Sunday, 31 May 2020 00:00

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

   ከሁሉም በፊት መኖር ይቀድማል!
                            
            አንዳንድ መጽሐፍቶች በደፈናው ‹ልብ ወለድ› ይባላሉ፡፡ ነገር ግን ዘመን በማይነቀንቀው እውነት የታነፀ ይዘት አላቸው፡፡ እንደ’ኔ፤ እንደ’ኔ ‹ልብ ወለድ› ከማለት ይልቅ ‹ምናባዊ ታሪክ› ቢባሉ ወይም የቋንቋ ሊቃውንት በሚያወጡላቸው የተሻለ ስም ብንጠራቸው የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዕውነት የሚታመነው ከልብ የመነጨ መሆኑ ሲታወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ‹‹እውነቴን ነው፣ ከልቤ ነው›› እያለ ሲናገር ‹እምነታችንን› ለመግዛት በመሆኑ የሚለውን አንጠራጠርም፡፡
ወዳጄ፡- ልባዊነት ግለሰብን ማዕከል ያደረገ የጥሬ ሰብዓዊነትና የተፈጥሮ ፍትህ መቅድም ነው፡፡ አእምሯዊነት ደግሞ ዕውቀትና ልምድን መሰረት ያደረገ፣ ግለሰባዊና ማህበራዊ ግንኙነቶችን ያገናዘበ፣ የበዳይ፣ ተበዳይ ጉዳዮችን ያለ አድልዖ ለማስተናገድ የሚሞክር፣ በጋራ ስምምነት በረቀቀና በፀደቀ ሕግ ለመተዳደር የሚጥር የአስተሳሰብ ዘይቤ ነው… የምክንያታዊነትና ሚዛናዊነት ፋኩሊቲ!!
ወዳጄ፡-  መነሻችንን በመጽሐፍ ‹ይዘት› የጀመርነው ያለ ነገር አይደለም፡፡ ‘The man who sold his Ferari’ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አጋጥሞህ እንደሆነ ለመጠየቅ እንጂ፡፡ የመጽሐፉ መንፈስ ባጭሩ እንዲህ ይመስላል፡-
ሰውየው በዕውቀትና በልምድ የደረጀ፣ ሁሉ በእጁ፣ ሁሉ በደጁ የሞላለት፣ ዝነኛ የሕግ ሰው ነው፡፡ ዕረፍት የሚነሳውና በውስጡ የሚመላለስ አንድ ጥያቄ ግን አለ… ፍቺ የሚፈልግለት፡፡
ጥያቄው ‹‹የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?›› የሚል ነው፡፡ ላይ ታች እያለ መልሱን በማፈላለግ ላይ እንዳለ…
‹‹በከንቱ አትድከም›› አለው አንዱ፡፡
‹‹ምነው?››
‹‹እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን መመለስ የሚችሉት በክህኖተ መንፈስ የበቁና የነቁ ወይም የላቀ አእምሮ (extraordinary perception) ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡”
‹‹የት ይገኛሉ?››
‹‹አልፕስ ተራራዎች አካባቢ ይታያሉ ይባላል››
‹‹የቡድሂስት መነኩሴዎች ይሆኑ?››
‹‹ምናልባት!››
‹‹የትም ቢሆን እሄዳለሁ›› አለ… ሰውየው.. ቁርጥ አድርጎ፡፡ ዝግጅቱንም አሳምሮ ተነሳ:: በአውሮፕላን፣ በመኪናና በአጋሰስ ተጉዞ ከተባለው አካባቢ ቢደርስም… መንገዱ እንዳሰበው ቀላል አልሆነም፡፡ በበረዶዎቹ ተራራዎች ላይ መጓዝ ነበረበት::… ለብዙ ቀናት በእግሩ በመጓዙ ስንቁን ጨረሰ:: ውርጩ አንሰፈሰፈው፡፡ ወደ ኋላም ለመመለስ፣ ወደ ፊትም ለመራመድ አልቻለም፡፡… አቅም አጣ፡፡ በሰመመኑ ውስጥ ከሞት ጋር ሲታገል…
‹‹አንተ ማነህ?›› የሚል ድምፅ ድንገት አነቃው፡፡ እጆቹና እግሮቹ ተንቀጠቀጡ:: ትንፋሹን አሟጦ ማንነቱንና የመጣበትን ጉዳይ ለእንግዳው ተናገረ፡፡
‹‹የሕይወትን ትርጉም ፍለጋ አልከኝ?››
‹‹አዎን አባቴ›› አለ… እንዳቀረቀረ፡፡
‹‹ቀና በል፡፡ የሕይወት ትርጉም ማለት ይሄ ነው›› አሉና የሆነ ነገር ሰጡት፡፡ ወዲያው… ነፍሱ ተመለሰ፡፡ ምን ይሆን?... እንመለስበታለን፡፡
*   *   *   *
ወዳጄ፡- በመጀመሪያው ውይይት ውስጥ ልባዊነትንና አእምሯዊነትን ድልድይ ሆነው የሚያቆሯኝዋቸው ምክንያታዊነትና ሚዛናዊነት መሆናቸውን ጠቅሰን ነበር:: የምክንያታዊነት ጥበብ የሚለካው፡- የመላው ማህበረሰብ ዕድገትና ስልጣኔን፣ የምርጥ መገልገያ መሳሪያዎችን ወይም የቴክኖሎጂን ዓይነትና ብዛትን፣ የኢኮኖሚ ግንኙነትና የመካከለኛ ገቢ ግምትን፣ ተፈጥሮ በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚኖራትን ተለዋዋጭነት በመቋቋም ረገድ ያለውን ዝግጁነትና መሰል ጉዳዮችን መሰረት ባደረገ ዕሳቤ ላይ በመቆም፣ እንዲሁም ተያያዥነት ባላቸው  ማዕዘናትና ሰበቦቻቸው ነፀብራቅ የሆኑትን የታሪክ፣ የዕምነት፣ የሳይንስና ጥበብ ዕድገትን በመመርመርና በማገናዘብ ይሆናል፡፡ የሚዛናዊነት ልክ ደግሞ የሚታወቀው ሰዎች በሰላም፣ በነፃነትና በእኩልነት የመኖር መብታቸውንና ሉዓላዊ ደህንነታቸው እንዲከበር የሚኖሩበት ሥርዓት በሚፈጥረው ፍትሃዊ መደላደል ነው፡፡ ምክንያታዊነት ህሊናን ያከበረ የደስታ ምንጭ መሆን እንዲችል ተፈጥሮ ታግዛለች:: ተፈጥሮ ራሷን የምትገልጠው፣ ወደ ዕውቀትነት የምትቀየረውም በምክንያት ነውና፡፡
ሃይማኖት እስከ ጀመረበት ጊዜ ድረስ የጥንት ሰዎች እንኳን የፍጥረትን ታሪክ መሽቶ የሚነጋበትን ምክንያት እንኳን አልተገነዘቡም:: ብርሃንና ጭለማ የሚከሰተው በአማልክቶቻቸው ቁጣና ሳቅ ይመስላቸው ነበር፡፡ ከእምነት ጎን የተፈጠረው ሳይንስ ደግሞ የፍጥረት አጀማመር ‹ይሁን› ተብሎ ወዲያው የሚሆን፣ ‹ይቅር› ተብሎ የሚቀር ነገር አለመሆኑን አሳወቀ፡፡ ተፈጥሮ የራሷ ሕግና ሥርዓት እንዳላት፣ ሚዛኗን ጠብቃ የምትራመድ የለውጥ ሂደት መሆኗንም አረጋገጥኩ አለ፡፡
የጊዜው ሊቃውንት እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች የሚጣረሱት በኛ የመረዳት አቅም አለመዳበር የተፈጠረ የትርጉም ስህተት እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት በጥብቅ ሲጠኑ በመካከላቸው የጎላ ልዩነት ወይም የሚቃረን ይዘት የላቸውም በማለት ማስረጃቸውን አቀረቡ፡፡ እንደ ምሳሌም፡- ሁለተኛይቱ የቅዱስ ጴጥሮስ መልዕክት፣ ምዕራፍ ሶስት፣ ቁጥር ስምንትን እንድናነብ ጋበዙ፡፡
ጴጥሮስም፡- ‹‹በእግዚአብሔር ዘንድ፡- አንድ ቀን እንደ ሺ ዓመት፣ ሺ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ይቆጠራል›› ይላል፡፡ በዳዊት መዝሙር ስድስት፣ ቁጥር አራት ላይም ተመሳሳይ ፍቺ የሚሰጥ አረፍተ ነገር መከተቡን አስታወሱ፡፡ በእምነትም ዘንድ ፍጥረት ሂደት መሆኑ ተቀባይነት አገኘ፡፡… ልባዊነትና አእምሯዊነት፣ ሳይንስና ዕምነት እኩል ተመዘኑ፡፡
ወዳጄ፡- በዚህም ቢባል በዚያ የፍጥረት ታሪክ የ‹መኖር› ታሪክ (existence) መሆኑን ልብ በል፡፡ ከመኖር በፊት ምንም የለም:: ዛሬ ደግሞ የመኖርና አለመኖር ጉዳይ … እኛን ጨምሮ የሰው ልጆች ፈተና ሆኗል:: ጉዳዩ የከረረው በድህነታችን ላይ ኮሮና የተጨመረ ጊዜ ነው፡፡ … ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ፡፡   
ወዳጄ፡- እኛ ከሌለን ፖለቲካ፣ እኛ ከሌለን ምርጫ፣ እኛ ከሌለን መንግስት የለም:: ዘፋኙ… ‹‹እኛ ከሌለን ባዶ!›› እንዳለው:: እዚህ አገር ‹‹ልምድ ለማዳበር›› ካልሆነ በስተቀር እስከዛሬ በእውነተኛ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ መንግሥት የለም፡፡ ኮሮና ብሶ ችግሩ ቢከፋ’ኮ ለምርጫ የተመደበው በጀትና ቁስ ወደ ጤናና ምግብ ተደራሽነት መዞሩ አይቀሬ ነው፡፡ …አያድርስ እንጂ!!
ሊቃውንቱ ‹‹Life before Philosophy!›› ይላሉ፡፡ መጀመሪያ እኛ! ለማለት:: ችግራችንን በአሸናፊነት እስክንወጣ ምርጫ መራዘሙ ተገቢ ነው፡፡ የግድ እንመራረጥ ብንል እንኳ ተጨባጭ ሁኔታው አይፈቅድም:: ‹‹ሱሪ ባንገት›› ብሎ ነገር ደግ አይደለም:: አደጋ አለው፡፡  ቀድሞ የነበረው ጨቋኝ አስተዳደር አሁን የለም፡፡ አገሪቱ እየተመራች ያለችው ዓለም አጨብጭቦ በሸለማቸው የለውጥ ሃይሎች መሆኑ እየታወቀ፣ ለምርጫ መጣደፍ ሰብዓዊነትን መፈታተን ያስመስላል፡፡ …አይመስልህም ወዳጄ?
*   *   *
ወደ መጽሐፋችን ስንመለስ፤ ሞት አፋፍ ደርሶ የነበረው ሰውዬ ነፍስ መዝራቱን ተጨዋውተናል፡፡ መነኩሴው ‹‹እንካ! የህይወት ትርጉም›› ብለው የሰጡት አንድ ኩባያ ትኩስ ሻይ ነው፡፡ እሷን ፉት ባይል አልቆለት ነበር፡፡
ወዳጄ፡- የህይወት ትርጉም ማለት እጅግ የሚያስፈልግህን ነገር በተገቢው ወቅት ማግኘት ማለት ነው፡፡…ከሁሉም በፊት ‹‹መኖር›› ይቀድማላ!! ልብ፣ አእምሮ ምክንያትና ሚዛናዊነት እያልን ከመፈላሰፍም በፊት “መኖር” ይቀድማል፡፡
ሠላም!!

Read 1317 times