Print this page
Saturday, 06 June 2020 14:33

“እኅ‛ናት” ልብ ወለድን በወፍ በረር

Written by  ታገል አምሣል
Rate this item
(0 votes)

   የመጽሐፉ ርእስ፡- እኅ‛ናት
ደራሲ፡- ደሣለኝ ስዩም
ዘውግ ፡- ረጅም ልብ ወለድ
ዋጋ፡- 61፡00 ብር
እኅ‛ናት በአማርኛ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ የተለየ አሻራ ይኖረዋል? ዳኝነቱን ላንባቢ ለመስጠት ያህል፣ የእኀ‛ናትን የሥነ ጽሑፍ ጣሪያ ከፍ ያደረጉትና ኪናዊ ውበቱን ላቅ ያደረጉ ያልኳቸውን ስልቶች ዘርዘር አድርጌ ላቅርብ፡፡ ይህን ስል ግን ሥነ ጽሑፍ የተቀመጠለትን ወርድ፣ ቁመትና ይዘት በውል በማጤን፣ የት ጋ እንዳለ መፈረጅ አይቻልም ማለት አይደለም፡፡
“ከተቀመጠለት መሥፈሪያ ተሻግረን የማሰብ ልዕልናችንና ሌላ የተሻለ መለኪያ የመቅረጽ እድላችን በቀደመ ሚዛን ሊገታ አይገባም!” የሚል ካለ፤ ዓለም ፈጽማ ”እፎይ ጨረስኩ!“ ያለችው አንድም ነገር እንደሌለ በመጠቆም፣ ሜዳውም ፈረሱም ያው!
እኅ‛ናት ልብወለድ ነው፤ Existentialism የተሰኘ ፍልስፍናን ተከትሎ የተጻፈ ልብወለድ፣ ገልጠው ሳይጨርሱ ንቅንቅ እንዳይሉ የአንባቢያንን ስሜት ሰቅዞ የመያዝ አቅም የተጎናፀፈ ጥሩ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ነው፡፡ የገጽ ሽፋኑ ቀለም፣ ርእሱ፣ ሽፋኑ ላይ ያለው ሕጻን የታቀፈች እናት ምስል በቀላሉ ነጋሪ አለመሆናቸውን የምናውቀው ታሪኩን አንብበን ስንፈጽም መሆኑ ልከኛና የተናበበ ዝገግጅት እንደሆነ ያሳምናል፡፡ ሽፋኑን ገልጠን ወደ ታሪኩ ስንገባ፡
“እንደዛር እሚጎነትል ሐቅ እንድጠይቅ እሚያስጥር
ያራቡኝን ያጠሙኝን የነሱኝን የሐቅ እድር
እንድጠይቅ እንድጠይቅ   እሚያረገኝ እርር ክርር
ነፍሴን ከልቤ እሚያሟግት  በሐቅ ርሀብ እስክጣጥር፤”
---ብሎ ይጀምራል በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ”ማነው ምንትስ”  ግጥም፡፡  ለመኖር ስትል የተሠማራችበት መንገድ፡ ከምትኖርበት ማኅበረሰብ ደንብና ስርዐት ጋር ተጣርሶባት፣ ፈታኝ የማንነት ቀውስ ውስጥ የተነከረች ምስኪን ሴት በምናባችን እንድንሥል ይጋብዘናል፡፡ በስንኞቹ ጥሩ ንግር/ፍንጭ ይሰጠንና እንግዳ ስሜት ቋጥረን ወደ ውስጥ እንድንዘልቅ በዋና ገጸ ባሕሪው በበረከት ሙግት ላይ ይወዝተናል:: በረከት ከራሱ ጋር ሲሞግት፣ እኛ የሙግቱ ሥረ ነገር ያስጨንቀናል፡፡ አብረን በጥያቄ  እንማሠላለን፣ ችግሩን ለማወቅ  እንፍጨረጨራለን፣ ለመፍትሔ  እንጓጓልን:: በበረከት ኹኔታ ስሜታችን ተሰቅዞ እያለ ደግሞ ዜማ የተባለች ደግ እንስት አምጥቶ ጭላንጭል የተስፋ ብርሃን ያሳየናል፡፡
የበረከት ዝርክርክነት አሳዝኖን ሳያበቃ፣ የዜማ ደግነትን በተስፋ ያሞቀንና የችግራቸው ተካፋይ፣  ሸምጋይ፣
የምስጢራቸው አጋር እንድንሆን ያነሳሳናል፡፡  ከሁለቱ ጋር በቅጽበት ያስተሳሰረን ምትሀታዊ ፍቅር ለዘመናት አብሮን ያደገ ያህል እንደጠፈነገን፤ በረከትን መስቀል አደባባይ፣ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አስፓልት ዳር ያቆመውና አንድ ልብ ሰባሪ ትእይንት ይጋብዘዋል፡፡ አንዲት ሥጋዋ ያለቀ፣ አጥንቷ የሚቆጠር፣ ድህነት ያደቀቃት ምስኪን እናት ለልመና በተቀመጠችበት ጎዳና ደመናው እያጓራ፣ መብረቅ ጥርሱን እያፏጨ፣ ከባድ ዝናብ ሊወግራት  ሲያንዣብብ ወደ የት እንደምትጠጋ ግራ ገብቷት፣ በዚያ ላይ አንድያ ልጇ ካጠገቧ ተሠውሮባት ትይዘው፣ ትጨብጠው ቸግሯት፣ ስትቅበዘበዝ፣ በረከት በሴትዮዋ የጭንቅ ሰረገላ አንባቢን አሳፍሮ እየሾፈረ፣ በዐይነ ኅሊና ጎጃም- አቸፈር- ይስማላ ጊዮርጊስ የአንዲትን እናት ሕይወት በድንቅ ምልሰታዊ ትርክቱ ያስኮመኩመናል፤ ለስሜታችን ምንም ፋታ ሳይሰጥ ልባችንን አንጠልጥሎ ስግሪያውን ይቀጥላል፡፡
ውብ አረንጓዴ የገጠር መንደር፣ በየእርሻው የበቆሎው እሸት የሞላበት አካባቢ ይወስደንና  ይልሱት ያጡ የነጡ የድሃ ድሃ ቤተሰቦች ያስተዋውቀናል፡፡  ከመንደሩ ወጣ ብሎ ከእርሻው ዳር ከተሠራች፣ የአንድ  ከበርቴ ፈረስ ማረፊያ ከነበረችና ከበርቴውን ደርግ ሲያስረው ጠያቂ ባጣች፣ የዘመመች ሰቀላ በስደት የምትኖር ድሃ እናት፤ የጠገበ የአፍለኛው ወያኔ ካድሬ ባሏ ዘወትር ሰክሮ ሲቀጠቅጣት፣ በዱላ ብዛት በሽተኛ ሆና ሥጋዋ አልቆ፣ ጅማቷ ደቅቆ፣ መልኳ ረግፎ፣ አጥንቷ  ሲቀር፣ ነፍሷን ለማትረፍ ስትል ለሥራ ያልደረሱ ለመብል ያላነሱ ሁለት ወንድ ልጆቿን ይዛ እግሯ እንደመራት መጥታ በችጋር የምትጠበስ እናት፤  ብርድ፣ ነፋስ፣ ዝናብና ፀሐይ እንዳሻው በምታስተናግድ ያልተመረገች ሰቀላ ቤት ያረፈች እናት፤ ትለብሰው- ታለብሰው፣ ትጎርሰው- ታጎርሰው ፣ ታነጥፈው ትደርበው ..  የሌላት  ምስኪን እናት፤ ወተት የሌለው የለተተ ጡቷን በተስፋ ለሚመጠው፣  ለታቀፈችው ለአብርሓምና በመማሪያ ጊዜው የእለት ጉርስ አጥቶ ከእናቱ ጋር በሰቆቃ ለሚርመጠመጠው በረከት፣ ባልበላ አንጀቷ የማይወጣ እንባዋን በመከራ ስትጨምቅ፣ በረከት የልጅነት መንፈሱ በሰቆቃ ሲታረስ፣ በጨቅላ እድሜው ለመፍትሔ ሲያምጥ ያስቃኘናል፤  በምሥል ከሳች ትርክቱ አብረን በሀዘን እንድንማቅቅ፣ በጭንቅ እንድንወረስ፣ ለመፍትሔ ስንጥር  እንድናምጥ ያስገድደናል፡፡
ደራሲው እስከ 57ኛው ገጽ ሁሉን ዐወቅ ተራኪ ከዳር አስቁሞ፣ በሦስተኛ መደብ ሲያስተርክልን ከቆየ በኋላ ቆም ይልና ዋናው ገጸ ባሕሪ የራሱ ታሪክ መሆኑን ይነግረናል:: በራሱ ታሪክ አፍሮ አሊያም የሥነ ጽሑፍ አቅም አንሦት? ባልታወቀ ምክንያት ራሱን እንደደበቀ ይነግረንና በአንደኛ መደብ ታሪኩን መተረክ ይጀምራል፤ ይህም ደራሲው ይሁነኝ ብሎ የተከተለው አንድ ስልት በመሆኑ የፈጠረው ኪናዊ ውበት በግልፅ ይታያል፡፡  
በቁጥብና ውብ አገላለጽ የልጅነት ገጠመኙንና የማኅበረሰቡን አኗኗር ዘይቤ ይተርክልናል፡፡  በአምልኮ ቦታ፣ የካህኑን ስብከት ከመጤፍ ሣይቆጥሩ፣ አፍ ለአፍ ገጥመው፣ ሐሜትና አሉባልታ ሲወቅጡ የቆዩ ምዕመናን፣ አንድ ሰሚ ያጣ ገበሬ “ታቦት ሰርቋል” በሚል ተወንጅሎ ከፊታቸው ሲቆም ግን ሁለንተናቸው ጆሮ ሲሆን፤ ለደቦ ፍርድ፣ ለጭፍን ውንጀላ፣ ”ይሰቀል!“ ለማለት ሲያሰፈስፉ፣ በንጹሕ ሰው ጀርባ በትር ለማሳረፍ ሲጋፉ፤ በአማኝ የቁጭት ስሜት ሲደነፉ ትእይንቱን  በምናባችን እየከሰተልን፣ ሀይማኖታዊ ጉድፉን በጥበብ ያስቃኘናል፡፡  
ደራሲው እናት፣ ወጣት፣ ሴት በሚሉ አርእስት ባስቀመጣቸው ክፍሎች፣ በህወሃት አገዛዝ ሥር በነበርንባቸው ዓመታት ለፖለቲካ ግብዓት የሚደሰኮረውና ለእነዚህ ሦስቱ የተደረገው ተጨባጭ ነገር ፍፁም ተቃራኒ መሆኑን ይልቁንም የፖለቲካ ተሿሚዎች ያደርሱት የነበረው ግፍና ዝርፊያ ምን ያህል አማራሪ እንደነበር በፍጹም ኪነታዊ ለዛ ያጋራናል፡፡
ደራሲው እንዲህ በመሣሠሉ የሕይወት ግፍጫዎች ይዞ የተነሳውን ጭብጥ “ከምንም ነገር ቅድሚያ የኑሮ ኅልውናን የማረጋገጥ ፍልስፍና /Existentialism philosophy ሕይወት ዘርቶ ያሳየናል፡፡ ለዚህም የገጸ ባሕሪ አሳሳሉ ትልቅ ድርሻ ተጫውቶለታል:: ለአንዲት ቅጽበት ታይተው ከሚጠፉት እስከ ዋና ገጸ ባሕሪይው እያንዳንዳቸው በቂ ሚና ተሸክመው እንዲመጡና አሻራቸውን በደማቅ ጽፈው እንዲያልፉ አድርጎ ስለቀረጻቸው ከአንባቢ ምናብ በቀላሉ የሚሠወሩ አይደሉም፡፡ ሁሉም ገጸ ባሕሪያት መሠረታዊ ጥያቄያቸው ኅልውናን ማስከበር /Existence ይሆንና  በቀደመ መለኪያ ንጹሕ ከሚሉት  ማንነታቸው፣ ከማኅበረሰብ ደንብና ስርዐት ትንቅንቅ ሲገጥሙ እናያለን፡፡  ጽሑፉ የተዋቀረበት ቅርፅ ከአተራረኩ ጋር ተሰናኝቷል፡፡ ይህም ለጽሑፉ ከሰጠው ኪናዊ ውበት ባሻገር እያንዳንዱ ገጸ ባሕሪ በሌላው ላይ ተጽእኖ ሳያሳድር፣ ዋና ገጸ-ባሕሪያትንም ሳያደበዝዝ፣ በአንባቢው ምናብ እንዲነቀስና የራሱን ታሪክ ጽፎ እንዲሔድ ሰፊ እድል ሰጥቷል፡፡   
ሌላው የመጽሐፉ ጥሩ ብቃት የአካባቢውን ዘዬ፣ የቀበሌኛ ቃላት፣ የንግግሮችን ኹነትና ስሜት በሚገባ መጠቀሙ መቼቱንና ገጸ ባሕሪያቱን የበለጠ እንድንወዳቸው አድርጓል፤ የቋንቋ ብቃቱንም አንሮታል፡፡ አልፎ አልፎ የሚጠቀማቸው የአሽሙርና የዘይቤ አገላለፆች ደግሞ የበለጠ ኪናዊ ውበት አላብሰውታል፡፡ በረከት ”ሃያ ሁለት ብሮች ኪሴ ሰፍቷቸው ከዛና እዚህ እየተወዛወዙ ሲደንሱ አንቄ እንዳወጣኋቸው ተሰምቶኝ ራሴን መስቀል አማረኝ“ ብሎ ሲያሸሙር፤ ለብሮቹ ልዩ ትኩረት የሰጠበትንና  ያዘነላቸውን ምክንያት እንድናጠይቅ፣ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን በዚህ ኹኔታ እንደሚገኙ እንድናስብ፣ የአብዛኞቻችን የየጓዳችን ዕውነት መሆኑን አስበን እንድንቆጭ፤ሌላም ሌላም ጥያቄ እንድናነሣ ያሳስበናል፡፡
መቼት ገላጻውም ልዩ ነው፡፡ በብዙ መጻሕፍት በተለይም በድንቅ የመቼት አሣሣል የምናውቃቸው ከበዓሉ ግርማ መጻሕፍት ሀዲስ፣ የኅሊና ደወል፣ ከፍቅረ ማርቆስ ደስታ ከቡስካ በስተጀርባ፣ ከክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር፣ ከኃይለ መለኮት መዋዕል ጉንጉን ... ከመሣሠሉ ግሩም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፤ ከተለመደው በተራኪው አማካኝነት በሰፊ የመግለፅ ዘዴ እኅ‛ናት ይለያል፡፡ አጭርና ቁጥብ በሆነ መንገድ ትእይንት ፈጥሮ፣ በትእይንቱ መቼቱን፣ በመቼቱ ትእይንቱን በደንብ ማየት እንድንችል ያደርገናል፡፡  
ለምሣሌ ዜማ ለበረከት ያለፈ ሕይወቷን ልታጫውተው ተቀጣጥረው፣ ጭፈራ ቤት በተገናኙበት ምሽት፣ ጭፈራ ቤቱን አልተረከልንም፤ ትእይንቱን በምልሰት ያሁን አድርጎ ሲያቀርብልን፣ እያንዳንዱን ሁኔታ በዐይነ ኅሊናችን ዐየነው እንጂ፡፡ የታቦት ሌባውን በብረት ምጣድ በእሳት ለብልበው ሲቀጡት መቼቱን አልተረከልንም፤ትይንቱን በዐይነ ኅሊናችን ከስቶ የጎደለውን ሞልተን በሙላት እንድንረዳው አደረገን እንጂ:: ደራሲው መንገር የፈለገውን ጉዳይ እጅግ በተመጠነና ውብ በሆነ አገላለፅ ጥቁምታ ይሰጥና  አንባቢ እስከፈለገውና እስከሚችለው ድረስ እንዲለጥጠው፣ እንዲተነትነው፣ እንዲተረጉመው እድል ይከፍታል፤ ለአንባቢው የማስፋፋትና በዐቅሙ ልክ ተርጉሞ የመረዳት ሥራ በመስጠት ያነበበው በልቦናው ማሕደር ሕያው ሆኖ እንዲቀመጥለት ያግዘዋል፡፡ ይህም በብዙ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ያልተለመደ ነው፡፡ ይሄ መንገድ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጽእኖ ሥር ለወደቀው፣ ረዣዥም ጽሑፎችንና ሰፊ ገላጻዎችን ለማንበብ ጽናት እያነሰው ለሚገኝ፣ ከንባብ እየራቀ ያለን ስልቹ ትውልድ ወደ ንባብ ለመመለስ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡


Read 1312 times