Saturday, 13 June 2020 11:25

ፈተናዎችን የስኬት መንደርደርያ ያደረገው አየር መንገድ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 - በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ከደረሰበት ኪሳራ በራሱ እያገገመ ነው ተብሏል
          - ግዙፍ አየር መንገዶች ከ12ሺ -22ሺ ሠራተኞችን እየቀነሱ ነው
                      
            በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በስኬታማነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከሰሞኑ ባልተለመደ መንገድ ለጋዜጠኞች፣ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ለታዋቂ ግለሰቦች የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማ፣ አየር መንገዱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች እየቀረበበት ያለውን ቅሬታ ለማጥራትና አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች ማሳየት ነበር።
አየር መንገዱ በቅርቡ ካስመረቀውና በአመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ካለው አዲሱ ተርሚናል የጀመረው ጉብኝት፣ የአየር መንገዱን የስልጠና ማዕከል፣ የካርጎ አገልግሎትና በቅርቡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የመንገደኞች አውሮፕላንን ወደ ካርጎነት የለወጠባቸውን አሰራሮች ያስቃኘ ሲሆን በአየር መንገዱ በኩል የሚገቡ በተለያየ ወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን ለማቆያነት የሚገለገልበትን ሥፍራም ያካተተ ነበር።
በቀን 40ሺ ሰዎችን ያስተናግድ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ የአቅሙን 10 በመቶ ብቻ እየሰራ፣ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ ቢደርስበትም በፍጥነት የመንገደኛ አውሮፕላኖችን ወንበሮች በመፍታትና፣ ወደ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላንነት በመቀየር፣ በመላው ዓለም የዕቃ ማጓጓዝ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። የአለም ምግብ ድርጅትና የአለም ጤና ድርጅት፣ ከኮቪድ 19 ጋር የተያያዙ መድሃኒቶችንና ልዩ ልዩ የሕክምና ግብአቶችን እንዲሁም የነፍስ አድን ምግቦችን በአፍሪካ ውስጥ ለሚገኙ አገራት ለማዳረስ እንዲያስችለው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተመራጭ የማከፋፈያ ማዕከል አድርጎት እየሰራ ይገኛል። አየር መንገዱ ለእነዚህ የምግብና የመድሃኒት ዕቃዎች ማስቀመጫ የሰራቸው መጋዘኖች፣ እንደየ ዕቃዎቹ ባህርይ የአየር ሁኔታቸውን የሚቆጣጠር ቴክኖሎጂ የተገጠመለትና በብቁ ባለሙያዎች የተደራጀ መሆኑ ደግሞ ድርጅቶቹ አየር መንገዱ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላም ቢሆን፣ አሁን እያከናወነ ያለውን የጭነት አገልግሎት ተግባር እንዲቀጥል ምርጫቸው እንዲሆን አድርጐታል።
አየር መንገዱ በኮቬድ 19 ወረርሽኝ የገጠመውን ፈተና ወደ ስኬት በመቀየር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር ከሚቆጠር ኪሳራ አውጥቶ፣ ከመንግሥት አንዳችም የበጀት ድጎማ ሳይጠይቅ፣ አሁን ከሚገኝበት የስኬት ደረጃ ላይ መድረሱ እጅግ አስደማሚ መሆኑ ተነግሮአል።
የአየር መንገዱ የበረራ ማሰልጠኛ ሲሙሌተር ማዕከል በጉብኝቱ ውስጥ ከተካተቱት የአየር መንገዱ ክፍሎች አንዱ ነበር። ይህ የስልጠና ማዕከል ለአገር ውስጥ የበረራ ሰልጣኞች ትምህርት  የሚሰጥበት ሲሆን ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ለሚመጡና በሰዓት 1ሺ ዶላር የመክፈል አቅም ላላቸው ሰልጣኞችም አገልግሎቱን ይሰጣል።
በማዕከሉ የሚሰጠው ስልጠና በኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ሳቢያም አልተቋረጠም። ይህም ለአየር መንገዱ ከፍተኛ ገቢ ከሚያስገኙ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል። አንድ አብራሪ ከቃል ትምህርቱ በተጨማሪ ለ40 ሰዓታት ያህል በሲሙሌተር ላይ ስልጠና ከወሰደ ያለ ምንም ችግር አውሮፕላን ማብረር የሚችል ቢሆንም፣ የአየር መንገዱ ሰልጣኞቹ የንድፈ ሀሳብና የሲሙሌተር ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ፣ የአየር ላይ የብቃት ማረጋገጫዎችንም ሰጥቶ፣ አብራሪው ለበረራ ብቁ መሆኑን አረጋግጦ ነው ለሥራ የሚያበቃው።
ሌላው የአየር መንገዱ የገቢ ምንጭ ደግሞ የአውሮፕላኖች ጥገና ነው።  አየር መንገዱ ከራሱ አውሮፕላኖች ውጪ ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች የሚመጡለትን አውሮፕላኖች በመጠገን ከፍተኛ ገቢ ያገኛል። አየር መንገዱ ከአፍሪካ ከስድስት በላይ ደንበኞች አሉት። ይህ የጥገና ማዕከል በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ሥራውን ከማቆም ይልቅ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ወደ እቃ ጫኚነት በመለወጥ ሥራ ላይ ተወጥሮ ይገኛል።
የአየር መንገዱ የተለያዩ ክፍሎች በስፋት በተቃኙበት የጉብኝት ፕሮግራም ላይ የአየር መንገዱ የሥራ ኃላፊዎች እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ከሚያጋጥሙት ሕገወጥ ተግባራት፣ የአደንዛዥ እፅ ዝውውሮችና ተፈላጊ ወንጀለኞችን ለጊዜው የሚያቆይበት ነው የተባለውን ይህንኑ ስፍራ ለእንግዶች አስጎብኝቷል።
የድርጅቱ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ወልደ ማርያም፤ አየር መንገዱ በተለያዩ ጊዜያት እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ጉዳዮች ቢያጋጥሙትም፣ ሁሉንም በከፍተኛ ትግልና ጥረት እያሸነፈ እዚህ መድረሱን ጠቁመው፣ አገሪቱ ካላት አጠቃላይ ወጪ ምርቶች ከምታገኘው ገቢ የበለጠ ከአየር መንገዱ እያገኘች እንደሆነ ተናግረዋል። ይህንን የአገር ኩራትና ለአገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነ ስኬታማ ተቋም፣ በተለያየ መንገድ እየኮረኮሙ ለማዳከም የሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች፤ የአየር መንገዱን ስም ያለ አግባብ እያጠፉ ይገኛሉ ተብሏል። ይህ ድርጊታቸው አገሪቱ አለኝ ለምትለውና በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ኩራቷ በሆነው ተቋም ላይ ብቻ ሳይሆን በአገርና በሕዝብ ላይ የተቃጣ እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው ያሉት ሃላፊዎቹ፤ እንዲህ አይነት ድርጊት ፈጻሚዎችን በሕግ ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንደማይሉም ተናግረዋል።
ከ14 ሺ በላይ ቋሚና 3 ሺ የሚሆኑ ጊዜያዊ ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን እጅግ ፈታኝ ችግሮችና ፈተናዎች በቅርቡ ያገጠመውንና በርካታ የአለማችንን ግዙፍ አየር መንገዶች ለመውደቅ ያንገዳገዳቸውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተቋቁሞ አሁንም በስኬት እየተንደረደረ በመብረር ላይ የሚገኝ የአገር ኩራት ነው ያሉት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልድ ገ/መድህን ናቸው፡፡
አየር መንገዱ በየወሩ ለሰራተኞቹ የሚከፍለውን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወርሃዊ ደመወዝ ሳያቋርጥ ሁሉንም ሰራተኞቹን ይዞ መቀጠሉም በዚሁ የጉብኝት ፕሮግራም ላይ ተነግሯል።
የአለማችን ታላላቅ አየር መንገዶች፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ጉዳት መቋቋም ተስኖአቸው በሰራተኞች ቅነሳ፣ በበጀት ድጎማና መሰል እርምጃዎች ላይ ይገኛሉ። የአለማችን ትልቁ አየር መንገድ ሉፍታንዛ ከ22 ሺ በላይ ሰራተኞቹን ሊቀንስ እንደሆነ ሰሞኑን የገለፀ ሲሆን አየር መንገዱን ለመታደግ ከጀርመን መንግሥት 9 ቢሊዮን ዩሮ መቀበሉ ተዘግቧል። የብሪትሽ ኤርዌይስ በበኩሉ፤ 12 ሺ ሰራተኞቹን ለማሰናበት ማሰቡን ቢቢሲ ዘግቧል።     


Read 1051 times