Saturday, 30 May 2020 11:54

የህዳሴ ግራንድሞል አክሲዮን ባለድርሻዎች፣ ተጭበርብረናል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  “በ6 ወር ሥራ ይጀምራል የተባለው ኩባንያ በ3 ዓመት ሙሉ የውሃ ሽታ ሆኗል”

               ከ3 አመት በፊት የተመሠረተው ህዳሴ ግራንድ ሞል አክሲዮን ማህበርን ለማቋቋም ከእያንዳንዳቸው የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደደረሰ እንደማያውቁና ህጋዊ የአክሲዮኑ ባለቤት መሆን የሚችሉበትን ውልም እስከ ዛሬ መዋዋል እንዳልቻሉ ባለአክሲዮኖች ገለፁ፡፡
“ገንዘባችንን ተጭበርብረናል፣ በ6 ወር ውስጥ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ የነበረው ድርሻ የገዛንበት ኩባንያም ላለፉት 3 ዓመታት የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል” ሲሉ ለአዲስ አድማስ የተናገሩት ባለ አክሲዮኖቹ፤ የአክሲዮን ሽያጩን ያከናወኑ ግለሰቦችንም በቢሮአቸው ማግኘትና ጉዳዩ የደረሰበትን እንኳ ማወቅ አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከ3 አመት በፊት ህዳሴ ግራንድሞል አክሲዮን ሲመሠረት እያንዳንዳቸው ከ2 መቶ ሺህ ብር በላይ በመክፈል የአክሲዮን ድርሻ መግዛታቸውን የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ገንዘባቸውን በባንክ ገቢ ካደረጉ በኋላ ግን አደራጆቹን እስከ ዛሬ ማግኘት እንዳልቻሉና የባለአክሲዮኖች ስብሰባም ተደርጐ እንደማያውቅ ተናግረዋል::
“የአክሲዮን ድርሻ የገዛንበትን ደረሰኝ ብቻ በእጃችን ይዘን ተቀምጠናል” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ በህጉ መሠረት ወደ ውልና ማስረጃ ሄደን የአክሲዮኑ ድርሻ ባለቤቶች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ፊርማ መፈረም ሲገባንም እስካሁን ያንን ማድረግ አልተቻለም ብለዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት ገንዘቡ ይኑር አይኑር የምናውቀው ነገር የለም” ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ “በ6 ወር ይጠናቀቃል ለተባልነው ኩባንያ እውን መሆን 3 አመት ታግሰን መፍትሔ በማጣታችን በቅርቡ ክስ ለመመስረት ዝግጅት እያደረግን ነበር፤ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት አደናቀፈን እንጂ” ብለዋል፡፡
ገንዘቡን የሰበሰቡ አካላት አክሲዮኑን እያደራጀን ነው፤ ከአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት እየጠየቅን ነው ታገሱ የሚል ምላሽ በተወካዮቻቸው አማካይነት ሲሰጧቸው እንደቆዩ የሚገልፁት የአክሲዮን ባለድርሻዎቹ፤ አክሲዮኑን በሚያደራጁበት ወቅት ግን በ6 ወር የሚያልቅ መሆኑንና መሬቱም መዘጋጀቱን እንደነገሯቸው ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ገንዘባችን ለ3 አመታት አየር ላይ ቀርቶብናል የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ገንዘባችንን ያስመልስልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሸምሰዲን አብዱራህማን በበኩላቸው፤ ኩባንያው እውን የሚሆንበት ጊዜ ዘግይቷል የሚለው የባለአክሲዮኖች ቅሬታ ተገቢነት ያለው መሆኑን፣ ነገር ግን መዘግየት ያጋጠመው ለከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው የሚቀርቡ የመሬት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ነው ይላሉ፡፡
መንግስት ፕሮጀክቱን በቀናነት ተመልክቶ ሊረዳን ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የባለስልጣናት መቀያየር ሂደቱን አዘግይቶብናል የሚሉት አቶ ሸምሰዲን ባለአክሲዮኖች ጉዳዩን በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጠይቀዋል፡፡
የባለአክሲዮኖች ገንዘብ የተሠበሰበው በዝግ አካውንት መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ “ገንዘባችን የት እንደደረሰ አናውቅም የሚለው ቅሬታ ሊነሳ የሚችል አይደለም” ብለዋል፡፡
እስካሁን ገንዘባችን ይመለስ የሚል ጥያቄ ከባለአክሲዮኖች በይፋ ቀርቦ እንደማያውቅ ጠቁመው፤ እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚቀርብ ከሆነም ጉዳዩ በጠቅላላ ጉባኤ ውሣኔ የሚያገኝ እንጂ በስራ አስኪያጆች የሚወሰን አይደለም ብለዋል፡፡ እኛ ከቢሮአችን የትም ሄደን አናውቅም፤ ቢሮም የቀየርነው ቀድሞ የነበርንበት ዋጋው ውድ በመሆኑ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ተሰውረውብናል የሚለውም መሠረተ ቢስ ቅሬታ ነው፤ የትም አልሄድንም ብለዋል፡፡ ባለድርሻዎች የአክሲዮን ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጥ ፊርማ ማስፈረም ያልተቻለውም በሰው ሃይል እጥረት መሆኑን አቶ ሸምሰዲን አብዱራህማን ገልፀዋል፡፡  


Read 12085 times