Saturday, 30 May 2020 12:55

‹‹የበለጠ ንቃት፤ የበለጠ ጥንቃቄ፤ የበለጠ ሃላፊነት ይጠበቅብናል››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - አዲስ አበባ ውስጥ በማህበረሰብ ደረጃ ስርጭት እንዳለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል እንዴት?
     - ሳንዘናጋ ከተጠነቀቅን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር እንቀንሳለን፤ መዘናጋቱ ከቀጠለስ? … ከዚያም የባሰ ብዙ ሰዎች ይጠቃሉ
    - በሀዘንም በደስታም ሰዎች እንደቀድሞው ሰላም ነው ብለው ከተገናኙ የአብነት አካባቢ ሁኔታ ይፈጠራል፤ በአንድ ሰው ምክንያት ብዙ ሰዎች
     ይያዙና ሙሉ መንደር ወደ መዘጋት ይደረሳል
         የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተግባሩ ይግዛው በሰሞኑ የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ሥርጭትን አስመልክተው በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ መንስኤውንና ውጤቱን በጥልቀት ይተነትናሉ፡፡ በቀጣይ ሳምንታት ምን ሊመጣ ይችላል? ለሚለውም ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ አነጋግራቸዋለች፡፡

               ቫይረሱ በማህበረሰቡ እየተሰራጨ ነው
በተላላፊ በሽታ ሰዎች ህመም የሚያሳዩት ወይም በላብራቶሪ ምርመራ በሽታው የሚገኝባቸው በአብዛኛው ለበሽታው ከተጋለጡ ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስን ስንመለከት ያለው ነገርም ይሄ ነው፡፡ አሁን በበሽታው ተይዘው እያገኘናቸው ያሉ ሰዎችም ከአንድና ከሁለት ሳምንት በፊት የተጋለጡ ናቸው፤ አንድ ሰው ዛሬ ተጋልጦ ዛሬውኑ ምልክት አያሳይም፡፡ በላብራቶሪም ቢመረመር በሽታው አይገኝበትም፡፡ እንግዲህ አሁን ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ተጠቂዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታትና 10 ቀናት ገደማ ለበሽታው የተጋለጡ ናቸው፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው ስንል፤ ባለፈው አንድ ወር የተዘናጋነው በሚገባ ያላደረግነው ነገር ውጤት ነው ለዚህ ያበቃን፡፡ ከዚህ ተነስተንም ሁለት ነገሮችን ነው የምንገነዘበው፡፡ ትክክል ነው፤ ከዚህ በፊት አይተነው በማናውቀው ሁኔታ፣ ባለፈው ሳምንትና 10 ቀናት በየቀኑ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ ነው፡፡ ይሄ አንድ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከበፊቱ የተሻለ እየመረመርን ነው፡፡ በቁጥር ደረጃ ማለት ነው፡፡
በአንድ በኩል ቫይረሱ በማህበረሰቡ እየተሰራጨና ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል እያደረሰ እንደሆነ፣ በቁጥርም ደረጃ ድምፁን አጥፍቶ ከገመትነው በላይ ሰዎች በቫይረሱ እየተጠቁ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ይሄ በአንድ በኩል ቫይረሱ አደገኛ ስለሆነ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እያደረግን ያለነው የጥንቃቄ እርምጃ የቫይረሱን የመተላለፍ አቅም የሚመጥን አይደለም:: ይሄንን ደግሞ በተግባር እያየነው ነው፡፡ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ነው የመዘናጋትና በሽታው የለም እንዴ?›› ወደሚል ጥርጣሬና እኛን አይጎዳንም ወደ ማለት በማዘንበል በመንገድ ላይ፣ በገበያ ቦታ አሁን በቅርቡ ደግሞ ተዘግተው የነበሩ የእምነት ተቋማት ተከፍተዋል፣ በትራንስፖርቱም ሆነ በሁሉም ቦታ መደረግ ያለበት መሰረታዊ ነገር በደንብ እየተደረገ አይደለም፡፡ ዋናው የቫይረሱ መተላለፊያ አካላዊ ቅርርብ ነው:: ስለዚህ ከመዘናጋታችንና በሚገባ መደረግ የነበረበትን ባለማድረጋችን ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እርግጥ ነው የተወሰኑ መልካም ነገሮችም አድርገናል፡፡ መሀል ላይ ለቀቅ ስንልና መዘናጋት ስንጀምር ቫይረሱ ድምፁን አጥፍቶ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን ያሳያል፡፡
በቀጣዮቹ ሳምንታት ምን ይጠበቃል?
ከዚህ ተነስተን በቀጣይ ምን ይመጣል ስንል፣ የሚመጣው ነገር በምናደርገው ጥንቃቄና በምንሰራው ሥራ ይወሰናል፤ ስለዚህ መዘናጋቱን ትተን ጥንቃቄውን ዛሬ ነገ ሳንል መተግበር ይገባናል፡፡ በህብረተሰብ ጤና ሳይንስ የሚሰጡትን የመከላከያ እርምጃዎች ሰው ሀላፊነቱን ተረድቶ ከተገበ መንግሥት ደግሞ እነዚህ ነገሮች በአግባቡ መፈፀማቸውን ከተከታተለ፣ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር መግታት እንችላለን:: ቫይረሱን ባናጠፋው እንኳን መቀነስ እንችላለን፡፡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርና ታመው የሚተኙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ ወረርሽኙን እየተቆጣጠርነው እንሄዳለን፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ምን ይፈጠራል ለሚለው፣ በቀጣይ ምን እንሰራለን የሚለው ይወስነዋል፡፡ ባለፈው አንድ ሳምንት ምንድን ነው የሰራነው? በዚህስ ሳምንት ምን እንሰራለን? በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ሳምንታት ምን እንሰራለን? ጥሩ ሥራዎች ከሰራን የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር እንቀንሳለን፣ መዘናጋቱ ከቀጠለ ከዚህም የባሰ ብዙ ሰዎች ይጠቃሉ፡፡ ስለዚህ የወረርሽኙን እድገት የሚወስኑት እኛ የምንወስዳቸው እርምጃዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የላብራቶሪ ምርመራ አቅማችን እያደገ ሲሄድ አሁንም የተለየ ውጤት ልናይ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር አሁን ሪፖርት የሚደረጉት ብቻ ናቸው ብለን አናምንም፣ ምናልባት ከዚህ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ግን ያልተመረመረና ቫይረሱ ያለበት ሰው ይኖራል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ ነው የመመርመር አቅማችን ሲያድግ የተለየ ውጤት ልናይ እንችላለን የምለው፡፡ ብዙ ቁጥር የማግኘት ዕድል እንደሚኖር ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ለምሳሌ ትላንት ከ5 ሺህ በላይ (5015) መርምረን 137 ተገኝቷል፤ የምርመራ አቅማችን ወደ 10 ሺህና ከዚያ በላይ ሲደርስ የምናገኘውም የተጠቂ ቁጥር ከፍ እያለ ስለሚሄድ፣ ትርጓሜ ስንሰጥ ይሄንንም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ሥርጭቱ ወደ ማህበረሰብ ደረጃ አድጓል?
ሥርጭቱ ወደ ማህበረሰብ ስርጭት አድጓል ወይ? አዎ ይህ ግልጽ ነው፡፡ ቢያንስ አዲስ አበባ ውስጥ በማህበረሰብ ደረጃ ሥርጭት እንዳለ በደንብ ይታያል፡፡ ለዚህ ማስረጃዎቹ ደግሞ አብዛኞቹ በሽታው ከማን እንደያዛቸው ራሱ አያውቁም፡፡ ማህበረሰባዊ ሥርጭት አለ የምንለው አንደኛ በርከት ያሉ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ስናገኝ፣ ሁለተኛ እነዚህ ሰዎች ከማን እንዳገኙት እንኳ ማወቅ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ አሁን’ኮ ማንኛውም ሰው በሽታው አየር ላይ ዝም ብሎ አይደለም የሚይዘው፤ ከሰው ነው ነገር ግን ከየትኛው ሰው እንደያዘው መለየት ካልቻለ፣ የበሽታው ስርጭት በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት እንዳለ ያሳየናል፡፡
የአካባቢ መዘጋትን (Lock down) በተመለከተ በመንደር ብቻ ሳይሆን ሆነ በከተማ ደረጃም ሆነ በአገር ደረጃ ይዘጋል ይህን ያልተገበርነው እኛ ብቻ ነን:: ለምሳሌ ቻይና ቫይረሱ የተቀሰቀሰበትን ከተማ የውሃንን እንቅስቃሴ በመገደብ ነው ቫይረሱን መቆጣጠር የቻለችው:: ምክንያቱም በሽታው ያለባቸው ሰዎች እዛ ነው ያሉት፡፡
ሰዎች ከዚያ ከተማ እንዳይወጡ እንዳይገቡ ከተደረገ ሁሉም ቤቱ እንዲቆይ ከተደረገና የታመሙትን ሰዎች ቶሎ መርምሮ በመለየት ለሌላ እንዳያዛምቱ ማድረግ እንዲሁም ሌላው ሰው በበሽታው እንዳይጠቃ ራሱን ጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ይታወቃል፡፤ ከባድ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከትላል፤ ግን ወረርሽኝን ለመግታት ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም፡፡ በሌላ መንገድ ስታይው፤ ሰዎችን ለይቶ ማቆያ ለሁለት ሳምንት ስናቆያቸው፣ በዚያ ጊዜ ውስጥ ወይ ይታመማሉ ወይም በላብራቶሪ ምርመራ በሽታው እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ይረጋገጣል ያልተገኘባቸው ወደ ሕዝቡ ይቀላቀላሉ፡፡
ከአብነቱ መንደር መታጠር የምንማረው?
አሁን ህብረተሰቡ መገንዘብ ያለበት፣ የአብነቱ መንደር መታጠር ትልቅ ተሞክሮ ሊሰጠን ይገባል፤ አሁን ቫይረሱ ማን እንዳለበት፣ ማን እንደሌለበት፣ አይታወቅም:: አብዛኛው ሰው ምልክቱ ስለማይታይበት መንገድ ላይ ይንቀሳቀሳል:: ስለዚህ ሰዎች በሀዘንም በደስታም እንደ ቀድሞው ሰላም ነው ብለው ከተገናኙ ልክ አብነት አካባቢ እንደተፈጠረው በአንድ ሰው፣ ብዙ ሰው ይያዝና ወደ መዘጋት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ይሄ ደግሞ ብዙ አገሮች ላይ ተከስቷል፡፡ አሜሪካም ጣሊያንም ውስጥ ተከሰቷል፡፡ ደቡብ ኮሪያም ተስተውሏል፡፡ አንድ ሰው የእምነት ተቋም ላይ ሄዶ፣ ሌላ ቦታ ለቅሶ ላይ፣ አሜሪካ በስራ ቦታ - የስጋ ማቀነባበሪያ ውስጥ አንድ ሰው በመያዙና ጥንቃቄ ባለመደረጉ በኋላ ከ600 በላይ ሰዎች እንዲያዙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይሄ ትምህርት ሊሆነን ይገባል፡፡ ይሄ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ሰዎች ለሰርግም ሆነ ለሀዘን፣ ማህበራዊ ሁኔታዎች የሚያስገድዱን እንኳ ቢሆን፣ ጊዜው እንደማይፈቅድልን ተንዝበው ርቀትን መጠበቅ፣ ንክኪን ማስወገድ፣ እጅን መታጠብ፣ አፍና አፍንጫን ሁሌም ከቤታቸው ሲወጡ መሸፈን በጣም አስገዳጅ ካልሆነ ከቤት አለመውጣት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የሚያስከፍለን ማህበራዊ ዋጋ ቢኖረውም ያለነው አስቸጋሪና ክፉ ጊዜ ላይ ነውና አጠቃላይ ህይወታችን ጊዜውን በሚመጥን ጥንቃቄ መመራት አለበት፡፡ ይን ጊዜ ካለፍን ወደ ወትሮው ወደ ለመድነው እንቅስቃሴያችን እንመለሳለን፡፡ አፅንኦት መስጠት የምፈልገው ‹‹ፒክ›› የሚባለው ጊዜ መቼ ይመጣል ለተባለው፤ ቀድመን በምንሰራው ስራ የሚወሰን ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ የበለጠ ንቃት፤ የበለጠ ጥንቃቄ፤ የበለጠ ሀላፊነት ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ካደረግን ጊዜውንም ማዘግየት የተጠቂውን ቁጥርና የጉዳቱን መጠንም መቀነስ እንችላለን ለማለት እወዳለሁ፡፡



Read 1645 times