Print this page
Sunday, 07 June 2020 00:00

“የእንቦጭ ማጥፊያ መድሃኒትን አግኝቻለሁ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 • በመጀመሪያ ዕጽዋቱን አሳየን በሚሉት አልተስማማሁም
   • በ30 ቀን ሙሉ ለሙሉ ጣናን ከእምቦጭ ነፃ ማድረግ ይችላል
   • ርጭት በተደረገ በ24 ሰዓት ውስጥ ቅጠሉን ማድረቅ ይጀምራል

          መሪጌታ በላይ አዳሙ ይባላሉ፡፡ የባህላዊ መድሃኒት ጥናትና ምርምር በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የእንቦጭ አረምና ሌሎች አረሞችን ማጥፋት በሚችሉ መድሃኒቶች ምርምር ላይ እየሠሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከሰሞኑም የጣናን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘውን የእንቦጭ አረም
ማጥፋት የሚችል መድሃኒት ከእጽዋት መስራታቸውንና ተሞክሮም ውጤታማነቱ መረጋገጡን ይናገራሉ፡፡ በአዲሱ የእምቦጭ ማጥፊያ ግኝት ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ መሪ ጌታ በላይ አዳሙን በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፡፡


             የእንቦጭ አረም መድሃኒት ማግኘትዎን ሰምተን ነበር…
አዎ መድሃኒቱን አግኝቻለሁ፡፡ ከእጽዋት የተዘጋጀ ኦርጋኒክ የፀረ-አረም መድሃኒት ነው፡፡ ይህ መድሃኒት በብዝሃ ህይወት ላይም ሆነ በሌሎች የውሃ ውስጥ እንስሳት ላይ ጉዳት ሳያመጣ እምቦጭን ብቻ ለይቶ መግደል የሚችል ነው፡፡  
የመድሃኒቱ ውጤታማነት በሙከራ ተረጋግጧል?
አዎ፤ የሙከራው ጉዳይ በአማራ ክልል ባህርዳር ዩኒቨርስቲ፣ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተቋቋመ ኮሚቴ፣ ሙከራ ተደርጐ ውጤታማነቱ ተመስክሮለታል:: ከኢንስቲትዩቱም የእውቅና ደብዳቤ ተጽፎልኛል፡፡ ሌላው በውሃ ላይ እና በውሃ ውስጥ ያሉ ተህዋስያንን በተመለከተ፣ የሚያስከትለውን የጐንዮሽ ጉዳት አስመልክቶ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ባደረገው ሙከራ፤ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያመጣ አረጋግጦ የዕውቅና ደብዳቤ ሰጥቶኛል፡፡  
ታዲያ ወደ ተግባር ያልተገባው ለምንድን ነው?
ወደ ስራ ለመግባት ያልተቻለበት ምክንያት አለ፡፡ ይሄን የምርምር ውጤት ከሠራሁ በኋላ ለአማራ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ መስሪያ ቤት፣ መድሃኒቱ ታይቶ ወደ ተግባር እንዲገባ በደብዳቤ ጠይቄ ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ በመጀመሪያ መድሃኒቱ የተቀመመበትን እጽዋት አሳየን የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡልኝ፡፡ ይሄ ደግሞ የሚሆን አይደለም፡፡ የባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ሳላገኝ ዕጽዋቱን መንገር ለኔ ማስተማመኛ ስለማይሰጠኝ ያንን ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ሌላው ደግሞ የጣና እና አጠቃላይ የውሃ አካላት ኤጀንሲ የሚባል በቅርቡ የተቋቋመ ተቋም አለ፡፡ ከእነሱ ጋር ለመስራት ተነጋግረን ነበር፤ ነገር ግን እነሱም በተመሳሳይ መጀመሪያ እጽዋቱን አሳየን የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡት፡፡ ይሄ ደግሞ እንዳልኩት ገና ፓተንት ያላገኘ ጉዳይ ነውና የሚሆን አይደለም፡፡ ፓተንቱ እስኪገኝ እንኳ መድሃኒቱ የሚገኝበትን እጽዋት ለማሳየት በመጀመሪያ የውል ስምምነት ሊኖረን ይገባል:: ያንን ሳያደርጉ ነው መድሃኒቱ የተገኘበትን ዕጽዋት አሳየኝ  የሚሉኝ:: ይሄ ደግሞ ተገቢ አካሄድም አይደለም:: የፓተንት መብት የማገኘው መድሃኒቱ በተግባር ከተፈተሸ በኋላ በመሆኑ ነገሩን አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡
በመቀጠል ምን ለማድረግ ነው ያሰቡት?
በቀጣይ በተለይ መድሃኒቱ እንቦጭን አያጠፋም ብሎ የሚጠራጠር ካለ፣ በተለይ መንግስት ግብረ ሃይል አቋቁሞ ለሁለተኛ ጊዜ ሙከራውን ማሳየት እችላለሁ፡፡ እንተማመንበታለን ከተባለ ደግሞ በፍጥነት ወደ ስራ ገብተን የውሃ አካላችንን ማዳን ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ መንግስት ጉዳዩን  በዚህ መልኩ ተረድቶ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥበት እጠይቃለሁ፡፡  
መድሃኒቱ እንዴት ነው እምቦጭን የሚያጠፋው?
እንቦጭ የሚኝበት ቦታ ላይ ርጭት ይደረጋል፡፡ ርጭቱ በተደረገ በ24 ሰዓት ውስጥ ቅጠሉን ማድረቅ ይጀምራል፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ ግንዱ ብሎም ወደ ስሩ ወርዶ፣ ከእነ ስሩ አድርቆ ያጠፋዋል:: ይሄ ሂደት ግፋ ቢል 15 ቀናት ቢፈጅ ነው:: እስከ 30 ቀን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ጣናን ከእምቦጭ ነፃ ማድረግ ይቻላል:: መድሃኒቱን እንዳጋጣሚ ሆኖ አሳዎች ለምግብነት ይፈልጉታል፡፡ አሣዎች ያንን መድሃኒት ለማግኘት ሲሉ የእንቦጭን ስር ይመገቡታል:: ስለዚህ እነሱም እንቦጭን የማጥፋት ስራ በትብብር ይሠራሉ ማለት ነው:: በዚያው ልክ የአሣ ብዝሃ ሃብቱንም በፍጥነት ማባዛት ይቻላል ማለት ነው፡፡ መድሃኒቱ አሣዎች ኖሩም አልኖሩም ግን አረሙን ከእነ ስሩ አድርቆ ሙሉ ለሙሉ ያጠፋዋል፡፡
መድሃኒቱን በብዛት ማምረት ቢፈለግ በቂ እጽዋት አለ ብለው ያምናሉ?
አዎ፤እጽዋቱ በኢትዮጵያ አለ፡፡ በብዛት ማራባትም ይቻላል፡፡ በእጽዋቱ የተጋጋጡ ተራራዎችን ማልበስ እንችላለን፡፡ ቅጠሉንም እየሸመጠጥን መሠል አረሞችን ማጥፋት እንችላለን፡፡ የኛን ችግር ከቀረፍን በኋላም መሠል ችግር ላለባቸው ሀገራት መድሃኒቱን መላክ እንችላለን፡፡ ሃብቱ በእጃችን ነው ያለው፤ ያውም በበቂ መጠን::  የስራ እድልንም ይፈጥራል፤ አካባቢንም እንጠብቅበታለን:: በሰፊው እርስ በእርስ ተመጋግቦ የሚሄድ መድሃኒት ነው፡፡  






Read 1377 times