Monday, 08 June 2020 00:00

ኢሰመጉ፤ በሰብአዊ መብት አያያዝና በአምነስቲ ሪፖርት ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  - የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚፈጸሙት በመንግሥት ሃይል ብቻ አይደለም
     - የሲቪክ ማህበራት ለሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው

              ከሰሞኑ አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም አምኒስቲ ኢንተርናሽናል፣ ባለፈው 1 ዓመት በአማራና በኦሮሞ ክልሎች በመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች ተፈጽሟል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ያጠናቀረውን ሪፖርት የክልሎቹ መንግስታት ውድቅ አድርገውታል፡፡ ከወትሮው በተለየ ከመንግስት ውጭም አንዳንድ ወገኖች ሪፖርቱን ሚዛናዊነት ይጎድለዋል ሲሉ ተችተውታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔስ ምን ይላል? የጉባኤው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ በአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝና በአምነስቲ ሪፖርት ዙሪያ ለአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ሃሳባቸውን አጋርተውታል፡፡ እነሆ፡-

               በቅርቡ መንግሥትንም ታጣቂ ሀይሎችንም እኩል ተጠያቂ የሚያደርግ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት አውጥታችሁ ነበር፡፡ ይህን ሪፖርት ለማዘጋጀት መነሻ የሆናችሁ ምንድን ነው?
ሪፖርት ሳይሆን አጭር መግለጫ ነው ያወጣነው፡፡ መግለጫው ተፈፅመዋል ተብለው የሚታሰቡ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያካትት ሳይሆን በአጠቃላይ ሁኔታዎች ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይና የመፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ ነው:: በዚህም መግለጫ ይሁን በሌሎች ሪፖርቶቻችን ላይ መነሻ የምናደርገው በዋናነት በየአካባቢው የሚገኙ አባላቶቻችንና  ጽ/ቤቶቻችንን ነው፡፡ ከእነዚህ የመነሻ መረጃዎችን እንቀበላለን፡፡ እነዚያንም ይዘን በተለይ ድርጊቱ የተፈፀመባቸውን ሰዎች ለማግኘትና ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን፡፡ ጎን ለጎንም ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላትን ለማግኘት እንጥራለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ገለልተኛና በስራ ሃላፊነታቸው ተጨማሪ መረጃ ይኖራቸዋል ብለን የምናስባቸውን ለማግኘት እንሞክራለን፡፡ በአጠቃላይ እነዚህን ሂደቶች ተከትለን ነው ምርመራ የምናደርገው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያለ ችግር መመርመር ይቻላል ይላሉ?
ሁኔታው አስቸጋሪ ነው፡፡ በቀደሙት አመታት አስቸጋሪው ነገር በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው አካል ነው፡፡ በዚያው ልክ የጥቃቱ ሰለባ ደግሞ ነፃው ሕዝብ (ሲቪል ማህበረሰብ) ነበር፡፡ ያኔ ሕዝቡ ጋ ደርሶ መረጃዎችን ማግኘት ቀለል ይል ነበር፡፡ አሁን ግን በአመዛኙ የብሄር ማንነትን ማዕከል ያደረጉ ጥቃቶች ናቸው የሚስተዋሉት:: በዚህ ምክንያት ደፍሮ መረጃዎችን ለተቋማችን ለመስጠት በሕብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ለመስራት አስቸጋሪ የሚያደርጉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ በሁለት ጎራዎች ተከፍሎ ነው ጥቃት እየተፈፀመበት ያለው፡፡ በአንድ ወገን መንግሥትን ትደግፋለህ በሚል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ታጣቂውን ትደግፋለህ በሚል በሁለት ጎራ ነው ጥቃት የሚፈፀምበት:: ይህ ሁኔታ መረጃዎችን ለማግኘት እጅግ ከባድ ያደርገዋል፡፡ በፊት ማህበረሰቡ ጥቃት የሚደርስበት ከመንግሥት ወገን ብቻ ስለነበር፤ መረጃዎች ለማግኘት ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም፡፡
መንግሥት በሰብዓዊ መብት አያያዝ በኩል ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እናንተ እንደ ሰብአዊ መብት ተቋም ምን ትላላችሁ?  
በእርግጥ ከመንግሥት በኩል የሚወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች አሉ፡፡ ከቀደሙት አመታት የተሻሉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይሄ ማለት ግን ሁሉም የተሟላ ነው ማለት አይደለም:: ጊዜ የሚፈልግ ነገር አለ፡፡ የሰብዓዊ መብት ይዘትን ማሻሻል ጊዜ የሚፈልግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የፀጥታ ሀይሉ እንቅስቃሴዎች ባለፉት አመታት ከነበረው  አሁን የተሻለ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡
በመግለጫችሁ ላይ ምን ያህል ሰው ጉዳት እንደ ደረሰበት በአሃዝ የተጠናቀናረ መረጃ አላቀረባችሁም፡፡ ለምንድን  ነው?
አስቸጋሪ የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛ የሰው ሀይልም ያስፈልጋል:: እንደ ልብ የሰው ሀይልም ማንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ ይሄን ለማድረግ አሁን የኮሮና ሁኔታም አለ፡፡ ሁለተኛ፤ መረጃዎችንም ለማግኘትም ገለልተኛ አካል ያስፈልጋል:: በተለይ የብሄርን፣ የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን በተመለከተ ገለልተኛ አካል ማግኘት ያስቸግራል:: ስለዚህ አሁን ማድረግ የምንችለው ነገሩን በመረጃ ማጣራት ነው፡፡ ነገሩ የብሄርና የፖለቲካ ጉዳይ ሲሆን ደጋግሞ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን መመርመር ያስፈልጋል:: መረጃዎችን ብናገኝም የመረጃዎችን እውነተኛነት በቅጡ ማረጋገጥ ያስፈልጋል:: ያንን ለማድረግ ደግሞ አሁን ያሉት ሁኔታዎች አይፈቅዱም፡፡  
በአሁኑ ወቅት ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የበለጠ በምክንያትነት የሚጠቀሰው ምንድን ነው?
ቀደም ሲል በምናወጣቸው መግለጫዎች ላይ መንግሥትን ነበር የምንወቅሰው፡፡ መንግሥትን ይበልጥ ስንወቅስ የነበረውም ድርጊቱን ራሱ ፈፅሞታል ብለን ሳይሆን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከሕግ ውጪ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የሚፈጽሟቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማስቆም አልቻለም በሚል ነው፡፡ አሁንም በመግለጫችን ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀናል:: በተለይ ትጥቅ ያልፈቱ አካላት በሕዝቡ መሀል መንቀሳቀሳቸው ተገቢ አልነበረም:: ትጥቅ ፈተው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማስቻል ይገባ ነበር፡፡ ይሄን መንግሥት ማድረግ አልቻለም ወይም ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት እነዚህ ነገሮች በሙሉ መስመር ውስጥ ገብተው፣ የንፁሃን ዜጎች መብት መከበሩ መረጋገጥ ነበረበት፡፡ ጥፋቱ ግን በሁለቱም ወገን ነው ያለው፡፡ በመንግሥትም ከመጠን ያለፈ ሀይል የመጠቀም አዝማሚያ ይታያል፤ ከታጣቂዎቹ ወገንም ንጹሃንን ለሞት የሚዳርጉ ጥቃቶች እየተፈፀሙ ነው፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው ትላላችሁ?
መፍትሄ ሊሆን የሚገባው በአንድ አገር ውስጥ ብቸኛ ሀይልን መጠቀም የሚችለው መንግሥት ነው፡፡ ከመንግሥት ውጪ ያሉ የታጠቁ አካላት በሙሉ ትጥቃቸውን የሚፈቱበትና ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመለሱበት ሁኔታ ሰብዓዊ ቀውስ በማያስከትል መልኩ ሊፈለግ ይገባዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑ ያወጣውን ባለ 72 ገጽ ሪፖርት እንዴት ይመለከቱታል?
በእርግጥ አሁንም ካሉብን ውስንነቶችና የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር አምነስቲ ወይም ኢሰመጉ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተጨማሪ በርካታ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ:: የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሲኖሩ ጥሰቶችን ተከታትሎ እርምት እንዲወሰዱ ለማድረግ ያስችላል፡፡ አምነስቲ ያወጣውን መግለጫ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ እርግጥ የትኞቹም መግለጫዎች ቢሆኑ ሙሉ ለሙሉ አካታች ይሆናሉ ተብለው አይጠበቁም፡፡ ምክንያቱም መሬት ላይ ሲወረድ የተለያዩ ውስንነቶች ይገጥማሉ፡፡ ምናልባት የገንዘብ አቅም፣ የጂኦግራፊ፣ የጊዜ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የአምነስቲ ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ የተሟላ ነው፤ እንከን የለሽ ነው ማለት አይቻልም፡፡  ሪፖርቱ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ግን ቢያንስ አሁን በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎችን ለማመላከት የሚረዳ ነው፡፡
በሪፖርቱ ከእርስዎ ተቋም ምልከታ ጋር የሚጣጣሙ ጉዳዮች ተካተውበታል ይላሉ?
እኛ አጠቃላይ ምርመራ ያደረግንበትን መግለጫ በቅርቡ እናወጣለን፡፡ በዚያ መግለጫ ላይ ማየቱ የተሻለ ይሆናል፡፡ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ግን በየአካባቢው ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች ብቻ የሚፈፀሙ አይደሉም:: በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎችና ቡድኖች የሚፈጽሟቸው ኢ- ሰብዓዊ ጥቃቶችም በዚያው ልክ አሉ፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ትኩረት ማድረግ ያለባቸው በመንግሥት የሚፈጸሙት ጥቃቶች ላይ ነው፤ ታጣቂዎችን መቆጣጠር የመንግሥት ድርሻ ነው የሚል መከራከሪያ አምነስቲ ያቀርባል:: ይህ መከራከሪያ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል?
በመርህ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅና የማስጠበቅ ሃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ በእርግጥም መንግሥት ጥቃቶችን ያለመፈፀም ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካላት አለመፈፀሙን የማረጋገጥና የዜጎችን መብትና ሕይወትን የመጠበቅ ድርብ ሃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ መንግሥት ላይ የሚጣል ሃላፊነት ነው ማለት አይደለም፡፡ በተለያዩ ደረጃ ያሉ የማህበረሰብ አደረጃጀቶችና ቡድኖች ለሰብዓዊ መብት መከበር የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ምንም እንኳ የጎላ ሃላፊነትና ግዴታ በመንግሥት ላይ የሚጣል ቢሆንም፣ በሌሎች አካላት የሚፈፀም ጥቃትም አካላቱን በተናጠል ተጠያቂ ያደርጋል፡፡
መንግሥት ከተለያዩ ተቋማት የሚወጡ የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከቱ ሪፖርቶች የሚያስተናግድበትን ቅኝት እንዴት ያዩታል?
በዋናነት በመንግሥት በኩል በተለይ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኩል የሚሰጡ አስተያየቶችን በቀናነት መመልከቱ ነው የሚጠቅመው፡፡ ላወቀበት መርዝ መድሃኒት ነው ይባላልና እነዚህን ሪፖርቶች ለመቃወም ከመጣደፍ ይልቅ ተቀብሎ ህፀፆችን በማረም ላይ ጊዜ ቢወስድ የተሻለ ይሆናል፡፡ “የሚወጡ ሪፖርቶች የመንግሥትን አካሄድ ጥላሸት ለመቀባት ነው“ ብሎ ደምድሞ መቀመጡ የትም አያደርሰንም፡፡ ቀደም ሲልም በመንግሥት በኩል የሰፋ ልምድና እውቀት ያላቸውን ግለሰብ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር አድርጎ በመሾም የሄደበት ርቀት የሚደነቅ ነው:: ግን በኮሚሽነሩ ብቻ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ ኮሚሽኑም በራሱ በነፃነት እንዲሰራ ማድረግ ያስፈልጋል:: ከዚህ አንፃር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ በአንዳንድ የመንግሥት አካላት የተያዘው አቋም ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ መድረስ የምንፈልግበት ቦታ ላይ ለመድረስ ይሄኛው መንገድ አያዋጣም፡፡ ኮሚሽኑ ካሉበት እጥረቶች አንጻር ሳይገደብ በጣም ጥሩ ነገሮች እየሰራ ነው፡፡ ሌሎች የሲቪክ ማህበራትም ለኮሚሽኑ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ መንግሥትም የገባውን ቃል ማክበር አለበት፡፡
በአገሪቱ ያሉ የኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ምን እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል ይላሉ?
መጠነ ሰፊ ነው ጉዳዩ፡፡ ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በኩል የዛሬ ሁለት አመት በታየው ቁርጠኝነት ልክ እየሄደ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አሁን ወደ ቀድሞ ሁኔታ የመመለስ አዝማሚያ ይስተዋላል:: ለመሻሻል ቃል በተገባው ልክ ወደፊት መቀጠል እንጂ ወደ ኋላ መመለሱ ጥሩ አይደለም፡፡
ሁላችንም ብንሆን ስለ ሰብዓዊ መብት ራሳችንን ማስተማር ይገባናል፡፡ የእነ አምነስቲንም  ሆነ የኮሚሽኑን ሪፖርት ከማጣጣል ይልቅ ተቀብሎ እርምት ማድረግ ላይ ማተኮሩ የበለጠ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ይዘትን ለመገንባት ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ህብረተሰብ ተደማጭነት ያላቸው አካላት፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም አሁን ከኮሮና በተጨማሪ ምርጫም እየመጣ ነው:: ምርጫ በተፈጥሮው ይዞት የሚያመጣው ውጥረትም አለ፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች ወደ መስመር ባልገቡበት ሁኔታ ምርጫ ውስጥ ስንገባ የሚያመጣው ችግር ይኖራል፡፡ ከዚህ አንጻር ተቀራርቦ በሰላማዊ መንገድ መወያየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ግምገማችሁ ምን ይመስላል?
ይሄን በሚመለከት በተለይ በማረሚያ ቤቶች ላይ ያሉትን አያያዞች በሚመለከት መግለጫ አውጥተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለይቶ ማቆያ ያሉ ሰዎችን የጤና አጠባበቅም አስመልክቶ መግለጫ አውጥተን ነበር:: አሁን ደግሞ አዋጁ ከወጣ በኋላ ባሉ የሰብዓዊ መብት ይዞታዎች ላይ ያተኮረ መግለጫ እያዘጋጀን ነው፡፡ እንደተጠናቀቀ ይፋ እናደርጋለን፡፡  


Read 2639 times