Saturday, 13 June 2020 13:22

ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ለጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፡- እባካችሁ የአዛውንቶቹን ሞት አሳምሩ!

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(3 votes)

             ግንቦት 20
ግንቦት 20 የደርግ አስተዳደር የወደቀበትና ሕወሓት/ኢህአዴግ ሥልጣን የያዘበት ቀን ሆኖ የፊተኛውን መስከረም ሁለትን በመተካት ለአንድ ትውልድ ያህል ሲከበር ቆይቷል። ዕለቱን አስመልክተው ሰሞኑን ቁጭት የተመላበት ትንተና የሰጡት የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን “እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤቱ ሆኖ እያቃጠለው በፍቅር ይዘክረዋል” ብለዋል። እሱን እርግጠኛ ባንሆንም ግንቦት ሃያ በሀገሪቱ ታሪክ ወሳኝ ከሚባሉ ቀናት አንዱ መሆኑ ላይ መስማማት እንችላለን።
ግንቦት 19 ቀን 1983 የደርግ አስተዳደር ተፍረክርኮ ሁሉም እግሬ አውጪኝ የተያያዘበት ወቅት፤ በአመራር ላይ ለነበሩት ደግሞ ከፍተኛ የጭንቀት ጊዜ። ባለሥልጣኖች ከሀገር እንዳይወጡ በደህንነት ሃላፊው ኮሌኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ ክትትል ይደረግባቸው ነበር። በቅርቡ እንደሰማነውም ቤታቸው በደህንነት አባላት የተከበበም ነበሩ። እንደዛም ሆኖ አንዳንዶች ባገኙት መንገድ ለመሽሎክ ሞክረዋል። ኮሎኔል ለገሰ አስፋው ከገበሬ ጋር ተመሳስለው ለመውጣት ሲሞክሩ ተይዘዋል። በጋሻው አታላይ ጂቡቲ ቢገቡም ተላልፈው ተሰጥተዋል። አምባሳደር ካሣ ከበደ ደግሞ በግርግሩ ወቅት ተጀምሮ በነበረው ኢትዮጵያውያን ይሁዶችን ወደ እስራኤል ካጓጓዘው ‘ዘመቻ ሰለሞን’ ጋር ተቀላቅለው እልም ብለዋል። ከሀገር መውጣት ያልቻሉት አንድም በቤታቸው ተቀምጠው የመጣውን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል። ሌሎች ደግሞ እስከ መጨረሻው እጅ ላለመስጠት ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ሞክረዋል። በዚህ ረገድ እንደ ጠ/ሚኒስትሩ ተስፋዬ ዲንቃና ዶ/ር አሻግሬ ይግለጡ እድለኛ የለም። ለማይካሄድ ድርድር ወደ ለንደን አቅንተዋል። በዛው ወደ አሜሪካ!
እንግዲህ የተወሰኑት ባለሥልጣኖች መጨረሻቸውን አስልተው ይሁን ምን ባይታወቅም በዛ ቀውጢ ሰዓት ልክ ነው ያሉትን የራሳቸውን ውሳኔ ወስነዋል። በጣሊያን ኤምባሲ ጥገኝነት መጠየቅ ከዚህ ውስጥ አንዱ ነው። እንደ ቀልድ በተገባበት ኤምባሲ ግን በሕይወት መውጣት አስቸጋሪ እየሆነ ነው።
ጥላ ከለላ
የፖለቲካ አለመረጋጋትም ሆነ ሌሎች ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በሚፈጥሯቸው አጣብቂኞች ምክንያት ኤምባሲዎችንም ሆነ ሌሎች የዲፕሎማሲ ማዕከላትን ከለላ ማድረግ አዲስ ነገር አይደለም። በዘመናዊ ታሪክ ግን የሀገራችንን ባለሥልጣኖች ያህል ረዥም ጊዜ የቆየ መኖሩ ያጠራጥራል። በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ካገኙት የተወሰኑትን እናንሳ።
ኤሪክ ሆኔከር
ቀድሞ ምሥራቅ ጀርመን ትባል የነበረችውን ሀገር ለረጅም ጊዜ መርተዋል። ኮሎኔል መንግሥቱ በግንቦት 1981 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገባቸው የኚህ ሰው እንግዳ ሆነው ነው። አዛውንቱ ሆኔከር ጎርባቸቭ ባመጣው ‘ጣጣ’ ኮሚኒዝም ተንኮታክቶ ጀርመንም ወደ ውህደት ስትዘልቅ በአንድ ጀምበር ከመሪነት ወደ ወንጀለኛነት ተቀየሩ።
አዲሶቹ ሰዎችም ጀርመኖችን ከከፋፈለው በርሊን ግንብ ጋር በተያያዘ፥ ከሀገሪቱ ወደ ምዕራብ ጀርመን ለማምለጥ በሞከሩ ሰዎች ላይ ስለተወሰዱ ርምጃዎች እንዲሁም በምስጢር እየተለቀሙ ተወስደው የት እንደደረሱ ስለማይታወቁ ከሺህ በላይ ዜጎች ጉዳይ መልስ የሚሹ ጥያቄዎች እንዳሉ ለሆኔከር ግልፅ አደረጉ። በዛ ዕድሜአቸው ወህኒ ከመውረድ በሥልጣን ዘመናቸው በርካታ ቺሊያውያንን ከጄኔራል ፒኖሼ በትር በመታደጋቸው ውለታ አለባቸው በሚል ሞስኮ በሚገኘው የቺሊ ኤምባሲ መሸሽግን መረጡ።
ከሰባት ወራት በዃላ ግን የቺሊ መንግሥት ሆኔከርን ‘ሥራህ ያውጣህ’ ብሎ በጉልበት አስወጥቷቸው ለፍርድ ቀርበዋል። ሆኖም ግን የሆኔከር የጤና ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ከአምስት ወር በኋላ ክሱ ተቋርጦ ተለቀ’ዋል። ሆኔከር 18 ዓመት የመሯት ጀርመንን ለቀ’ው ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት ቺሊ በማምራት በ81 ዓመታቸው በጉበት ካንሰር እስከ ሞቱበት ድረስ የመጨረሻ ቀናቸውን እዛ አሳልፈዋል።
ማኑኤል ኖርየጋ
የፓናማ ፕሬዚዳንት የነበሩት ማኑኤል ኖርየጋ ከቀድሞ ወዳጃቸው አሜሪካ ጋር በተጣሉበት ወቅት አቅማቸውን በአግባቡ ያጤኑ አይመስልም። ለአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ይሰሩ እንደነበር የሚነገረው ጄኔራል፤ እህል ውሃቸው ሲያልቅ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ተወንጅለው በቀድሞ አለቆቻቸው ተፈላጊ ሆኑ። አሜሪካ ጄኔራሉን ለፍርድ ለማቅረብ የሥልጣን ጊዜአቸው እስኪያበቃ አልጠበቀችም። በአንድ የ1981 ክረምት ሃገሪቱን ወረረች። የተገዳደረ አልነበረም። በወረራው አምስተኛ ቀን ላይ መግቢያ መውጫ የጠፋባቸው ጄኔራል፣ በሀገሪቱ ቫቲካን ኤምባሲ ከለላ ጠየቁ።
አሜሪካኖቹ ከደጅ ሆነው በሥነልቡና ውጊያ የተካኑ ባለሙያዎችን አሰማርተው ወኔአቸውን ይሰልቡት ጀመር። ኖርየጋ ከአስር ቀን በላይ በኤምባሲው መቆየት አልቻሉም። እጅ ሰጡ። ፍሎሪዳ ድረስ ተጠፍንገው ለፍርድ ቀረቡ። ከዛ በኋላ ያለው ሕይወታቸው አንዱን እስር ሲጨርሱ ለሌላው ሀገር መሰጠት ነበር። ኖርየጋ ዙር አዳርሰው በመጨረሻ ተላልፈው የተሰጡት ለሀገራቸው መንግሥት ነበር። በ83 ዓመታቸው በከፊል እስር እያሉ በጭንቅላት ዕጢ ታመው ሞተዋል።
መሀመድ ናጂቡላህ
ከ1980 እስከ 1984 አፍጋኒስታንን የመሩት ዶ/ር መሀመድ ናጂቡላህ ግን ለሀኪም ቤትም አልበቁም። የናጂቡላህ መንግሥትን ያቆመው የሶቪየት ሕብረት ጦር በጎርባቸቭ ትዕዛዝ አገሪቱን ለቅቆ ሲወጣ ያ ሥርዓት እንዳበቃለት ግልፅ ነበር። ክርክሩ መቼ በሚለው ላይ ነበር። እንደተገመተውም፤ በ1984 ዓ.ም መንግሥታቸው ወድቆ ኮሽታ ሳያሰሙ፣ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ወደሚገኙበት ህንድ ሊበሩ ወደ አየር ማረፊያው ሲያመሩ፣ ጣቢያውን የሚቆጣጠሩት ቀድሞ ወዳጃቸው የነበሩ ጦር አበጋዝ መንገዱን ዘጉባቸው። ወደ ቤተመንግሥቱ መመለሱም የማያስተማምን ቢሆንባቸው ሕንድ ኤምባሲ ጥገኝነት ጠየቁ። ሕንድ አዲስ ከሚመጣው መንግሥት ጋር ችግር ውስጥ ላለመግባት ጥያቄውን ውድቅ አደረገችው።
ናጂቡላህ በመጨረሻ ካቡል በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግቢ ውስጥ ከለላ አግኝተው ለአራት አመታት ቆይተዋል። እንዳሁኑ ኢንተርኔትና ዩቲዩብ ያልተስፋፋበት ወቅት ነበርና ፕሬዚዳንቱ አብዛኛውን ጊዜአቸውን የሚያሳልፉት የሕንድ ፊልም በመመልከት ነበር ይባላል። እንደተፈራውም ታሊባን በየመንደሩ ያሉትን የጦር አበጋዞች አሸንፎ ሙሉ ለሙሉ ካቡልን ሲቆጣጠር ዲፕሎማሲ ገለመሌ የለ በቀጥታ የተመድ ቅጥር ግቢ ገብቶ፣ ፕሬዚዳንቱንና ወንድማቸውን አውጥቶ በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደል በዘለለ ሬሳቸውን በአደባባይ ሰቅሎ መጫወቻ አድርጎታል።
ጁሊየን አሳንዥ
አውስትራሊያዊው ጁሊየን አሳንዥ የመንግሥታት ምሥጢር በመዘርገፍ የሚታወቀው የዊኪ ሊክስ ድርጅት መሥራች ነው። ነዋሪነቱ በእንግሊዝ የነበረው አሳንጅ፤ በ2003 ስዊድን በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ለጥያቄ ስለምትፈልገው ተላልፎ እንዲሰጣት አቤት ትላለች። አሳንጅ ጥያቄውን በመቃወም ለንደን በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲሟገት ነበር። ነገር ግን የፍርድ ቤቱ አካሄድ አሳልፎ ወደመስጠቱ ያደላ ስለመሰለው በኢኳዶር ኤምባሲ ከለላ ጠይቋል።
ከኤምባሲው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሰባት ዓመት ከተቀመጠበትና በቅርቡ እንደታወቀው ሁለት ልጆች ካፈራበት መጠለያ ተላልፎ ተሰጥቷል። የአሳንዥ ፍርሃት እንግሊዝ ወይም ስዊድን ሳይሆኑ ምስጢሬን ዘርግፏል ብላ ለምትከሰው አሜሪካ ተላልፎ መሰጠትን ነው። በስዊድን የሚጠየቅባቸው ጉዳዮች ይርጋ ጊዜ በማለፉ በስለላ ወንጀል ለምትፈልገው አሜሪካ ተላልፎ ይሰጥ አይሰጥ የሚለው ክርክር  እስኪጠናቀቅ በእንግሊዝ ማረሚያ ቤት ይገኛል።
ወደ ቤላ ጉዞ
እነዚህ ያነሳናቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ታሪኮች ላለፉት 29 ዓመታት ጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው ከሚገኙት ሁለት የቀድሞ ባለሥልጣኖች ጋር ሲተያይ የእነሱን ቆይታ ቀልድ ያደርገዋል። በደርግ መንግሥት በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ለመመርመር በአቶ ግርማ ዋቅጅራ መሪነት የተቋቋመው ልዩ አቃቤ ሕግ በታህሳስ 1987 የዘር ማጥፋት ክስ ሲመሰርት፣ የሀገርም ሆነ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ስቦ ነበር። አንዳንዶች ጭራሽ “የአፍሪካ ኑረምበርግ” የሚል ስም ሰጥተውት ነበር። የክሱ ሂደት መጓተት በዛም ላይ አዲሱ መንግሥት እነዛኑ ወንጀሎች በተራቀቀ መንገድ ሲፈፅማቸው ‘ማንን ሆነሽ’ በሚል ዘይቤ ቀስ በቀስ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት መቀነስ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሂሳብ ማወራረጃ እየመሰለ መጣ። በዛም አለ በዚህ ክሱ መቋጫ ያገኘው ከ15 ዓመት በኋላ ዋነኞቹ ተከሳሾች ላይ የሞት ፍርድ በማስተላለፍ ነው። ከዛ በኋላ ያለው ምህረቱም ሆነ የሞት ቅጣቱ ወደ እድሜ ይፍታህ መቀነስ፣ ከፍርድ ቤት ውጪ የተካሄደ ጉዳይ ነው።
በአካል ተገኝተው ቅጣታቸውን የተቀበሉት 16 ተከሳሾች ለማህበረሰቡ ያለባቸውን እዳ ከፍለው ከሃያ አመት እስር በኋላ በ2004 ነፃ ሆነው ወጥተዋል። ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታና ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ በሚገርም ብርታት ለማጣቀሻነት የሚውሉ ግሩም ማስታወሻዎችን ፅፈው፣ ከሞት ፍርድ በኋላም አዲስ ሕይወት እንዳለ አሳይተዋል።
በአሳዛኝ መልኩ ደግሞ ለሦስት አስርት አመታት ያሃል ከእስር በማይተናነስ ሁኔታ  ቆይተው ከአጥሩ ውጪ ያለውን ፀሀይ ለማየት ያልታደሉት ሁለት የቀድሞ ባለሥልጣኖች አሁንም መጨረሻቸው አይታይም። የመንግሥት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህና ኤታ ማዦር ሹም ሌተና ጄኔራል አዲስ ተድላ አምና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ ተብሎ ከተነገረ በኋላ ምህረቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሳሾችን አይመለከትም ተብሎ ተመልሰን ማስጀመሪያው መስመር ላይ ቆመናል። አሁን ወሬውም የለም። ሰዎቹ ከውጪው አለም ይልቅ ቤላ የሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲን ቤታቸው አድርገዋል። በእውነቱ ከዚህ በኋላ ሌላም ነገር መልመድ አስቸጋሪ ነው። በአንድ ወቅት የጣሊያን አምባሳደር የነበሩት ጁሴፒ ሚስትሬታ ላ ስታምፓ ለተባለ የሀገራቸው ጋዜጣ የሰዎቹ አይምሮ ራሱ ጤነኛ መሆኑ ይገርመኛል ብለዋል።
ስለ ሰዎቹ የጤንነትና አኗኗር ሁኔታ አልፎ አልፎ ከሚነገረው ውጪ ብዙም አይታወቅም። ባለፈው ጊዜ የቅርብ ተጠሪ ነኝ ያሉ ግለሰብ በጀርመን ድምፅ ቀርበው እንዳስረዱት፣ መታወቂያ ስለሌላቸው ውክልና ለመስጠትና ጠበቃም ለመቅጠር አይችሉም። በግቢው ውስጥ የሕክምና መሳሪያዎች ባለመኖራቸው በቂ ህክምና ማግኘት ዳገት ሆኖባቸዋል። ስለዚህ በደም ብዛት፥ ስኳር፥ የልብ ሕመምና ግላውኮማ በሚባለው የዓይን ሕመም  ይሰቃያሉ። በዓመት ሶስት ጊዜ ብቻ ከአራት በማይበልጡ ሰዎች ከመጎብኘት ውጪ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክም ሆነ በአካል መገናኘት አይችሉም። (የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት በግቢው በሚገኘው የጣሊያን ተራድዖ ድርጅት ለጉዳይ በሄደበት ወቅት የነበረውን ጥብቅ ፍተሻ ያስታውሳል። ስልክ በሩ ላይ ትቶ መሄድ ብቻ ሳይሆን ከባትሪው ማለያየትም ግዴታ ነበር። ከበሩ በቀጥታ መሄድ የሚቻለው ወደተጠሩበት ክፍል ብቻ ነው። ወለም ዘለም የለም!)
ስለ ጉዳዩ የዘገቡ አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኅን በጉዳዩ ላይ የመገረም አይነት እንጂ ብዙ አዲስ መረጃ ይዘው አልመጡም። አደገኛ ቦታዎች በመሄድ በመዘገብ የሚታወቀው ቫይስ ኒውስ፥ የእንግሊዙ ዘ ታይምስ እንዲሁም ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ዘገባ አቅርበዋል። የዛሬ ሁለት አመት ገደማ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር የነበሩት ጁሴፒ ሚስትሬታና የኤምባሲው አንደኛ ፀሀፊ ጁሊያኖ ፍራኚቶ ያዘጋጁት ‘ኢ ኖቲ ኦስፔቲ’ (“የታወቁት እንግዶች”) መፅሀፍን ተከትሎ አንዳንድ መረጃዎች ወጥተዋል። ለምሳሌም በመጀመሪያ ኤምባሲው ውስጥ የገቡት ስምንት ሲሆኑ ብዙም ሳይቆዩ ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ሥዩም መኮንን፥ ሚኒስትሮቹ ወሌ ቸኮልና ፋሲካ ሲደልል እንዲሁም ቀድሞ የአሥመራ ከንቲባ የነበሩት አፈወርቂ ብርሃኔ ግቢውን  ለቅቀው መውጣታቸው ተጠቅሷል። አራቱ እዛው ለመቅረት ወስነዋል።
አቶ ሃይሉ ይመኑ
ኤምባሲ በገቡበት ወቅት የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። አለቃቸው አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ከቀናት በፊት ለድርድር ለንደን ተጉዘዋል። ለቀናትም ቢሆን በውክልና ጠ/ሚኒስትር ሆነዋል። በተረፈ ስለ አቶ ሃይሉ ብዙ አይታወቅም። ኤምባሲው ውስጥ ከገቡት ውስጥ የደርግ አባል ያልነበሩት እሳቸው ብቻ ነበሩ። የሥራ አመራር ሰው ናቸው። እንደ ማዕድንና ኢንዱስትሪ የመሣሠሉ መሥሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት አገልግለዋል። የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ሹመትም የዚህ ሁሉ አገልግሎት ውጤት ነው።
በአንድ ወቅት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ ለመንግሥቱ ሃይለማርያም በእጅ የፃፉት ነው ተብሎ በአንዳንድ ድረገፆች የወጣ ደብዳቤ፣ በመንግሥት አስተዳደር ደስተኛ እንዳልነበሩ፣ ሆኖም ስሜታቸውን ለመናገር ድፍረት እንዳጠራቸው ያሳያል። በደፈናው ራሳቸውን ገደሉ በሚባለው ጉዳይ ከእነ ኮሎኔል ብርሃኑ በስተቀር በምስክርነት ሊቆጠር የሚችል የለም። ያንን ርምጃ ለመውሰድ የወሰኑት ምንስ የፈፀሙት ወንጀል ቢኖር ነው የሚል ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ነው። አቶ ሃይሉ በኤምባሲው ለሳምንትም የቆዩ አይመስልም። 
ሌተና ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን
ኮሎኔል መንግሥቱ ሀገር ጥለው ወደ ዚምባብዌ ከሄዱበት ግንቦት 13  ቀን ጀምሮ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነት ወድቆባቸው ለአንድ ሳምንት ያህል መርተዋል። በቅርቡ በሸገር ሬዲዮ የጨዋታ እንግዳ ሆነው ከቀረቡት ኢንጂነር ካሳ ገብሬ እንደሰማነው፣ ጄኔራሉ መንግሥቱ ሃገር ጥሎ ሊወጣ እንደተዘጋጀ ያውቁ ነበር። ተስፋዬ ገብረኪዳን ከ108 የደርግ አባላት አንዱ ነበሩ። ለረጅም አመታትም የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ወደ በዃላው ከሚታወቁባቸው የኤርትራ ክፍለሃገር (ራስ ገዝ) አስተዳዳሪ እንዲሁም በግንቦት 1981 ከተደረገው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ በተሰየመው ችሎት ዋና ዳኛ ነበሩ። በሕብረተሰቡ ዘንድ ለዘብ ባለ ፀባይ ይታወቃሉ።
ጣሊያን ኤምባሲ ለመሄድ ከመወሰናቸው በፊት በአዲስ አበባ የአሜሪካን ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ ለነበረው ሮበርት ሁዴክ ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ፖል ሄንዝ የተባሉት የፀጥታ አማካሪና  ፖለቲካ ተንታኝ ተናግረዋል። ነገር ግን ጉዳይ ፈፃሚው አዲስ ከሚመጣው መንግሥት ጋር ያቃቅረኛል በሚል ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገባቸው እኚሁ ሰው አስረድተዋል።
ስለ ጄኔራሉ የኤምባሲ ኑሮ የሚታወቅ ነገር ቢኖር ጭንቅላታቸው ላይ ደም ረግቶ በተንቀሳቃሽ ወንበር ይዘዋወሩ እንደነበር ተነግሯል። በአሳዛኝ ሁኔታ ግን ጣሊያን ብሔራዊ በዓሏን ያከበረችበት ዕለት ለጄኔራሉ የመጨረሻ ቀን ሆኗል። ተስፋዬ ገብረኪዳን ግንቦት 25 ቀን 1996 ዓ.ም ከብርሃኑ ባይህ ጋር በተፈጠረ ፀብ ምክንያት 13 አመት በኖሩበት የጣሊያን ኤምባሲ አርፈዋል። ኮሎኔሉ ስለ አደጋው ለጄኔራሉ ቤተሰቦች በፃፉትና በወቅቱ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በወጣው ደብዳቤ እንደተመለከተው፤ በሁለቱ መካከል የቆየ አለመግባባት እንደነበረ፤ ባልታሰበው ትንቅንቅ ምክንያት ተያይዘው መስታወትና ጠረጴዛ ላይ እንደወደቁ፤ ጄኔራሉ ግን የበለጠ ጉዳት ደርሶባቸው በግቢው ባሉ ሀኪሞች ክትትል ቢደረግላቸውም ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም። ጄኔራሉ የስድስት ልጆች አባት እንደሆኑም ከደብዳቤው መረዳት ይቻላል። ቀብራቸው አብዛኛውን ውጭ ሀገር የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
ሌተና ጄኔራል አዲስ ተድላ
ኤምባሲው ውስጥ ከነበሩት ውስጥ ብዙም ስማቸው የማይነሳው አዲስ ተድላ ናቸው። ከደርግ አባላትም ቢሆን ይህን ያህል ጎልተው የወጡ አልነበሩም። የአየር ሃይል ባልደረባ የነበሩት አዲስ፤ በአብዛኛውን ያገለገሉት በማዕከላዊ ፕላን ውስጥ ነው። በግንቦት 1981 የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ከመሪዎቹ አንዱ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ ራሳቸውን ሲያጠፉ አዲስ ተድላ በቦታው ላይ ተሾሙ። ክርስቶፈር ክላፋም የተባሉት ተመራማሪ፣ ሹመቱ ለቦታው በመመጠናቸው ሳይሆን ታማኝነታቸውን በማስላት የተሰጠ መሆኑን ስለ ኢትዮጵያ አብዮት በፃፉት መፅሀፍ ገልፀዋል።
አሁን በሰባዎቹ ዕድሜ ላይ እንዳሉ የሚነገርላቸው ሌተና ጄነራሉ፤ አዲስ የሕይወታቸውን ግማሽ ሊያክል ጥቂት አመታት የቀረው ጊዜ በአንድ ግቢ ከእስር ብዙም በማይተናነስ ሁኔታ ድምፃቸውን አጥፍተው ቆይተዋል። በአንድ ወቅት ውጪ ሃገር የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ፣የአሜሪካ መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ፣ ሰዎቹን እንዲያስፈታ ውትወታ ጀምረው ነበር። ምን ያህል ርቀው እንደተጓዙ ባይታወቅም።
ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ
አሁን በሰማኒያዎቹ የዕድሜ ክልል እንደሚገኙ የሚነገረው ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ምሁር ከሚባሉ የደርግ አባሎች አንዱ ናቸው። የሀረር ጦር አካዳሚና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ሕግ ክፍል ምሩቅ ናቸው። በሀረር አካዳሚ ተመልሰው እንዳስተማሩም ይነገራል። የደርግ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴን መርተዋል። የኢሰፓ ፖሊት ቢሮ አባልና የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርም ነበሩ። በሕዳር 1979 ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የደርግን አስተዳደር ጥለው አሜሪካ በቀሩበት ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ተሹመዋል። ከዛ ቀድሞም ቢሆን ከውጪ መንግሥታት ጋር በሚደረጉ ምስጢራዊ ግንኙነቶች ደርግን በመወከል የሚሳተፉት እሳቸው ነበሩ። በዚህም የተነሳ በርካታ ሀገሮችን ጎብኝተዋል።
በ1969ኙ የሶማሊያ ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ ጦር የሠለጠነውና የታጠቀው የአሜሪካን መሣሪያ ስለነበር ተጨማሪ ትጥቅና መለዋወጫ ለማግኘት በተደረጉ ጥረቶች ተሳትፈዋል። መጨረሻው ባይታወቅም በወቅቱ ቬትናም ከአሜሪካ ጦር የማረከችውን በርካታ መሣሪያ ለመግዛት እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። በአጠቃላይ በደርግ ሥርዓት ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሚባሉት አንዱ ነበሩ። ልጆቻቸው አንዳንዴ እየመጡ እንደሚጠይቋቸው ከደብዳቤአቸው ይዘት ግምት መውሰድ ይቻላል።
ሕጋዊ አቋም
እንደ ኮሎኔል መንግሥቱ ሁሉ የሁለቱ ሰዎች የፍርድ ሂደት በሌሉበት ተካሂዶ ሞት ተፈርዶባቸዋል። አሁን ያሉበት ሁኔታ ከእስር ቤት (ካልባሰ) ብዙ የራቀ ባይሆንም፣ በኢትዮጵያ  መንግሥት ቁጥጥር ስር ባለመሆናቸው 29ኙ አመታት እንደ እስር አልተቆጠሩም። በዚህም ምክንያት የምህረቱ ተጠቃሚዎች አልሆኑም። ጣሊያንም ከማስጠለል ባለፈ የፖለቲካ ጥገኝነት አልሰጠቻቸውም። የጣሊያን መንግሥት በተደጋጋሚ የሚገልፀው የሞት ቅጣት ተፈፃሚ ለሚሆንባቸው ሀገሮች ሞት ሊያስፈርድ በሚችል ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን አሳልፌ አልሰጥም የሚል ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ሁለቱ መንግሥታት የቃላት ጦርነት ውስጥ ይገቡ ነበር። ያ ካለፈ ብዙ ጊዜ ሆነው።
“ጩኸቴን ብትሰሙ•••”
ከቅጣት ዓላማዎች መካከል፡- ተመሳሳይ ድርጊት በድጋሚ እንዳይፈፀም መቀጣጫ ማድረግ፤ ወንጀለኞችን ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ማግለል፤ ተበዳዮች ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ከዋና ዋናዎቹ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። በማንኛውም መመዘኛ ቢታይ፣ ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህና ሌተና ጄኔራል አዲስ ተድላ እነዛ ደንቦች ተፈፅመውባቸዋል። አይን ላጠፋ አይን የሚለው  የባቢሎኑ ንጉሥ ሃሙራቢ ሕግም፣ በታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ እንጂ በዘመናዊ አመራር ውስጥ ሥፍራ የሚሰጠው አይደለም። ሰዎቹን ለመፍታት በቂ አስተዳደራዊም ሆነ ግብረገባዊ ምክንያቶች አሉ።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ እባካችሁ ሰዎቹን አሁኑኑ በሕይወት ከዛ ግቢ አስወጧቸው፡፡ እንግሊዛዊው የሀሳብ ሰው ቶማስ ሆብስ ‘ሌዋታን’ የሚለው፤ አድራጊ ፈጣሪ የሆነው ‘መንግሥት’ የተባለው መዘውር ቁልፍ በእጃችሁ ላይ አለ። ያንን በማድረግ የዚህ አሳዛኝ ተውኔት ተሳታፊ የሆነውን ሕብረተሰብም ከፀፀት ታደጉ - ከደሙ ንፁህ ነኝ ሊል አይችልምና።


Read 1155 times