Saturday, 30 May 2020 12:02

በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል አስቸኳይ ውይይት እንዲደረግ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ (ህወኃት) መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ መካረር በአስቸኳይ ውይይት እንዲፈታ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ መካከል እየተፈጠሩ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶችና መካረሮች ሀገሪቱን ወደ ግጭት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ለአዲስ አድማስ የገለፁ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ልዩነትን ለመፍታት በሁለቱ አካላት መካከል ውይይት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
የባይቶና አመራር አባሉ አቶ ክብሮም በርሄ በሰጡት አስተያየት፤ …በሁለቱም ወገኖች የሚስተዋሉ ማስፈራሪያዎችና እልሆች ቆመው ችግሮች በውይይት በይቅርታና በእርቅ ሊፈቱ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ችግሩ ሠፍቶ ሀገሪቱ ማንም አሸናፊ ወደ ማይሆንበት ግጭት እንዳትገባ ከፍተኛ ስጋት አለ›› ብለዋል፡፡
የአረና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተክለእዝጊ ወ/ገብርኤል በበኩላቸው፤ በፌደራልና በክልሉ መንግስት መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ብቸኛው መፍትሔ ውይይትና መነጋገር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ጦርነትን አይፈልግም፤ ጦርነት ሰልችቶታል፤ ሰላም ነው የሚፈልገው›› ያሉት አቶ ተክለእዝጊ፤ ‹‹ሁለቱም ወገኖች በእርጋታ ወደ ውይይት የሚያመሩበት እድል መፈጠር እንዳለበት›› ጠቁመዋል፡፡
ከትግራይ ቲቪ ጋር ከሰሞኑ በዚሁ ጉዳይ ላይ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር በኋላም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ በሰጡት አስተያየት፤ ‹‹ጦርነትን ማንም ሊጀምረው ይችላል፤ የሚጨርሰው ግን አይታወቅም፤ ስለዚህ ዋነኛ መፍትሔው ውይይት ነው›› ብለዋል፡፡ በእልህና ሰዶ በማሳደድ የሚደረጉ የፖለቲካ አካሄዶች የትም እንደማያደርሱ ያስገነዘቡት አቶ ስዬ፤ ሁለቱ አካላት ቆም ብለው ወደ ውይይት የሚመጡበትን መንገድ እንዲያስቡ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም በፌደራል መንግሥቱና ትግራይን በሚያስተዳድረው ህወኃት መካከል የተፈጠሩ የፖለቲካ ቁርሾዎች በውይይት መፈታት እንዳለበት አበክረው የሚያምኑ አንዳንድ ምሁራንና ፖለቲከኞች፤ ራሳቸው ወደ ውይይት ለማምራት የሚቸገሩ ቢሆን እንኳን በአሸማጋዮች አማካይነት ወደ ንግግር መምጣት እንዳለባቸው ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡


Read 23105 times