Print this page
Saturday, 13 June 2020 11:57

ውዳሴ ዘዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

  በመንግስት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ያልተማረረና ያልተራገመ ሰው በባትሪ ተፈልጎ አይገኝም ብሎ መወራረድ የሚቻል ይመስለኛል:: ጥሩ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ለመሃላ ተፈልጎ ቢገኝ እንኳ አንድ ሰሞን ለወረት ያህል ከመስራት በዘለለ ደግመው ቢሄዱ ሊያገኙት አይችሉም፡፡ (ለምሣሌ፡- የቀድሞው የውልና ማስረጃ ጽ/ቤት በመልካም አገልግሎት አሰጣጡ አንድ ሰሞን የተመሰገነና መነጋገሪያ ቢሆንም ዘላቂነት ሊኖረው ባለመቻሉ ዛሬ ተረት ሆኗል::) ሰሞኑን በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የገጠመኝ መልካም ሁኔታ ብርቅ ሆኖ ታየኝና በዚህ ሳምንት ማስታወሻዬ ትኩረት ላደርግበት አሰብኩ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግል የህክምና ተቋማት በብዙዎች ዘንድ ከእግዜሩ/ከአላህ ቀጥለው “ምውትን ወደ ህያውነት” የሚመልሱ ተደርገው እየታዩ ነው፡፡ ዝናቸው በሰፊው ይናፈሳል፡፡ እነዚህ የግል ተቋማት ከሚያስከፍሉት ገንዘብ አኳያ የሀብት መለኪያ ተደርገው እየተወሰዱም ነው:: በእነዚህ ተቋማት መታከም በተለይም የነፍሰጡሮች የወሊድ አገልግሎት በአስር ሺዎች ብር የሚከፈልበት መሆኑ እንደ ዝና እየተቆጠረ ነው፡፡
በአንጻሩ ወደ መንግስት የጤና አገልግሎት ተቋማት ለህክምና የሚሄድ ሰው፤ የኔ ቢጤ ያጣ የነጣ ድሃ ብቻ ነው፡፡ ወደነዚህ ተቋማት መሄድ ታክሞ ለመዳን ሳይሆን ወደ ሲዖል እንደመገስገስ እየታየ ነው፡፡ ወደነዚህ ተቋማት መሄድ የድሃ ድሃ ተደርጎ የሚያስቆጥር ነው:: እንዲህ ያለው የእይታ መንሸዋረር ሊከሰት የቻለበት አንዱ ምክንያት ከዓመታት በፊት በመንግስት የጤና ተቋማት በነበረው ግድየለሽ አገልግሎት አሰጣጥ የተነሳ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የመንግስት የጤና ተቋማት በቁጥር አነስተኛ ስለነበሩ በርካታ ቁጥር ያለውን ተገልጋይ በአግባቡ ለማስተናገድ ባለመቻላቸው፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት አልቻሉም ነበር:: በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች በወቅቱ ብቅ ብቅ ብለው ወደነበሩት የግል የህክምና ተቋማት በመሄድ ባልተንዛዛ ቢሮክራሲ መስተናገድ መቻላቸው አስደሰታቸው፡፡ ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡
ባለቤቴ የዛሬ 4 ዓመት ሦስተኛ ልጃችንን የወለደቺው በምንኖርበት የወረዳ የጤና ጣቢያ ነበር፡፡ በወቅቱ የተደረገላት የእርግዛና ክትትልም ሆነ የተሰጣት የወሊድ አገልግሎት ከጠበቅነው በላይ አስገርሞን ነበር፡፡ በወጪ ደረጃም አምስት ሣንቲም አልከፈልንም:: በቀጣይ ለህፃኑ የተደረገውም ህክምናና የክትባት አገልግሎት ቀልጣፋና ምንም ዓይነት ወጪ የተደረገበት አልነበረም:: አራተኛ ልጃችንን ስታረግዝም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደዚሁ ጤና ጣቢያ አቀናች፡፡ የእርግዝና ክትትል ስታደርግ ቆየችና የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ ስትሄድ በሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት አካባቢ እንደምትወልድ ተነገራት፡፡
ከቀናት በኋላ ግን የህመም ስሜት ተሰማትና ከሌሊቱ 6 ሰዓት ወደ ጤና ጣቢያው ሄድን፡፡ የክትትል ካርዷ ቀርቦ በተረኛው ሀኪም ታየች፡፡ ከቀኗ በፊት የምጥ ስሜት መከሰቱ አስጊ በመሆኑ ለተሻለ ህክምና ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈራል ተጻፈላት፡፡ በመኪና ልወስዳት ስዘጋጅ ጤና ጣቢያው ራሱ የሪፈራል ወረቀቱን አዘጋጅቶ፣ ራሱ አምቡላንስ ጠርቶ፣ ከተቀባዩ ምኒልክ ሆስፒታል ጋር በስልክ ተነጋግሮ፣ አንድ የጤና ባለሙያ መድቦ፣ በአምቡላንስ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ወስዶ ለእለቱ የሆስፒታሉ ተረኛ ሀኪሞች ከምርመራ ሰነድ ጋር አስረከበ፡፡
የምኒልክ ሆስፒታል የእለቱ ተረኛ ሀኪሞችም ተቀብለው፣ አስፈላጊውን ምርመራ አድርገው፣ አልጋ አመቻችተው ወደ ማዋለጃ ክፍል ወሰዷት፡፡ ከሰዓታት በኋላ በባለሙያ እገዛ በሰላም ተገላገለች፡፡ ህፃኑ ግን መወለድ ከሚገባው ጊዜ ቀድሞ ስለተወለደ በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ማሞቂያ ክፍል እንዲገባ ሀኪሞች ወሰኑ፡፡ ተጠራሁና “ህፃኑን አቅፈህ ወደ ማሞቂያ ክፍል ውሰድ” ተባልኩ፡፡ አንድ ባለሙያ አስፈላጊውን ሰነድ ይዞ እየመራኝ 50 ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ማሞቂያ ክፍል ህጻኑን አደረስኩ:: የማሞቂያ ክፍል የህክምና ባለሙያዎች በሰነዱ መሰረት ህፃኑን ተቀበሉኝና እኔ ካርድ እስካወጣ ሳይጠብቁ ወዲው ህክምና ጀመሩ…
ባለቤቴ ከማዋለጃ ክፍል ወጥታ ወደ ወላዶች ማረፊያ ክፍል ተዛወረች፡፡ ለእርሷም አስፈላጊው የህክምና ክትትል እየተደረገላት ነው፡፡ ከአንድ ቀን በኋላ በማሞቂያ ክፍሉ አጠገብ ለእናቶች ማረፊያ ወደተዘጋጀ ክፍል ተዛወረች፡፡ እዚያ ሆና ልጇን በፈለገቺው ሰዓት ማየት፣ ሲፈቀድላት ማጥባት ወይም ጡቷን አልባ በጡጦ መስጠት ትችላለች፡፡ ለህፃኑ አስፈላጊው መድኃኒት ከሆስፒታሉ ፋርማሲ ይመጣለታል፡፡ ለእርሷም ምግብ ከሆስፒታሉ በየሰዓቱ ይቀርብላታል… ህፃኑ መዳኑ በሀኪም ተረጋግጦ ወደ ቤትሽ ሂጂ እስክትባል ድረስ ግን ከዚያ ክፍል መውጣት ፈጽሞ ክልክል ነው፡፡ ከሳምንት በኋላ ባለቤቴንና ልጃችንን ይዤ ወደ ቤቴ በሰላም ተመለስኩ… ለዚህ ሁሉ አገልግሎት አምስት ሣንቲም አልከፈልኩም፡፡ በግል የህክምና ተቋም ወልዳ ቢሆን ኖሮ ግን ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ መጠየቄ ጥርጥር የለውም…
ይህንን ዝርዝር ሁኔታ ያቀረብኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አንደኛ፡- በእኛ ሀገር፣ በመንግስት የህክምና ተቋማት ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ቀልጣፋና ተገልጋዩን የሚያረካ አገልግሎት መኖሩን የዓይን እማኝነቴን ለመግለጽ ነው፡፡ ሁለተኛ፡- እንዲህ ያለውን አገልግሎት ማግኘት የሁሉም ዜጎች መብት በመሆኑ ያልሰሙና ያላዩ ሰዎች መረጃ እንዲገኙ ሲሆን፤ ሦስተኛ፡- ለተገልጋይ እርካታ ለመፍጠር የሚደረግን እንዲህ ዓይነት ጥረት በአርአያነት አንስቶ ምስጋና በማቅረብ ሆስፒታሉን ለበለጠ ጥረት ለማነሳሳት በማሰብ ነው፡፡
ጽሁፌን ከመቋጨቴ በፊት ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ታሪክ ጣል አድርጌ ማለፍ ወደድሁ፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዘመናቸው ያላስጀመሩት ነገር የለም:: ት/ቤት፣ ፋርማሲ፣ ሆቴል፣ የአማርኛ የጽሕፈት መኪና (ታይፕ ራይተር)፣ ስልክ፣ ፖስታ፣ ወዘተ. እያልን መቀጠል እንችላለን:: ንጉሱ ለዘመናዊ ህክምና በጣም ጉጉ ነበሩ:: ሬኔል ሮድ የተባለ የእንግሊዝ መልእክተኛ፣ በ1890 ዓ.ም አዲስ አበባን ለመጎብኘት በመጣ ጊዜ፣ ንጉሱ በቤተ-መንግስታቸው አቀባበል አደረጉለት:: በዚሁ ወቅት የኤክስሬይ (ራጅ) መሳሪያ ይዞ መምጣቱንና ካህናቱን በመፍራት ወደ ቤተ-መንግስት እንዳላመጣው ነገራቸው፡፡ ንጉሱም “ዝም ብለህ ነው ወዳጄ ይዘህ መምጣት ነበረብህ” ማለታቸው ይነገራል፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በአገሪቱ የህክምና አገልግሎት ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሲሆን፤ ስራ የጀመረው በ1903 ዓ.ም ነበር:: ይህንን ሆስፒታል የመራው የመጀመሪያው አስተዳዳሪ ፈረንሳዊው ዶ/ር ቪታሊን እንደሚባል የታሪክ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ (በነገራችን ላይ ታዋቂው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል መርፌ ወጊ (ሀኪም) ነበር፡፡ እውቁ የእግር ኳስ ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማም ሆስፒታሉን አስተዳድረዋል)
የህዝብ ጤናን ለመጠበቅ የተመሠረተው ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በረጅም ጊዜ የአገልግሎት ዘመኑ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች  ከጊዜ  ወደ  ጊዜ  እያደጉ  መጥተዋል::  የተገልጋዩም ቁጥር ጨምሯል::  ሆስፒታሉ በሀገሪቷ የህክምና ተቋም ታሪክ ቀዳሚ በመሆኑ የህክምናውን ጫና ተሸክሞ ማለፉ  ይታወቃል:: በዚያ ወቅት የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ህዝብ ያስመረረ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ዛሬ “ታሪክ” ሆኗል!
ሆስፒታሉ 62 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ይዞታ ያለው ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዳልነበረውና ባዶ መሬቱን በአግባቡ እንዳልተጠቀመበትም ይታወቃል፡፡ከምስረታው ጀምሮ ማስፋፊያዎች ባለመከናወናቸው፣ በቂ በሆነ የሰው ኃይል ባለመደራጀቱና በተለያዩ ተጽዕኖዎች ውስጥ እንዲያልፍ መገደዱ የሆስፒታሉን አገልግሎት አርኪ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ በሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩትን በርካታ ችግሮች ለማቃለል ከ2001 ዓ.ም ወዲህ (ከመቶኛ ዓመቱ ወዲህ) መሰረታዊ  ለውጥ መደረጉን ሰምቻለሁ፡፡ ዛሬ  ሆስፒታሉ የይዞታ ካርታ አግኝቷል፡፡ ለቀደምት የአገልግሎት መስጫ ክፍሎቹ እድሳት ተደርጎላቸዋል፡፡ ከ7 ወለል በላይ ያለው ዘመናዊ የህክምና መስጫ ህንፃ አስገንብቷል፡፡  የሆስፒታሉን  ጊቢ ተዘዋውሬ እንዳየሁት አሁንም ተጨማሪ አዳዲስ ግንባታዎች በመከናወን ላይ ነው፡፡
ዳግማዊ  ምኒልክ  ሆስፒታል  ከሚታወቅባቸው  ሥራዎቹ  አንዱና ብቸኛው  “የአስክሬን ምርመራ” ነው:: ዛሬ ግን ሆስፒታሉ የሀዘን ብቻ ሳይሆን የደስታ ብስራት፣ የእምቦቀቅላ ህፃናት  የመወለድ ዜማ የሚሰማበት ስፍራ ሆኗል:: ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት ጠቅላላ ህክምና፣ ከአንገት በላይ፣ የውስጥ ደዌ፣ የነርቭ፣ የአጥንትና የጥርስ የህክምና አገልግሎቶችን በመስጠት ህሙማንን በመርዳት  ላይ ይገኛል፡፡ የዓይን ባንክም መኖሩን አይቻለሁ፡፡
አዲስ የማስፋፊያ ህንጻ መገንባቱ ደግሞ ሆስፒታሉ  አገልግሎቱን በተሻለ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ አስችሎታል፡፡ ከዚህ በፊት ይሰጡ ያልነበሩ የእናቶች የድህረ  እና የቅድመ ወሊድ ክትትሎችና የማዋለድ፣ እንዲሁም የህጻናት ህክምና አገልግሎቶችን ለመጀመር አስችሎታል:: ሆስፒታሉን ጽዱና ምቹ በማድረግ ዘመናዊ የሆነ የሆስፒታል አገልግሎት ሥርዓት ለመከተል ጥረት  እያደረገ ነው፡፡
በተለይም በእናቶችና በህፃናት ህክምና አገልግሎት ክፍል ሙያው በሚጠይቀው መሰረት ህይወት ለማትረፍ ቅድሚያ የሚሰጡ፣ ርህራሄ ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡ የመድኃኒት አቅርቦቱ አስደሳች ነው:: ለተኝቶ ታካሚዎችም የምግብ አቅርቦት ያደርጋል:: የጽዳት፣ የጥበቃና የምግብ አቅርቦቱ በአቅራቢ ድርጅቶች (out source) የሚከናወን ነው፡፡
በጥቅሉ ሲታይ የሀገራችን የመንግስት የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋዩን ፍላጎት በማሟላት ረገድ ብዙ ይቀረዋል። ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልም ቢሆን፤ ከላይ የተጠቀሱት በጎ ተግባራትና መልካም የሚባሉ ለውጦችን ቢያስመዘግብም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች አሉት፡፡ ሌላው ቀርቶ የቢሮ ቁጥሮች ለተገልጋይ ሊታይ በሚችል መልኩ ባለመጻፋቸው “ፋርማሲው የት ነው? ላቦራቶሪውን አሳዩኝ? ካርድ ክፍሉን አመላክቱኝ?...” የሚለው ቢሮ ፈላጊ ውጣ ውረድ አይጣል ነው፡፡
ከባለሙያዎች ጋር በተያያዘ፤ ሁሉም ባለሙያዎች ሙያቸውን “የእርካታ ምንጭ” አድርገው እየሰሩ አለመሆኑ ይስተዋላል:: ዛሬም ህይወት ለማትረፍ የማይተጉ፣ ርህራሄ የሌላቸው፣ ቅንነት የጎደላቸው፣ የሙያ ስነ ምግባር የሌላቸው፣ ደንታቢስ፣ ሰው ጤፉ፣… የሆኑ “ባለሙያዎች” መኖራቸውንም ታዝቤያለሁ፡፡ በተረኛነት ጊዜያቸው ተኝተው የሚያንኮራፉ “አገልጋዮችን” አስተውያለሁ:: የተጠናከረ ጥበቃና ቁጥጥር ባለመኖሩ ግቢው ውስጥ ዛፍ ስር ቁጭ ብለው ጫት የሚቅሙ ሰዎችን አይቻለሁ:: የሆስፒታሉ ጥበቃ የሚከናወነው በጥበቃ ድርጅት ቢሆንም፤ ጥበቃው የላላ፣ የጥበቃ ሰራተኞቹ እርስ በራሳቸው የሚወዛገቡና የማይግባቡ፣ ለፈለጉት ሰው መኪናውን ይዞ እንዲገባ የሚፈቅዱ፤ ላልፈለጉትና ጉቦ ላልሰጣቸው የሚከለክሉ… መሆናቸውንም በአንድ ሳምንት ቆይታዬ ተመልክቻለሁ፡፡
በአጠቃላይ፤ በዳግማዊ  ምኒልክ  ሆስፒታል  ያየሁት የአገልግሎት አሰጣጥ በአርአያነት የሚጠቀስና ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ሆስፒታሉ ከፍ ሲል የጠቃቀስኳቸውን ችግሮች ፈትቶ እንደ  እድሜ ቀዳሚነቱ በአገልግሎት አሰጣጡም ልቆ የተሟላ ባለ ታሪክ እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ፡፡
ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡



Read 1756 times