙበት ሁኔታ እንዲመቻችም ኮሚሽኑ በማሻሻያ ሰነዱ ጠይቋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር የሰብአዊ መብትን የሚጥሱ ሁኔታዎች እንደ የታማሚዎችን የግል ሚስጥር አለመጠበቅ፣ ለአድልኦ ሊደረጉ የሚችሉ የቅጣት ድንጋጌዎች መቀመጣቸውንም ኮሚሽኑ ጠቅሷል - በሰነዱ፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር ምክንያት በተለይም በአነስተኛ የንግድ ስራ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የኢኮኖሚ ማነቃቂያና ማህበረሰባዊ እገዛ የሚደረግባቸው መንገዶችም ሊመቻቹ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ባቀረበው ምክረ ሀሳብ ጠቁሟል፡፡  

Read 1057 times