Print this page
Saturday, 30 May 2020 11:55

በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር በአፍሪካ ማዕቀፍ ብቻ እንዲከወን “አብሮነት” ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚደረግ ድርድር በአሜሪካ መንግሥት ተቋማት አደራዳሪነት ሳይሆን አፍሪካዊ በሆነ ማዕቀፍ ብቻ እንዲከወን አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) ጠየቀ፡፡
አብሮነት ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው፤ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል እንዲቀጥል ስምምነት የተደረሰበት የድርድር ሂደት ከምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት በፀዳ መልኩ፣ በአፍሪካዊ ማዕቀፍ መደረግ ይገባዋል ብሏል፡፡ በቀጣይ በሶስቱ አገራት መካከል ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር በከፍተኛ ጥንቃቄ፣ በሳል ዲፕሎማቶችን ባሳተፈ መልኩ እንዲመራ የጠየቀው አብሮነት፤ ድርድሩ ሊደረግ የሚገባውም በውሃ ክፍፍል ጉዳይ ላይ ሳይሆን በግድቡ የውሃ አሞላል ጊዜ ላይ ብቻ መሆን እንዳለበት ጠቁሟል፡፡
ግድቡን በውሃ የመሙላት መብትም ከድርድሩ መጀመር ወይም ከድርድሩ መሳካት ጋር እንዳይያያዝ፣ በማንኛውም ጊዜ የመሙላት መብታችንን አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስቧል - አብሮነት::
ከአሁን በኋላ በግድቡ ላይ የሚደረጉ ድርድሮችንም በችኮላና በተድበሰበሰ መልኩ ሳይሆን በግልጽነት፣ በአሳታፊነትና ተቋማዊ በሆነ አሰራር እንዲከወን የጠየቀው አብሮነት፤ ድርድሩ በአፍሪካዊ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካሄድ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ አደራዳሪዎች ለግብጽ ወገንተኛ አለመሆናቸውን ማረጋገጥም እንደሚገባ መክሯል፡፡
በሌላ በኩል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ከሰሞኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ድርድሩን ከሚመሩተ አካላት ጋር ባካሄደው ስብሰባ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ከብሄራዊ ጥቅም አንፃር ከመንግሥት ጎን እንደሚሰለፉ አረጋግጧል::
የግድቡን ብሄራዊ ጥቅም ተፃርረው የሚቆሙ ፓርቲዎች ላይም የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰዱና በይፋ ለሕዝብ እንዲጋለጡ እንደሚደረግ አስገንዝቧል፡፡


Read 11200 times