Print this page
Saturday, 30 May 2020 14:10

አዳማዊ ሁለንታ

Written by  ማርቆስ ዘመንበረ ልዑል
Rate this item
(1 Vote)


                  [መንደርደሪያ]
ብዙ ፊልሞች ራሳቸውን ተለጣጣቂ በማድረግና (በተለይም ይሄ በኮሚክ ቡክ ተኮር ፊልሞች ላይ ይዘወተራል) ታሪኮቻቸውን አንዱን ካንዱ በማቆላለፍ፣ የራሳቸው Universe ሲያሻቸው multi verse ይፈጥራሉ። በዚህ ሁለንታ ውስጥ የራሳቸውን ገጸባሕርያት የሚያጫውት፣ የራሱ የመጫወቻ ሰፊ ምናባዊ አመክንዮዎች በመፍጠር ታሪኮቻቸውን ያንሸራሽራሉ።
የዚህ ተለጣጣቂ ጽሑፍ ርዕስ መነሻም ከዚሁ ጋር ከሚመሳሰለውና በደራሲ አዳም ረታ መጻሕፍት ላይ ከሚስተዋለው የማሸጋገር እና የማስተሳሰር ቴክኒክ ጋር ተቀራራቢነት ስላለው ነው። የሁለንታውን ባሕርያት ከዚህ በታች የምንዳስስ ይሆናል።
መንታዌነት
ተሳታፊነትና ታዛቢነት
በተለያዩ መጻሕፍቱ ላይ ያሉ ገጸባሕርያት የተሳታፊነትም የታዛቢነትም ባሕርይ የተሰጣቸው ናቸው። በአንድ ጊዜ ማሕበረሰባቸው ውስጥም  ተነጣይ ባይተዋር ሆነውም ይገኛሉ። ለዚህ የስንብት ቀለማቷ - “ቹቹ” እንደ ማሣያ መወሰድ ትችላለች። እንደዚሁ መረቅ በተሰኘው መጽሐፉ ላይ የምናያቸው ገጸባሕርያትም በማሕበረሰባዊነት ቡልኮ ውስጥ ባይተዋርነታቸውን የከተቱ ታዛቢዎች ሆነው ይስተዋላሉ።
ነጭና ጥቁር
ሌላው የመንታዌነት ነጸብራቅ ክፉና ደግ፥ ነጭና ጥቁር የሚለገጡበትን ደምሳሳዊ ተናጥሎ ማዋሐዱ ነው። የደራሲው ገጸባሕርያት ግራጫው መሐል የተቀመጡ የነጭና ጥቁር ዉሕድ ናቸው። ይሄም በዘልማድ በልብወለዶች ላይ የምንመኘውን ፍጹማዊ Heroic ገጸባሕርይ በመተው፣ የአንድን ተራ ሰው ውስጣዊና ውጫዊ መፍጨርጨሮች ከእነ ጉድፉና ከእነ ሕጸጹ በማቅረብ ለእውነታ ይበልጥ የቀረበ ያደርገዋል።
ተሻጋሪነት እና ዳግም መግጠም
እንደ ድኅረ ዘመናዊ ድርሰት ባሕርይ፣ ለጡዘቱ የተጠናቀቀ እልባት አለመስጠት የአዳም መጽሐፍ አንድ ባሕርይ ነው። ነገር ግን ደራሲው የራሱን “ሁለንታ” ፈጥሯል ከሚያስብሉኝ ምክንያቶች ሌላው ገጸባሕርያቱን ከመጽሐፍ መጽሐፍ ባልተሟላ መገለጥም ቢሆን በማሻገር እና ከሌሎች ደራስያን መጻሕፍትም በማዛመድ፣ ለገጸባሕርያቱ እልባት ያልተሰጠው ትረካ፣ የዞሮ መግጠሚያ ዕድል መስጠቱ ነው። በ”ግራጫ ቃጭሎች” ላይ የምናውቀው “መዝገቡ” “አፍ” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ በልጁ በኩል ተገልጦ እናያለን። “መግደላዊት” የምትባል ‘ኤልዛቤል’ በተባለው አጭር ትረካ ላይ ከእናቷ የምትነጠል ሕጻን፤ በዚሁ ‘አፍ’ ልብወለድ ላይ ከእናቷ ጋር ተገናኝታ፣ ታሪኩ እልባት ሲሰጠው ይታያል። ደራሲው የፍቅር እስከ መቃብሯን ሰብለወንጌል፥ ራሱን ደራሲውንና መጽሐፉን፥ ከሌላ መጽሐፉ የተሻገረ ውሻን ሳይቀር በሽግግሩ እያቆላለፈ በመጻፍ የራሱን የትስስር ገመድ ዘርግቷል።
ክበባዊነትና አማራጭ አውታር
አማራጭ አውታር (Alternative Dimension በተለይም የጊዜ) በጊዜ ወደ ኋላ ከመሄድ ጋር በሚመጣ መዛነቅ (Paradox) የሚፈጠር የጊዜ መስመር እንደሆነ ሣይንሳዊ መላ ምቶች ይተነብያሉ።
አለንጋና ምሥር ላይ የሚገኝ አንድ አጭር የደራሲው አጭር ልብወለድ፣ ይህን እንደ ቴክኒክ የሚከተል በAlternative endings የሚያበቃ ሆኖ ተቀምጧል። ታሪኩ አጨራረሱ በተለያዩ አማራጭ ፍጻሜዎች በመቅረቡ በሣይንሳዊ መላምቶቹ ውስጥ በጊዜ ወደ ኋላ እየተመላለሱ፣ አንድ ነገር ቢያርሙ ወይም ቢያዛንፉ የሚፈጠር አይነት መዛነፍ፣ በታሪኩ አጨራረስና መሐል በተለወጡ አንዳንድ ሐሳቦች ተንጸባርቋል።
ከረሜሎች በተሰኘ አጭር ታሪክ ውስጥ ደግሞ በጥቂት ቃላት ለውጥ ብቻ አንድ ታሪክን በመደጋገም በየጊዜው የማይለወጥ ክብ አኗኗርን ሊያሳየን ይሞክራል።
ስለአልተነገሩ ጥቃቅኖች
አዳም ረቂቁን በማግዘፍ ይታወቃል። ለዝርዝር ጉዳይ ያለው ጥንቁቅነት እጅጉን አስደናቂ ነው። ኮርኒስ ላይ ስላለች ስለእየ አንድ አንዷ የታሪክ ደቃቅ ብናኝ ያለው የትርጉም አሰጣጥ፣ ግዘፉን ጉዳይ የሚዳኝበትን መንደርደሪያ ጥሩ ግንባታ ያለው እንዲሆን አድርጎለታል። ለብዥታ እና ፍዘ ልቡና ከሰጠው ከፍተኛ ቦታ ጋር ተደማምሮ ግዘፍ የምንሰጣቸውን ነገሮች በማጠየቅ ረገድ የተዋጣለት ማሕበራዊ ሪቮሉሽነሪስት ሆኖ ይቀርባል። #ሎሚ ሽታ”ላይ ያለው “ጸጥታ ነጋሲ” የሚለው ሽራፊ ክፍል ብቻውን ለዚህ ትልቅ ማብራሪያ ነው።
 ብዝኀ አውታርና ኳንተማዊነት
ምናብን ከሚሰጠው ግዙፍ ቦታ አንጻር ያልተወራለት ሣይንሳዊ ልብ ወለድ ደራሲም ነው።
ጊዜ’ታዊ ሽረት
“ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” በምትለው ትረካ ውስጥ ያለው የጊዜ መዛነቅ፣ ደራሲው Spacetime/ ጊዜ’ታን ምን ያህል አርቅቆ እንዳስቀመጠው ያሳየናል። ለጊዜ የምንሰጠውን ነጠላ መንገድ ተጓዥነት በማጠላለፍና ተመላሽ ትናንት በመፍጠር ይሞግተናል።
ብዝኀ አውታር
”ግራጫ ቃጭሎች” በተሰኘው ረዥም ልብ ወለድ  ላይ ታይተው የሚሰወሩ፥ ደብዛዛ ዓለማትን በማምጣት እጅግ ቅዥበታዊ የሚያስብል ትዕይንት ይፈጥራል። ይሄን ከእምነታዊ እና ማሕበራዊ ‘Superstition’ ጋር ከተያያዙ የ’ሥውራን መኖርያ’ በመባል ከሚታወቁ ሥውር አውታሮች እስከ ሣይንሳዊ መላምት የሆነው ብዝኀ አውታር (Multi-dimensional reality) ድረስ የታረቀ ተረክ በመፍጠር፣ ቸል ከተባሉ ማሕበረሰባዊ አመኔታዎች እስከ ጥናት የሚደረግባቸው ረቂቅ ሣይንሳዊ መላምቶች የሚጎተት ትሥሥር በመፍጠር የሚያስደምም ምናባዊነቱን ያሳየናል።
ደሴቶችና የክቡ መሐል
ሁሉም ክበብ የራሱ መሐል አለው። ለሥነ ጽሑፋዊ ድርሰቶች መሐላቸው መሪው ገጸባሕርይ ሆኖ ይሄን እውነታ ተደግፎ በብዛት ይስተዋላል። ገጸባሕርይው ጎጆ መሐል እንዳለ ምሰሶ የጽሑፉን ዘለቄታ ይደግፋል።
ደሴቶች
በአጭርም ሆነ በረዥም ልብ ወለዶቹ ውስጥ ብዙዎቹ ገጸባሕርያት ከየራሳቸው የትረካ ደሴት በእነሱ እይታ ታሪካቸውን የመተረክ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል። በአንደኛው ትረካ ውስጥ ፍጹም መጥፎ ተደርጎ የተሳለ ገጸባሕርይ፣ በራሱ አፍ ወይም በሌላ ተራኪ አንደበት ታሪኩ ሲነሳ፣ ጭምት ወይም መልአካዊ አቀራረብ ይይዛል። በዚህም ከላይ ያነሳነው ከነጭነትና ጥቁርነት መሐል የሰፈረ ውሕድ የገጸባሕርይ እውነታ መፍጠር ያስችላል።
በሌላ በኩል፤ ከላይ ብዝኀ አውታር ብለን ካነሳነው ጋር አያይዞ፣ መላምታዊ ከሆነው እነዚሁ አውታሮች ውስጥ የሚገኝ ነጸብራቅ መንትያ እውነታ (Double ganger) በሌላው ሰው ምናብ ውስጥ በመፍጠር በግዙፍ ፕላኔት ላይ የሚደረግን አምሳያ ፍለጋ ወደ ረቂቁ የሐሳብ ጠፈር ውስጥ ያሰርገዋል።
የክቡ መሐል
በሕዋ ሣይንስ ጥናት መሠረት፤ የሁለንታ መሐል የሆነው ነጥብ/ The center of the Universe ሁለንታ በየቅጽበቱ በመስፋቱ ምከንያት እንደ ልኬት አንጻራችን ይለያያል። በዚህም ሁሉም ሁለንታው ላይ ያለ ነጥብ ሁሉ መሐል ሆኖ ያገለግላል።
ከላይ በጠቀስነው የደሴት ትረካ ስልት መሠረት፤ የደራሲ አዳም ረታ ልብ ወለዶች ዋና ገጸባሕርይ በሚል ማሠሪያ ያልቋጠሩ ናቸው። ሁሉም በመጽሐፋዊ ሁለንታው ቦታ የተሰጣቸው ገጸባሕርያት፣ የታሪኩ መሐል ሆነው ይቀርባሉ። ይሄም ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን የፍጹማዊ እኩይነት እና ሠናይነት የሚያጠይቅ ጽንሰ ሐሳብ ደጋፊ ነው።
ሥነጽሑፋዊ ታማኝነት (ማገባደጃ)
‘አዳማዊ ሁለንታ’ የተሰኘውን ተለጣጣቂ ጽሑፍ መነሻ ሐሳብ እንዲሁ ከመቋጨት በአንድ ወቅት ከአንዲት ወዳጄ ጋር ስለ አዳም መጻሕፍት ባደረግነው ጭውውት፣ የተናገረችውን ቃል በቃልም ባይሆን ልጥቀስና ላብቃ፡፡
“--ጥቂት ገጽ በአግባቡ አርትኦት ያልተደረገለት ጽሑፍ ይዞ ወደ ማተሚያ ቤት መሮጥ ልምድ በሆነበት ዘመን፤ በጥሩ ቴክኒክ የተዋቀረና ብዙ የተለፋበት፣ ውበት ያለው እንደ ‘የስንብት ቀለማት’ ያለ ልብ ወለድ ማበርከት ለሥነጽሑፍ ታማኝነት ነው።--”

Read 1471 times