Saturday, 06 June 2020 14:31

ዓለምን ያነቃነቀ፣ የእልፍ ጥቁሮችን ዕጣ ያንጸባረቀ የአንድ ጥቁር ሞት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም…
በአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ከተማ 38ኛው ጎዳና ዳር…
ጥቁሩ ሰው ጥቁር አስፓልት ላይ በደረቱ ተነጥፎ ቃተተ፡፡
እጆቹ በሰንሰለት እንደተጠፈሩ አስፓልቱ ላይ ተዘርሮ የሚቃትተው ጥቁሩ ፍሎይድ፤ አንገቱን በጉልበቱ ረግጦ ለሚያሰቃየው ፈርጣማ ነጭ ፖሊስ የምህረት ተማጽኖ አሰማ፡-
“እባክህ… መተንፈስ አልቻልኩም!... እባክህ…” በማለት እንደ ምንም ደጋግሞ ሊለምነው ሞከረ፡፡
ነጩ ፖሊስ ግን ከስምንት ደቂቃ በላይ አንገቱን ረግጦ ሲያሰቃየው ለቆየው ጥቁር የሚራራ ልብ አልነበረውም፡፡ ከሞት ጋር እየታገለ በሰለለ ድምጽ ለሚለምነው ሰው፣ የትንፋሽ አፍታ ሊሰጠው አልፈቀደም፡፡ ጉልበቱ ስር ተዝለፍልፎ ሲቃትት የሚሰማው ሰው፣ የልብ ትርታው ይቀጥል ዘንድ አልወደደም - እስከ መጨረሻው መጨከን የሚችልበት ነጩ ፖሊስ ዴሪክ ቾቪን፡፡
ጥቁሩ ጆርጅ ፍሎይድ፣ ከነጩ ፖሊስ ጉልበት ስር ጸጥ አለ!
ይህንን አሳዛኝ ክስተት በቅርብ ርቀት ተደብቃ ስትከታተል የነበረች አንዲት ቅንና አዛኝ ታዳጊ፣ የሆነውን ሁሉ በሞባይሏ ቀርጻው ነበርና በማህበራዊ ድረገጾች አሰራጨችው፡፡ አለም ሰው በሰው ላይ ያደርገዋል ተብሎ የማይታመነውን ድርጊት፣ ከአጭሩ ቪዲዮ ላይ እያየ ደነገጠ… አዘነ… ተናደደ… ብዙ ነገር ሆነ፡፡
ዴሪክ ቾቪን በተባለው ነጭ ፖሊስ በአሰቃቂ ሁኔታ አደባባይ ላይ የተገደለው የ46 አመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ጉዳይ መላውን አለም ያስደነገጠና ታላላቅ መገናኛ ብዙሃንን ለወራት ከቆዩበት የኮሮና ዘገባ ያወጣ አነጋጋሪ አለማቀፍ ዜና ሆነ፡፡ ከአንድ መደብር ግዢ ፈጽሞ የከፈለው ዶላር ሃሰተኛ ነው በሚል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለውና በአሰቃቂ ሁኔታ ለሞት የተዳረገው ጆርጅ ፍሎይድ፤አሜሪካውያንን በተለይ ደግሞ የቀለም ልዩነት ያንገበገባቸውን ጥቁሮች በቁጣ አነደዳቸው፤ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ወደ ጎዳና እንዲወጡ ፈነቀላቸው፡፡
በሚኒያፖሊስ በሺህዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን የቀለም ልዩነትንና ዘረኝነትን በመቃወም ጎዳናዎችን አጥለቀለቁ፡፡ ተቃውሞው ወደ ሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ለመዛመት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ “የጥቁር ሕይወት ዋጋ አለዉ” ፣ “ፍትሕ ከሌለ ሰላም የለም”፣ “መተንፈስ እፈልጋለሁ” እና የመሳሰሉ መፈክሮችን ያነገቡ በርካታ ተቃዋሚዎች፣ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ጎዳናዎችን አጥለቀለቁ፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ፣ ሰላማዊው ተቃውሞ ቁጣ ወደተቀላቀለበት የአመጻ ድርጊት ተለወጠ፡፡ ከዋሽንግተን እስከ ኒውዮርክ፣ ከካሊፎርኒያ እስከ ቺካጎ በቁጣ የነደዱ ተቃዋሚዎች ፖሊስ ጣቢያዎችን፣ መኪኖችን፣ መደብሮችን፣ መጋዘኖችንና ሌሎች ተቋማትን በእሳት ማጋየታቸውንና መዝረፋቸውን ተያያዙት፡፡
ነገሩ ያሰጋው የዶናልድ ትራምፕ መንግስት፤ ዋሽንግተንን ጨምሮ በ23 ያህል የአሜሪካ ግዛቶች የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን አሰማራ፤ ከ40 በሚበልጡ የአገሪቱ ከተሞችም የሰዓት እላፊ ገደብ ጣለ፡፡ የዘረኝነት ጥቃት ያንገበገባቸው በርካቶች ግን፣ የሰዓት ዕላፊ አዋጁም ሆነ የኮሮና ቫይረስ ስጋት ሳይገድባቸው ከዳር እስከ ዳር ለተቃውሞ መትመማቸውንና አሜሪካን በእሳት መለብለባቸውን አላቋረጡም፡፡ ከቺካጎ እስከ ፊላዴልፊያ፣ ከሎሳንጀለስ እስከ ሲያትል ተቃዋሚዎችና ፖሊስ ተፋጥጠው ውለው ማደርና በአስለቃሽ ጭስ መሯሯጥ ያዙ፡፡
“የተቃዉሞ ሰልፈኛውን ለቁጣና ለጥፋት የሚገፋፉት ግራ አክራሪዎች ናቸዉ” በማለት ተቃውሞውን ያወገዙት ትራምፕ፤ ስርዓት እንዲከበር ደጋግመው ቢማጸኑም የሚሰማቸው አላገኙም፡፡ የትራምፕ መንግስት ፍሎይድን በጭካኔ የገደለውን ዴሪክ ቾቪንን ጨምሮ አራት ፖሊሶችን ከስራ ማሰናበቱንና የግድያ ወንጀል ክስ መመስረቱን ይፋ ቢያደርግም፣ እርምጃቸው ለተፈጸመው ግፍ የሚመጥን አይደለም ያሉ ተቃዋሚዎች፣ የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ከማቃጠል እስከ ሃውልት ማፍረስና እሳት ማንደድ በቁጣ ድርጊታቸው ገፉበት፡፡
ተቃውሞው መልኩን እየቀየረ ወደለየለት ብጥብጥ መግባቱ ያሰጋው የትራምፕ መንግስት፣ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ህግ ጥሰዋል ያላቸውን ተቃዋሚዎች እየተከታተለ ማሰሩን የዘገበው አልጀዚራ፤ እስካለፈው ሃሙስ ድረስ በአገሪቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡ ፖሊስ ብዙዎችን ባሰረና ቀናት በተፈራረቁ ቁጥር ግን፣ ቁጣውና ተቃውሞው እየተቀጣጠለ ተስፋፋ እንጂ አልቀነሰም፤ ይባስ ብሎም ከአሜሪካ ወጣና ወደ ሌሎች የአለም አገራት ተስፋፋ፡፡
በአሜሪካ ጥቁሮች ላይ የሚፈፀመው ቀለምን መሰረት ያደረገ ግፍና ጭቆና እንዲቆምና የጥቁሮቹ ጥያቄ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጠው የሚጠይቀውን ተቃውሞ በመደገፍ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ብዙዎች በተለያዩ የአለማችን አገራት  ሰልፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከአሜሪካ ወደ ፈረንሳይ የተሻገረው የተቃውሞ ሰልፉ ከካናዳ እስከ ብሪታንያ፣ ከጀርመን እስከ ብራዚል፣ ከኒውዚላንድ እስከ ሜክሲኮ፣ ከሆላንድ እስከ ኢራን፣ ከኬንያ እስከ ኮንጎና ታንዛኒያ፣ ከእስራኤል እስከ ፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር፣ ከዴንማርክ እስከ ጣሊያን፣ ከጃፓን እስከ ኒውዚላንድና ሌሎችም የአለማችን አገራት ተስፋፍቶ ቀጥሏል፡፡
የሮማው ሊቃነ ጻጻስ ፍራንሴስን፣ የእንግሊዙን ቦሪስ ጆንሰንና የቱርኩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቩልት ካቩዝኮሉን ጨምሮ የበርካታ የአለማችን አገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት የፍሎይድን ግድያ በማውገዝ ዘረኝነትንና ቀለምን መሰረት ያደረገ ግፍና ጭቆናን በመኮነን ላይ ናቸው፡፡ ከትናንት በስቲያ የወጣው የዘ ጋርዲያን ዘገባ፣ በፍሎይድ የትውልድ ከተማ ሂዩስተን 60 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት የሀዘን ጉዞ መደረጉን የጠቆመ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሟቹ አስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ ፍሎይድ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅቶ እንደነበር ለማረጋገጥ መቻሉን አመልክቷል፡፡
በአሰቃቂ ሁኔታ በግፍ የተገደለውና አለምን በተቃውሞ ያጥለቀለቀውን ጆርጅ ፍሎይድ ለማሰብ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ የቀብር ስነስርዓቱም በመጪው ማክሰኞ በሂዩስተን እንደሚከናወን መነገሩን አልጀዚራ ባለፈው ሃሙስ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡

Read 5958 times