Monday, 08 June 2020 00:00

ዘላለም ናፋቂው ብዕረኛ!

Written by  ሻሎም ደሳለኝ
Rate this item
(1 Vote)


             በ2012 ዓ.ም ከወጡ የግጥም መድበሎች ውስጥ “የምድር ዘላለም” የተሰኘው የዲበኩሉ ጌታ መጽሐፍ አንዱ ነው። መፅሐፉ 106 ያህል ግጥሞችን በ202 ገጾች አካትቷል:: በመድበሉ ውስጥ ከቁጥር እንደተኳረፉ የጥንት ዘመን ሰዎች እድሜያቸውን ያላሰሉ ግጥሞች እንዳሉ ሁሉ የልደት ቀናቸው የታወቀ፣ የተቆጠረ፣ የተሰፈረ  ድርሰቶችም አሉ። ተቆጠሩም አልተቆጠሩ፣ ተሰፈሩም አልተሰፈሩ እድሜያቸው የትየለሌ፣ ዘመናቸውም እስከ ዘለዓለም እንዲሆን ተብለው በደራሲው የተሸመኑ ናቸው። በጎጥ ያልታጠሩ ፤ በደም ያልሰከሩ።
“ማነህ መዝሙር ያለህ” የተሰኘው ግጥም ይሄን ሃሳቤን ያስረዳልኝ ይመስለኛል። ይሄ ግጥም ከ2005-2008 ዓ.ም ድረስ ሲገመድ ሲበጠስ ፣ ሲቀጠል ሲበጠስ ቆይቶ እንካችሁ የተባለ ነው።
ዘመን - ድንበር የማይጋርደው ምስል
በቃሎችህ የምትስል
***
በዩኒቨርስ ሰማይ
እኩል የወጣህ ፀሐይ
ካለህ…አውጣው - ቅኔህ ይታይ…
ለአንድ ሉል
                      የሰው ዘር ውል . . .
የብርቱ ገጣሚ አገሩ የት ነው? ድንበሩስ? ምናቡ አይደለምን? ነው እንጂ! ገጣሚው መላዕክ ነው። ለመድበሉ ጥሩ ስም አውጥቶለታል። አልያም ስምን መላዕክ ብቻ አያወጣም፤ ገጣሚ ጭምር እንጂ። “የምድር ዘላለም”!
“እሱ” በተሰኘው ሌላ ግጥሙ ላይ እንዲህ ይለናል…
ህግ፣ ሐሳቡን ከዘላለም አቆራኝቶት
እየተራመደው ዘመኑን መች ደርሶት።
በስንኞቹ ልሳን ገጸ ሰቡ የሚተርክልን ሐሳብ ከዘላለም አቆራኝቶት “የቆመበቱ ወይም የመሻቱ ዘመን ላይ መች ደርሶበት” እያለን ይመስላል። ነገር ግን እሱ ሰም ነው ፤ ወርቁ “ወሰኔ ይህ ዘመን አይደለም፤ ድርሰቴ ዘላለማዊነት ነው” የሚል ነው።
ኪነትን ማክበር ከከያኒው የሚጠበቅ ግዳጅ ነው። ዲበኩሉ “ኪነት ኩሩ ጣዖት” ብሎ በሰየመው ድርሰቱ በኩል…
ጡ’ፍ ኩራተኛ ጣዖት
በቀላል ‘ድባብ ዝግጅት’
አይነግስ አይከብር ታቦት
ዓመት ሙሉ ዋዜማ በዓሉ አንድ እለት… ይለናል።
ከያኒው በኪነት ፊት አደግድጎ መቆም እንደሚገባ ይነግረናል። በአገም-ጠቀም ኪነት እጅ አትሰጥምና። መልኳንም አትገልጥምና። የኪነትን ሸብ ረብ ፈላጊነት፣ ሽር ጉድ ናፋቂነት ያመላክተናል። እንዲህ ካልሆነ ግን እንደ “ማነህ መዝሙር ያለህ” ሦስት ዓመትና ከዛም በላይ ዘመናትን ኪነት ጣዖት፣ ከያኒ ባርያዋን እንደምታሽ ይጠቁማል። ገጣሚ ዲበኩሉ ጌታ “ማነሽ” በተሰኘ ግጥሙ በኩል ግጥም የምታፅፈውን መንፈስ እንዲህ ይጠይቃታል። ነገሩ የተፃፈው ለሴት ይመስላል። ላጤነው ሰው ግን ከዛም ይሻገራል።
ያልተለየኝ ሥሜት በሕዋሴ አስርጾ
ዐካል የለሽ ምስል በእዝኔ ቀርጾ
መንፈስሽ እንደ መቅደስ ማደሪያው
አድርጎኝ
በየአደባባዩ ምታስለፈልፊኝ
የስምሽን ቅኔ የምታዘርፊኝ
እያለሽ የሌለሽ
እረቀሽ የጎላሽ
ኧረ አንቺ ሰው ማነሽ
ማነሽ ኧረ ማነሽ? … እያለ ምንነቷን ይጠይቃል። መቼስ ገጣሚው በስንኞቹ በር “አንቺ ሰው” እያለ እንደምን ለመንፈስ የተገጠመ መሰለህ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የዛር አመጣጥ አፈ ታሪክን የሚያጠናው ራይደልፍ ሞላቨር  መዝግቦት የሚገኘውን ታሪክ ከዊኪፒዲያ ላይ ዘግኜ ላካፍላችሁ።
“አዳምና ሔዋን ከገነት ከተባረሩ በኋላ 30 ጥንድ ልጆች የነበሯቸው ሲሆን አንድ ቀን እግዚአብሔር ሊጠይቃቸው ሲመጣ 15ቶቹን እና ቆንጆ የሆኑትን ልጆቻቸውን በዋሻ ደብቀው፣ 15ቱን ጥንድ ብቻ ለእግዚአብሔር አሳዩ። እግዚአብሔርም በማዘን ዋሻው ውስጥ ያሉት 30ዎቹ ቆንጆ ልጆች እስከ ዘላለሙ እማይታዩ ይሁኑ ብሎ ተራገመ። እኒህ እንግዲህ የዛር መንፈስ ወይንም ዛር ሆኑ።” ይላል። በዚህ አግባብ ቆሌ ወይም ዛር ለሰው የቀረበ ጉዳይ ነውና ገጣሚው ለሰው የተፃፈ አድርጎ ቢያቀርበው የሚገርም አይሆንም። አንቺ ሰው እያሉ ዛር መጥራት ትችት ላይ የሚጥል አይሆንም። በነገራችን ላይ ገጣሚና ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬም ግጥም የምታፅፈው መንፈስ (ዛሬ/ቆሌ) እንዳለችና ስያሜዋም “አስዬ ጨብራሪት” እንደምትባል ይናገር ነበር፡፡
ደራሲው ውለታ የሚገደው፣ የአበው ነገር የሚከብደው ይመስላል፡፡ ከ”መምህሩ እስከ የቡና አጋፋሪው” ያወሳሳል። ያወድሳል። ያሞግሳል። ከገጣምያንም ዮሐንስ አድማሱን፣ ሰለሞን ዴሬሳንና ሙሉጌታ ተስፋዬን ይዘክራል።
ፊደል መግደፍ ከግጥም አፈንግጦቶች አንዱ ነው። እንደ ሰለሞን ዴሬሳ የምስክርነት ቃል ከሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ ፊደል መግደፍ የጀመረው ጋሽ ስብሃት ነው። ገጣሚ ዲበኩሉ ጌታ በበኩሉ፤ “ማለፊያ” ብሎ በሰየመው የመድበሉ መግቢያ ላይ እንደሚነግረን ከሆነ፣ ከቃል ፊት ያሉትን ብቻ ሳይሆን በቃል መሀልም ሆነ ከቃል ዳር ያሉ ፊደላትን ይገድፋል። ምክንያት የሆነውንም ጉዳይ ሲገልፅ ውበትን መፍጠር እንደሆነ ይናገራል። አለፍ ካለም የማን ይጠይቀኛል “ነፃነቱ ወይም ትዕቢቱ” የወለደው ሊሆን እንደሚችል ይናገራል።
ግጥም እንዲህ ነው እንዲያ ነው ተብሎ አይወሰንም። ሀሳቡ ነው ወይስ ኪነቱ ግጥምን ተወዳጅ የሚያደርገው የሚለው  ብዙ ገጣምያንን ጎራ ከፍለው እንዲከራከሩ አድርጓል።  “የምድር ዘላለም” ውስጥ የተካተቱ ግጥሞች ለሀሳብ ያደላሉ። ሙዚቃዊነታቸው እንደ ሰማይ ተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ ብሎ ቶሎ ይጠፋል። ይሁነኝ ተብለውም እንደተደረጉ ያስታውቃሉ። መድበሉን የሐሳብ ጥላ ወርሶታል። እኔ በግሌ ከሀሳባዊነቱ ይልቅ በሙዚቃዊነቱ እማረካለሁ። ከሚባለው ነገር ይልቅ ለተባለበት ነገር ቀልብ እሰጣለሁ። ግጥም ኪነትም አይደል? ኪነትስ ምን?
ገጣሚ ዲበኩሉ ጌታን የፒያሳና የቅዳሜ ነገር፣ እንደ ብዙ ደራሲያን የሚንጠው ጉዳይ ይመስላል። በወጣቶቿ በኩል ሕይወትን እንድናጣጥም ይጋብዘናል። በእነ ስም አይጠሬ ምግባር ደግሞ ተክዞ ያስተክዘናል። የስጋ ተጫራቾች ሲርመሰመሱ እነ ጥፋት ልምዱ ታሪክ ሲንዱ ያሳየናል።
ተረት ላይሆን ታሪክ ያባቶቹን ሀውልት
እንደሰረሰረ … እንደቦረቦረ
ቁጥቋጦ ላይቸግን ዋርካ እንዳስነቀለ
ልጅ ላይኖር የልጅ ልጅ ባ’ድ እያስደቀለ
-----አለ!!!
‘ስኳር‘ ዳዲና ማሚ
አረምን በመዝለል ሰብሉን አራሚ…
አሉ
የዘመንን ንፍር ውኃ እንዳፈሉ
በእናበላለን ፣
ወዝን እየበሉ
ወንዝን እየበከሉ አሉ…!
መናኛውን ብቻ እያወሳ፣ መአት ብቻ እየዘረዘረ አያስጨፈግገንም። ከበረከቷም ያቀምሰናል።
የሆነ ሆኖ፣
ይህ እንዳለ ሆኖ!
ጡቶች ይስቃሉ
ይፍለቀለቃሉ
በየአደባባዩ ውበት ይለቃሉ
ከደረት ላይ ነጥረው ልብን ይደቃሉ…!
ቡናውም ይጨሳል
እጣኑ ይጣራል
ፈንድሻው ይስቃል
ፍጥረት ወጣትነት
ነቅቶ ይዘምራል
ተግቶ ይወርባል። (ለዚህ ይሆን ለመኖርም ለመሞትም ፒያሳ ሂድ የሚለን ጋሼነት)።
ኤፍሬም ስዩም፣ የፒያሳን ቅዳሜ ከቦሌ ቅዳሜ አንፃር ሲገልጠው፡-
“የቦሌ ቅዳሜ ያራዳን አይመስልም የቦሌ ቆንጆ ሕልም ከፒያሳ ቅዠት አይስተካከልም“ ይላል። ዲበኩሉ (ሲያገዝፈው?) በቅዳሜና በፒያሳ ጥምረት የሚወለደውን ውበት የሚያነፃፅረው ከምድራዊቷ ቦሌና ቅዳሜ ሳይሆን ከሰማያዊቷ ፀሐይ ጋር ነው።
“ከዚህ ሁሉ ደግሞ ቅዳሜ ይልቃል
የፒያዛ ፈገግታ ከፀሐይ ይደምቃል…” እንዲል።
ዲበኩሉ ወጣት ገጣሚ ነው። ህልሙ ትልቅ ብዕሩም ጥልቅ መሆኑን መድበሉ ይጠቁማል። ነገው ብሩህ ፤ ምኞቱም ዘላለማዊ መሆን ነው። ግጥም በወጣትነት ያምራል ፤ ፍቅርም እንደዛው። አምናለሁ! ፍቅርና ወጣትነት ጥሩ ግጥም ይሰጡናል።
መልካም ቅዳሜ!


Read 618 times