Saturday, 13 June 2020 12:19

ከፖለቲከኞች ድርሳን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       --የበረሃ ሕልመኞች የጎሣ ታሪክን እያወቁ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የጎሣ ሁኔታ እያዩ፣ የቀየስነውና የዘረጋነው የጎሣ ሥርዓት ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ትክክል ነው፣ ወደፊትም አጠናክረን እንቀጥልበታለን እያሉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅርብ ታሪኩ የአመራር ግትርነት ምን ያህል ችግር እንዳስከተለ ያውቃል:: ለምሳሌ ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ የነበራቸው ምኞት ቀና ቢሆንም፣ የአስተዳደራቸው ግትርነት በሕዝቡና በራሳቸውም ላይ ያስከተለው ጉዳት ምን ያህል እንደነበር ይታወቃል፡፡
አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ጊዜ ቆራጭ ፈላጭ ሥልጣናቸውን አላስነካም፣ አላስደፍርም ብለው በአንድ በኩል ዕድሜ እስኪጫናቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደርግ ሕልመኞች ከሥልጣን ወንበራቸው ላይ ጎትተው እስከሚወስዷቸው ድረስ የሙጥኝ ብለው ቆዩ፡፡ በደርግ ሕልመኞች ጊዜም ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ በአንድነትና በሀገር ፍቅር ስም፣ በግትርነት፣ በእልክና በጭካኔ ስሜት ምክንያት በወቅቱ ባለመወሰዳቸው ሀገሪቱ የደረሰባት ምስቅልቅልና መሪውም ለስደት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የበረሃ ሕልመኞች አዲስና ግትር አቋም ይዘው መጡ፡፡ አገሪቱ በጎሣ ሥርዓት ትመራለች፤ ምድራዊ አከላለልዋም በጎሣ ላይ የተመሠረተ ይሆናል በማለት ይህን አቋማቸውን ለሃያ ሰባት ዓመታት ነክሰው ይዘዋል፡፡ ይህ ግትርነት የሰፊው ሕዝብ ባህሪ አይደለም፡፡ የተሳሳተ አመራር ባህሪ ነው፡፡
እኛ ዜጎች በተሳሳተ አመራር በጎሣ መስመር እንድንኮለኮል ተደረግን፡፡ በየቀበሌያችን እንደ አዲስ በየጎሣችን መመዝገብ አለባችሁ ተባልን:: እያንዳንዳችን ጎሣችንን የሚያመለክት የቀበሌ መታወቂያ በየደረት ኪሳችንና በየቦርሳችን እንድንይዝ ተደረግን:: ለምሳሌ እኔ “ትግሬ” ተብዬ ተመዘገብኩ:: ለምን እንደዚህ ይሆናል? መመዝገብ ካለብኝ “ኢትዮጵያዊ” በሚል ነው ብዬ ተከራከርኩ:: በወቅቱ የነበረው ወጣት ታጋይ የምዝገባ ኃላፊ “ግዴታ ነው” አለኝ፤ ቁጣን ባዘለ አነጋገር፡፡ አተኩሮ እየተመለከተኝ፣ “በትግሬነትዎ አይኮሩም እንዴ?” አለኝ፡፡ ለጊዜ የምለው ነገር ቸግሮኝ፣ “የመኩራትና ያለመኩራት ጉዳይ አይደለም...” ብዬ ዝም አልኩ፡፡ ባለቤቴ “አማራ” ተባለች፡፡ ልጄም በአባቷ “ትግሬ” ነች ተባለች፡፡
የጎሣ ፖለቲካ ሀገርን ለከፋፍለህ ግዛ አሰራር፣ ለሙስና መስፋፋት፣ ብቃት ለሌለው አመራር ለሙስና እና ለሌሎች ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ችግሮች በመዳረግ አንድነትን እንደሚያዳክም ሕዝብ ከልምድ ያውቀዋል:: በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተካሄዱ አያሌ ጥናቶችም ይህን ያረጋግጣሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ሌላ ለምሳሌ የናይጄሪያን ልምድ በአጭሩ እንመልከት፡፡
እንደሚታወቀው የናይጄሪያ መንግሥት ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ሲሆን በውስጡ ከ300 በላይ ጎሳዎች እንዳሉ ይታወቃል:: በጣም ትላልቆቹ ጎሣዎች ዩሩባ፣ ሀውሳ እና ኢግቦ ናቸው፡፡ ሀገሪቱ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1960 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ከሆነች በኋላ የፈጠረችው የፖለቲካ ሥርዓት በሦስቱ ዋና ዋና ጎሣዎች ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ 36 ስቴቶች (ክፍለ ሀገሮች/ ክልሎች) አሏት:: ስቴቶቹ ሆን ተብሎ አንዳቸውም የጎሣ ስም እንዳይኖራቸው በሕግ ተደንግጓል:: ስሞቻቸው ሁሉ ከታወቁ ከተሞች፣ ወንዞች፣ ከፍተኛ ቦታዎችና ሌሎች የታወቁ የአካባቢ የተፈጥሮና የታሪክ ምልክቶች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ የጎሣ ፖለቲካ በናይጄሪያ ውስጥ ስለሚፈጥረው ችግር ዕውቀትና ልምድ የሚያካፍሉን ናይጄሪያዊ ምሁር ዲ. ቲ. ኦርጂያኮ ናቸው፡፡ ጽሑፋቸው “ ” የሚል ነው፡፡
እንደሚታወቀው የበረሃ ሕልመኞች በ1983 አዲስ አበባ በገቡ በዓመቱ አካባቢ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ ቅድመ ዝግጅት ይደረግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ቅድመ ዝግጅት በ1984 በአዲስ አበባ ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ የሕግ ጥናት ሲምፖዚየም ማካሄድ ነበር:: ናይጄሪያዊ ምሁሩ የጥናት ጽሑፋቸውን አዲስ አበባ ያቀረቡት በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ የጥናቱ ትኩረት በጎሣ በተከለለ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማደራጀት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ለማመልከት ነው፡፡ እንዲህ በማለት ይጀምራሉ፡-
 “ዋናዎቹ ሦስት የፖለቲካ ድርጅቶች ከሞላ ጎደል በጎሣ ክልል ላይ የተመሰረቱ ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ላይ ከባድ ችግሮችን ፈጥሯል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ከግለሰቡ ዕምነት የመነጨ በመሆን ፈንታ በመጣበት አካባቢ ላይ የተመሰረተ መሆን ከሞላ ጎደል ግዴታ ሆነ፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ውድድር የጎሣ ክልል ውድድር እየሆነ መጣ:: ውሳኔዎችም ሁልጊዜ የሚወሰኑት ብሔራዊ ግቦችን በሚጎዳ መልኩ የጎሣ ጥቅሞችን ለማርካት ብቻ ሆነ፡፡”
ናይጄሪያ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ሪፐብሊኳን በየጊዜው አሻሽላለች፡፡ የመጀመሪያው ሪፐብሊክ በጎሣ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት በተፈጠረ ችግር ከፈረሰ ከ14 ዓመታት በኋላ (እ.ኤ.አ በ1979) ሁለተኛው ሪፐብሊክ ተመሰረተ፡፡ ዲ. ቲ. ኦርጂያኮ ሪፐብሊኩን መለስ ብለው ሲያዩ የሚከተለውን ይላሉ፡-
“አዲስ ሕገ መንግሥት ከጨበጥንና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ከዘረጋን በኋላ... በሀገራችን አዲስ የፖለቲካ ጎሕ ቀደደ፤ ናይጄሪያ ከ30 ወራት አሰቃቂ  [የቢያፍራ] የእርስ በርስ ቀውስና ጦርነት ወጥታ ወደ ጠንካራና የተባበረች አገር ተሸጋገረች የሚል ዕምነት ነበረን፡፡ ሆኖም ስህተታችንን /የፓርቲዎች በጎሣ ክልል ላይ የተመሰረቱ መሆን አደገኛነቱን መዘንጋታችንን/ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልወሰደብንም፡፡ የመጀመሪያው ስህተታችን የመጀመሪያው ሪፐብሊክ ዓይነት የፓርቲ ሥርዓት /በጎሣ ላይ የተመሰረተ/ እንዲቀጥል ማድረጋችን ነው፡፡”
ካለፈው ልምዳቸው በመማር ናይጄሪያውያኖች ሦስተኛውን ሪፐብሊካቸውን ለመመሥረት ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ የክልል አወሳሰንንና የፓርቲ አመሠራረትን በተመለከተ ምን ማሻሻያዎችን አደረጉ? በመጀመሪያ የጎሣ ፌደራሊዝምን በሕግ አንቅረው አስወገዱ:: ዲ. ቲ. ኦርጂያኮ “ከጎሣ ፈደራሊዝም ለማምለጥ ምን አደረግን?” ብለው ይጠይቁና መልሱን እንደሚከተለው ይሰጣሉ፡-
“በጎሣ ላይ የተመሠረተ ፈዴሬሽን የመፍጠሩ ሁኔታ ሁልጊዜ አጓጊ ነው፡፡ በዚህ አጓጊ ሁኔታ ብንማረክ ኖሮ አሁን ያሉን 30 [በኋላ 36 የሆኑ] ክፍለ ሀገሮች ሳይሆን ይኸኔ ከ200 በላይ ክልሎችን መሥርተን ነበር፡፡ ናይጄሪያ ይህን ችግር የፈታችው በቋንቋ ቡድኖች ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የራስን ፍላጎት በሟሟላትና ራስ መቻል ላይ የተመሠረቱ ስቴቶችን በማቋቋም ነው፡፡”
ከላይ የተጠቀሱትን ሀሳቦች ያካተተው ጥናት የቀረበው የዛሬ 26 ዓመት በ1984 ነው:: ጥናቱ አዲስ አበባ በነበረው ሲምፖዚየም ላይ ሲቀርብ የበረሃ ሕልመኞች የአቅራቢውን ንግግር ሳይሰሙ፣ ጽሑፉን ሳያነቡ፣ ውይይቱንም፣ ክርክሩንም ሳይከታተሉና ምክርም ሳያገኙ አልቀሩም፡፡ ምክር አግኝተው ከነበረ ግን እንዳልተጠቀሙበት አሁን ግልጽ ሆኗል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ከቀረበ ከ26 ዓመታት በኋላ አደሌኬ አደግባሚ እና ቻርለስ ኡቼ (Adeleke Adeghbami እና I.N. Charles Uche) የተባሉ ሌሎች ናይጄሪያውያን ምሁራን፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የጎሣ ፖለቲካን በተመለከተ “Ethnicity and Ethnic Politics: An Impediment to Political Development in Nigeria” (“ጎሣና የጎሣ ፖለቲካ፣ ለናይጄሪያ የልማት ዕድገት እንቅፋት”) በሚል ርዕስ በጋራ አንድ ጥናት አቅርበዋል፡፡
ምሁራኑ የጎሣ ፖለቲካ የማያባራ የእርስ በርስ ጥላቻ እንደሚያስከትል፣ ሙስናን ለማስፋፋት እንደሚያመች፣ የሀገር ፖለቲካና ኢኮኖሚ እድገትን እንደሚገታ፣ ሕዝብን ለድህነት እንደሚዳርግ፣ ሰላም እንደሚነሳና በአጠቃላይ የአገር ራስ ምታት እንደሆነ በድጋሚ ይገልጻሉ፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ዘርፈ ብዙ መዘዝ ያለው በመሆኑ እንደ ራሰ ብዙ ደራጎን (hydra-headed monster) ይመስሉታል:: በመቀጠልም በዋናው ጥናታቸው አንድ ንኡስ ክፍል ውስጥ Ethnic Politics in Some African Nationals በሚል ንኡስ ርዕስ የሚከተለውን ይላሉ፡- “እንደ አንጎላ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን ያሉ አገሮች በአስጊ ሁኔታ በጎሳ ፖለቲካ ተዘፍቀዋል፡፡
በመጨረሻም ጥናታቸውን ሲያጠናቅቁ የሰጡት ምክር የሚከተለው ነው፡-
“The study recommended that, Nigeria should imbibe the spirit of oneness and stamp out ethnicity in the conduct of the affairs of the nation, in order to experience national unity and peace which are essential ingredients for the nation’s development, progress, stability and national integration.”
(የናይጄሪያ በውስጥዋ የአንድነት መንፈስን ማስረጽና ጎሰኝነትን ከአሰራር ሥርዓቷ ሥረ መሠረት ውስጥ ማስወገድ አለባት፡፡ ይህንን ማድረግ ያለባት ብሔራዊ አንድነትንና ሰላምን ለማስፈንና በዚህም መንገድ ብሔራዊ እድገትን፣ ልማትን፣ መረጋጋትንና መቀራረብን ለማምጣት ነው)::
የበረሃ ሕልመኞች የጎሣ ፖለቲካን በጓዳቸው፣ በአፍሪካ ጎረቤቶቻቸው፣ በብዙ የቅርብና ሩቅ እሲያ አገሮች (የመን፣ ምያንማር፣ ስሪላንካ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ባንግላዴሽ...) የሰላም ጠንቅ፣ የሰው ሕይወት እልቂትና ስቃይ፣ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ምክንያት መሆኑን እያዩ፣ እየሰሙና እያወቁ እንደ አምልኮ አክርረው በመያዝ በእልህ እየገፉበት ነው፡፡
በሌላ በኩል “ተሳስተናል”፣ “ከስህተታችን ተምረናል”፣ ወዘተ. የሚሉ ቃሎችን እየሰማን ነው፡፡ ብዙ የተሐድሶ ምዕራፎችን አገላብጠናል:: ሆኖም ነገሮች “ዛሬም እንደዚያው” እየሆኑ፣ አሊያም ሲባባሱ ነው እያየን የመጣነው፡፡ የአሁኑ የበረሃ ሕልመኞች ቁርጠኛ የተሐድሶ ዙር፣ ቁርጠኛ ለውጦችን ማምጣት አለበት:: በአሁኑ ጊዜ መምጣት ካለባቸው በርካታ ቁርጠኛ ለውጦች አንዱና ዋናው የጎሣ ፖለቲካቸውን ማስወገድ ነው፡፡ የበረሃ ሕልመኞች በወጣትነት ስሜት፣ በግርድፍ ማርክሲዝም- ሌኒንዝም-ስታሊንዝም፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሀሳብ ተማርከው፣ በቅንነት፣ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል በሚል እምነት፣ የዛሬ 27 ዓመት መጥተው በጎሣ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም በሀገሪቱ ላይ አሰፈኑ::
የናይጄሪያ ምሁራኑ ከአገራቸው ልምድ ተነስተው ከሰጡት ምክር፣ በሌላው ዓለም ዙሪያ ከሚታዩ የጎሣ ግጭቶችና የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ በቅርቡ ካገኘው ልምድና በተደጋጋሚ ከገለፀው በመነሳት የጎሣ ፈደራሊዝም፣ በአገራችን በሕግ እንደመጣ፣ በሕግ መወገድ አለበት፡፡
በጎሣ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ የደም ግንኙነት እንጂ የአዕምሮ ውጤት አይደለም:: አንድ ሰው የጎሳ አባል የሚሆነው አውቆት፣ አምኖበት መርጦትና ወዶት አይደለም፤ ተወልዶበት እንጂ፡፡ ለምን እንዲህ ሆንክ ተብሎ ቢጠየቅም “የተወለድኩበት ነው” ከማለት ያለፈ መልስ አይኖረውም፡፡ አንድነት የሚፈጠረውና የሚጠናከረው በዘር ቆጠራ ሳይሆን በአዕምሮ ፈጠራ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ የሰው ልጅ አንድነትን ለመፍጠር የተገደደው ምክንያታዊ በሆነ ውስጣዊ የአዕምሮ ግፊት ነው፡፡
ዛሬም እንደ አገር አንድነታችንን የምናጠናክረውና ህልውናችንን የምናረጋግጠው በአዕምሮአችን በምንፈጥረው ዕውቀት፣ በብልህነትና በምናዳብረው ባህሪ ነው:: መመራት ያለብን በጎሣ ፖለቲካ ሳይሆን በአዕምሮ ፖለቲካ ነው::---
(በቅርቡ ለንባብ ከበቃው
የዶ/ር ሃይሉ አርአያ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 1213 times