Saturday, 30 May 2020 13:42

አለም በኮሮና መፈተኗን ቀጥላለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ይህ ነው የሚባል አዲስ ተስፋ ሰጪ ነገር የለም… ሰከንዶችና ደቂቃዎች በተፈራረቁ ቁጥር፣ አለም አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ሞት መርዶዎችን እያደመጠች፣ አዳዲስ ተጠቂዎችን እየቆጠረች ቀናት መምጣት  መሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ አመሻሽ ላይ ይህን ዘገባ እስካጠናቀቅንባት የመጨረሻዋ ደቂቃ፣ ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም ከ5,833,766 በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፤  ከ358,426 በላይ የሚሆኑትንም ለሞት ዳርጓል፡፡ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 2,526,872 መድረሱን ወርልዶ ሜትር ድረገጽ ይጠቁማል፡፡  ባለፉት 44 አመታት በቬትናም፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታንና ኮርያ ጦርነቶች ካጣቻቸው ዜጎቿ አጠቃላይ ቁጥር በላይ ሰዎችን ባለፉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ  በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ባጣችው አሜሪካ፤የሟቾች ቁጥር ባለፈው ሐሙስ አመሻሽ 102,293 ሲደርስ፣ የተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ ከ1,750,377 አልፏል -  በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 30 በመቶ ያህሉ በአሜሪካ ይገኛሉ ማለት ነው፡፡ ኮሮና ቫይረስ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ዶክተሮችና ነርሶችን ጨምሮ ከ62 ሺህ በላይ የህክምና ባለሙያዎችን ማጥቃቱንና ከ291 በላይ የሚሆኑትንም  ለሞት መዳረጉን ሲኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡ በመሪዎቿ መዘናጋት የኮሮና ተጠቂና ሟች ዜጎቿ ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ በሚገኝባት ብራዚል፤ የተጠቂዎች ቁጥር 414,661 መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣  በአገሪቱ የሟቾች ቁጥር እስከ መጪው ነሃሴ ወር ድረስ 125 ሺህ ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት የተደረጉ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ ብራዚልን ጨምሮ በላቲን  አሜሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ፣ በአገራቱ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፋ ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ የተባበሩት  መንግስታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም ከትናንት በስቲያ ማስታወቁንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ሩስያ በ379,051፣ ስፔን በ283,849፣ እንግሊዝ በ267,240 ተጠቂዎች በአለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጠቂዎች የተመዘገቡባቸው ቀጣዮቹ ሶስት  አገራት መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንግሊዝ በ37,460፣ ጣሊያን በ33,072፣ ፈረንሳይ በ28,596፣ ስፔን በ27,118 ሟቾች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሞት  የተዳረጉባቸው አሜሪካን የሚከተሉ ቀዳሚዎቹ አራት የአለም አገራት እንደሆኑም ተነግሯል፡፡

የክትባትና የመድሃኒት ጉዳይ
ለኮሮና ቫይረስክትባትለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በአውሮፓ ህብረት አስተባባሪነት በአለማቀፍ ደረጃ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች 10 ነጥብ 4 ቢሊዮንዶላር ለማግኘት መቻሉን ዘጋርዲያን ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፤ኮሮና ቫይረስን ለማከም እንደሚረዳ በተነገረውና አወዛጋቢ ሆኖ በቀጠለው ክሎሮኪን የተባለው የወባ መድሃኒት ላይ ሲያደርግ የነበረውን ሙከራ፣ መድሃኒቱ ከደህንነት ጋር ተያይዞ አደጋ ሊያደርስ ይችላል በሚል ስጋት እንዲቋረጥ መወሰኑን ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡በመድሃኒቱ ላይ የሚደረገው ሙከራ እንዲቋረጥ የተደረገው መድሃኒቱ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን የመሞት እድል እንደሚጨምር በቅርቡ የወጣ አዲስ ጥናት መጠቆሙን ተከትሎ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፤ በመድሃኒቱ ላይ በተለያዩ ሀገራት የተጀመሩ ሙከራዎችም የሚቋረጡ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል ብሏል።
የአውሮፓ ህብረት አገራት መንግስታት፣ ዜጎቻቸው ይህንን መድሃኒት እንዳይጠቀሙ በህግ መከልከል መጀመራቸውንም አልጀዚራ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከብሪታኒያ በተውጣጡከአንድሺህበላይበጎፈቃደኞችላይሙከራ ያደረገበትን "ChAdOx1 nCoV-19" የተሰኘ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ክትባት፤ በቀጣይ ደግሞ በኬንያ ሊሞከር መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በአፍሪካም ቁጥሩ እያሻቀበ ነው
በአፍሪካ እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ124 ሺህ ማለፉን እና ከ3 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከ26 ሺህ በላይ ሰዎች የተጠቁባት ደቡብ አፍሪካ፤ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ቀዳሚዋ የአፍሪካ አገር ስትሆን፣ 797 ሰዎችን ያጣችው ግብጽ ደግሞ በሟቾች ቁጥር በአንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በዚምባቡዌ በአንድ ቀን ውስጥ የተመዘገበው በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ሐሙስ ከእጥፍ በላይ በመጨመር 132 መድረሱን የዘገበው አናዶሉ ኤጀንሲ፤በጋና ከሰሞኑ በርካታ የሕዝብተወካዮችምክርቤትአባላትና ሰራተኞች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ፣ አባላቱ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ፓርላማው ላልተወሰነ ጊዜ ተዘግቶ እንዲቆይ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ገልጧል፡፡
እስካለፈው ሐሙስ ድረስ ከ7ሺህበላይሰዎችበቫይረሱበተያዙባትና 34 ሰዎችበሞቱባት ጋና፤ምርመራከተደረገላቸውየፓርላማአባላትናሰራተኞችመካከልአስራ አምስቱበቫይረሱመያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ፣በርካታየፓርላማአባላትበቫይረሱሊጠቁይችላሉየሚልስጋትበመፈጠሩ፣ አባላቱ ፓርላማው እንዲዘጋናስብሰባበኢንተርኔትአማካኝነትእንዲደረግ ሃሳብ ማቅረባቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በማላዊ ከደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ተመልሰው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ እና በስታዲየም የሚገኘው የለይቶ ማቆያ የሚሰጠውአገልግሎትደረጃውን የጠበቀ አይደለም በሚል ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ የነበሩከ400 በላይሰዎችምርመራ ሳይደረግላቸው አምልጠው መጥፋታቸውን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፤ ሌሎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ የአገሪቱ ዜጎችም በተመሳሳይ ማምለጣቸውን አመልክቷል፡፡
የናይጄሪያውፕሬዚዳንትሙሐመዱቡሃሪ፣የኮሮና ቫይረስወረርሽኝበፈጠረውችግር ሳቢያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የገጠመው የአገሪቱ መንግስት፤ ከውጭ አገራት ምግብ ገዝቶ ማስገባት የሚችልበት ገንዘብ እንደሌለው ከሰሞኑ ያስታወቁ ሲሆን የአገሪቱአርሶአደሮችሕዝቡንመቀለብ የሚችልምግብበበቂ መጠንእንዲያመርቱጥሪ አቅርበዋል፡፡
በካርቱም በሚገኝ ወህኒ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን ማሳየታቸውን ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕ ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን የዘገበው ዳባንጋ ድረገጽ፣ አብረዋቸው ታስረው የነበሩ 3 የቀድሞ ሚኒስትሮች ቫይረሱ እንዳለባቸው መረጋገጡንና ሌሎች 3 ሰዎችም በጸና መታመማቸውን አመልክቷል፡፡
የዛምቢያ የጤና ሚኒስትር በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው በምርመራ መረጋገጡን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከትናንት በስቲያ የዘገበ ሲሆን የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትርም ባለፈው ሳምንት በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን አስታውሷል፡፡

ንግድና ኢኮኖሚ
የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በፈረንጆች አመት 2020 በአማካይ እስከ 12 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ እንደሚያጋጥመው አስታውቋል፡፡
የተመድ የቱሪዝም ድርጅት በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፣አለማቀፉ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እ.ኤ.አ ከ1950ዎቹ ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ግዙፍ ቀውስ ውስጥ መግባቱንና ከመስኩ የሚገኘው ገቢ በዚህ አመት በ70 በመቶ ያህል ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡ባለፈው ሚያዝያ ወር ወደ እንግሊዝ በአውሮፕላን የገቡ መንገደኞች ቁጥር ካለፈው ወር በ99 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የዘገበው ዘጋርዲያን፤ በተጠቀሰው ጊዜ ወደ አገሪቱ የገቡት መንገደኞች ቁጥር 112 ሺህ 300 ብቻ መሆኑን አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ባለፉት 11 አመታት ታሪኩ ከፍተኛው የገቢ ማሽቆልቆል ያጋጠመው ታዋቂው የመኪና አምራች ኩባንያ ኒሳን፤ በኢንዶኔዢያና በስፔን ያሉትን ፋብሪካዎች ሊዘጋ መወሰኑን ከሰሞኑ ይፋ ማድረጉ ተነግሯል፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኩዌት አየር መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ገቢው በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ሳቢያ ከአጠቃላይ ሰራተኞቹ ሩብ ያህሉን ወይም ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑትን ከስራ ለመቀነስ መወሰኑን የዘገበው አልጀዚራ፤የእንግሊዙ አየር መንገድ ኢዚጄት በበኩሉ 30 በመቶ ሰራተኞችን እንደሚቀንስ ማስታወቁን አመልክቷል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ 7 ሺህ ያህል ሰራተኞቹን ከስራ ሊያሰናብት መወሰኑን ከሰሞኑ ያስታወቀ ሲሆን ኦል አፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፤የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በገጠመው ቀውስ ሳቢያ ለሰራተኞቹ የዚህን ወር ደመወዝ ለመክፈል እንደማይችል ከሰሞኑ ማስታወቁን ዘግቧል፡፡

ስፔን ብሔራዊ ሃዘን ላይ ናት
ስፔናውያን በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ወጎኖቻቸውን ለማሰብ ባለፈው ረቡዕ የህሊና ጸሎት ያደረጉ ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ ለ10 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሃዘን ታውጇል፡፡ከ27 ሺህ በላይ ዜጎቿን በቫይረሱ በተነጠቀችው ስፔን፤ የአገሪቱ ሰንደቅ አላማ እስከሰኔ 5 ቀን ድረስ ዝቅ ብለው እንደሚውለበለቡም ተዘግቧል፡፡

ከ6 ወጣቶች አንዱ ስራ አጥሆኗል
በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሰዎችን ከስራ ገበታቸው እያፈናቀለ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤ በተለይም ወጣቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂ ማድረጉንና በአለማችን ስራ ከነበራቸው ከ29 አመት በታች የሚገኙ ወጣቶች መካከል ከ6ቱ አንዱ ለስራ አጥነት መዳረጉን ተመድ ሰሞኑን ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ሲኤንቢ ኒውስ በአሜሪካ ባለፉት ስምንት ሳምንታት ውስጥ ብቻ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከስራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን ሲዘግብ፣ በፈረንሳይ ደግሞ ባለፈው ሚያዝያ ወር ብቻ ከ850 ሺህ በላይ ሰዎች ከስራ ገበታቸው መፈናቀላቸውንና የአገሪቱ ስራ አጦች ቁጥር ከ4.5 ሚሊዮን ማለፉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከትናንት በስቲያ አስነብቧል፡፡  
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በፊንላንድ የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር ባለፈው ሚያዝያ ወር ብቻ በእጥፍ በማደግ ከ433 ሺህ በላይ መድረሱን አልጀዚራ የዘገበ ሲሆን የአለም የኢኮኖሚ ፎረም በበኩሉ፤ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ አለማቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከስፖንሰሮች ሊያገኝ የሚችለውን የ10 ቢሊዮን ዶላር ማጣቱን አመልክቷል፡፡

አንዳንድ ነገሮች
የኦስትሪያ መንግሥትየኮሮና ቫይረስስርጭትንለመግታትበማሰብየጣለውንየሰዓትእላፊ ገደብ እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ ለዜጎቻቸው ጥሪ ሲያስተላልፉ የከረሙት የአገሪቱ ፕሬዚዳንትአሌክሳንድርቫንደርቤለን፣ ከሰሞኑ ራሳቸው ገደቡን በመተላለፍ በመዲናዋ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ከሚገባው በላይ ማምሸታቸውና ይህን ተከትሎም ለዚህ ያልተገባ ድርጊታቸው በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው ተነግሯል፡፡
በጎረቤት ኬንያ ደግሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ልጅ፣ መንግሥትኮሮና ቫይረስንለመቆጣጠርያስቀመጠውንየሰዓትእላፊሕግበመጣስ በሞምባሳበሚገኝ አንድ የምሽትክለብ ውስጥ ሲዝናናመገኘቱንና የራሱንናየቤተሰቡንሕይወትአደጋላይበመጣሉእንደገሰጹትመናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፈረንሳውያን የወይን አምራቾች በኮሮና ቫይረስ ህክምና ራሳቸውን አሳልፈው በመስዋዕትነትና በቁርጠኝነት እየሰሩ ለሚገኙ የአገሪቱ የህክምና ባለሙያዎች 5 ሺህ ጠርሙስ ሻምፓኝ በነጻ በስጦታ መልክ እንደሚያበረክቱ መግለጻቸውን ፍራንስ24 ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡
በህንድ ከሰሞኑ መንታ ልጆችን የወለዱ ወላጆች ለልጆቻቸው “ኳራንታይን” እና “ሳኒታይዘር” የሚሉ ስሞችን ማውጣታቸውንና ሁለቱም ነገሮች አስከፊውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ወሳኝ በመሆናቸው ለልጆቻቸው ስም እንዳደረጓቸው ወላጆቹ መናገራቸውን የዘገበው ደግሞ አልጀዚራ ነው፡፡
በተደረገላቸው ምርመራ በኮሮና ቫይረስ እንደተጠቁ ተረጋግጦ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩት ጁዋና ዙኒጋ የተባሉት ቺሊያዊት የ111 አመት የዕድሜ ባለጸጋ፣ ከሰሞኑ ከቫይረሱ አገግመው ከለይቶ ማቆያ ቦታ መውጣታቸውንና ለ112ኛ አመት የልደት በዓላቸው እየተዘጋጁ እንደሚገኙ የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው፡፡
“የምግብ መሸጫ መደብሮች ከሰሞኑ ሊዘጉ ነውና፣ ፈጥናችሁ ምግብ ገዝታችሁ ከዝኑ” የሚል ሃሰተኛ የማስጠንቀቂያ መልዕክት በፌስቡክ አሰራጭቷል የተባለው ሲንጋፖራዊ የታክሲ ሾፌር፣ በአራት ወራት እስር መቀጣቱንም አልጀዚራ ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡

Read 12389 times