Saturday, 13 June 2020 11:15

“የደቡብ የሰላም አምባሳደሮች ኮሚቴ ጥናት የወላይታን ሕዝብ አቋም አያንፀባርቅም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  ወላይታ ራሱን ችሎ ክልል የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው - (የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ፤)
                         
              የደቡብ ክልልን የአዳዲስ ክልል አደረጃጀት አስመልክቶ የደቡብ የሰላም አምባሳደሮች ቡድን ለፌዴሬሽን ምክር ያቀረበው ጥናት፤ የወላይታን ሕዝብ አቋም እንደማያንፀባርቅ የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ወብን) አስታወቀ። የወላይታ ሕዝብ ራሱን ችሎ ክልል የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለውም የወብን የጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ጳውሎስ ቦጋለ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
የሰላም አባሳደሮች ኮሚቴው በክልሉ የተለያዩ ዞኖች እየተዘዋወረ ህብረተሰቡን ሲያወያይ በውይይቱ ላይ እንደ ፓርቲ ወብንም እንደተሳተፈ የሚገልፁት አቶ ጳውሎስ፤ በወቅቱ የወላይታ ሕዝብ ራሱን ችሎ ክልል መሆን እንደሚፈልግ ፓርቲው በገለፁበት ወቅት የሰላም አምባሳደሮች ኮሚቴ የወላይታ ዞን ጉዳይ በሂደት እንደሚታይና እልባት እንዳላገኘ ነበር ሀሳብ የተቀበሉት ይላሉ አቶ ጳውሎስ። ይሁን እንጂ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የቀረበው ጥናት የወላይታ ዞን በሰሜን ኦሞ (አሞቲክ) በሚባለው ውስጥ ለመካተት እንደተስማማ የሚገልፅ በመሆኑ አንቀበለውም ብለዋል። ይህንን ሀሳባቸውንም ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሰላም አምባሳደሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ፤ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን  ወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ወብን)፣ የሲዳማ አርነት ፓርቲ (ሲአን) እና የጋሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ጋዴፓ) አመራሮችን በጉዳዩ ዙሪያ ባወያዩበት ወቅት ገልፀንላቸዋል ብለዋል - አቶ ጳውሎስ።
የወላይታ ሕዝብ ራሱን ችሎ ክልል የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት ስላለው ጥያቄውም ሊመለስ የሚገባውም በሕገ መንግሥታዊ መንገድ ነው የሚሉት የጽ/ቤት ሃላፊው፣ “ይሁን እንጂ ወላይታ ክልል ሲሆን የስራ ቋንቋው ወላይትኛ፣ የክልሉ መቀመጫ ሶዶ ከተማ፣ የራሱ አርማና የክልል ሕገ መንግሥት እንዲኖረን እንፈልጋለን፤ እነዚህን ሁሉ ተቀብሎ ከወላይታ ክልል ጋር እሆናለሁ የሚል ዞን፣ ልዩ ዞንም ሆነ ልዩ  ወረዳ ካለ ተቀብለን ለማስተናገድና አብረን ለመኖር ዝግጁ ነን” ከዚህ ውጪ መንግሥት በቀጣይ ወላይታን በተመለከተ እንደ አማራጭ የሚያቀርባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ካሉም ለወላይታ ሕዝብ ቀርቦ፣ ሕዝቡ ተወያይቶና ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ የሚወሰን ይሆናል ብለዋል - አቶ ጳውሎስ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ከመካሄዱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደቡብ ክልል የዞን አመራሮች ጋር ከተወያዩ በኋላ የወላይታ ዞን አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የወላይታ ሕዝብ ከዚህ ቀደም ያጣቸውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና የነፃነት መብቶች ለማግኘት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ሲያቀርብ መቆየቱን ይገልጻል። ይሁን እንጂ የደቡብ ክልልን አደረጃጀት ለመወሰን ከዚህ ቀደም የተሰራው የ1 ለ 55 አደረጃጀት የሕዝብን መብት የሚጋፋና የሕዝብን ባህልና ታሪክ ግምት ውስጥ ያስገባ አለመሆኑን ገልፆ፤ የወላይታ ሕዝብ በመሟገቱ ውድቅ መደረጉን የዞን አስተዳደሩ መግለጫ አስታውሷል።  
የፌደራል መንግሥት ጉዳዩን በሌላ መንገድ ለመፍታት በሚል የደቡብ የሰላም አምባሳደሮች ኮሚቴን አቋቁሞ እንደነበር፣ ኮሚቴው ሕዝቡን ባወያየበት ወቅት የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በቦታው መገኘታቸውንና የሕዝቡን ፍላጎት መግለፃቸውን፣ ቀደም ብሎ ዞኑ ለደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄ አቀርቦ ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩን በቅሬታ መልክ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን ያተተው የዞን አስተዳደሩ መግለጫ፤ ይሁን እንጂ የሰላም የአምባሳደሮቹ ኮሚቴ ሕዝቡን ሲያወያይ የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች ለኮሚቴው የገለፁት ፍላጎትም ሰኔ 2 ቀን 2012 ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ለተገኙ የክልሉ የተለያዩ ተወካዮችና የፌደሬሽን ም/ቤት አባላት ያቀረበው የመጨረሻ ምክረ ሀሳብ መርህን የሚጋፋና የሕዝቡን ባህልና ታሪክ ግምት ውስጥ ያስገባ አለመሆኑን ገልፆ እንደማይቀበለው ገልጿል።
የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በውይይቱ ላይ በተሰጣቸው እድልም የሕዝባቸውን ውክልና በሚገባ በማስረዳት፣ የወላይታን ሕዝብ ፍላጎትና አቋም ያብራሩ ሲሆን የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በመሆኑ ሊመለስለት የሚገባውም በሕገ መንግሥታዊ መንገድ እንደሆነ ያተተው የዞኑ መግለጫ ይህን አልፎ በወላይታ ላይ የሚደረግን ክብረ ነክ ዘለፋና እንቅስቃሴ ዞኑ እንደማይታገስ በማስጠንቀቅ መግለጫውን ቋጭቷል።
በወላይታ ዞን ጥያቄ ዙሪያ ለደቡብ የሰላም አምባሳደሮች ኮሚቴ ቅርበት ላላቸው የኮሚቴው አባል ደውለን ስለጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቅናቸው ሲሆን እኒሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኮሚቴው የበላይ አካል የሆኑት ሰው ጉዳዩን ጨርሰን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበን አጀንዳችንን ዘግተናል ከአሁን በኋላ በጉዳዩ ላይ አስተያየትም ሆነ ምላሽ የሚሰጠው ምክር ቤቱ ብቻ ነው በማለት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።   

Read 11181 times