Sunday, 31 May 2020 00:00

ግንቦት- የመንታዎች እናት!

Written by  -በአዲሱ ዘገየ-
Rate this item
(0 votes)


“--ቤተሰብ የሥጋ ዝምድና ያላቸው ሰዎች፣ ባንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ኅብር ውጤት ነው፡፡ የሚቀራረቡ የሚተሳሰቡ የሚዋደዱና እንደ ዘመድ የሚተያዩ ጓደኛሞች፣ አብሮ አደጎች፣ ቤተኛ ወይም ቤተሰቦች ይባላሉ፡፡ እኒህ ያንድ ቤት አባላት እርስ በርስ የሚኖራቸውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያሳይ ቀን በግንቦት ይከበራል፡፡--”
    
                (ካለፈው የቀጠለ)
፫. ራስ ገዝነት፡- የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጳጳሳት መሰብሰቢያ ቀን ርክበ ካህናት በመባል ትጠራለች፡፡ ይህን ጉባኤ ለማስተናገድ ከሚመረጡ ሁለት ወራት አንዷ ግንቦት ናት፡፡ በመሆኑም በዚህ ወር በ1870 በቦሩ ሜዳ የተከናወነ የሃይማኖት ክርክር ተስተናግዷል፤ በክርክሩ ላይ አፄ ዮሐንስና ንጉሥ ምኒልክ የታደሙ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ይህ ዓይነት ክርክር እንደማይካሄድ የታወጀበት የመጨረሻው ጉባኤ ሆኖ አልፏል፡፡
“በጥቁር ጳጳስ አልባረክም!” የሚል ሀሳብን የሚያቀነቅኑ የካቴድራል ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን ነበሩ፤ እኒህ ካህን ተቃውሟቸውን በሀገሪቱ ሣምንታዊ ጋዜጣ ይጽፉ ነበር፤ ወቅቱ 1920 ነበር፡፡ ከላይ የቀረበውን ሀሳብ በብርቱ የሚቃወሙ የሀገሬው ምሑራን ደግሞ በዚያው ጋዜጣ ላይ የአጸፋ መልሳቸውን እያቀረቡ ካህኑን እስከ መዝለፍ ደርሰው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች የበላይ ጠባቂና መምህር፣ ጳጳስና ፓትሪያርክ የሚሾመው ከግብጽ ሀገር ነበር፡፡ ጥቁር፤ጳጳስም ሆነ የእምነት መሪ መሆን የማይችልበት ዘመን ነበር፡፡ እኔና ጥቂት ጓደኞቼ አባቶችን የሚያንቋሽሽ ጽሑፍ የጻፉትን ካህን ልጅ፣ አቧሬ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን ቃለ መጠይቅ አድርገናቸው ነበር፡፡ እግረ መንገዳችንን የተባለው እውነት መሆን አለመሆኑን እንዲያረጋግጡልን ጠየቅን፡፡ እሳቸውም “ቤተሰቡ በሙሉ አባቴ በጻፈው ነገር የተናደዱ ሰዎች በመርዝ ገድለውታል!” ብለው እንደሚያምኑ ገለጹልን፡፡ ጥቁርን በአባትነት መንበር ማስቀመጥ ከሃይማኖታዊ ጉዳይነቱ በላይ ፖለቲካዊ ብሎም የኅልውና ጉዳይ መሆኑ ዘመናውያን ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ እንኳ ያጋጭ ነበር፡፡ እኒህ የሥላሴ ካህን ለቤተሰባቸው ጽፈው ባስቀመጡት ማስታወሻ ላይ የዘር ግንድ ሐረጋቸው ከይሁዳ ዘር እንደሚመዘዝ ገልጸዋል፡፡ ይህን ክርክር ያስተዋለና የካህኑን የሕይወት ታሪክ የተረዳ አካል፤ ማን ለማን መብት ዘብና ጥብቅና ቆሞ፣ ማን እንዲያሸንፍ እያደረገ እንዳለ ወለል ይልለታል፡፡  
ክርክሩ በጦፈበት ወቅት “ኢትዮጵያውን መሾም አለባቸው!” የሚለው ቡድን ጭብጥ ሚዛን እየደፋ መጣ፡፡ ወዲያውኑም በ1921 ግንቦት ላይ የመጀመሪያዎቹ አራት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት (አቡነ አብርሓም፣ አቡነ ይስሐቅ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ሚካኤል) ከግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ጋር በግብጽ ካይሮ ከተማ ሥርዓተ-ሲመት ተከናውኖላቸው ተሾሙ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ የተሾመው ግንቦት 1940/1 ላይ ነው፡፡ ግንቦት 1963 ደግሞ የሁለተኛው ፓትሪያርክ ሥርዓተ-ሲመት በካቴድራል ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተከናወነ፡፡
የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፓትሪያርክ በተሾሙበት ዓመትና ወር ላይ እስራኤል ነጻ እና ሉዓላዊት ሀገር የሚል ዕውቅና ተሰጣት፤ ጊዜያዊ መንግሥትንም መሠረተች። ወዲያውኑ ጎረቤት የዐረብ ሀገራት ማለትም ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ሶርያ፣ ኢራቅና ሳዑዲ ዐረቢያ ባንድነት እስራኤልን ወረሩ። ይህ ከተከናወነ ከ19 ዓመታት በኋላም የእስራኤል አየር ኃይል የግብጽ፣ የዮርዳኖስና የሶርያን አየር ኃይል በቦምብ ሲደበድብ “ወደ ስድስቱ ቀን ጦርነት” መግቢያ ዋዜማ ነበር፡፡
በ1952 የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ የውጭ ጣልቃ ገቦች በሀገሪቱ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን እያስገቡ ማስቸገራቸውን የሚቃወም ስብሰባ በአዲስ አበባ የየሀገራቱን አምባሳደሮች ጠርተው አከናወኑ፡፡ እነዚህ የተጠሩ ሀገራት ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ግብጽ፣ ሶቪዬት ኅብረት፣ ብሪታኒያ እና ዩጎዝላቪያ ናቸው፡፡ በማግስቱ በወጣው ዜና ስብሰባው የተጠራው “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮች ላይ የባዕዳንን ጣልቃ ገብነት በብርቱ እንደሚቃወመውና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ማናቸውንም አካላት ለማስጠንቀቅ የተጠራ ስብሰባ ነው!” ተብሎለታል፡፡ በተጠቀሰው ዓመትና ወር ላይ የዮርዳኖስ ንጉሥ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገብተው ለአራት ቀናት ያህል ጉብኝት አድርገው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
በ1956 የግብጽ ፕሬዚዳንት ጋማል አብደልናስር እና የወቅቱ የሶቪዬት ኅብረት መሪ ኒኪታ ክሩስቼቭ በአስዋን ግድብ ሥራ ላይ የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ ለማስለወጥ በሚረዳው የፈንጅ ማፈንዳት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው በጋራ አከበሩ፡፡ በዚህ የክብር በዓል ላይ የኢራቁ ፕሬዚዳንት አሪፍና የየመኑ አቻቸው ፕሬዚዳንት ሳላህ ተገኝተዋል፡፡
፬. ተንከባካቢነት፡- ግንቦት ወር ላይ ከሚከበሩ በዓላት የሕፃናት ሞግዚቶች ቀን፣ የእናቶች ቀን፣ የነርሶች ቀን፣ የልጆች ቀን፣ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አንገብጋቢ ወቅታዊ ትኩሳቶችን መነሻ አድርገን ከምናከብራቸው በዓላት የመገናኛ ብዙኀን ርዕሰ ጉዳያቸው ያደረጉት የነርሶች ቀንን ነበር፡፡ የነርሶች ሙያዊ ኃላፊነት  በሕፃናት ሞግዚቶች እና በእናቶች ሚና ይገለጻል፡፡ ምክንያቱም ነርስ ማለት የበሽተኛ፣ የቁስለኛ፣ የሕመምተኛ ተንከባካቢ ናት፡፡ ሕፃናትን መንከባከብ፣ መጠበቅ፣ መመገብ ላይ ተሰማርታለች፡፡ እንደ ሠራተኛ/ወታደር ንብ፣ አውራውን/ንግስቲቱን መንከባከብ፣ መመገብና መጠበቅ ሥራዋ አድርጋለች፡፡ ለደከሙና ለተቸገሩ ጊዜያዊ ረፍትን በሚሰጥ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ መሰማራት በነርስ ክብካቤ ይገለጻል፡፡ የመድኃኒትና የሕክምና ክትትል ቢሰጥ በነርስ ነው፡፡ ጡት አጥቢነት፣ መጋቢነት፤ ተከባካቢነት ጥበቃና ጥንቀቃ ከነርስ ይገኛል፡፡ ዓለምን ያዳረሰውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመታገልና ለመቋቋም ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉ ነርሶች በርካቶች ናቸው፡፡
ነገር ግን ከዚህ ላይ በታሪክ የምትወሳዋን የአንዲት ነርስ አጋጣሚ ላውሳ፤ ዘመኑ 1966 ግንቦት ወር ላይ ነው፡፡ የኤርትራ ነጻነት ግንባር አባላት ጊንዳ ውስጥ በሉተራን ሚሲዮን ሆስፒታል የሚሠራ ዶክተርን ለመጥለፍ ጥቃት እያደረሱ ነው፤ ወደ ሆስፒታሉ በመግባት ላይ ሳሉ በመካከል ከጥቃት አድራሾች በተተኮሰ ጥይት ያንዲት ሴት አስታማሚ ነርስን ሕይወት አጠፋች። ነርስነት ባንዱ፣ ታማሚ ወይም አገልግሎት ተጠቃሚ በመጣ ሕመም ለመጥፋት ራስን ዝግጁ አድርጎ መቆምና መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ነርሶችን ስናከብርና ስንወድድ ራሳችንን ማክበርና መውደድ እንደሆነ ያሳያል፡፡ የልጆች ጤና የሚጠበቀው፣ ልጆችን በየወቅቱ መመገብና መንከባከብ የሚቻለው ጤናማ ነርሶች በመኖራቸው ነውና “ዕድሜ ለነርሶች ቀን!” ይሉ ምርቃት ተገቢ ነው፡፡
፭. አፍሪካዊነት፡- የነጻ ንግድ ቀን (ለአፍሪካውያን ወይም በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት) አምራቾች የተሻለ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ለማብቃት የሚረዳ ንቅናቄን በተመለከተ የሚከበር የወርሀ ግንቦት በዓል ነው፡፡ ይህም  ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ዕቃዎችን ማምረትና በምርቶች ላይ አዳዲስ ዕሴቶችን በማከል ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር ማድረግ እና አካባቢያዊ ምሕዳርን የማይጎዱ ማኅበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸው አገልግሎትና ምርቶችን በጥራት ማምረት፣ ለሠራተኞችም ምቹ የመስሪያ ቦታዎችን መፍጠር ዓላማው ያደረገ በዓል ግንቦት ታስተናግዳለች፡፡
ወርኀ ግንቦት የጥቁር አፍሪካውያን ድል የሚደምቁባቸው ቀናትን ይዛለች፡፡ በአሜሪካ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የቆዳ ቀለምን መነሻ ያደረገ የትምህርት አቅርቦት ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚጻረር ድርጊት ነው ብሎ የበየነው በ1946 ነበር፡፡ የጎረቤት ሀገሯ ኬንያ (በ1955) ነጻነቷን ከተቀዳጀች 9 ወራት በኋላ ራሷን በራሷ/በዜጎቿ የማስተዳደር ፈቃድን ያገኘችበት ወር በመሆኑ በየዓመቱ እንደ ድል በዓል የሚከበር የነጻነት ቀኗ ወርኀ ግንቦት ላይ ይውላል፡፡ በዚሁ ወር በ1971 ደግሞ በጥቁሮች የሚመራ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን የያዘባት ሀገር የቀድሞዋ ሮዴዥያ፣ ያሁኗ ዚምባብዌ ናት፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስናመራ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንቷ የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ፣ ሀገሩን ለመምራት የሚያበቃውን ቃለ መሐላ 1986 የፈጸመባት ወሩ ግንቦት ናት፡፡
፮. ቤተሰባዊነት፡- ግንቦት አቻቻይና አደላዳይ ወር ናትና ያባቶች ቀንም ይከበርባታል፡፡ አባታዊ ፍቅርን አንድ አባት ለቤተሰብ አባላቱ የሚገልጽበት፣ የአባወራነቱ ሚና የሚለካበት ወር ናት፡፡ የወሯን ኮከብ ጉልህ ሚና ገላጭ ነው፡፡ ትእምርታዊ ፋይዳው የቤተሰባዊ ደህንነትን ማስጠበቅ፣ ሀገረሰባዊ/ቤተኛዊ ጉዳይን ጠብቆ ማዝለቅ፣ ቤተሰባዊ አንድነትን ማጠናከርና ማጽናት የሚተገበርበት ቀንን ትወክላለች፡፡ የዓለማቀፉ የቤተሰብ ቀን፤ የቤት ሰዎች ኅብራዊ ትስስርን ታሳያለች፡፡ ታዛዥ፣ አገልጋይ፣ ተቀላቢ፣ ግብረ በላ፤ ቤተኛ የቤት ውልድ እያንዳንዱ ያላቸውን የሥራ ድርሻ ማመልከቻ ናት፡፡ የትውልድ የዝምድና ደረጃ ሐረግ፣ መከተቻ፣ ዙሪያ ገብ ዐውድ ምን እንደሚመስል በኑሮ ይገለጥባታል፡፡ ወቅቱ ቤተሰባዊ መቀራረብ ፈጥሯል፡፡ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባላት ቤቴ ቤቴ የሚልበት፣ ለትዳሩ፣ ለንብረቱ የሚተጋበትና የሚያስብበት፣ ጎንበስ ቀና የሚያበዛበት እንዲሆን አግዟል፡፡ ቤተሰብ የሥጋ ዝምድና ያላቸው ሰዎች፣ ባንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ኅብር ውጤት ነው፡፡ የሚቀራረቡ የሚተሳሰቡ የሚዋደዱና እንደ ዘመድ የሚተያዩ ጓደኛሞች አብሮ አደጎች ቤተኛ ወይም ቤተሰቦች ይባላሉ፡፡ እኒህ ያንድ ቤት አባላት እርስ በርስ የሚኖራቸውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያሳይ ቀን በግንቦት ይከበራል፡፡
፯. የአካባቢ ጥበቃ፡- ወርኀ ግንቦት ከአካባቢ የአየር ንብረት ጥበቃ ጋር በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ የሚገናኙ ክብረ በዓላት ይከወኑባታል፡፡ ከነዚህ መካከል የዓለማቀፉ ብዝኀ-ሕይወት ቀን፣ የዓለም ጸረ-ሲጃራ ቀን፣ ብሔራዊ የሕዝብ ፓርኮችና ደኖች ቀን፣ ዛፎችን የመንከባከብ ቀን፣ በኢትዮጵያ የሚከበረው የአረንጓዴ አሻራ ቀን እና የያዝነው የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን ይጠቀሳሉ፡፡ በዓለም ላይ የሥነ-ፍጥረታት ዝርያዎች እየተመናመኑ መጥተዋል፡፡ ሰውና ተፈጥሮ በቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ የአካባቢ የአየር ንብረት ስለተቃወሰ፣ ሰደድ እሣትና የጎርፍ አደጋዎች መበራከታቸው ይነገራል፡፡ ስለዚህ ጤናማ የአየር ንብረት እንዲኖር የሚያደርጉ ቀዬአዊ የሀገሬው ዕውቀቶችን ማስጠበቅ የሚያስችል ንቅናቄ፣ በአካባቢ ጥበቃ ስም ይከበራል፡፡
በዓለም ላይ ያለው አየር ለብክለት እየተዳረገ ነው፤ በዚህም የተፈጥሮ ሀብቶች ሊመናመኑ እንደቻሉ ይጠቀሳል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በበኩሉ፤ በዚህ ዓይነት የአካባቢ የአየር ንብረት ለውጥና ቀውስ ፍሬ ውጤት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይህም ሐቅ የወቅቱ የመገናኛ ብዙኀን ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ የተፈጠረውን አካባቢያዊ ቀውስ ለመታደግ እንደ አማራጭ ከሚጠቀሱ መፍትሔዎች መካከል በሀገርበቀል ዕውቀቶች የተፈጥሮ ሃብቶችንና ሰውን ማስማማት አንዱ ነው፡፡ ይህን ለማስቻልም የሀገሬው/የአካባቢው ሰዎችን ማድመጥ፣ መቀበልና መስማት ያሻል፤ ምክንያቱም የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነት የሰመረ መሆን ይጠበቅበታልና፡፡ ያንድ አካባቢ ማኅበረሰብ ሰላማዊ ግንኙነትን፣ ስምምነትን፣ በሰውና ተፈጥሮ መካከል ያለ ግጭትን መዳኘትና ማስማማት የሚያስችሉ ዕውቀት ይዘዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ ሥነ ፍጥረታት ተደጋግፈው እንዲኖሩ የሚያስችሉ አካባቢያዊ ዕውቀቶቻቸውን አክብሮ ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ አልያ የሚከተሉት አብነቶች በተፈጥሮ አደጋዎች አማካይነት መስተናገዳቸው የየለት ዕጣ ፋንታ መሆኑ አይቀርም፡፡
በግንቦት ጥንትም ሆነ ዛሬ ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንደሚበረከቱ ለማሳየት እማኝ አናበዛም፡፡ ሰሞኑን የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት (የእኛንም ጨምሮ) በጎርፍ መጥለቅለቅ ብቻ ማውሳት ይበቃል፡፡ የርዕደ መሬት ወይም የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ እና የከባድ አውሎነፋስ ጥቃቶች ዓለምን ሲያምሱ ነበር፤ አሁንም ድረስ አሉ፡፡ ሰሞኑን በሀገረ አሜሪካ ከ66 ዓመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የርዕደ መሬት ተከስቶ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡ የመሬት ባህርይ በሰለጠነበት የጸደይ ወቅት መሬቷ ሞልታ ስትገነፍል፣ የዋጠቻቸውን ዳግም በሚያስመልስ መልኩ ስትንቀጠቀጥ፣ አውሎ ነፋስ ምድርን ሲያጥረገርግ ታይቶባታል፡፡ ከዓለማችን በግንቦት ወር በርዕደ መሬት ከባድ ጥፋት ከደረሰባቸው ቦታዎች መካከል በኢራን (1980) የኮራሳን ግዛት፣ በቻይናዋ (2000)  ሲቹዋን ግዛት፣ በሰሜናዊ አልጀሪያ (1995)፣ በፓኪስታን ኬታ አካባቢ (1926)፣ በሰሜናዊ ፔሩ (1982)፣ በሀገራችን ወደ ማጀቴ ግድም በ1953 ወዘተ በደረሱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች በድምሩ ከሁለት መቶ ሽህ በላይ ሰዎች አልቀውበታል፡፡ ከባድ የአውሎ ነፋስን በተመለከተ በባንግላዴሽ (1977)፣ ከአስር ሽህ በላይ ሰዎችን ማጥፋቱ በሰነዶች ሰፍሯል፡፡
ግንቦት የመንታዎች እናት!  


Read 1367 times