Print this page
Saturday, 06 June 2020 14:16

ቅጥ አምባሩ የጠፋው ፖለቲካችን!

Written by  ሔኖክ ገለታው
Rate this item
(0 votes)

   ”--የመጠፋፋት ፖለቲካችን ዓይኑን አፍጥጦ፤ ጥርሱን አግጥጦ በርግጥም በኢትዮጵያችን መቀጠል/ አለመቀጠል አጣብቂኝ የመላምት መቀዣበር ውስጥ የከተተን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ዛሬ ነው፡፡ ዛሬ ከትናንት “የጭቆናና የብዝበዛ ትርክት” በሚቀዱ ዕሳቦቶቻችን ሳቢያ ታሪክ ለመማርያ ሳይሆን ለመኖርያ መዋል ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡--”
        
              አንጋፋው ብዕረኛ ዩሱፍ ያሲን፤ ሥነ-ጽሑፋዊም ፖለቲካዊም ፋይዳው ግዘፍ የነሳ አንድ መጽሐፍ አላቸው፡፡ “ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት” ይሰኛል፡፡ የኢትዮጵያችን ቀጣይነት የሚረጋገጠው ሁላችንም ከመልከ ብዙ ማንነቶቻችን የተሻገረ የዜግነት ጠለል ስንፈጥር ነው የሚል ድንቅ ጭብጥ አለው፡፡ ዩሱፍ ይህንን የዜግነት ማዕቀፍ (Frame) አብዝተው የሚሽቱት ግን ለኢትዮጵያ ሕልውና በተለየ ሁኔታ ሰፍሳፋ ሆነው አይደለም፡፡ እዚህና እዚያ ያሉ መቆራቆሶች፣ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያሉት የተራራቁና የማይታረቁ የሚመስሉ ፍላጎቶች፣ አንዳንዴም የሚጋጩ ትልሞች ሳያሳስባቸው ቀርቶም አይደለም፡፡ ከቡድኖች ጥቅምና መዳረሻ ሕልም አንጻር ያለውን ይፋዊም ሆነ ስውር አጀንዳን በቅጡ ሳይመረምሩት ቀርቶም አይደለም፡፡ በመሬት ሊሆን የሚችለው ብቸኛ እውነታ ሌላ ሆኖባቸው እንጂ፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ዜጋ ሊያኖራቸው የሚችል አሰባሳቢ ጥላ ካልተበጀላቸው በስተቀር በቋንቋ፣ በብሔር፣ በኃይማኖት፣ በአኗኗር ይትበሃል የሚታይባቸው መደበላለቅ በእርሳቸው ቋንቋ “እንዲለያዩ ሳይሆን አብረው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል”፡፡ በዩሱፍ ጥልቅ መረዳት ላይ ቆመን ጉዳዩን ስናጤን፤ የልሂቃኖቻችን ነገን አርቆ የመተለም ችግር የሚመነጨው ለዚህ ይመስላል፡፡ የማንነት ፖለቲካ የውሉ ሁሉ አልፋና ኦሜጋ ሆኖ መታሰሩ ከዚህ ፈቅ እንዳይሉ እግር ተወርች እንደሆነባቸው መገንዘብ አይገድም፡፡ በኢትዮጵያችን ሥር ሰድዶ የገነገነው የዘውግ ፖለቲካ፣ ወጥ የሆነ ቀመርም ሆነ መርሆዎች የሌሉት፤ ለአንዱ በጅቶ ለሌላው በሚፋጅ ብየና የተቃኘ ነቢብ ነው፡፡ ሳናኳኩል እናስቀምጠው ካልን ፖለቲካችን የምንታዌነት (Dualism) አስተሳሰብ ከመነሻ እስከ መድረሻ የቀየደው አደገኛ መረብ ነው፡፡
ምንታዌነት (Dualism) ምንድነው?
“Dualism” ለሚለው የእንግሊዝኛ ንባበ ቃል (Terminology) “ምንታዌነት፡- መንታ፣ ኹለትነት፣ ጣምራ” የሚለው አማርኛ ስምም ይሆነዋል ተብሎ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይኽ ምንታዌነት የተሰኘ ንባበ ቃል በፈርጀ ብዙ የጥናት ዘርፎች ላይ በተለያየ ብየና ስለሚያገለግል ለሃሳባችን ስሙርነት “አስፈላጊ ነው” ያልነውን መርጠን እንጠቀማለን፡፡ መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) የተባሉ ምሁር “(ኢ)ዩቶፕያ” በተባለ መጽሐፋቸው “ምንታዌነት” በአውሮፓውያን የጨለማ ዘመን ተግባራዊ ይደረግ የነበረ የኹለት ባህሪ አስተምህሮ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የስታንፎርድ የፍልስፍና ኢንሳይክሎፒዲያም ንባበ ቃሉን “The Division of something conceptually into two opposed or contrasted aspects, or the state of being so divided” በማለት የኹለት ተቃርኗዊ ዕሳቤዎች መገለጫ መሆኑን ያጠናክረዋል፡፡ የንባበ ቃሉን ብየና አስመልክተን ሃሳቦችን ዋቢ ያደረግነው እንበለ ምክንያት አይደለም:: በዋናነት በሀገራችን ውስጥ በገቢር ፈጥጦ የሚታየውን የማይታረቅ በሚመስል ደረጃ በባላንጣነት የታጀበ ፖለቲካ በመጠኑ ለመዳሰስ ያመቸን ዘንድ ጽንሰ-ሃሳባዊ ዳራ ለማስቀመጥ እንጂ፡፡
እንግዲህ የምንታዌ (ኹለትዮሽ) አስተሳሰብ መኖር በራሱ ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ ዓለም ራሷ የሁለት ተቃራኒ ነገሮች ድምር መሆኗን ስንገነዘብ ስለ ሃሳብ ብዝኀነት የቲዮሪ መዓት ሳንዘበዝብ ተቃራኒ ሃሳቦች መኖራቸው በራሱ ችግር አለመሆኑን ማመን አይገደንም፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያችን ነባራዊ ሁኔታ ግን ከአቶ ልደቱ አያሌው “መድሎት” እና ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “መደመር” መጽሐፍት በተሻገረ “ሦስተኛ አማራጭ” ወይም “የመሃል ፖለቲካ” በፓርቲዎችም ሆነ ልሂቃን ተዋስዖ ውስጥ ቦታ የተነፈገው ስሌት (ፍኖት) ሆኖ ስናገኘው ነገራችን ከተቃራኒ ወደ ተቃርኖ መሻገሩን ልብ እንላለን፡፡ ይኽ ነው እንግዲህ የአንዱ ትልምና ፍላጎት ከሌላው ጋር ተደጋግፎ ሊኖር የሚችልበት የማርያም መንገድ መጥፋቱ የፖለቲካ ምንታዌነትን ወልዷል ብለን እንድናምን ቀጥተኛ መነሻ የሚሆነን:: መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) በአውሮፓውያን ዘመነ ጽልመት ውስጥ የምንታዌነት አስተሳሰብ (አስተምህሮ) ስለ መጥለቅለቁ ናሙና አድርገው በመጽሐፋቸው ውስጥ ከጠቀሱት ለማሳያ እንዲረዳ ማንሳት ለሃሳባችን ጥሩ ማንጸሪያ ይሆነናልና ጥቂት እንቆንጥር፡፡
“…ምንታዌነት ማለት... ተረጋግቶ መኖርና ቤተሰብ ማስተዳደርን ከመስፋፋትና ከማደግ ተቃራኒ እንደሆኑ ማሰብ፣… እኩልነትንና አብሮነትን መፈለግን ለእውነት ከመቆምና ከጀግንነት ተቃራኒ እንደሆኑ ማሰብ፣… የግል ጥቅምና የጋራ ጥቅም በተፈጥሯቸው ተቃራኒ እንደሆኑ ማሰብ፣… የተለመዱና በስፋት ያሉ ነገሮችን እንደ ተራ፣ አልፎ አልፎ የሚከሰቱትን ደግሞ እንደ ተፈላጊ ነገር ማየት፣… የመንግሥት ሥራና የሕዝብ ፍላጎትና ባህሪ በተፈጥሯቸው ተቃራኒ እንደሆኑ አድርጎ ማየት፣…” (ገጽ 239-243)
እነኚህ የተጠቀሱ ተቃራኒ የመሰሉ ሃሳቦች ኹሉ ማሰርያ ቃላቸው “እንደሆኑ ማሰብ፣ አድርጎ ማየት” የሚሉ ናቸው፡፡ ይኽ ዓይነቱ የምንታዌ አካሄድና ዕምነት ደግሞ በሁለት ዋልታዎች በጠነከረ ድምጽ ስለሚስተጋባ የመሃል (ሦስተኛ) መንገድ ሊታይ አልያም ሊፈጠር አይችልም፡፡ ቢፈጠርም “መሃል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል” እንደሚባለው ይሆንና ተቀባይነት ያጣል:: “በዘመን ያልተገለጸ እውነት እንደ ውሸት ይቆጠራል” የሚባለው ብሂል በጥቂት ልባሞች እየተቀነቀነ አስተዋይ ትውልድ እስኪፈጠር ሳይሻግት እንዲቀመጥ ካልተጻፈ በስተቀር ክፉ ውርሱ በቅብብል ይቀጥላል፡፡
የእኛ የምንታዌነት ፈርጆች
ቀደም ሲል በብየና ደረጃ ለመግለጽ እንደሞከርነው “ምንታዌነት” የተለየ ሃሳብን በአቋም ደረጃ መያዝ ወይንም ማንጸባረቅ አይደለም፡፡ ከአቋሜ አለያም አስተምህሮዬ በተቃራኒ ካለው ጋር አብሬ ለመጓዝ ያዳግተኛል ብሎ አንዱ ሌላውን አደጋ (ሥጋት) አድርጎ ማሰብ ነው፤ ምንታዌነት:: ፖለቲካችን በዚህ ቅርቃር ውስጥ ወድቋል ስንልም በነቢብ ሳይሆን በገቢር፣ የአንዱ ወገን ሃሳብ በሌላኛው ማኅበረ ፖለቲካዊ ቤዝ (Constituency) መድረስ የለበትም፤ “አጥፊው ነው” የሚለው አቋም በካራና በክላሽ ደጀን ማግኘቱን ከግምት ወስደን ነው፡፡ የፖለቲካችን ምንታዌነት ዓቢይ በሚባል ደረጃ ሦስት ዋልታዎች ላይ ያርፋል፡፡ በሰው ልጅ የመኖር እውነትም ሆነ ዑደት ውስጥ እነኚህ ሦስት ዋልታዎች ደግሞ ወሳኝ ናችው፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ የሚቆም፤ ሌላው በሌላኛው ላይ የሚነባበር ነው፡፡ እነኚህ ሦስት ዋልታዎች ትናንት፣ ዛሬና ነገ ናቸው፡፡ እነኚህ የሕይወት ድልድዮች በመልክ በመልኩ ካልተሰናሰሉ ተቃርኖዎቻችን ሁሌም ለኅላዌያችን አደጋ ሆነው መቀጠላቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከእውነት መታረቅ ዋናውና ትልቁ መፍትሔ ቢሆንም የፖለቲካችን ምንታዌነት ፈጥጦ የታየባቸውን እነኚህን ሦስት ዋልታዎች በስሱ መመርመር ደግሞ ለነገ የማይባል ሥራችን ነው፡፡
ሀ) ትናንት ፤ በታሪካችን ላይ
የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ፤ በታሪክ ላይ ያለው አለመስማማት “ምንታዌ” ወዳልነው ደረጃ መሻገሩ ሳይገለጥላቸው የቀረ አይመስልም፡፡ ለዚህ ግምት አብነት ይሆነን ዘንድ በአንድ ዲስኩር ባሰሙበት መድረክ የተናገሩትን መጥቀስ ተገቢነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ሙስጠፌ እንዲህ ነበር ያሉት “…በዚህች ሀገር ብሔራዊ መግባባትና አንድነት እንዳይመጣ እያደረጉ ካሉ ነገሮች አንዱ በታሪክ ዙርያ ያለው ውዝግብ ነው፡፡ በኃይማኖቶቻችን፣ በባህሎቻችን፣ ወዘተ… ዙርያ በመካከላችን መቻቻል፣ መግባባት አለ:: በታሪካችን ዙርያ ግን ይኽ የለም:: በታሪክ ላይ መነታረክ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አብሮ ለመኖር በታሪክ መስማማት የግድ አይደለም፡፡”
ይኽ ሃሳብ የመጠፋፋት ቋፍ ላይ ለቆመው ታሪካችን የዋህ (Simple) ማመቻመች ሊባል ይችላል፡፡ “አንተም ተው፣ አንቺም ተዪ” ዓይነት እሳቱን የማጥፋት ሳይሆን እቶኑን የመሸሽ ምክረ-ሃሳብ የታዘለበት ነው፡፡ “ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ” እንዳለው ከያኒ ሆኖ ግን ታሪክ የትናንት ፖለቲካ ቅሪት በመሆኑ፤ የዛሬያችንንም የነጋችንንም ፍኖት የሚቀይስበት ወሳኝ ሚና እንዳለው በአቶ ሙስጠፌ ንግግር ብዙም ከግምት የገባ አይመስልም፡፡ በታሪካችን ላይ ያለው ምንታዌ ዲስኩር በ”አጥፊ” እና “ጠፊ” ላይ የተቸነከረ መሆኑ የቀደሙ መንግሥታትን በጥንካሬና ድክመታቸው ልክ አስልቶ ሚዛናዊ ለመሆን የቸገረበት ዘመን ላይ ነን። ይኽ አዎንታዊ አካሄድ ቦታ ያጣው ደግሞ ታሪክ ለዛሬና ነጋችን ትርጉሙ ትልቅ መሆኑ በሁለቱም ወገን በመታመኑ ይመስላል፡፡ በርግጥ ይኽ ታሪክ ላይ ክችች ያለ አተያይ አሁን አሁን ለዘብ ያለ ቢመስልም፣ አንድን ሥርዓተ መንግሥትና መሪውን በፍትሐዊ የታሪክ ሚዛን ለመዳኘት ችግር ሆኖ ጽልመቱ ብቻ ለአንድ ወገን ፤ አብርሆቱ ብቻ  ደግሞ ለሌላው ወገን መታየቱ መግፍዔው ምንም ይሁን ምን ታሪክ ላይ ተደጋግፎ ለመሄድ ያለመቻላቸውን ያሳያልና በከባድ የምንታዌነት አዙሪት ላይ ለመውደቃችን አስረጂ ነው፡፡
ለ) ዛሬ ፤ በሕልውናችን ላይ
የመጠፋፋት ፖለቲካችን ዓይኑን አፍጥጦ፤ ጥርሱን አግጥጦ በርግጥም በኢትዮጵያችን መቀጠል/ አለመቀጠል አጣብቂኝ የመላምት መቀዣበር ውስጥ የከተተን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ዛሬ ነው፡፡ ዛሬ ከትናንት “የጭቆናና የብዝበዛ ትርክት” በሚቀዱ ዕሳቦቶቻችን ሳቢያ ታሪክ ለመማርያ ሳይሆን ለመኖርያ መዋል ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የትናንት የጽልመት/አብርሆት ተረክ፣ “ዛሬን እንዴት እንኑር?” ለሚለው አጣብቂኝ ጥያቄ እርሾ ሆኗል፡፡ “በመቃብራችን ላይ” የሚለው ኢህአዴግ ወለድ ቋንቋ ለፖለቲካ ተዋንያኑ “በክልላችን ላይ” በሚል ሸፈፍ ተደርጎ መገዛዘቻ መፈክር ሆኗል፡፡ በአጭሩ ጭልጥ ያለ ምንታዌ ውስጥ ጨምሮናል:: ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት ፌዴራላዊ (ያልተማከለ) አስተዳደር ያስፈልጋታል? ለሚለው ቀሊል ጥያቄ “ዘውጋዊ” (Ethnic) ወይም “መልክዓ ምድራዊ” (Geographic) የሚሉት ጽኑዕ አቋሞች በየትኛውም ሳይንሳዊ አመክንዮ የማይገሰሱ፣ የአንዱ ለአንዱ ዶግማዎች የሆኑበት ተዓምረኛ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንዷን አላባ (element) ነጥሎ መበየኛ ከሚያደርግ ቋንቋንም፣ አኗኗርንም፣ አሰፋፈርንም ማዕከል ያድርግ የሚለው የመሃለኞች ሃሳብ፣ ለዘመናችን ፖለቲከኞች “ጭምብል” ነው፡፡ የክልሎች አስተዳደራዊ ወሰን እንደየ ሁናቴውና አመቺነቱ ተለዋዋጭ የመሆኑ እውነታም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ተምኔት ነው፡፡ “ይኼ የኔ፤ ያም ያንተ” እንጂ “ሁሉም የእኛ” የሚለው ማስታረቂያ የዘውጉን ግዛታዊ አንድነት የሚፈታተን “ጠንቀኛ” ሃሳብ በመሆኑ ጦር ሊያሰባብቅ ይችላል፡፡ ምንታዌነት ከዚህ ወዲያ ከየት ሊመጣ?!
ሐ) ነገ ፤ በመጻዒ ዕድላችን ላይ
`Fund for Peace (FFP)` የተባለ የዓለማችን ተቋም “Fragile States Index” በሚል ወቅታዊ ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያ የመፍረስ ጋሬጣ ከተደቀነባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስለመሆኗ አሟርቷል፡፡ የተቋሙን ሟርት በጸሎትም በጥይትም ማስቆም ብንችል እንኳን፣ በመጻዒ ዕድላችን ላይ ሳይቀር በፖለቲካ ኃይሎቻችን መካከል ያለው አለመስማማት የምንታዌነት አድማሱ የት ድረስ እንደሰፋ አመልካች ነው፡፡ ነጮቹ ደጋግመው የሚሉት “Learn from yesterday, Live for today and Hope for tomorrow” አባባል፣ በኢትዮጵያችን ነባራዊ እውነታ ቦታ ያለው አይመስልም:: በትናንትና በዛሬ እውነታ የቱንም ያህል የተራራቀ መረዳት ቢኖር ፤ ነገ ለሁላችንም እኩል መሆኑ ላይ መግባቢያ ፈልጎ የጋራ ሀገር በመፍጠሩ ረገድ ዛሬም የሚደመጡ ተቃርኖዎች መኖራቸው “የእኛስ እርግማን ይሆን” ያስብላል፡፡ በአንድ ወገን፤ የኢትዮጵያ ሥነ መንግሥት የተዋቀረበት መንገድ ግዛተ ዓጼ (Empire) መሆኑን በመግለጽ የመፍትሔው ቁልፍ ከፌዴራላዊ ሥርዓትም ከፍ ማለት አለበት የሚሉ ቡድኖች፣ ታንክም ባንክም በያዙበት ክልል ጽንፍ ላይ ቆመዋል:: በግልጽ ቋንቋ “እንዳንጠፋፋ ፌዴሬሽኑን ወደ ኮንፌዴሬሽን ለቀቅ እናድርገው” እያሉ ነው፡፡ ይኽ አቋም አይደለም በመሬት በመርህ መታሰቡን የማይቀበሉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በተጻራሪ መኖራቸው ደግሞ  የነገራችን መራራቅ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ በርግጥ “ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ሀቀኛ ማድረግ” የሚለውን መፈክር ያነገበው ወገን ቁጥሩ ቀላል አለመሆኑ እንደ ማስታረቂያ ሊታይ የሚችል ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ “ከዲሞክራሲ በመለስ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ያስፈልጋታል” የሚል ሌላ ወገን መኖሩ ደግሞ ለፌዴራላዊ የራስ ገዝ አስተዳደር እንቅፋት መስሎ የሚታያቸው ወገኖች እሪታቸውን እንዲያቀልጡ ምቹ ሆኖላቸዋል። ምንታዌው አካሄድ ባልኖርንበት ነገም ላይ ጥላውን ስለ ማጥላቱ ጥሩ ማመሳከርያ አይሆነንም ታዲያ?!
መውጫ
በጽሑፉ መንደርደርያ የጠቀስናቸው ዩሱፍ ያሲን “ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት” በተባለው መጽሐፋቸው፤ በሀገራችን ውስጥ ራሳቸውን (ማንነታቸውን) በብሔር፣ በቋንቋ ተናጋሪነት፣ በኃይማኖት፣ በመደብና ሌሎችም ስብስቦች የሚገልጹ ወገኖችን ጥያቄ ለመመለስና ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የእያንዳንዳችንን ፍላጎት ማክበር የሚችል የዜግነት ማዕቀፍ ከመፍጠር ውጪ አማራጭ የለንም ይላሉ፡፡ ዩሱፍ በዜግነት (ዜጋ) የመብት ጥላ በሚበጅ የሕግ ማሰርያ ከኢትዮጵያ ሸክም በላይ የመሰለን ጥያቄ ሁሉ መልስ ማግኘት ይችላል ባይ ናቸው:: (መጽሐፋቸው ቢነበብ መልካም ነው)፤ ገለታው ዘለቀ (አባቴ አይደሉም) የተባሉ ተቀማጭነታቸውን በምዕራቡ ዓለም ያደረጉ ጸሐፊ በበኩላቸው፤ ሀገራችን አሁን ከገባችበት ማኅበረ ፖለቲካዊ ቀውስ ለመውጣት ኢትዮጵያውያን “አዲስ ኪዳን መግባት ይኖርብናል” ይላሉ:: ይኽ ምክራቸውም ቢሆን ጊዜ ተወስዶ ቢታሰብበት ትናንትን፣ ዛሬንና ነጋችንን ከጠረነፈብን የምንታዌ አካሄድ  መውጫ ዕድል ላያጣልን ይችላልና ገንዘብ ብናደርገው ይበጃል፡፡ ሠላም!  


Read 2501 times