Saturday, 06 June 2020 14:28

የኮሮና ጥቃት በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   • በአውሮፓ እግር ኳስ የዋጋ ተመን ውድድሮች ቢቀጠሉ በ17.7%፤ ቢሰረዙ በ26.5% ይወርዳል KPMG
     • ‹‹የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ቢቀጠሉ 6.6 ቢሊዮን ዩሮ፤ ቢሰረዙ 10.5 ቢሊዮን ዩሮ ማክሰራቸው አይቀርም፡፡ KPMG
     • የዓለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ዓመታዊ ገቢ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከኮሮና በፊት ከነበረው ገቢ 9 በመቶ ቀንሷል FORBES

         (ካለፈው የቀጠለ)
ከሁለት ሳምንት በፊት ኬፒኤምጂ የተባለ ዓለምአቀፍ ተቋም ባሰራጨው ሪፖርት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በአውሮፓ እግር ኳስ ያጋጠመውን የፋይናንስ ቀውስ ማንም ሊቋቋመው አይችልም፡፡ የኬፒኤምጂ ልዩ ቡድን ባቀረበው ትንታኔ ወረርሽኙ በሁሉም ባለድረሻ አካላት ላይ መጠኑ ይለያይ እንጂ ኪሳራ ደርሷል፡፡ KPMG የእግር ኳስ ክለቦችና ተጨዋቾቻቸው በፋይናንስ እንቅስቃያቸው እና በዲጂታል መረብ ያሉባቸውን ሁኔታዎች በጥልቅ በመተንተን የሚሰራ ከመሆኑም በላይ፤ የእግር ኳስ ኢንዱስትሪውን ባለድርሻ አካላት በውሳኔያቸው ልዩ ፈጠራ እና አቅም እንዲኖራቸውም ያማክራል፡፡ Player value not immune to pandemic ፡ An analysis of the impact of the COVID-19 crisis on football players’market values በሚል ርእስ በKPMG የቀረበው ትንታኔ፤ በወረርሽኙ ሳቢያ በተጨዋቾች  ላይ የደረሰውን የዋጋ ማሽቆልቆል እና ተያያዥ ተፅእኖዎችን ተመልክቷቸዋል::  በአውሮፓ 10 ትልልቅ ፕሮፌሽናል ሊጎች እና 4185 ተጨዋቾቻቸው ላይ በሚያተኩረው ትንታኔ የክለቦችና የተጨዋቾቻቸው ዋጋ የቀነሰው በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑ ተዘርዝሯል፡፡  ከ24 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ተጨዋቾች በየክለቡ  መብዛታቸው፤  በተጨዋቾች ስብስብ ለመጠናከር ወደ የየራሳቸው አካዳሚዎች ክለቦች ማተኮራቸው፤ በነፃ ዝውውር ተጨዋቾችን ለማግኘት  ክለቦች መስራታቸው፤ የኮንትራት ውሎች መራዘማቸው፤ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ የሚካሄድበት ጊዜ በቂ አለመሆኑ፤  በኮሮና ሳቢያ ክለቦች ለፋይናንስ እጥረትና ለኪሳራ መጋለጣቸው፤ በክለቦች መካከል የተጨዋቾች ውሰትና ቅይይር መለመዳቸውና በገበያው ከሻጮች ይልቅ ገዢዎች በመብዛታቸው ነው ተብሏል፡፡ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ በአውሮፓ እግር ኳስ ሊጎች፤ ክለቦችና ተጨዋቾች ላይ ያጋጠመው የዋጋ ማሽቆልቆል ለሚቀጥሉት አመታት የሚዘልቅ መሆኑንም ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ያለፉትን 3 ወራት የየሊጎቹ ውድድሮች በመቋረጣቸው ብቻ ያጋጠሙት ኪሳራዎች አሳሳቢ ሲሆኑ፤ የሚሰረዙ ካሉም ጭራሽኑ የተስተዋሉት ችግሮች ይባባሳሉ፡፡ በKPMG የቀረበው ትንታኔ በአውሮፓ እግር ኳስ የደረሰውን ኪሳራ ያሰላው ሁለት ሁኔታዎችን በማገናዘብ ሲሆን፤ ከኮሮና በፊት የነበራቸው የዋጋ ተመን፤ ውድድሮች ከተሰረዙና ውድድሮች ካቆሙበት ከቀጠሉ የሚኖራቸውን የዋጋ ተመን በማነፃፀር ነው፡፡
በሌላ በኩል በጦርነቶች፤ በተፈጥሮ አደጋዎች፤ በተለያዩ ግዜያት ዓለምን ባጋጠሟት የኢኮኖሚ ቀውሶች ያን ያህል መናጋት ውስጥ የማይገቡት ፕሮፌሽናል ስፖርቶች በኮሮና ቫይረስ ግን ክፉኛ መመታታቸውን ፎርብስ መፅሄት አስታውቋል፡፡ የዓለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ዓመታዊ ገቢ ከ1 ዓመት በፊት ከነበረው በ9 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በሚቀጥሉት ዓመታትም ማሽቆልቆሉን የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የዓመታዊ ገቢ መቃወስ ሁሉንም አይነት ሊጎች እና ስፖርቶች እያዳረሰም ነው፡፡ በአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ የደሞዝ ቅነሳዎች እየተደረጉ ናቸው፡፡ በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ክለቦች የተጨዋቾች ደሞዝን በ70 በመቶ እንዲቀንስ አድርገዋል፡፡ በቦክስ ስፖርት ግጥሚያዎች በመሰረዛቸው እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ያጡ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችም አሉ፡፡
ዋጋቸው የወረደባቸው 5 ተጨዋቾች
የኮሮና ወረርሽኝ ሳይጠበቅ የብዙ ታላላቅ እግር ኳስ ተጨዋቾች ዋጋ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል፡፡  ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫን ማሸነፍ የቻለው የ21 ዓመቱ ኪሊያን ምባምፔ ዋጋቸው ከወረዱ ተጨዋቾች የመጀመርያው ተጠቃሽ ነው፡፡ በፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴንትዠርመን ክለብ የሚጫወተው  ኪሊያን፤ ከኮረና በፊት  225 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ነበረው፡፡ በፈረንሳይ ሊግ 1 ውድድሮች ከተሰረዙ በኋላ ግን ይህ ግምቱ  ወደ 177 ሚሊዮን ዩሮ ወርዷል፡፡ የፈረንሳይ ሊግ 1 ቢቀጥልም ኖሮ  ዋጋው መውረዱ አይቀርም ነበር- ወደ  188 ሚሊዮን ዩሮ:: ከዚህ በታች በቅደም ተከተል የቀረበው- ከኮሮና በፊት (ውድድሮች ከተሰረዙ)  ውድድሮች ካቆሙበት ከቀጠሉ  ተጨዋቾች  የሚኖራቸው የዋጋ ተመን ነው፡፡
ኪሊያን ምባምፔ -225 ሚሊዮን ዩሮ (177 ሚሊዮን ዩሮ) 188 ሚሊዮን ዩሮ
ኔይማር -175 ሚሊዮን ዩሮ (137 ሚሊዮን ዩሮ)  149 ሚሊዮን ዩሮ
ራሂም ስተርሊንግ- 150 ሚሊዮን ዩሮ (129 ሚሊዮን ዩሮ)  134ሚሊዮን ዩሮ
ሊዮኔል ሜሲ- 175 ሚሊዮን ዩሮ (127 ሚሊዮን ዩሮ)  134 ሚሊዮን ዩሮ
መሐመድ ሳላህ- 155 ሚሊዮን ዩሮ (124 ሚሊዮን ዩሮ)  131 ሚሊዮን ዩሮ
በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት በአውሮፓ እግር ኳስ ተጨዋቾች ላይ ካጋጠመው የዋጋ ማሽቆልቆል ጋር በመያያዝ አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው የጁቬንትሱ ክርስትያኖ ሮናልዶ ሲሆን፤ በ78. 4 ሚሊዮን ዩሮ ወጋ ተተምኖ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያው 45 ደረጃ እንደተሰጠው ትራንስፈርማርከት በተሰኘ ድረገፅ  መግለፁ ነው፡፡ የ34 ዓመቱ ክርስትያኖ ሮናልዶ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጣሊያኑ ጁቬንትስ ክለብ ባሳለፈው ቆይታ  ተፈላጊነቱን እንዳሳጣው  የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከ2018 ጀምሮ በጁቬንትስ ክለብ 73 ጨዋታዎችን አድርጎ 53 ጎሎችን ቢያስመዘግብም ከፍተኛ ገቢውን እየሰበሰበ ያለው ከሜዳ ውጭ ነው፡፡ የጀርመኑ ዌብሳይት ትራንስፈርማርከት  በታዋቂው ማናጀር ጆርጌ ሜንዴዝ ስር ያሉ 11 ምርጥ ተጨዋቾችን በመለየትና በማሽቆልቆል ላይ ያለውን ዋጋቸውን በመስራት በኢንስታግራም ሲለጥፍ ክርስትያኖ ሮናልዶ ግን ለዚሁ የገበያ ትንታኔ እውቅና በመንፈግ ድረገፁን እንዳገደው ታውቋል፡፡ ትራንስፈርማርከት ከኮሮና በፊት ለክርስትያኖ ሮናልዶ የሰጠው የዋጋ ተመን 125.26 ሚሊዮን ዩሮ ነበር፡፡
ዋጋቸው የወረደባቸው 5 ክለቦች
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ የተጨዋቾች ዋጋ ተመን ማሽቆልቆሉ  የታላላቅ ክለቦችን አጠቃላይ ዋጋ እንዲወርድ ማድረጉንም  የኬፒኤምጂ ትንታኔ አረጋግጧል፡፡ በተለይ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑል በከፍተኛ ደረጃ ዋጋው መቀነሱ በውድድር ዘመኑ ከነበረው ስኬት ጋር የማይመጣጠን ሆኗል፡፡ እንደ ኬፒኤምጂ ትንታኔ ከኮሮና በፊት በቡድን ስብስቡ 1.2 ቢሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን የነበረው ሊቨርፑል ሊጉ ካቆመበት ቢቀጥል 203 ሚሊዮን ዩሮ ሙሉ ለሙሉ ከተሰረዘ ደግሞ 293 ከዋጋው መውረዱ አይቀርም፡፡ የስፔኖቹ ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎናም በቡድን ስብስባቸው ከኮሮና በፊት የነበራቸው ቢሊዮንን የተሻገረ የዋጋ ተመን ይወርዳል:: ከዚህ በታች በቅደም ተከተል የቀረበው- ከኮሮና በፊት (ውድድሮች ከተሰረዙ)  ውድድሮች ካቆሙበት ከቀጠሉ  ክለቦች  የሚኖራቸው የዋጋ ተመን ነው፡፡
ማንችስተር ሲቲ  - 1.24 ቢሊዮን ዩሮ (961 ሚሊዮን ዩሮ) 1.05 ቢሊዮን ዩሮ
ሊቨርፑል -  1.20 ቢሊዮን ዩሮ (907 ሚሊዮን ዩሮ) 997 ቢሊዮን ዩሮ
ሪያል ማድሪድ -  1.168 ቢሊዮን ዩሮ (851 ሚሊዮን ዩሮ) 944 ቢሊዮን ዩሮ
ባርሴሎና -  1.136 ቢሊዮን ዩሮ (808 ሚሊዮን ዩሮ) 903 ቢሊዮን ዩሮ
ማንችስተር ዩናይትድ -  (923 ሚሊዮን ዩሮ)) 714 ሚሊዮን ዩሮ 716 ቢሊዮን ዩሮ
የውድድራቸው ዋጋ የወረደባቸው 5 ሊጎች
ኬፒኤምጂ በሰራው ትንታኔ በአውሮፓ የሚካሄዱ 10 ፕሮፌሽናል የሊግ ውድድሮችን የዳሰሰ ሲሆን የኮሮና ተፅእኖ በተጨዋቾችና በክለቦች ላይ የፈጠረው የዋጋ መውረድ የየሊጎቹን ደረጃ እና የዋጋ ተመን እንደቀነሰው ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ ከዚህ በታች በቅደም ተከተል የቀረበው- ከኮሮና በፊት (ውድድሮች ከተሰረዙ)  ውድድሮች ካቆሙበት ከቀጠሉ  ሊጎቹ የሚኖራቸው የዋጋ ተመን ነው፡፡
የፈረንሳይ ሊግ 1 - 3.73 ቢሊዮን ዩሮ (2.72 ቢሊዮን ዩሮ) 3.082 ቢሊዮን ዩሮ
የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ - 6.64 ቢሊዮን ዩሮ (4.74 ቢሊዮን ዩሮ) 5.395 ቢሊዮን ዩሮ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ - 10.513 ቢሊዮን ዩሮ (7.84 ቢሊዮን ዩሮ) 8.864 ቢሊዮን ዩሮ
የጀርመን ቦንደስ ሊጋ -  5.189 ቢሊዮን ዩሮ (4.097 ቢሊዮን ዩሮ) 4.581 ቢሊዮን ዩሮ
የጣሊያን ሴሪኤ - 5.72 ቢሊዮን ዩሮ (4.229 ቢሊዮን ዩሮ) 4.734 ቢሊዮን ዩሮ
ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች
በሳምንቱ መግቢያ ላይ ታዋቂው የቢዝነስ መፅሄት ፎርብስ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት እንደተገለፀው የዓለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ባለፈው 1 ዓመት ከ3.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተከፍሏቸዋል:: የፕሮፌሽናል ስፖርተኞቹ ዓመታዊ ገቢ የተሰላው በደሞዝ እና የቦነስ ክፍያዎችን እንዲሁም የተለያዩ የማስታወቂያ እና የስፖንሰርሺፕ ገቢዎችን የሚጨምር ነው፡፡ በዓለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ዝርዝር ላይ 21 የተለያየ አገራት ዜግነት ያላቸው እና በ10 ፕሮፌሽናል ስፖርቶች የሚገኙ ተካትተዋል፡፡ 68 የአሜሪካ፤ 5 የእንግሊዝ፤ 4 የስፔን፤ 3 የፈረንሳይ እንዲሁም እያንዳንዳቸው 2 የብራዚል፣ ጃፓንና፣ ጀርመን ዜግነት ያላቸው ይገኙበታል ፡፡  ከ100ዎቹ ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች 35 የቅርጫት ኳስ፤ 31 የእግር ኳስ እንዲሁም 15 የቤዝቦል ስፖርቶችን በመወከል ይጠቀሳሉ:: በደረጃው ዝርዝር ሁለት የሜዳ ቴኒስ ፕሮፌሽናል ሴት ስፖርተኞች  የገቡ ሲሆን እነሱም ጃፓናዊቷ  ናኦሚ ኦሳካ እና ሴሪና ዊልያምስ ናቸው፡፡ ናኦሚ ኦሳካ በ37.4 ሚሊዮን ዶላር 29ኛ እንዲሁም ሴሪና ዊልያምስ በ36 ሚሊዮን ዶላር 33ኛ ደረጃን አግኝተዋል፡፡
የሜዳ ቴኒስ ስፖርት የምንግዜም ምርጥ ሮጀር ፌደሬር የዓለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን ደረጃ በአንደኛነት የሚመራው በ106.3 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ፌደረር ከዓመታዊ ገቢው በቀጥታ ከደሞዝ የወሰደው 6 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን  ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሰበሰበው ደግሞ በውድድር ዘመኑ ከ13 ትልልቅ ኩባንያዎች ጋር በመስራት ነው፡፡ ከፌደረር ጋር ከሚሰሩ ኩባንያዎች መካከከል ናይኪ፤ ክሬዲት  ሱሲ፤ ባሪላ እና ሮሌክስ ሰዓት ይጠቀሳሉ፡፡
ከእግር ኳስ ተጨዋቾች መካከል ክርስትያኖ ሮናልዶ በ105 ሚሊዮን ዶላር  እንዲሁም ሜሲ በ104 ሚሊዮን ዶላር   ዓመታዊ ክፍያ በማግኘት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ ኔይማር በ95.5 ፤ ማሀመድ ሳላህ በ35.1፤ ኪሊያን ማብምፔ በ33.8፤ አንድሪዬስ ኢንዬስታ በ29.6፤ ሜሱት ኦዚል በ28.7፤ ፖል ፖግባ በ28.5፤ ኦስካር  በ27.5 እንዲሁም አንቶኒዮ ግሪዝማን በ26.7 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢያቸው እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይይዛሉ፡፡
የፎርብስ መፅሄት የ2020 የዓለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች የደረጃ ዝርዝር የወጣው ከጁን 1 /2019 እስከ ጁን 1/ 2020 እኤአ ድረስ ባገኙት ክፍያ መሰረት ሲሆን ከዚህ በታች የቀረበው ከ1 እስከ 10 ያለውን ደረጃ የሚይዙት ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች  ናቸው::
ሮጀር ፌደሬር (ሜዳ ቴኒስ) 106.3 ሚሊዮን ዶላር
ክርስትያኖ ሮናልዶ (እግር ኳስ) 105 ሚሊዮን ዶላር
ሊዮኔል ሜሲ (እግር ኳስ) 104 ሚሊዮን ዶላር
ኔይማር (እግር ኳስ) 95.5 ሚሊዮን ዶላር
ሊብሮን ጀምስ (ቅርጫት ኳስ) 88.2 ሚሊዮን ዶላር
ስቴፈን ኪውሪ (ቅርጫት ኳስ) 74.4 ሚሊዮን ዶላር
ኬቪን ዱራንት (ቅርጫት ኳስ) 63.9 ሚሊዮን ዶላር
ታይገር ውድስ (ጎልፍ) 62.5 ሚሊዮን ዶላር
ኪርክ ኮውዚን (አሜሪካን ፉትቦል) 60.5 ሚሊዮን ዶላር
ካርሰን ዌንትዝ (አሜሪካን ፉትቦል)  59.1 ሚሊዮን ዶላር
ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች
 በስፖንሰርሺፕ ውሎች
እንደፎርብስ መፅሄት ከሆነ የዓለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ባለፈው 1 ዓመት ከማስታወቂያ ውሎች፤ ከልዩ ልዩ የመታሰቢያ ምርቶች ሽያጭ እና ከልዩ የተሳትፎ ክፍያዎች 1.1 ቢሊዮን ዶላር አግኘተዋል፡፡ 51 ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች በናይኪ የስፖርት ትጥቅ አምራች ስፖንሰርሺፕ ሲያገኙ፤ 16 ከጀርመኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ እንዲሁም 13 ከፔፕሲ ኩባንያ ምርቶች ጋር ውሎችን  ፈፅመዋል፡፡ ይሁንና በሚቀጥለው አንድ አመት የፕሮፌሽናል ስፖርተኞች የስፖንሰርሺፕ አመታዊ ገቢ በ37 በመቶ እንደሚቀንስ የፎርብስ ትንታኔ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡት በስፖንሰርሺፕ ውሎች ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙ 5 ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ናቸው፡፡
ሮጀር ፌደረር 58 ሚሊዮን ዶላር
ከፓስታው ምርት ባሪላ ጋር በሚሰራበት የስፖንሰርሺፕ ውል በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ማግኘቱ ትልቁ ገቢው ነው፡፡ ስፖንሰር ያደረጉት ኩባንያዎች Rolex, Mercedes Benz, Uniqlo, Wilson, Mercedes-Benz, Jura, Lindt Chocolate, Credit Suisse, Sunrise, Net Jets, Moet & Chandon, Gilette, Procter & Gamble
ሊብሮን ጀመስ 55 ሚሊዮን ዶላር
ከአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ ጋር የተፈራረመው የህይወት ዘመን የስፖንሰርሺፕ ውል 1 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ አለው፡፡ Coca-Cola, Nike, Upper Deck, McDonald’s, Samsung, Microsoft  ሌሎቹ ስፖንሰሮቹ ናቸው፡፡
ፊል ሚከልሰን 40 ሚሊዮን ዶላር
ለ15 ዓመታት ከትልቁ ባንክ ባርክሌይ ጋር የሰራ የጎልፍ ተጨዋች ስፖርተኛ ሲሆን ከሌሎች ስፖንሰሮቹ Callaway, KPMG ይገኙበታል፡፡
ታይገር ውድስ 37 ሚሊዮን ዶላር
በፕሮፌሽናል ስፖርት ለ20 ዓመታት የቆየው ታይገር ውድስ ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያገኘ ሲሆን የገንዘብ ሽልማቶቹ ከዚህ ገቢው 10 በመቶ ቢሸፍኑ ነው፡፡  Under Armour, AT&T, Coca-Cola, Titleist, Rolex, General Mills ከታይገር ውድስ ስፖንሰሮች ይጠቀሳሉ፡፡
ስቴፈን ኩሪ 37 ሚሊዮን ዶላር
ባለፉት 3 የውድድር ዘመናት 207 የቅርጫት ኳስ ግጥሚያዎችን ከክለቡ ጎልደን ስቴት ጋር አሸንፏል:: ባለፉት ሁለት አመታት ደግሞ በአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ከፍተኛው የማልያ ሽያጭን እያስመዘገበ ነው፡፡ ከስፖንሰሮቹ መካከል Under Armour, Samsung Electronics, Coca-Cola, Kia Motors ይጠቀሳሉ፡፡


Read 211 times