Saturday, 13 June 2020 11:02

ኮሮና አሁንም በአለማቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)


           ባለፈው እሁድ ትልቁ ቁጥር ተሰማ…
አለማችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ የማይታወቀውን ከፍተኛ ዕለታዊ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር አስመዘገበች - 136,000 ሰዎች በአለማችን የተለያዩ አገራት በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ፡፡
በነጋታው ሰኞ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ካለፉት 10 ቀናት በ9ኙ በየዕለቱ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ጠቁመው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትና ሞት ምንም እንኳን በአውሮፓ አገራት የተወሰነ መቀነስ ቢያሳይም፣ በአለማቀፍ ደረጃ ግን ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ እንደሚገኝ አስጠንቅቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉትም፣ ነጋ ጠባ መስፋፋቱን የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ወደ 7.6 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ማጥቃቱን፣ የሟቾች ቁጥር ከ420 ሺህ ማለፉንና ያገገሙት ደግሞ 3.8 ሚሊዮን እንደደረሱ የወርልዶ ሜትር ድረገጽ መረጃ ያረጋግጣል፡፡
ኮሮና በመላው አለም እንደ አሜሪካ ክፉኛ ያጠቃው አገር የለም፡፡ በአገሪቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ 2,069,973 የደረሰ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥርም ከ115,243 ማለፉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከአለማችን አገራት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በመመርመር ላይ በምትገኘው አሜሪካ፤ በየዕለቱ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ናሙናዎችን እንደምታደርግና በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች  ቁጥር ከፍ ማለቱም ከዚህ የምርመራ አቅም ከፍ ማለት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በተያያዘ ዜና ደግሞ በአሜሪካ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ፣ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን በመቃወም ከሰሞኑ ከተደረጉ ሰልፎች ጋር በተያያዘ በርካታ ወታደሮች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው ተነግሯል፡፡
ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ሃይል የተቀላቀለበትና ያፈነገጠ ድርጊት መፈጸማቸውን ተከትሎ፣ ሁኔታውን ለማረጋጋትና በቁጥጥር ስር ለማዋል በስፍራው ከተላኩት ከ1 ሺህ በላይ ወታደሮች መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ መያዛቸውን እንጂ ማንነታቸውን ወይም ትክክለኛ ቁጥራቸውን መንግስት ይፋ አለማድረጉ ተነግሯል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ 775,581 ሰዎች የተጠቁባት ብራዚል፤ በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከአሜሪካ በመቀጠል ከአለማችን አገራት የሁለተኛነት ደረጃን የያዘች ሲሆን፣ ሩስያ በ502,436 ተጠቂዎች ትከተላለች፡፡ ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱባት እንግሊዝ እና ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የሞቱባት ብራዚል፣ ከአሜሪካ በመቀጠል በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሞቱባቸው ሁለቱ የአለማችን አገራት መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የአለም ሰላም በ“ዘመነ - ኮሮና”
ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባለፈው ረቡዕ የአመቱን የአለማችን የሰላም ሁኔታ አመላካች ሪፖርት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በአለማችን ፖለቲካ መረጋጋት፣ አለማቀፍ ግንኙነትና የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ጥቁር ጥላውን በማሳረፍ፣ ግጭቶችና ብጥብጦች እንዲባባሱ እያደረገ ነው ብሏል:: ወረርሽኙ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫና በተለይም በእርዳታ የሚኖሩና ከፍተኛ የብድር ዕዳ ያለባቸው አገራትን ሰላም በማናጋት ረገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሊቀዛቀዙ እንደሚችሉና በዚህም በተለያዩ አገራት ግጭቶች ሊባባሱ እንደሚችሉ ገልጧል፡፡
መንግስታት ወረርሽኙን ለመግታት ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ መከልከላቸው ወይም የእንቅስቃሴ ገደቦችን መጣላቸው ለሰላም መደፍረስ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ያስገነዘበው ሪፖርቱ፣ መንግስታት ለቫይረሱ በሚሰጡት ምላሽ አለመርካት ወይም አለመደሰትም አሜሪካ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ውስጥ እንደታየው ሁሉ የሌሎች አገራት ዜጎችንም ለተቃውሞ፣ ለብጥብጥ፣ አመጽና ሰላምን ማደፍረስ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል አስምሮበታል፡፡
ቫይረሱ አለማችን ለረጅም አመታት ገንብታው የቆየችውን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት በማፈራረስ፣ ሰብዓዊ ቀውሶችን በማባባስ፣ አለመረጋጋትና ግጭቶችን በማበረታታትና በመቀስቀስ፣ የአገራትን ሰላም የማደፍረስ አቅሙ እጅግ ሃያል መሆኑንም የተቋሙ ሪፖርት ያመለክታል:: የአለማችን አገራት የሰላም ሁኔታ እንደ ባለፉት 12 አመታት ዘንድሮም ለ9ኛ ጊዜ ማሽቆልቆል እንደታየበት የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ በ2020 የፈረንጆች አመት የ81 አገራት ሰላም ሲሻሻል፣ የ80 አገራት ሰላም ደግሞ ወደ ከፋ ደረጃ መውረዱን  አመልክቷል፡፡
ላለፉት 11 አመታት የአለማችን እጅግ ሰላማዊት አገር ሆና የዘለቀችው አይስላንድ፣ ዘንድሮም በአንደኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ኒውዚላንድ፣ ኦስትሪያ፣ ፖርቹጋልና ዴንማርክ ይከተሏታል፡፡ አፍጋኒስታን እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ሰላም የራቃት የአለማችን ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ሶርያ፣ ኢራቅና ደቡብ ሱዳን ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡


Read 4026 times