Print this page
Saturday, 13 June 2020 11:32

መፍጨርጨሪያዎቻችን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ...ኑሮን (ፖለቲካን) ማማረሩ ምንም ፋይዳ እንደሌለው እስካሁን ካልተገነዘባችሁ መቼም አትገነዘቡም፡፡ ማማረሩ የማይቀር ከሆነ ደግሞ አዲስ አይነት የማማረሪያ መንገዶችን ቢያንስ መሞከሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ማማረር ካልቀረ የሚመር እና የሚሰለች ባይሆን አይሻልም? ምን ትላላችሁ?! የኑሮን ሱሪ ባንገት ማጥለቅ እና ማውለቅ ከተለማመዳችሁ፣ በአዲስ ዘዴ ማማረርን መለማመድ እንዴት ያቅታችኋል?
ብዙዎቻችሁ፣ የኑሮ ጫማ ጠቧችሁም ሚስት እያገባችሁ ልጅ እየወለዳችሁ መሆኑን ተመልክቻለሁ፡፡ ጋብቻ፣ ጥሩ ኑሮን የማሸነፊያ ብልሃት ነው፡፡ ጎበዞች ናችሁ፡፡ ልጅ መውለዱ ደግሞ ቆራጥ ተፍጨርጫሪ ያደርጋል፡፡
በዛ ላይ፣ ‹ልጆች የራሳቸውን እድል ይዘው ይወለዳሉ› ብላችሁ ታምኑ የለ? በዚህ አይነት ጊዜ፣ የኑሮ አውሬ እንደ ቀን ጅብ ሁሉንም እየነከሰ ባለበት ሁኔታ፣ ልጅ መውለድ ራስ ወዳድነት ነው ብዬ አስብ ነበር፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡
‹ከእጅ ወደ አፍ› ሳይሆን፣ እጅ ታስሮ አፍ ብቻ በሚያዛጋበት የኢኮኖሚ አቅም፣ ሌላ አፍ መጨመር እብደት ይመስለኝ ነበር፤ ተሳስቻለሁ:: እናንተ እንደ ሁልጊዜውም፣ በምክንያታዊነት ሳይሆን በደመ ነፍስ የምትሰሩት ነገር ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ለካ ልጅ ከቤት እና ከገቢ በፊት ያስቀደማችሁት፣ ለምታደርጉት መፍጨርጨር ምክንያት እንዲሆናችሁ ነው፡፡ ልጅ ለካ መፍጨርጨርን ለማነሳሳት የሚያገለግል፣ ለመኖር ምክንያትን የሚፈጥር “ኢንሴንቲቭ” ነው፡፡ አሁን እኮ ነው የገባኝ (የእኔ ነገር)፡፡
ሕይወት መፍጨርጨር በሆነበት ሀገር፣ ልጅ “ማፍጨርጨሪያ” ነው፡፡ እልህ መቀስቀሻ፣ የማታገያ፣ ሮጥ-ሮጥ ማድረጊያ ክኒን ነው፡፡ ልጅ፣ የኑሮ “ሬድ ቡል” ነው፤ ወይንም ነዳጅ:: ለምሳሌ፤ ወፍ እንደ እናንተ አታደርግም፡፡ መጀመሪያ ጎጆ መስራት አለባት፡፡ ምግብ በሚገኝበት የአመቱ ወቅት ውስጥ ነው፣ የትዳር ጓደኛ የምትፈልገው:: የትዳር ጓደኛ ፈልጋ፣ ጎጆው ሙሉ መሆኑን ስታረጋግጥ ነው እንቁላሏን የምትጥለው:: እንቁላሉ ሲፈለፈል፣ ራሱን እስኪችል ድረስ፣ ጫጩቱን መንከባከብ እና መጠበቅ አለባት:: ወፏ ጫጩቱን ጥላው ወደ ‹አረብ ሀገር› አትሄድም፡፡ እናት ጫጩቱን የማሳደግ ሃላፊነት አለባት፡፡ ‹የወለድኩትን ወላጆቼ ያሳድጉ› በወፍ የአስተሳሰብ ምህዳር አያራምድም፡፡
እናንተ ግን ወፍ አይደላችሁም፤ ልጅን መውለድ እና አለማሳደግ ትችላላችሁ፡፡ ልጁ ይዞ በሚመጣው የራሱ ዕድል ወላጆች ሲጠቀሙም ተመልክቻለሁ፡፡ አጎቶቹ እና አክስቶቹ ከባህር ማዶ ይልኩለታል፡፡ መቼም አክስቶቹ ባህር ማዶ፣ አጎቶቹ በስደት በረሀ ተበትነው የሆነ ቦታ ላይ ያልበቀለለት አንድ ሰውም አይገኝም፡፡ ልጅ በመውለዱ የሚጠቀመው ወላጅ ነው፡፡ እናትም አረብ ሀገር ሰራተኛ ለመሆን ያላትን ማመንታት ወደ ተግባር ቀይራ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በር ላይ ለስደት እንድትቆርጥ ያደርጋታል፡፡ ስለዚህ ልጅ ጥሩ ነው፤ ልጅ ይበረታታል፡፡
ጫት ማቆም ያቃታቸው፣ ሲጋራ ላይ መወሰን የተሳናቸው፣ መጠጥ ገንዘባቸውን የመጠጠባቸው ሰዎች፣ ልጅ በመውለድ ሱሳቸውን ሲያቆሙ አስተውዬ ተደስቻለሁ:: ልጅ መፍጨርጨሪያ ብቻ ሳይሆን “Rehab for Addiction” ጭምርም ነው፤ ማለት ይመስላል፡፡ ልክ ሀይማኖት ውስጥ በመግባት ሕይወታቸውን አትርፈዋል እንደሚባሉት፣ ከሱስ ብዛት ከመጣ የጤና እጦት ምክንያት የቀረበ ሞታቸውን፣ ልጅ በመውለድ ራሳቸውን የሰበሰቡ ብዙ ናቸው፡፡
እንግዲህ በድሮ ጊዜ ልጅ፡- የወላጆቹን፣ የአያቶቹን ስም ማስጠሪያ ነበር፡፡ የእነሱን ስም ለማስጠራት ካልሆነ፣ ሌላ አገልግሎት አልነበረውም፡፡ አይንን (የራስን)፣ በአይን (በልጁ) ለማየትም ልጅ ይወለድ ነበር (ወይንስ አሁንም እንደዛ ነው?)፡፡ እንደ መስታወት የሌላ ሰውን መልክ ከማንፀባረቅ ወይንም ከማሳየት ውጭ ሌላ አገልግሎት የለውም ነበር፡፡ የሚያኮሩ የልጅ ምንነት ፍቺዎች አሉን፤ የሚያኮራ ሀገር ላይ፡፡
ዘንድሮ ደግሞ፣ ቅድም በጠቃቀስኳቸው የልጅ አገልግሎቶች ላይ፣ አዳዲስ እና የተሻሻሉ ጥቅማ ጥቅሞች ተገኝተዋል:: ልጅ፡- ኢንሴንቲቭ፣ ወጥሮ ለመኖር የሚያስገድድ መወጠሪያ፣ ማፍጨርጨሪያ፣ ለስደት ማነሳሻ፣ ገንዘብን ላለማጥፋት ጥቅም ላይ ማዋያ፤ ቁጠባን የሚያበረታታ መቆጠቢያ፣ የተበታተነ ሀሳብን መሰብሰቢያ፣ ሱስ ማቆሚያ... ወዘተ እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡ እዚህ ላይ ልጁ ከተወለደ በኋላም ወላጅ መፍጨርጨር ያቃተው ከሆነ፣ አሊያም ተፍጨርጭሮ ድሮ ከነበረበት ምንም ፈቅ ማለት ከተሳነው፣ ልጁ ያለ አገልግሎት እንደሚወሰድ የሚመር ክኒን ወይንም  የሚያሳምም መርፌ ይሆናል፡፡
ልጁ ወላጆቹን መቀየር ወይንም ማከም ካቃተው፣ ራሱን ማሳደግ መጀመር መቻል አለበት፡፡ ብሎም፣ ወላጆቹን ጨምሮ ለማሳደግ እንዲሟሟት ይገደዳል:: ሕጻናት ልጆቻቸውን ሜዳ ላይ በትነው፣ መንገደኛውን፣ ወጪ ወራጁን የሚያስለምኑ ወላጆች፣ በልጆቻቸው አማካኝነት የሚያድጉ ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን ተንከባክበው የሚያሳድጉ ሳይሆን ልጆቻቸው ወላጆቻቸውን ተሯሩጠው ያሳድጓቸዋል:: በልጆቻቸው የሚያድጉ ወላጆች ብዙ ናቸው፡፡ ብዙ ሆነው ግን የብዙሀኑን የሚመለከት ሚስጥራቸው እንደተጠበቀ ይቀጥላል፤ የሕፃናቶቹ ብዝበዛ:: ለህጻናቱ እስካሁን አልተነገራቸውም፡፡ ቢነገራቸውም የዋህ ናቸውና አይገባቸውም፡፡ ገብቶአቸው ማመፅ የጀመሩ ዕለት፣ እነሱም ልጅ ሳይሆኑ አዋቂ ሆነዋል፡፡--
(ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው የደራሲ ሌሊሳ ግርማ “ነጸብራቅ” የተቀነጨበ)


Read 2663 times
Administrator

Latest from Administrator