Saturday, 13 June 2020 11:28

የዘጠነኛው ደመና ዙፋን

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት-ሰነበታችሁሳ

ሰኔና ሰኞ ገጠመ አይደል! ያው እንግዲህ ሲባል ስለምንሰማ ነው! ግን… አለ አይደል…በ“ሰኔና ሰኞ ገጠመ” አይነት እየሆነ ያለው  ነገር ሁሉ ‘የተጻፈልን ነው’ በሚል ልናደርግ ከሚገቡን ነገሮች መዘናጋቱ አሪፍ አይደለም:: የምትሆነውን እያንዳንዷን ነገር ከእድልና ከመርገምት ነገር ጋር እያስተሳሰርን መዘናጋቱ ብልህነት አይሆንም፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከዚህ አሁን ግዴታ ከሆነው የፊት መሸፈኛ ነገር ጋር በተያያዘ ምንም እንኳን ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ አሁንም ገና የሚስተካከሉ ነገሮች አሉ፡፡ በየጊዜው ትንሽ ግራ የሚያጋቡ ሰዎች ታያላችሁ:: መሀል ከተማ አካባቢ የሆነ ነው:: እድሜው ቢበዛ ከአስርና  ከአስራ አንድ ዓመት የማይበልጠውና ጎስቆል ያለ ልጅ ፊቱን ሳይሸፍን ሮጥ፣ ሮጥ ሲል አንድ ደንብ አስከባሪ ያስቆመዋል፡፡
“የታለ ማስክ ያደረግኸው?”
ልጁ ከኪሱ ሸብሸብ ያለች ፊት መሸፈኛ ላጥ አድርጎ አሳየው፡፡ ደንብ አስከባሪው ምናልባት የሽንኩርት በኪሎ እስከ ሠላሳ አምስት ብር መግባት አስጨንቆት ይሁን፣ ወይ ትልቁንም ትንሹንም ማገዱ ስልችት ብሎትም ይሁን ልጁን “አድርግ” እንኳን ሳይለው ትቶት መንገዱን ቀጠለ፡፡ ልጁ ግን ፊት መሸፈኛውን አድርጎ ቀጠለ፡፡
ደንብ አስከባሪዎችን በተመለከተ እግረ መንገድ ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ እኛን ህግ ማክበራችንን የሚቆጣጠሩ ሰዎች፣ እኛን የሚመከለከተው ህግና መመሪያ እነሱን እንደሚመለከት ልብ ቢሉ አሪፍ ነው፡፡  ምን መሰላችሁ… ስድስትና ሰባት ሆነው ሰብሰብ ብለው ሲጨዋወቱ ይታያሉና ነው፡፡
እናላችሁ…ምን ችግር አለ መሰላችሁ…በዚህ ጊዜ እንኳን፣ እንዲህ በተወጣጠርንበት ጊዜ እንኳን ለመሆን፣ ትከሻ ለማሳየት የምንሞክር አለን፡፡ የፊት መሸፈኛ ማስክ ማድረግ መከላከል ማለት ነው፡፡ እናላችሁ… ወይ አንገታቸው ስር የሚወሽቁ፣ ወይ ጭርሱን አውለቀው በጣታቸው እያወዛወዙ የሚሄዱ  አሉላችሁ፡፡ ይሄ እኮ የስፔይን ጫማ ማጥለቅ፣ የጣልያን ሱፍ ‘ገጭ የማድረግ’ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ እኮ፣ “ወዳጅ ደስ ይለው ጠላት እርር ይበል!” አይነት ነገር የሚባልበት ጊዜ አይደለም፡፡ አሁን ያለንበት እጅግ አስቸጋሪ ጊዜ ከምንም በላይ ህጎችና መመሪያዎች ሊከበሩ የሚገባበት ጊዜ ነው:: “እዩኝ፣ ከእናንተ የተለየሁ፣ ዘጠነኛው ደመና ላይ የተንፈላሰስኩ ነኝ፣” የሚባል ‘የሙሉ ኪስ፣ የባዶ ጭንቄ’  ጉራ የሚነሰነስበት ጊዜ አይደለም:: እናማ…አለ አይደል… “ህግ ባናከብር ምን የቆረጠው ነው ዝምባችንን እሽ የሚል!” አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፣ ይሄን ጀግንነታቸውን ለሌላ ያድርጉት፡፡ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ግን  የእያንዳንዱ ሰው እንቅስቃሴ የሁሉም ጉዳይ ነው:: የጥንቃቄ ህጎችን ያለማክበር ዝም ብሎ የአጉል ባህሪይ ጉዳይ ተብሎ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ችግር ላይ የሚከት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ 
እናላችሁ… በዚህም አስቸጋሪ ወቅት ከሌላው የተለዩ ‘ብሉብለድ’ ነገር ለመሆን የሚሞክራቸው ሰዎች ማየት አሳፋሪ ነው፡፡ ትናንትናና ዛሬ ፍጹም የተለያዩ ጊዜያት መሆናቸውን መገንዘብ ለምን እንደሚያቅታቸው መገመቱም አስቸጋሪ ነው፡፡    
አንድ አገልግሎት መስጫ ሰሞኑን የሆነ ነው፡፡ ወርሀዊ ሂሳብ ለመክፈል ሰዉ ተሰልፎ ተራ በተራ ይገባል፡፡ ስሙኝማ…እንዲህ አይነት ስፍራዎች ማህበራዊ ርቀት የሚባለውን መተግበሩ ፈታኝ እየሆነ ነው…በእኛው በራሳችን ምክንያት፡፡ ተነገረ! ተነገረ! ተነገረ! የቀበጡ፣ “ምንም አንሆንም፣” የሚሉ ሰዎች በበዙባቸው ሀገራት የሆነውን ሁሉ አይተናል፣ እያየንም ነው፡፡ ከምንም በላይ ማህበራዊ ርቀት መጠበቁ ሩቅ መንገድ የሚያስኬድ መከላከያ መሆኑን በባለሙያዎች ተደጋግሞ ተነገረን፡፡ ከዚህ በላይ ምን ቢደረግ ነው የምንስተካከለው! ካልጠበበ ስፍራ የአንዱ ደረት አንዱ ጀርባ ላይ የሚለጠፍበት ምን የሚሉት ግዴለሽነት ነው!
በነገራችን ላይ የፊት መሸፈኛ መደረጉ ብቻ በቂ መከላከያ የሚመስላቸው ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ እውነታው እንደዛ እንዳልሆነና የፊት መሸፈኛ አንድ ዘዴ ብቻ መሆኑ እየተነገረ ነው…በተደጋጋሚ፡፡ የጤና ባለሙያዎች በማህበራዊ ገጾቻቸው የቻሉትን ያህል ሊነግሩን እየሞከሩ ነው:: እውነት ለመናገር በአሁኑ ጊዜ ራሳችንን በእነሱ ቦታ አድርገን ማሰቡ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አይደለም በእኛ ግዴለሽነት፣ በሌሎች ሀገራት ህዝቡ መመሪያዎችን እያከበረ እንኳን የጤና ባለሙያዎችን መከራ እያየን ነው:: እናማ ምን እንሁን፣ ምን አድርጉን እያልን እንደሆነ አንድዬ ይወቀው እንጂ ሰው የይሆናል ምክንያት ሊሰጥበት አስቸጋሪ የሆነ ነገር ነው፡፡
እናላችሁ… በቀደም የአገልግሎት ሂሳብ ልንከፍል የተሰለፍንበት ስፍራም እንዲሁ ነበር፡፡ እንደ ላስቲክ አንዴ ወደ አንድ ሜትር ገደማ፣ አንዴ ወደ አንድ ከግማሽ ሴንቲ ሜትር እየተወዛወዝን ነበር፡፡ እናላችሁ…ሰዉ ሁለትም፣ ሦስትም እየተጠራ ተራ፣ በተራ እየገባ ነው:: እናማ ተራ ደረሰ፡፡ ይሄን ጊዜ አንዲት ሸልል ያለችና ስትራመድ ግራቪቲ የሚባል ነገር የሌለ የምታስምስል ‘ሴትዮ’ የመኪና ቁልፏን እያሽከረከረች አትኩሮታቸው ወደ ሌሎች ተገልጋዮች የነበሩትን ጥበቃዎች አልፋ በጎን በኩል ሹልክ ብላ ትገባለች፡፡ ምን አለፋችሁ… አይደለም በአካባቢው፣ ለስምንት ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሌላ አንድም ሰው የሚባል ፍጡር የሌለ አይነት ነበር፡፡
እናላችሁ…አለ አይደል…እኛ ቆመን ነበር እንጂ አስተኝታ እንደተረማመደችብን ቁጠሩት፡፡ አልፋን በቀጥታ ወደ መክፈያው ሄዳ የያዘችውን ቢል ወደ ገንዘብ ሰብሳቢው ገፋችው፡፡ ይሄኔ ነው አንድ ገና እንፋሎቱ ከላይ ሲተን ሊታይ ምንም የማይቀረው ጎረምሳ ቢጤ ጥበቃ ሮጥ ብሎ የመጣው:: ወደ ሂሳብ ተቀባዩ ጠረጴዛ ወርወር ያደረገችውን ቢል መልሶ ወደ እሷ ይገፋላታል፡፡
“ደጅ ውጪና ሰልፍ ያዥ!”
ብዙ ጊዜ ነገሬ ብላችሁ እንደሁ… አለ አይደል… እንዲህ አይነት ‘ብልጥነት’ የሚሞክር ሰው ሲነቃበት ለስለስ ብሎ ለማባበል፤ ሆድ ለማባባት ይሞክራል፡፡
“ምን መሰለህ፣ ሰው ታሞብኝ ሀኪም ቤት ለመሄድ ቸኩዬ ነው፣” አይነት ነገር፡፡
ይቺኛዋ ግን አይደለም መለሳለስ በአንድ ጊዜ ግስላ ነገር ሆነች፡፡ (“አራስ ነብር፣” ማለቱ እንዳይበዛባት ብዬ ነው፡፡ ደግሞላችሁ ይህን ሁሉ ጊዜ ድፍን ያለ ጥቁር የፀሃይ መነጽሯን አላወለቀችውም፡፡
“ተራዬ ነው!” ብላ ተመናጨቀችና መልሳ ቢሉን ወደ ሂሳብ ተቀባዩ ገፋ አደረገችው፡፡ (እኔ የምለው… የአንዳንዱ ‘ፈጣጣነት’ እንዴት ነው እንዲህ ጣራ ቀዶ የሚሄደው! እኛ ተገትረን እኮ እዛው ነን! ለነገሩ እኛን ‘ቁጥር ውስጥ ስላልከተተችን’ አይፈረድባትም፡፡)
ጥበቃው ምናልባት በሆዱ “የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ ነው እንጂ መንገድ ከመንገድ ነበር የማሯሯጥሽ!” አይነት ነገር እያለ መልሶ ወደ እሷ ገፋው፡፡
“ውጪልን፣ ሥራችንን እንሥራበት!”
እሷዬዋ ዝምብ ያረፈባትም አልመሰላት:: “አንተ ሰውዬ ልብ አድርግ፡፡ ነግሬአለሁ!” አለች ጣቷን ሳይሆን የመኪና ቁልፏን እየወዘወዘችበት:: እሱ የዋዛ ጎረምሳ አልነበረም፡፡
“አትረብሺ፤ ሰዉ ይክፈልበት!”
ይሄኔ እሷ የተዘዋዋሪ ዛቻዋን ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አሳደገችው፡፡
“አንተ ሰውዬ ከእኔ ነገር አለህ እንዴ!”
ቀጥሎ ወደ ማን ብትዞር ጥሩ ነው…ወደ እኛ!
“ይሄ ሰውዬ ከእኔ ነገር አለው እንዴ!”
ኸረ! “ተባለ እንዴ!” ማለት ይሄኔ ነው:: የሆነ ቅሰቀሳ ነገር መሆኑ ነው እኮ! (ሴትዮዋ እዛው በዛው፣ ዓይናችን ስር ከ‘ተራ ዜግነት’  ወደ አክቲቪስትነት ተሸጋገረች ማለት ነው! ቂ…ቂ…ቂ… አሀ…ባልበላነው ኬክ ‘ስትቀሰቅሰን’ ምን እናድርግ!)
ይሄኔ እሱዬው ነገሩ አንገቱ ላይ ስለደረሰበት ወረቀቱን ለቀም አድርጎ ይዞ ወደ ውጪ ወጣ:: ወጣቻታ፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ያለ ተራዋ ሾልካ እንደገባች እኮ ሁሉም አይቷታል! እናላችሁ.. ዘንድሮም በእንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ጊዜ ‘ስፔሻል ትሪትመንት’ ነገር ፈላጊዎች መኖራቸው ያሳዝናል፡፡
ምን መሰላችሁ…ወይ በፈራንካው፣ ወይ ‘ከጀርባ’ የሆነ የቻይና ግንብ ነገር ስላለን፡ ወይ በ‘አገር ልጅነት’ ምናምን ‘ስፔሻል ትሪትመንት’ የለመድን አለን፡፡ አለ አይደል…ለሌላው የሚዘጉ በሮች ሁሉ  ወለል የሚሉልን አይነቶች፡፡ ግን አሁን ጊዜው ሌላ ነው፡፡ ሀገርና ህዝብ የህልውና ጥያቄ ላይ ባሉበት ጊዜ የዘጠነኛ ደመና ዙፋን ፍለጋ ቅሽምና ነው፡፡ ግዴለም የዘጠነኛው ደመና ዙፋን ይቆይላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1928 times Last modified on Saturday, 13 June 2020 11:55