Print this page
Sunday, 14 June 2020 00:00

ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በትግራይ ፖለቲካ፣ ምርጫና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  - ምርጫው ነሐሴ ላይ እንዳይካሄድ የሚያደርግ ሳይንሳዊ ጥናት አልቀረበም
       - የትግራይ ህዝብ ተጨቁኗል የሚባለው ራሱ ተጨቁኛለሁ ሲል ነው
       - ትግራይ አገር ልሁን ካለች፣ በደንብ አገር መሆን ትችላለች
       - ህዝቡን ማዕከል ያደረገ ድርድር ያስፈልጋል


            በትግራይ ገዢ ፓርቲ (ህወኃት) እና በብልጽግና ፓርቲ መካከል ያለው ቅራኔ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ እንጂ እየተሻለ አልመጣም፡፡ እርስ በርስ የቃላት ጦርነት መወራወሩ እያየለ መጥቷል፡፡ የህወኃት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግንባር ፈጠረው የዘመቱበት ይመስላል፡፡ “ፈንቅል” የተባለ የትግል እንቅስቃሴ በክልሉ ወጣቶች እየተካሄደ መሆኑ ይነገራል፡፡  በሌላ በኩል፤ በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ አገራዊው ምርጫ ቢራዘምም የትግራይ ክልላዊ መንግስት በነሐሴ የራሴን ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ጀምሬአለሁ ብሏል፡፡  ይሄም ሌላው የውዝግብ መንስኤ ሆኗል::
በዚህ መሃል ችግሮችን በንግግር ተወያያቶ ለመፍታት ቅንጣት ታህል ተስፋ አይታይም - ከሁሉም ወገን፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙዎች መጨረሻው ያሰጋቸዋል - ያሳስባቸዋል፡፡  የቀድሞ የአየር ሀይል አዛዥ እንዲሁም በአ.አ.ዩ የፌዴራሊዝም መምህር የሆኑት ብ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡  


            ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የታየውን የለውጥ ሂደት እንዴት ይገመግሙታል?
ወደ ሁለት አመቱ ከመግባታችን በፊት በመጀመሪያ በተለይ ከ1983 በኋላ ያለውን ሁኔታ ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ ከ1983 መጨረሻ ጀምሮ ሀገራችን መጀመርያ በሽግግር ቻርተር ቀጥሎም በሕገ-መንግስቱ ወደ መሰረታዊ የስርዓት ሸግግር ጉዞ ጀምራለች:: በአንድ በኩል ወደ ካፒታሊዝም፣ በሌላ በኩል ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር:: ይሄ ሽግግር በአንድ ጊዜ ሁለት ጉልህ አላማዎችን የያዘ ከባድ ሽግግር ነበር፡፡ ወደ ካፒታሊዝም መሸጋገር ስንል ቀድሞ በእርሻ ላይ የተመሰረተ ኋላቀር ኢኮኖሚ እንዳለን ይታወቃል፡፡ ወደ ዴሞክራሲ ስንሸጋገር ደግሞ መብቶች የሚሰፉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ በአጠቃላይ ምን አይነት ስኬት ነበር? ምን አይነት ጉድለት ነበር? ምን አይነት ችግሮች ነበሩ? የሚለውን ማየቱ ይጠቅማል፡፡
እንግዲህ በአለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዴሞክራሲ ሲባል የህዝብ አገዛዝ ማለት ሲሆን ሁልጊዜ ማዕከሉ መብት ነው፡፡ ሲቪልና ፖለቲካዊ፤ ማህበረ-ኢኮኖሚዊ፤ የቡድን፤ የመልማትና ንፁህ አየር የማግኝት ወ.ዘ.ተ ናቸው:: እነዚህ መብቶች በግለሰብ፤ በፆታ፤ በሃይማኖት፤ ብሔር ወ.ዘ.ተ እኩልነት ይገለፃሉ፡፡ እንደ የአገሩ ሁኔታ የሚለያዩ ቢሆንም  አንኳር የሆኑት መብቶች ጎልተው የሚታዩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባ ዓመታት ምናልባትም ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት(ከፍተኛ ገቢ ያላት አገር እስክንገነባ ድረስ)  የመሬት ባለቤትነትና የብሔር ብሔረሰቦች መብቶች የተሳሰሩ ግን ጉልህ የመብት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ከ70 በመቶ በላይ ህዝብ አርሶ አደር እና አርብቶ አደር ነው፡፡ሁለተኛ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች “ብሄር የለኝም” የሚሉ ቢኖሩም፤ ነገር ግን አብዛኛው የዚህ ወይም የዚያኛው ብሔር አባል ነኝ የሚል ነው:: አብዛኛው ህዝብ የሚያሰለፉ ብቻ ሳይሆኑ እርስ በእርሳቸውም የተያያዙና አንዱን ከአንዱ ነጣጥሎ ለማየት የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡
የአገራችን ኢኮኖሚ መሰረቱ እርሻና እንስሳት ማርባት ነው፡፡ የመሬት አቅርቦት፤ የመሬት ዋስትና፤ ከፍተኛ ልማት ለማረጋገጥ የዕውቀትና የግብአት ጉዳይ፤ ከነዚህ ጋር የተሳሰሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች አቅም በፈቀደና በተሟላ ለማረጋገጥ የሚደረግ ፖለቲካዊ ትግል ነው ሰላምና ልማት የሚረጋገጠው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ካለምንም ተፅእኖ በራሱ ማስተዳደር ሲችል እና ከዛ በላይ ላሉ እርከኖች ደግሞ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እሴቶቹና ጥቅሞቹን የሚያረጋግጡለት መምረጥ ሲችል ነው::  ሁሉንም መብቶችና እኩልነቶች የሚረጋገጥበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
የግለሰብና የሃይማኖት መብቶች ጨምሮ ለምሳሌ የሴቶች እኩልነት ከማረጋገጥ አኳያ በከተማና በከፍተኛ የመንግሰት ተቋማት የሴቶች ቦታ ቁልፍ ሚና ቢኖረውም ወሳኙና መሰረታዊ ለውጥ ግን በገጠር የሴቶች እኩልነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ትግል ነው:: የገጠሪትዋ ሴት ካልተማረች፤ ልጆችዋ በበሽታ ወይም በትምህርት ቤት እጦት እቤት የሚውሉ ከሆነ፤ እንጨት ለመሰብሰብና ውሃ ለመቅዳት በቀን ሰዓታት የምትኳትን ከሆነ ኑሮዋ ጎስቋላ ይሆናል ብቻ ሳይሆን እኩልነት የሚባል የሰማይ መና ይሆናል፡፡ ለዚህም እላይ የተገለፁት ተግባሮች ወሳኝ ይሆናሉ፡፡
ይህ ሳይሆን ሲቀር የምግብ ዋስትና ይታጣል፤ ድርቅና ርሃብ አንድ ይሆናሉ፤ ለኢንዳስትሪው ግብአት ይቀጭጫል፤ ስራ አጥነት በእጅጉ ይስፋፋል ለፅንፈኞች የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥራል ሰላምም ሊታጣ ይችላል:: በከተማ ቢጀምርም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትርምስ ማዕከሉ ገጠሩ ነው:: ባለፉት100 ዓመታት ቀርፋፋ ቢሆንም ካፒታሊዝም ደረጃ በደረጃ አገራችን ውስጥ የገባባበት እና ብሔሮች እየበለፀጉ የሚሄዱበት ሁኔታ በመፈጠር ላይ ነው:: ምናልባት ከ90 ከመቶ በላይ ራስ በራስ የማስተዳደር መብቶች ለማረጋገጥ ሲታገል ነበር አሁንም እየታገለ ነው፡፡  የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመዘውር ማዕከላት የመሬት ጥያቄና የብሔር ብሔረሰቦች መብት የምንለው ለዚህ ነው፡፡
የአፄውም ሆነ የደርግ ሥርዓት የወደቁት እነዚህን መመለስ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ደርግ መሬት ላራሹን አውጆ ጥሩ ተቀባይነት አገኝቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እላይ የተገለፁትን ማለት የመሬት ዋስትናና የመሳሰሉትን ባለመተግበሩ ገበሬው አመፀበት፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ደግሞ በኢትዮጵያ ትቅደም ስም ለመደፍጠጥ ጦርነት በመክፈቱ ልጆችን በመማገዱ የውድቀቱ ምክንያት ሆነ፡፡
የኢሕአዴግ የትንሳኤ ምክንያቶች ደግሞ በእነዚህ ሁለቱ ጥያቄዎች ላይ የያዘው አቋም ነው:: ይሄን ለመፍታት የሚያስችል ቻርተርና ሕገ መንግሥት አዘጋጀ፡፡ መተግበር በመጀመሩም ለ25 ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የሰላም ብርሃን መታየት ጀመረ፡፡ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ የተመሰከረለት ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገት አረጋገጠ:: ነገር ግን የኢትየጵያ ህዝቦች በየጊዜው የሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች ችላ በማለቱ በተለይም በ1993፣ በ1994 በሲዳማ ህዘብ፤ በ1997 እና በ2008ና 2009 በመላ አገሪቱ እንዲያሻሽል የተሰጠው ዕድል በትዕቢት ሊጠቀምበት ስላልቻለና ዞሮ ዞሮ እሱም እንደ ቀደሙት እነዚህን መብቶች በማፈን መፃረር ጀመረ፡፡ በዚህ የተነሳ ወደቀ፤ ሞተ ተቀበረ፡፡
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እስክትሆን ድረስ መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ከእነዚህ ከሁለቱ የሚያልፍ አይሆንም፡፡ የመሬት ነገር ወሳኝ ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ አሁንም ሕይወቱ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው:: አሁንም ሥራ አጥነት የሚመነጨው ከገጠር ነው፡፡ ወጣቱ ከመሬት ጋር ካልተሳሰረ ችግር ይፈጥራል:: ኢንዱስትሪውም እሱን የማስተናገድ አቅም ላይ አልደረሰም:: ስለዚህ እርሻው ግብርናውና መሬት አሁንም ወሳኝ ሆነው ይቀጥላሉ:: ከዚህ አንፃር አሁንም በኢትዮጵያ የመሬት ጥያቄ ወሳኝ መሆኑን አለመረዳት ነው አገሪቱን እያናወጣት ያለው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መብትም በቀጥታ ራስን በራስ ከማስተዳደር፣ በራስ ሀብት ከመጠቀምና ራሱ በመረጠው አካል ከመተዳደር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህቺ አገር የብሔር ብሔረሰቦች የትስስራቸው አገር ናት፡፡ ከዛ አትበልጥም ከዛ አታንስም፡፡ ልዩነት እያላቸው አንድነታቸው በትስስራቸው ይገለፃል:: ሁሉም ዓይነት ትስስር:: ይሄን የሚክዱት ጥቂት ሰዎች እንጂ አብዛኞቹ የሚቀበሉት ጉዳይ ነው፡፡
 አሁንም እንደ ብሔር መደራጀት እንደ ብሔር ራስን በራስ ማስተዳደር እንደ ብሔር የራስ እድል የመወሰን ፍላጎቶች እንዳሉ መሬት ላይ ያለ ተጨባጭ ሃቅ ነው:: ኢሕአዴግ የወደቀበት ዋናው ምክንያት እኮ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ቀስ በቀስ እየጣሰ በመምጣቱ ነው:: በምስለኔ ለማስተዳደር በመሞከሩ ነው፡፡ የመሬት ጥያቄም በተመሳሳይ ለኢንቨስትመንት፣ ከተማ ለማስፋፋት እየተባለ መሬት ያለ በቂ ካሳ ገበሬው እንዲፈናቀል፣ ሕይወቱን ካስተሳሰረበት ያለ ምንም አማራጭ እንዲነጠልና እንዲገፋ መደረጉም ነው የኢሕአዴግ ውድቀት ምክንያት:: ለኢሕአዴግም የትንሳኤውም የውድቀቱም ምክንያት፣ የመሬትና የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ ነው፡፡
የመሬት ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በወቅቱ የነበረውን የመደብ ጥያቄ ወደ ብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ የለወጡት ጥቂት ልሂቃን ናቸው፤ የብሔር ጉዳይ ደግሞ በስሜት ለመነዳት ቅርብ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ ይሄ እንዴት ያዩታል?
ይህቺ አገር እኮ ከ1983 በፊት የነፃ አውጪዎች አገር ነበረች፡፡ የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የሶማሌ፣ የቤኒሻንጉል ወዘተ… የሚሉ በርካታ ነፃ አውጪዎች፣መሳሪያ ይዘው የሚዋጉበት አገር ነበረች፡፡ ያ ለምን ሆነ? የብሔር ትግል እኮ አንዱ የመደብ ትግል መገለጫ ነው:: ለምን እነ ሚኤሶን፣ ኢሕአፓ አላሸነፉም? የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ዓላማ፤ እስተራተጂ ስልት ስላልነበራቸው ነው፡፡ ጀግንነቱ እማ እነሱም አስመስክረው ነበር:: በስሜት መነዳት የሚለው ህዝብን መስደብ ነው፡፡ ህዝብ አይሳሳትም ማለቴ አይደለም:: ነገር ግን 17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሙሉ ወይም 29 ዓመታት የግንባታ ሁኔታ እንደ በግ በስሜት ይነዳ ነበር ማለት ፀረ- ህዝብነት ነው፡፡ ጉዳዩ የጥቂት ልሂቃን  አልነበረም፡፡ የጥቂቶች ቢሆንማ ኖሮ ስኬታማ አይሆንም ነበር፡፡
ፖለቲካው ደግሞ የሚገለፀው በልሂቁ ነው:: ለምሳሌ “አማራ ክልል አማራ ብሄር መሆን አይበጀውም፤ ኢትዮጵያዊነት ነው” የሚል አቋም ነበር የሚራመደው:: በኋላ ግን በአማራነቱ መደራጀት አለበት የሚል ተፈጠረ፡፡ በአማራነት መደራጀት አያስፈልግም የሚለው አስተሳሰብ ደግሞ የአማራ ህዝብን ጎድቶታል፡፡ ሌላው በብሔር ተደራጅቶ ሲታገል አማራው ግን በተበታተነ አኳኋን ነበር፡፡ ነገር ግን ለዚህ የብሄር መብት መረጋገጥ አማራው ታግሎለታል:: እኔ ሰሜን ሸዋ፣ ጎንደር፣ ወሎ ነበርኩ፤ ደርግ ገንጣይ አስገንጣይ እያለ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛብን ሕዝቡ ግን የምንታገልለትን አላማ ተረድቶ ሲደግፈንና አብሮን ሲታገል ነበር:: አማራው ባይደግፈን አዲስ አበባ አንገባም ነበር፡፡ እንዲያውም አብሮን ጋሻ ሆኖ ነው የታገለው፡፡ በደቡብም በኦሮሚያም ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችም እንደዚያው ነው፡፡
የብሔር ብሔረሰብ መብት ደግሞ እኛ አገር ብቻ አይደለም ያለው፤ አውሮፓም ሌላውም ጋ አለ፡፡ ለኛ አሁን የሚያስፈልገው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ሳያወላዱ ማክበር ነው:: የብሔር ብሔረሰቦች መብት ሲከበር ነው በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተሰመረተች ጠንካራዋን ኢትዮጵያ ማስቀጠል የሚቻለው:: ብሔሮች መብታቸው የበለጠ ሲረጋገጥ ነው ኢትዮጵያዊነት እየተጠናከረ የሚሄደው፡፡ እኛ ኢትዮጵያ መስላ የምትታየን የሀበሻ አገር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ትክክል አይደለም:: ይህቺ አገር የኩሽም የሌላውም አገር ነች፤ ይሄን ነው መረዳት የሚያስፈልገው:: ስለዚህ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት ሰጪና ነሺነት ቀርቶ የበለጠ የብሔሮች ትስስር የጐለበተባት ጠንካራዋ ኢትዮጵያን መፍጠሩና አንድነትን ማጠናከሩ ነው የሚበጀው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ለውጡ እየተጓዘበት ያለው መንገድስ ከዚህ አንጻር በእርስዎ ምልከታ ምን ይመስላል?
ዋነኛ መገምገሚያችን አሁንም የብሔር ብሔረሰቦች መብት አከባበር እየተጠናከረ ነው ወይስ ወደ ኋላ እየተመለሰ ነው፤ የመሬት ጥያቄስ እየተመለሰ ነው? የሚለው ነው፡፡ ኦሮሚያና አማራን ማአከል ያደረገው ዓመፅና ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያየ መንገድ ባደረጉት ተጋድሎ በመመቻቸቱ ነው አሁን ያለው አመራር ስልጣን ላይ የተቆናጠጠው፡፡   ለዚህ ለውጥ ምክንያት የሆኑ ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ምክንያት ቢኖሩም ዋናዎቹ ግን አሁንም የመሬትና የብሔረ ብሔረሰቦች መብት መሰረት ያደረገ ነበር፡፡ አሁን ይሄ አመራር ይህን ጥያቄ እየመለሰ ነው? እነዚህን መብቶች እያረጋገጠ ነው? ይሄ መንግሥት ለኢሕአዴግ ውድቀት ምክንያት የሆነን ከመሬት ጋር የተያያዘ ፖሊሲና አሰራር እያሻሻለ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ነው የሚነሳው፡፡
ሁላችንም እንዳስተዋልነው አመራሩ በመጀመሪያ 6 ወራት ብዙዎች ተስፋ ያደረጉበትን እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነው:: ጥሩ ተስፋ አሳይቶ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሁለቱንም የመደፍጠጥ አቅጣጫ ነው እየተከተለ የመጣው፡፡ ገበሬውን ማዕከል ያደረገ ሳይሆን ጥቂቶችን ያማከለ ሥራ ነው እያከናወነ ያለው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን በተመለከተ ደግሞ ከኢሕአዴግም በባሰ ሁኔታ ነው እየተደፈጠጠ ያለው፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች መብት ስለመደፍጠጡ ማስረጃዎ ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ስለ ሕገ መንግሥቱ ያለው አመለካከት ነው፡፡ አንዳንዴ ሕገ መንግሥቱ መቀየር አለበት የሚል ነገር ይነሳል፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም በነዚህ ጥያቄዎች ግልጽነት የሌለው እና የተምታታ የኋልዮሽ ጉዞ ነው:: ሁለተኛ ማሳያው ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በህዝቡ ዘንድ ከ2010 በፊት ከነበረው ኦህዴድ የተሻለ ተቀባይነት አለው? በኦሮሚያ አንዳንድ ዞኖች ያለው ኮማንድ ፖስት ሕገ-መንግሰታዊ ነው? አካሄዱ ግልፅነት እና ተጠያቂነት አለው? በደቡብ ክልል ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችስ ጉዳይስ? ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ በርካቶች እያቀረቡ ነው፡፡ ሲዳማ ክልል ጥያቄ ሲያቀርብ ብዙ ችግር ተከስቷል፤ የሰው ሕይወት ጠፍቷል:: እንደዚያም ሆኖ ሕዝበ ውሳኔው ተደርጎ 98 በመቶ ክልል መሆንን መርጧል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ክልል አልሆነም፡፡ ሌሎች ዘጠኝ ዞኖች ክልል እንሁን ብለዋል፡፡ ነገር ግን ለእነዚህ በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ ጥናት ይጠና ነው የተባለው፡፡ መሆን የነበረበት መብታችሁ ነው ተብሎ ጥያቄያቸውን በሕገ መንግሥቱ መሰረት መመለስ ነው፡፡
ለምሳሌ ወላይታ “ክልል ልሁን” ሲል ከሱ በላይ እኛ እናውቃለን በሚል አይጠቅምም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ይጠቅመኛል አይጠቅመኝም የሚለውን ሕዝቡ ነው መመለስ ያለበት መንግስት ህዝቡ እውቀት መሰረት እና ነፃነት በተላበሰ መልኩ እንዲከናወን ማመቻቸት ነው ዋናው ስራው መሆን ያለበት:: የብሔሮች መብት ሲረጋገጥ ነው ኢትዮጵያ ተጠናክራ የምትቀጥለው፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜትም እየዳበረ የሚሄደው፡፡ ሌላው ማሳያ በሱማሌ ክልል የተፈፀመው ነው:: የክቡር አቶ ሙስጠፌ ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ ሕዝቡን ማዕከል ያደረገ አልነበረም፤ ኢሕአዴግን ለውድቀት ያበቃው አንዱ ጉዳይ “እኛ የማናውቃቸውን ምስለኔዎች አንፈልግም” የሚል ተቃውሞ ነበር:: አሁንም ምስለኔ መሾም ቀጥሏል:: የአማራና አፋር መስተዳደሮች እንዴት ነው የተቋቋሙት? ለትግራይም ብልፅግና የሚባል መላክ ተጀምሯል፡፡ እነዚህ አካሄዶች አደገኛ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥትንም መጣስ ነው፡፡
ሌላው ማሳያ ምርጫ እንዳይካሄድ ማድረግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ባይችልም እንኳ በየአምስት አመቱ ግንቦት ላይ ምርጫ ሳያደርግ አልፎ አያውቅም ነበር፡፡
ምርጫው የተራዘመው በኮሮና ወረርሽኝ አይደለም እንዴ?
ኮሮና የመጣው እኮ አሁን ነው፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ለምንድን ነው ግንቦት ወር ላይ ማካሄድ ያልተቻለው፡፡ የቦርድ ሊቀ-መንበር ለመመረጥ ወራቶች፤ የቦርድ አባለት ለመሰየም መጓተት፤ የምርጫ አዋጅ ለመደንገግ ብዙ ጊዜ ነው የፈጀው ግን ለምን? 2010 የግርግር ዓመት ብንለው 2011 ዝግጅቱ ቢጀመር እንዴት አይደርስም:: ስልጣን ለማራዘም ሕገ-መንግስቱን ለመተርጎም በአንድ ወር አካባቢ የታየውን ሩጫ እስኪ አወዳድረው? ምርጫ ለማካሄድ ፍላጎት መኖሩን አጠራጣሪ ያደርገዋል:: ግንቦት ላይ ማካሄድ ይቻል ነበር:: ይሄ ይሁን ብለን እንለፈውና ነሐሴ ላይ ደግሞ ምርጫው እንዳይካሄድ የሚያደርግ ሳይንሳዊ ጥናት መች ቀረበ?  ዝም ብሎ ነው ምርጫውን ማካሄድ አይቻልም የተባለው:: ምርጫውን ማካሄድ አይቻልም ከተባለ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አግባብ ነበር መሄድ የሚገባው፡፡ ሕገ መንግሥታችን በመግባባት ላይ የተመሰረተ (consensus democracy)መንፈስ ነው ያለው:: ከመግቢያው ጀምሮ አንቀፆቹ የተዋቀሩት በዚያ መንገድ ነው፡፡ ይህ በሆነበት እንዲህ ያለ ችግር ሲያጋጥም ተቀባይነት ያላቸው ፓርቲዎች ተሰብስበው ተወያይተውና ተስማምተው ነው ቀጣዩን ሁኔታ ሊወስኑ ይገባ የነበረው::  እነ ኦፌኮና ኦነግ ያመጡት አቃፊ መንግስት የመመስረት አካሄድ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይሄ ሲሆን ቢያንስ ቅቡል የሆነ መንግሥት ኖሮ አገሪቷን ለምርጫ ማዘጋጀት ይቻል ነበር፡፡ ሕዝብ “ይሄ የኔ መንግሥት ነው” ሊለው ይገባል:: ብሄር ብሄረሰቦች የኔ መንግሥት ነው ብለው ሊያምኑት የሚገባ መንግሥት ነው መፈጠር ያለበት፡፡ “ይሄ መንግሥት የኔ አይደለም” የሚል እሳቤ በብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ እየሰፋ ከሄደ ሁኔታው አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡
በሌላ በኩል ህወኃት ለብቻው በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የእርስዎ አቋም ምንድነው?
ትግራይ ምርጫ ቢያካሂድ ፌደራል መንግሥት የሚጎዳው ነገር አለ? ሌላው ክልልም ያንን ቢያደርግ ፌደራል የሚጎዳው ነገር አለ? ትግራይ ምርጫ ማድረጉ ሌላውን ክልል የሚጎዳው ነገር አለ? የለም፡፡ ምርጫ የማድረግ ያለማድረግ ሙሉ መብት ደግሞ የሕዝብ ነው፡፡ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መብት ነው፡፡ በትግራይም በምርጫ ጉዳይ የመወሰን ሙሉ መብቱ የትግራይ ሕዝብ ነው፡፡ ህወሓትም ሆነ የፌደራል መንግሥት የመመረጥ መምረጥ መብትን ለትግራይ ሕዝብ መስጠት አይችሉም፡፡ ሕዝብ ነው የበላይ፡፡ የፌደራል መንግሥት ማድረግ የነበረበት ምርጫ ለማካሄድ ማመቻቸት ነው፡፡  እጁ ላይ አሳማኝ ጥናት ካለው ሕዝቡ እንዳይጎዳ ከትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መወያየት እና መግባባት ነው:: ምርጫ የህዝብ ሉዓላዊ መግለጫ ነው፡፡ የፌዴራል ይሁን የትግራይ መንግሥት ለህዝብ በችሮታ የሚሰጠው መብት አይደለም፡፡ ማንም ተምኖ ይገባሃል አይገባህም ብሎ የሚሰጠው አይደለም፡፡
የትግራይ ሕዝብ በዚህ ሰዓት ምርጫ እንዲካሄድ ይፈልጋል ብለው ያስባሉ?
እኔ ባለኝ ግንኙነት ባደረኩት ዳሰሳ፣ አብዛኛው ሕዝብ ምርጫ መደረግ አለበት የሚል አቋም  ያለው ይመስለኛል፡፡ አብዛኞቹ ፓርቲዎችም ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል አቋም ነው ያላቸው፡፡ ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያኔና ሌሎችም ፍላጎቱ አላቸው:: ነገር ግን በዋናነት ምርጫው እንዲካሄድ እየገፋ ያለው ሕዝቡ ነው:: ስለዚህ የሕዝቡን መብት መጠበቅ ይገባል:: ምንም ሳይንሳዊ ጥናት ባልቀረበበትና ሕዝብ ባላመነበት ሁኔታ ምርጫ አይካሄድም ማለት ውጤቱ አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ በኔ ግምት፤ በፌደራል ደረጃም ምርጫን ማካሄድ የማያስችል ሳይንሳዊ ጥናት አላየሁም፡፡ ነገር ግን ፓርቲዎች በሙሉ እንዲካሄድ አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ ይሄን አክብሮ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በትግራይ ግን ሕዝቡም አብዛኛው ፓርቲም ምርጫ እንዲካሄድ ይፈልጋል፡፡ መረዳት ያለብን ፌደራል ስልጣን እንጂ በሕዝብ ላይ የመወሰን መብት የለውም፤ ስልጣን የሰጡት ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው:: ለእነሱ ፍላጎት ነው መገዛት ያለበት፡፡ ምርጫ ቦርድ ደግሞ የሕዝብን መብት የመደፍጠጥ ስልጣንም መብትም የለውም፡፡ በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ አልተቻለም በማለቱ እኮ ሰዎች ሞተዋል፡፡
ይሄ በትግራይ ምርጫ ካልተካሄደ የሚለው የህወኃት አቋም ነው እንጂ የሕዝቡ አይደለም የሚሉ ሀሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ እርስዎ ደግሞ ሕዝቡ ፍላጎት አለው፤ በራሴ መንገድ አረጋግጫለሁ ይላሉ... እንዴት አረጋገጡ?
እኔ ሁኔታውን እከታተላለሁ:: እንደልኩት ዳሰሳ እንጂ ጠለቅ ያለ ጥናት አድርጌ አይደለም::  በኔ ግምት የትግራይ ሕዝብ በአብዛኛው በዶ/ር ዐቢይ በሚመራው ፓርቲ እምነት አጥቷል::  ከሻዕቢያ ጋር ተባብሮ ትግራይን ለማዳከም እየተሰራ ነው የሚል አመለካከት ሰፊ ነው:: አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሄ አስተሳሰብ ነው ያላቸው::  ህወሓት እንደ ገዢ  ፓርቲ ግዴታው ኮንትራቱ ሲያልቅ ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ ነው፡፡ መነሻው ምንም ይሁን ምን ምርጫ ይደረግ ማለቱ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ አሁን ችግር እየፈጠሩ ያሉት በሁሉም ቦታ ያሉ ጽንፈኞች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ሕዝብ ላይ በጽንፈኞች መንገድ መዘጋቱ ለትግራይ ሕዝብ ሞት እንደመፍረድ ነበር:: የፌዴራል መንግሰት ዝምታ የወንጀሉ ተባባሪ ያደርገዋል:: የመንግስት ሚዲያዎች፤ እነ ዋልታና ፋና ከሰሞኑ “ፈንቅል” እያሉ ሰላማዊ ሰልፍ አድርግና ህወሓትን ጣል ማለታቸው በኮሮና ወቅት ለሞት መጋበዝ ነው፡፡ ከአራት ሰው በላይ እንዳይሰበሰብ በተከለከለበት አገር ትግራይ ላይ ሲደርስ እንዲህ ማለታቸው በሕዝቡ ላይ እየፈረዱ ነው ማለት ነው፡፡ አመፅና ተቃውሞ በዚህ ሰዓት መቀስቀስ ሕዝቡን ወደ ሞት መምራት፣ በሕዝቡ ላይ ሞት መፍረድ ነው::
ፈለግነውም አልፈለግነው ህወሓት በአሁን ሰዓት ቅቡልነት አለው፡፡ ከውስጥ የሚገኘው ቅቡልነት እየተሸረሸረ ቢሆንም ከመሃል አገር ከሚሰዘነረው ጥቃት ለመከላከል በትግራይነት መንፈስ ነው ከነሁሉ ችግሩ የመቀበል አዝማሚያው ያለው፡፡ (externally induced legitimacy) ይሉታል ፡፡ ህዝቡ ህልውናውን ለማረጋገጥ ሲል ከህወሓት ጋር ያለን ችግር ይቆይ አሁን በጋራ የመጣብንን አደጋ መመከት አለብን ብሎ አቋም የያዘው፡፡
ትግራይ ውስጥ በተለይ ከ2007 ጀምሮ አካባቢ ከፍተኛ የለውጥ ፍለጎትና እንቅስቃሴ ነበር፡፡ መሪ አጥቶ በፈለገው መንገድ ለውጥ ለማምጣት አልተቻለም:: ክቡር ጠ/ሚኒሰትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እንደ መሪ ትግራይን ሲጎበኙ የነበረው ከፍተኛ ድጋፍ በለውጥ አመራር ያሻግሩናል ከሚል ነበር፡፡ በተቃራኒ አንዳንድ የህወሓት አመራሮችን 27 ዓመት ሙሉ ዞር ብላችሁ ሳታዩን እንዴት አሁን መጣችሁ የሚሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁንም በትግራይ ትልቅ የለውጥ ፍላጎት አለ፡፡ በህወሓት ውስጥ ትግል አለ፡፡ በኔ አመለካከት ለተራማጆቹ እንቅፋት እየሆነ ለአድሃሪያን በዶዘር ምሽግ እየቆፈረ ያለው በመሃል አገር ያለው ፀረ-ትግራይ ፖለቲካ ነው፡፡ ፀረ-ትግራይ ፖለቲካ ደግሞ ፀረ- ኢትዮጵያ ነው፡፡ ድሮ ህወሓት ነበር ሕዝቡን የሚመራው፡፡ አሁን ሕዝቡ ነው በትግራዋይነት ህወሓትን እየመራው ያለው፡፡ ስለዚህ ህወሓት አሁን ተወደደም ተጠላ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አለው፡፡
ህወሓት አሁን ምርጫው ካልተካሄደ የሚለው ይሄን አጋጣሚ ለመጠቀም ይሆን?
ሊሆን ይችላል፤ ግን ይሄ የሚያረጋግጠው ህወሓት በአሁኑ ወቅት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ነው፡፡ የሕዝብ መብት የምንለው እኮ የፈለገውን መምረጥን ነው፡፡ ዋናው ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ማረጋገጥ ነው:: እንደ 2007 እንዳይሆን፡፡ የሁሉም ነገር ማዕከል መሆን ያለበት የሕዝብ መብት ነው::
ከውዝግብና ውጥረት መውጣት የሚቻለው እንዴት ነው ብለው ያስባሉ?
ነገርየው በአግባቡ በብስለት ካልተያዘ አደገኛና ለመገመት አስቸጋሪ የሆነ ችግር ነው የሚፈጥረው፡፡ ነገር ግን ማስቀደም የሚገባው አሁንም ውይይትን ነው፡፡ የውይይቱ መነሻና መድረሻ ሊሆን የሚገባው ግን በሕገ መንግስቱ መሰረት የትግራይ ሕዝብ መብት ነው፡፡ ድርድር ማድረግ ነው መፍትሄው፡፡ በሀይል አንበረክካለሁ ከተባለ ግን የሚጫረውን እሳት ማቆም አይቻልም:: እኔ በአሁን ሰዓት ከትግራይም በላይ በኦሮሚያ ያለውን ውጥረት ነው የምፈራው:: ኦሮሚያ ውስጥ አሁንም አደገኛ ነገር ነው ያለው:: ደቡብም እንደዚያው በክልል ጥያቄ የተወጠረና በኮማንድ ፖስት ስር ያለ ነው፡፡ ኦሮሚያና ደቡብ ክልል ያለው ሁኔታ ምን ችግር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማንም መገመት አይችልም፡፡ትግራይ ላይ እሳት መጫር ኦሮሚያ ላይ ካለው ውጥረት ጋር ተደማምሮ ሊፈጥር የሚችለው ችግር እንዲህ በቀላሉ ላይቆም ይችላል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ራሱን መከላከል ፍትሃዊ ስለሚሆን አይሸነፍም፡፡
በትግራይ ‹‹ፈንቅል›› የሚል እንቅስቃሴ አለ በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ያሎት ምልከታ ምንድን ነው? ትግራይ ውስጥ ጭቆና አለ የሚል እምነት አለዎት?
ኢትዮጵያ ውስጥ ጭቆና የሌለበት ክልል አለ እንዴ? እንደሌሎች ክልሎች ሁሉ  እዚያም ጭቆና አለ፡፡ እንደ ሌላው ክልል ሁሉ እዚያም መዥገሮች እያስቸገሩ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ከሁለት ሦስት ዓመት ከነበረው የተሻለ ቢሆንም አሁንም መሰረታዊ ለውጥ አልተረጋገጠም:: ለዛ ነው ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ክቡር ዶ/ር ደብረፅዮንን መሰረታዊ ሪፎርም እንዲያደርጉ “አይዞኻ ናይና” (አይዞህ የኛ እንደማለት ነው) በከፍተኛ ደረጃ የደገፋቸው ሆኖም በኔ አመለካከት ከየትኛውም ክልል በተሻለ የሕዝብ ድጋፍ ያለው የትግራይ መንግሥት ነው:: በዚያው ልክ አንፃራዊ ሰላምም ያለው ትግራይ ውስጥ ነው፡፡
እነዚህ አዲስ አባባ ሆነው ሕዝቡ በጭቆና ውስጥ ነው ያለው የሚሉት ከፀረ- ትግራይ ፕሮፖጋንዳ እና ተግባር ይቆጠቡና አሁን ባለው ንቃት  ትግራይ ውስጥ ያሉትን መዥገሮችን እንዴት በጣጥሶ እንደሚያሸንፋቸው ለማየት በበቃን ነበር:: ‹‹ፈንቅል›› የሚል እንቅስቃሴ አዲስ አባባ ውስጥ በነ ዋልታና ባለ ገንዘብ እና ስልጣን ያላቸው ጌቶቻቸው የተፈበረከ የሃሰት ድራማ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ የትግራይን ህዝብ እርስ በርስ ለማዋጋት የተፈጠረ ዘንዶ የሚባል ሰራዊት ነበር:: የእውነት ሰራዊት ስለነበር ብዙ እንቅፋት ፈጠረ ግን ተሸነፈ፡፡ “ፈንቅል” ግን በፊልም የምናው አስቂኝ ድራማ ነው፡፡ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ፡፡
የፈንቅል እንቅስቃሴ ወዴት ሊያመራ ምን ደረጃ ሊደርስ ይችላል?
የሌለ ነገር የት ይደርሳል ብለህ ነው። የትም፡፡ ነገር ግን የትግራይ ህዝብ ለዲሞክራሲ፤ ለፍትሕ ቀጣይነት ባለው መንገድ የሚያደርገውን ትግል የፈንቅል እንቅስቃሴ ያደናቅፋል፡፡ ምክንያቱም ትኩረቱ ትግራይ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ሙስናን ከመታገል ይልቅ በውጭ ጠላቶች እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ትግራይ ውስጥ ከሚራመዱ ሀሳቦች መካከል መገንጠል አንዱ ነው ይሄ እውን የሚሆንበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል እምነት አሎት?
በመጀመሪያ ደረጃ በፌዴራል መንግስት ጥቃት እየደረሰብኝ ነው የሚል ህዝብና ሊህቅ ሁሉም ዓይነት መብቶቹ የራሱ ነፃ ሃገር የመመስረት ጭምር ማሰላሰሉ ባህሪያዊ ይመስለኛል። ጥያቄው በመነሳቱ መሸበር/ መደናገጥ የለብንም፡፡ በሕገ-መንግስት እውቅና ያገኘ የህዝብ ተፈጥሮአዊ መብት ነውና:: መሰረታዊ ችግሩ ከትግራይ ውጭ ያለው የፅንፈኞች ችግር ብቻ ነው እንዴ? በትግራይ ውስጥ ያለው ፀረ- ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እና ፖለቲካዊ ሙሱናስ? ነፃ ሃገር መመስረት ብቸኛው አማራጭ ነው ወይ? በኢትዮጵያ አገር ምስረታ የትግራይ ህዝብ ሚና መሰረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን እሴቶቹና ጥቅሞቹ የበለጠ የሚረጋገጡት በዴሞክረሲያዊ አንድነት አይደለም እንዴ? የመሃል አገር የፅንፈኞች ጥቃት ሲቀዘቅዝ እነዚህ ጥያቄዎች በሰከነ መንገድ ለመወያየት ዕድል ይመቻቻል፡፡ አንድነታችን ለማጠናከር እንደ ትልቅ እድል መታየት አለበት:: ታሪክ መሰረት ያደረገ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ብቻ ሳይሆን፤ ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤ ደህንነት ዴፕሎማሲ ወ.ዘተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እጅጉን የሚጠነክርበት እድል ከፍተኛ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ዋነኛው ወሳኝ ሕዝቡ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ምን እንደሚወስን የሚታወቅ ይመስለኛል፡፡  
በቀጣይ ከትግራይ ጋር ያለውም ሆነ የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር እንዴት ሊፈታ ይችላል?
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ ብዙ አደጋ አለ። በኔ አመለካከት በትግራይ ካለው ይልቅ በኦሮሚያ፣ በአማራ ደቡብ፣ ሶማሌ ያለው ያሳስበኛል። ስለዚህ ሕገ መንግስቱና የሕዝቡን መብት ማዕከል ያደረገ ድርድር በፖለቲካ ሀይሎች መካከል ያስፈልጋል። የፖለቲካ ሀይሎች ተደራድርው አቃፊ መንግሥት በመመስረት ብሎም ኮቪድ 19 ጦርነት አሸንፈው ነፃን ፍትሓዊ ምርጫ በማድረግ ሽግግሩ ፈር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ በትግራይ ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ ምርጫ እንዲካሄድ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መደገፍ አለባቸው፡፡ የፌዴራል መንግስት ከእልህ እና ከትዕቢት ወጥቶ በሰከነ መንገድ በሕገ መንግስቱ መሰረት የመተባበር ግደታ አለበት፡፡ ከኢህአዴግ ይማር፡፡ 2008ና 2009 ከህዝቦች ጋር መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ ቢደራደር ኖር ሞት ሳይሆን ትንሳኤ ነበር የሚሆነው፡፡
የትግራይ መንግስትና ፓርቲዎችም ከፌዴራል መንግስትና ከህዝቦች ጋር ሰላም እንዳይኖር ቀን ሌሊት እየሰሩ ያሉትን ፅንፈኞች አስወግደው በሰከነ ሁኔታ ሕገ መንግስቱና የህዝብ መብት ማእከል ባደረገ መልኩ ለመደራደር ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡



Read 4790 times