Tuesday, 16 June 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    ኢቲኒክ ፌዴራሊዝም ለድርድር የማይቀርብ ከሆነ--
በብሔርና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም አልመኘውም። ኢትዮጵያ ካላት የብሔር ብሔረሰቦች ዲሞግራፊ አንፃር አሃዳዊውንም ፈፅሞ አልደግፍም። ለብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋ ተግባራዊነት ዕውቅናን ሰጥቶ የሚዋቀረውን ጂኦግራፊያዊውን “Non-Ethnic.. Non-Territorial Autonomy” ፌዴራሊዝምን ግን እደግፋለሁ። አሁን ግን በተግባር ያለነው በየወቅቱ ለድርድር እንደማይቀርብ በሚነገረን በኢቲኒክ ፌዴራሊዝም መዋቅር ውስጥ ነው። የዚህ መዋቅር አንዱም ችግሩ፤ እራሱ በሕገ መንግስታዊ ማዕቀፍ ለብሔሮች ቃል የገባውን ለመተግበር ወገቤን ማለቱ ነው። ለምሣሌ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 3 እንደዚህ ይላል፦
“ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው። ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፡፡”
የቀድሞው የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግስት ይህን አንቀፅ ከወረቀት ላይ ባለፈ በተለይም ደቡብ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ሲያቅተው፣ እንደ አማራጭ አድርጎ የተቀበለው፣ 56 የሚያህሉ ብሔሮችን በአንድ ቋት ውስጥ አጭቆ ማዋቀርን ነበር (በአንድ ቋት ማድረጉ ለሕወሓት የሚያበረክተው የምርጫ ሚዛን ጠቀሜታው እንደተጠበቀ ሆኖ)። ይህን በአቶ መለስና በአቶ ኃ/ማሪያም የአመራር ዘመን የተቃወሙ ብሔሮች በጉልበት ባሉበት እንዲቆዩ ተደርጓል። ከለውጡ ወዲህ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱን ተከትሎ ግን ጥያቄዎቹ በስፋትና በጥልቀት እንደገና አገርሽተው መነሳታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። የዶ/ር ዐቢይ መንግስትም ለዚህ ለከረመ ጥያቄ ከአንዴም ሁለቴ በኮሚቴዎች ጥናት ችግሩን ለመፍታት ሙከራ አድርጓል። በትናንትናው ዕለትም በአቶ አባዱላና በዶ/ር አሸብር የተመራው ካውንስል ያቀረበው ጥናት ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ቀርቦ፣ አሁንም ከተወሰኑ ብሔሮች ተወካዮች ተቃውሞ ቀርቦበታል። የኔውን የከምባታ-ጠምባሮ ብሔር ተወካዮች ጨምሮ የሌሎች ብሔሮች ተወካዮች ዝምታም ቢሆን የአጥኚ ቡድኑ ጥናት ታች ባለው ሕዝብ ተቀባይነት ስለማግኘቱ ዋስትና የሚሰጥ ነው ብሎ ማለፍ የሚቻል አይደለም።
ከአራት ቀናት በፊት በራሴ ገፅ ላይ “የደቡብ ክልል ለመለስ ዜናዊ ኢቲኒክ ፌዴራሊዝም የጎን ውጋት መሆኑ የሚቀጥል ክስተት መስሎ ይታየኛል።” በሚል መግቢያ አንድ ፅሁፍ ማስነበቤ ይታወሳል። ዛሬም ይህንኑ እደግማለሁ። ለምሣሌ የከምባታ-ጠምባሮ ዞን ቀደም ሲል ሕገ መንግስቱ በፈቀደው መሠረት በዞን ምክር ቤት ደረጃ ተወያይቶና አፅድቆ ክልል ለመሆን ያቀረበውን ጥያቄ ለሚመለከተው አካል ማመልከቻ ማስገባቱ ይታወሳል። ይሁንና የአሁኖቹ አጥኚዎች ብሔሩ በተለጣፊነት መዋቅር እንዲካተት ሐሳብ አቅርበዋል።
እንደ ብሔሩ ተወላጅ አሁንም ቢሆን የዞኑ ተወካዮች ዝምታ የሕዝቡን ፍላጎት ያንፀባርቃል ብዬ ፈፅሞ አላምንም። በሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሠረተ ውሳኔ ደግሞ ነገ ከነገ ወዲያ ጥያቄው ላለመነሳቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እንደ ግለሰብና እንደ አንድ የብሔሩ ተወላጅም ተለጣፊነቱን ከብዙ ታሪካዊ ዳራዎች አንፃር የምደግፈው አይደለም። ስለዚህም መንግስት መውሰድ ያለበት እርምጃ አንድና አንድ ብቻ ነው፦ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በሚፈቅደው መሠረት፤ የሕዝቡን ፍላጎት በስብሰባ ሳይሆን በሪፍረንደም መጠየቅና በሪፍረንደሙም ውጤት መሠረት፣ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ!! ሕዝቡ በተለጣፊነት ከሌሎች ብሔሮች ጋር ጥምር ክልል መመስረት ምርጫው ከሆነ በተለጣፊነት ይቀጥል፤ ሕገ መንግስቱ በሰጠው መብት የራሱን ክልል መመስረት ከፈለገም፣ ሕገ መንግስታዊ መብቱን አክብሮ ውሳኔውን መቀበል!! ኢቲኒክ ፌዴራሊዝም ለድርድር የማይቀርብ ከሆነ፣ በራሱ የሕገ መንግስት አንቀፆች ውስጥ የተቀመጡትን መብቶች ማክበርም ለድርድር መቅረብ የለበትም!
(ከጌታሁን ሔራሞ ፌስቡክ)
***
ለካ ህጻናትን አስገድዶ መድፈር ያልበዛው--
አዲስ አበባ ከኮቪድ-19 ወረርሽን ጋር ተያይዞ 101 ልጆች ተደፈሩ፤ ወንድ ልጆችም አሉበት፡፡ የተደፈሩት ደግሞ በቤተሰቦቻቸው፣ በቤተ ዘመዶቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸው፣ . . . . በአባቶቻቸውም ጭምር ነው፡፡ ይህ ማህበረሰባዊ ዝቅጠት የወለደው ሰይጣናዊ ጥቃት ነው፡፡ አንዳንዶች እንስሳዊ/ ደመነፍሳዊ ይሉታል፤ እንስሳዊ ደመነፍስም ይህን አይፈቅድም፡፡
.ከዚህ በላይ ማህበረሰብን የሚያፈርስ አደጋ የለም፡፡ . . . ልጆች በጠባቂዎቻቸው፣ መከታዎቻችን ባሏቸው ሰዎች ሲደፈሩ ከማየት የበለጠ የሚሰቀጥጥ ሰይጣናዊ ተግባር የለም፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ በዚህን ያህል ቁጥር ሲፈጸም፣ ያውም እነዚህ ሀኪም ቤት በመሄዳቸው አደባባይ የወጡ ናቸው፡፡ በየቤቱ ተደብቀው የቀሩት ከዚህ እንደማይተናነሱ እገምታለሁ፡፡
.ከዚህም በላይ በአዲስ አበባ ከ14 -17 አመት ያሉ ልጆች እራሳቸውን እያጠፉ እንደሆነ እየተነገረ ነው፤ የእነዚህ ልጆች ራስን ማጥፋት ምክንያትስ ምንድነው? እንዲህ ያለው አስገድዶ መድፈር ተፈጽሞባቸው እንደሆነስ? ለካ ህጻናትን አስገድዶ መድፈር ያልበዛው፣ ማህበረሰቡ ህጻናቱን ስለሚንከባከብ አልነበረም፤ ኑሮ ባተሌ አድርጎት፣ ጊዜ ባለማግኘቱ ነው፡፡ ይኸው ጊዜ ሲያገኝ የገዛ ልጁን፣ የገዛ ቤተሰቡን፣ ቤተዘመዱንና ጎረቤቱን ይደፍር ገባ፡፡ ሙሉ በሙሉ ከተሞች በተዘጉባቸው አውሮፓና አሜሪካ እንዲህ አይነቱ ወንጀል አልተፈጸመም፤ ሊታሰብም አይችልም፤ በርግጥ ቀድሞም ቢሆን፣ የአስተሳሰብ መናወጥ ያለባቸው ናቸው በምእራቡ አለም ይህን አይነቱን ተግባር የሚፈጽሙት፡፡ እናም እድሜያቸውን ሙሉ ከማህበረሰቡ ተገልለው በወህኒ ይኖራሉ፡፡
.በሀገራችን በአስገድዶ ደፋሪዎች ላይ የሚሰጠው ቅጣት በተደፋሪዎች ላይ የሚሳለቅ ነው፤ በሬና ፈረስ የሰረቀ፣ ህጻን ከደፈረ ሰው በበለጠ እስራት የሚቀጣበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ወዳጄ አበረ አያሌው እዚሁ ፌስ ቡክ ላይ አጋርቶት እንዳነበብኩት፣ በቡሬ ከተማ አስገድዶ ደፍሮ፣ የልጅቱን ክብረ ንጽህና ገስሶ፣ አምስት አመት እስራት ተፈርዶበታል፡፡ የሚያስቀው ደግሞ፣ ሰብሳቢው ዳኛ አቶ አበራ ገበየሁ፣ ‹‹ሌሎችንም ለማስተማርና ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ›› ፍርዱን እንደሰጡ ማስታወቃቸው ነው፡፡ ... ‹‹ከእሷ ጋር አድሬ ሲነጋ ልሙት›› እያለ የሚዘፍን ማህበረሰብ፣ አስገድዶ ክብረ ንጽህና የገሰሰ አምስት አመት ታሰረን ሲሰማ ይጎመዥ እንደሁ እንጂ አይማርም፡፡
ምን መደረግ አለበት?
እነዚህን አውሬዎች ለህዝብ በየቴሌቪዥኑ ማሳየት፣ ማንነታቸውን ማጋለጥ፣ ማህበረሰቡ እራሱን ከነዚህ ሰዎች እንዲጠብቅ ማድረግ፣ የመጀመሪያው ተግባር መሆን አለበት:: እንዲህ አይነት ሰዎች አንድ ጊዜ ብቻ ጥቃቱን አድርሰው እንደማይቀመጡ፣ በተደጋጋሚ እንደሚፈጽሙት በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ከአስር አመት በላይ ታስረው ሲወጡ እዚያው ወንጀል ላይ የተያዙ በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ነው እንዲህ አይነት በሽተኛ ሰዎች እድሜያቸውን ከማህበረሰብ ተገልለው በማረሚያ ቤት የሚያሳልፉት፡፡ በሀገራችንም ይህ መደረግ አለበት፡፡
(ከበድሉ ዋቅጂራ ፌስቡክ)
****
አሜሪካ ምን እያስተማረን ነው?
እንኳን በአንድ አገር ሕዝብ ውስጥና፣ እንኳን በአንድ ከተማ የፖሊስ ኃይል ውስጥ ይቅርና በአንድ ቤተሰብም ውስጥ ጻድቅና ኃጥእ፣ የፍትሕ ሰውና ወንጀለኛ ይወለዳሉ፤ ጥያቄው እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት እናስተናግዳቸዋለን? ነው፡፡
ከመጀመሪያው እንነሣ፡- አንድ መለዮውን የለበሰና የታጠቀ የከተማው (ሚኒአፖሊስ) ነጭ ፖሊስ አንድ ጥቁር ዜጋን በግፍ ገደለ፤ አንድ ዜጋን አንድ ዜጋ ገደለ፤ መለዮ የለበሰውና የታጠቀው ሕግ አስከባሪው ዜጋ ሰላማዊውን ሰው በግፍ ገደለው፤ እንዲያውም አራት ሕግ አስከባሪዎች ነበሩ፤ ደስ የሚለውና የኢትዮጵያ ሕዝብም ሊማረው የሚገባ የሚኒአፖሊስ ከተማ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ሕዝብ በሙሉ መቆጣቱን ነው፤ ተቆጥቶና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጉ ገዳዮቹ ከሥራቸው ተሰናበቱ፤ ዋናው ገዳይ ታስሮ ክስ ተመሠረተበት፤ የአሜሪካ ሕዝብ ነጭ በደለ፤ጥቁር ተበደለ ሳይል አንድ ዜጋ ተበደለ ብሎ ጮኸ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ዓይነት ኅብረትና ይህንን ዓይነት ቁጣ ማሳየት መማር ያስፈልገዋል፤ በደርግ አገዛዝ በአራት ኪሎ በአንድ ገዳይ ላይ፣ በአዲሱ ከተማ በራጉኤል አካባቢ የአዲስ አበባ ነዋሪ አሳይቷል፤ ግፍ ሲፈጸም ቁጣን መግለጽ ለሕጋዊነት በኅብረት መቆም የማኅበረሰቡን የመንፈስ ልዕልና ያሳያል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን አጨንግፎ ወደ ንብረት ማቃጠልና ሰዎችን ወደ መጉዳት ሲለወጥ መጀመሪያውኑ ግፍ ከሠራው ፖሊስ ጋር መተባበርና አብሮ በመንፈስ መውደቅ ነው፤ ወይም አንድ ወሮበላ ፖሊስን ተከትሎ እሱ የሠራውን ግፍ ማራባት ነው፤ ይህ ለማንም አይጠቅምም፤ ማኅበረሰቡን አያሻሽልም፤ ኑሮን አያቃናም፤ ከግፈኛው ጋር የመንፈስ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ከግፈኛው እሻላለሁ ማለት ራስን ማታለል ነው፡፡
(ከመስፍን ወልደ ማርያም ፌስቡክ)
***
ከምክንያት በላይ የሆኑ ሰዎች ያስፈልጉናል!
በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ያለው ቅራኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና በጣም እየከረረ ነው፡፡ ችግሩ ከጥቂት የፖለቲካ አመራሮች ቃል መወራወር አልፎ እንዲህ አጋጣሚ እየጠበቀ ህዝብን ከጎን የማሰለፍና የመቦዳደን ውድድር ውስጥ እየገባ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ወቅታዊውን የጠ/ሚ ዐቢይ የፓርላማ ንግግር ተከትሎ አጠቃላይ በሁለቱም በኩል የቆመው ህዝብ ድባብ ከባለፉት ጊዜያት ጋር ካነፃፀራችሁት ምን ያህል ጥላቻና መራራቅ አገሪቱ ላይ እየገዘፈ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡ ችግሩ ሰሞነኛ ጩኸት ብቻ መስሎ ከተሰማን የዋህነት ነው፡፡
ይሄ ነገር ለማንም አይበጅም ! ታሪክ አንደሚነግረን፤ ህዝባችን አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት በላይ ድንጋይ ካቀበሉት እርስ በእርስ የመፈነካከት ባህሉ ከፍተኛ ነው:: የእብድ ገላጋዩን ምሁር፣ የፖለቲካ ተንታኝና የጦር ነጋሪት ወጋሪውን ሁሉ ወደ ጎን ትተን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ተሰሚነት ያላችሁ ሰዎች ሁለቱንም ወገኖች በሰከነና ፍፁም ገለልተኛ በሆነ መንገድ በማነጋገርና በማቀራረብ ለዚች አገር ትልቅ ውለታ ስሩ! ቢያንስ እናንተ ከምክንያት በላይ ሁኑ!
(ከአሌክስ አብርሃም ፌስቡክ)
***
የተዘነጋው የሕዝብ ቁጥር እድገት?!
ለዘመናት በርካታ ውጣ ውረዶችን ያሳለፉትና እጅግ በጣም የዘመነና የበለጸገ ማህበረሰባዊ ስርዓት ማነጽ የቻሉት ማያዎች ስልጣኔያቸውን ከዘሩበት የማያ ከተማ በድንገት ወጥተው የቀሩት ውስን የተፈጥሮ ሃብታቸው ከአቅሙ በላይ የሕዝብ ቁጥር በማስተናገዱና ተፈጥሮን የመንከባክባና የማከም ስራ ስላልሰሩ ነበር:: አንትሮፖሎጂስት (ያ)ጃሬድ ዳይመንድ፣ በቀላል ቋንቋ ይህንን ሲያስቀምጠው፤ “የዘመን አይሽሬው የማልቴዢያን ጽንሰ ሃሳብ” ውጤት ይለዋል፡፡ እኛስ ስለ ሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ስለ እምቦጭ፣ ስለ ፓርኮችና ደኖች በሰደድ እሳት መቃጠል፣ ስለ መሬት ለምነት ከምር መቼና እንዴት ማሰብ እንጀምር?
“ቁጥር አንድ ኢህአዴጎች” በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ያልተመጣጠነ የሕዝብ ቁጥር እድገትን ስለ መቆጣጠር ለወቅቱ ጠ/ሚ ፓርላማ ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ፋሽዝም ነው ብለው ተዘባብተው ነበር። እርግጥ ነው ሕዝብ ሃብት ነው፣ ነገር ግን ያልተገደበ የሕዝብ ቁጥር እድገት ደግሞ ያልተመጣጠነ የምርት አቅርቦት ጥያቄ መቀስቀስና የተፈጥሮ ሃብት፣ የውሃ፣ የመሬት፣ የማዕድን መራቆትና መመናመን የሚያስከትል ነው፡፡
ዛሬ በራሱ የፖለቲካ ርዕዮት ላይ የቆመ የሚመስለን “ከክልሌ ውጣ፣ መሬቴን ልቀቅ፣ ቅድሚያ ለኔ ይገባኛል“ በሚል አባዜ በብሔር መብት ስም የሚካሄደው የተካረረ የግጭትና የእልቂት ፖለቲካ፤ በአንድ በኩል ከፍተኛ  የሕዝብ ቁጥር እድገት ያስከተለው፣ የተፈጥሮ ሃብት መራቆት ወደ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ (Suitcase Politician) መሸጋገሩ “ለሻንጣ ፖለቲካኞች” እድል ስለፈጠረላቸው ነው፡፡
የደን ማልማት ንቅናቄውን ልዩነታችንን ጠብቀን ማገዝ የሚሻለው፣ ተፈጥሮ የሕልውናችን መሰረት ስለሆነች ብቻ ነው:: ለመጣላትም ቢሆን ከመከራና ከጭንቀት የጸዳች ተፈጥሮ ታስፈልገናለች፡፡ ሞራሉ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ደን መትከሉ በራሱ ግብ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም በማህበረሰባዊ ሳይንስ መሰረት የሕዝብ ቁጥር እድገትና የቤተሰብ ምጣኔ አብሮ ሊሰራበት ይገባል:: እርዳታ ሰጭ ሀገራት የሚረዱን በውዴታ ግዴታ የቤተሰባቸውን ቁጥር መጥነው ነው:: “የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ” በሚል የተማጽኖ ተረት፣ የዓለምን ሕዝብ በልመና ማስጨነቅ ማፈሪያ ባህል ማድረግ አለብን፡፡
(ከሙሼ ሰሙ ፌስቡክ)
***
ምቀኝነት ግን የግላችን ነው?
የእኛን ሰው እግዜር አገኘው አሉ፡፡ የልብህን አንድ መሻት ንገረኝና ይሆንልሃል አለው፡፡ ግን ደግሞ ላንተ ከሆነልህ እጥፍ ለባልንጀራህ አደርግለታሁ አለው አሉ:: የእኛ ሰው ትንሽ አሰብ አደረገና፤ አንድ አይኑን እንዲያጠፋለት ተማፀነ አሉ፡፡ የእኛን ምቀኝነት ለማሳየት የሚውል ወግ ነው፡፡ ግን ግን ምቀኝነት የግላችን ነው እንዴ? አሜሪካ ሀገር የተሰራ ጥናት ነው:: ተማሪዎች ላይ፡፡ ቅድመ ምሩቃን ላይ እንዳይመስልህ፤ ድህረ ምሩቃን ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ የህግ ወይም ባዮሎጂ ወይም ጂኦግራፊ ድህረ ምሩቃን ተማሪዎች እንዳይመስሉህ፡፡ የMBA ተማሪዎች ላይ እንጂ፡፡ የቀላል ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዳይመስሉህ፤ በአለም ላይ አሉ ከሚባሉት የቢዝነስ ትምህርት ቤቶች በአንዱ የሚማሩ ተማሪዎች ናቸው፤ ማንም ዘው ብሎ የማይገባባቸው፤ ሲመረቁም ዲግሪያቸውን በባይንደር ይዘው ስራ የማይፈልጉ፤ ስራ ያሉበት ድረስ የሚመጣላቸውና በኋላም የአለማችን ትልልቅ ኩባንያዎች የሚሰሩና የሚመሩ፡፡
ጥናቱ የተደረገው ተማሪዎቹ ምን ያህል ደሞዝ ቢከፈላቸው እንደሚመርጡ ለማወቅ ነው፡፡
ለጥናቱ ተካፋዮች በየግል የተጠየቁት፣ የትኛውን ደሞዝ ትመርጣላህ ወይም ትመርጫለሽ? የሚል ነው፡፡
ሀ. በአመት 200ሺ ዶላር ይከፈልሃል፤ ጓደኞችህ ግን 225ሺ ይከፈላቸዋል
ለ. በአመት 150ሺ ዶላር ይከፈልሃል፤ ጓደኞችህ ግን 125ሺ ይከፈላቸዋል
እስቲ አንተ ምረጥ፡፡ አንተማ የኛው ሰው አይደለህ∙! የኛው ሰው የሚመርጠውንማ ከላይ አይተነዋል፡፡ ባሏን ጎዳሁ ብላ የሚል ተረት ያለ ነገር ተረታችን አልሆነም፡፡ አብዛኞቹ የዚህ ምርጥ የቢዝነስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመረጡት ሁለተኛውን ነው፤ ባልጠጣውም አደፈርሰዋለሁ፡፡
እናልህ ወዳጄ, የኛን ሰው ለቀቅ አድርግው፤ ሀበሽኛ አይደለም. ሰውኛ እንጂ፡፡ ታዲያ እኛ ጠቢቡ ሰው ነን? Are we homo sapiens who are tired of being homo sapiens and are now aspiring to be homo deus? Or we are not yet homo sapiens?
ከምን መጣ ግን የመብለጥ ፍላጎት? ካልበለጥን ደስ የማይለን ለምንድን ነው? የሰው ልጅ ስልጣኔ መሰረት መብለጥ መፈለጉ ነው፤. ይህ ባይሆን ኖሮ አሁን የምናየው ስልጣኔ እውን አይሆንም ነበር፡፡ እንዲህ የሚሉ አሉ፡- የብልጫ፣ የመብለጥ፣ የበላይ የመሆን ፍላጎቱ ነው ጠቢብ ያደረገው፡፡ ሰው መሆን መብለጥ መፈለግነት ነው፤ ሰው መሆን ማለት እኩልነትን መጠየፍ ነው፤ እኩልነትን የሚፈልገው እኩል እስኪሆን ብቻ ነው፤ በውድድርም እኩል ለመሆን ይተጋል፤ እንዲህ ነው? ትጎበኘው፤ ታስበው፤ ታከብረው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?
ማስታወሻ፡- ከዚህ በላይ የጠቀስኩት የጥናቱን መሰረታዊ ሃሳብ ለማሳየት እንጂ የጥናቱን ዝርዝር በትክክል ላያስቀምጥ ይችላል::
(ከሙሉጌታ መንግስት አያሌው ፌስቡክ)
***
አባይ፣ ኢትዮጵያና ግብጽ
ኮረና ያደረገው ነገር ቢኖር ትልቁን አለም በቤታችን እንድንፈጥር መንገዱን እንድንፈልግ መግፋት ነው። ችግሩ ትልቁን አለም በትንሷ ቤታችን እንድናያት የሚያግዙንን የአዕምሮ ቴሌስኮፖች የማግኘትና የመጠቀም አቅም የማጎልበት ጉዳይ ነው። ለዚህም መጽሐፍትን ማንበብ፣ ፊልሞችን ማየት፣ ያገኘነውን ሃሳብ ማሰላሰልና ወጥ የሆነ ሌላ ሃሳብን የመፍጠርን አቅም መገንባት ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ ባህር አቋርጠው የሚያስገብሩ የእነ ካሌብ፣ የአገር ድንበሩ ውቅያኖስ ነው የሚሉ የእነ አምደ ጺዮንና ዘርዕ ያቆብ፣ ኢትዮጵያን ከዘመነ መሣፍንት በማውጣት አንድነቷን ጠብቃ ሃያልነቷን እንድትመልስ ህልሙን ሰንቆ ህይወቱን የገበረላት ቴዎድሮስ፣ የታላቆቹ አሉላ አባነጋና አብዲሳጋ፣ የምእራባውያንን የቀኝ ግዛት መስፋፋት በዲፕሎማሲም፣ በጦርም የገታው፣ ለስልጣኔ መምጣት ጠንክሮ የሠራው የምኒሊክ አገር ነች። አገራችን በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ነፃነትንና ኩራትን ከቀደምቶቻቸው ያጣጣሙ ሕዝቦች አገር ነች። ዛሬም ይህ ሕዝብ የሚፈልገው ጥሩ አመራር እንጂ አባቶቹ ያደረጉትን ለማድረግ ፍላጎቱ፣ አቅሙ፣ ዝግጅቱ አለው። እናም አሁን እያየነው ያለውን ወቅታዊ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች፣ ለሕዝባችን በማስረዳት ለተሻለው ነገ፣ የአባቶቻችንን አኩሪ ታሪክ ለመድገም የመሸጋገሪያ ድልድይ አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል። ይህን ለማድረግ ግን የፖለቲካ መሪዎች በሕዝብ መታመንን ይጠይቃል። ይህ ታማኝነት ሊመጣ የሚችለው ደግሞ ስርዓትን በማስተካከል፣ ባለ አቅምና ታማኝ መሪዎችን ወደፊት በማምጣት፣ አስተዳዳሪነት ያለ አድሎ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በእኩል ማገልገል መሆኑን በመረዳትና በተግባር ማሳየት ሲቻል ነው። ስለዚህም የደካሞች ፖለቲካ፣ ዘረኝነት፣ ለማኝነት ይቅርብን። ለእድገት፣ ለትልቅነት፣ ለሚገባን ሃያልነት እንስራ።---
ግብጽ በአባይ ግድብ ላይ ለምትሞክረው ማንኛውም ድርጊት፣ ከእሷ የተሻለ ኢትዮጵያ አማራጭ አላት። አለም አቀፍ የውሃ ሕግ የሚደግፈው እኛን ነው። ውሃ ሰጭ እንጂ ተቀባዩ ያላደረገን ጂኦግራፊ አለ። ምርጥና ለአገሩ የቆመ ጀግና ሰራዊትና ሕዝብ አለን። እናም በተቻለ መጠን ዲፕሎማሲው ላይ አተኩሮ መስራት፣ በጉልበት እንሞክራለን ካሉ ግን ገባሮችን ሁሉ መገደብ፣ አስፈላጊ ሆነ ከተገኘ የነሱንም አስዋን ማፍረስ ነው። ለግብፅ ደጋፊ የሆነ አቋም፣ የዝቅተኝነት ስነ ልቦና ያላቸው ዜጎች ካሉም፣ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል። በተቻለው ሁሉ ያለንን አማራጭ መጠቀም ይኖርብናል። የሚገርመኝ ከ25 አመት እድሜ በታች የነበረው ታላቁ እስክንድር፣ አገሩን ከመቆዶንያ እስከ ሕንድ ገዥ ሲያደርግ እያወቅን፣ በአባቶቹ ባህር ተሻግሮ ይገዛ የነበረ ሀገር ዜጋ ግን ለግብጽ ሲርድ ማየት ያሳፍራል። በድህነትና በተመጽዋችነት መኖር እዚህ ላይ ሊበቃን ይገባል።
እነዚህ ሰዎች፣ ለምን ከጉራቸው በፊት ከቅኝ ተገዥነት ነጻ አይወጡም። ይህን በአመት በቢሊዮኖች የሚወጣለትን የአሜሪካ ታዛዥ ጦር ማስፈራሪያ ለማድረግ ታሰቡ፣ ተሳስተዋል። ከዛ ውጭ ያባቶቻችን ልጆች መሆናችንን ንገሩልን። ግብጽ በየዘመናቱ በመጡ ሃያላን መንግስታት፣ በአሳይሪያ፣ ሱሚሪያ፣ ባቢሊን፣ ፐርሻያ፣ ግሪክ፣ ሮም፣ አረቢያ፣ ኦቶማን ቱርክ፣ እንግሊዝ አሁን ደግሞ በአሜሪካ የሞግዚት አስተዳደር የቀጠለች፣ የራሷ ማንነት የሌላት ሀገር ነች። ይህች ሀገር በበላይ ጠባቂዎቿ በኩል ለዘመናት ነጻነቷን ጠብቃ የቆየችውን ኢትዮጵያን ለመጉዳት የራሷን ዲፕሎማሲ ስትጠቀም ቆይታለች።
ለ1620 አመታት ያህል ከ110 ባላነሱ አቡኖቿ እድገታችንን ያወከችና በዚያው መንገድ መቀጠል የምትፈልግ ሀገር እንደሆነች የታወቀ ነው። የዮዲትና የግራኝ አህመድ ደጋፊ ነበረች። ከ1832-1876 ዓ.ም. ብቻ ከ16 ያላነሱ ጦርነቶች በኢትዮጵያ ላይ አካሂዳለች። በእነ እጼ ዮሃንስ፣ አሉላ አባ ነጋና በእነ ሞሃመድ ሃንፍሬ ተደቁሳ ብትመለስም። ሶማሌያ ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን በወጋችባቸው ጊዜያት፣ የሻብያን፣ የሕወሓትንና የኦነግን እንቅስቃሴ ወዘተ ደጋፊ ነበረች። በዚህም ከኛው ደካማነት ጋር ተዳምሮ ለኤርትራ መገንጠልና የባህር በር የሌለው አገር እንድንሆን አድርጋናለች። አሁን ደግሞ የእኛ ፖለቲከኞች አንዴ የብሔር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሃይማኖት ግጭት እየፈጠሩ አገር ያምሳሉ፤ ትራምፕ የአገራችንን ሉዓላዊነት የመካከለኛው ምስራቅ ሰላም መደራደሪያ እያደረገው ነው። በአለም ባንክና በአይኤምኤፍ ብድር ምክንያት አባይንና ሉዓላዊነታችንን እንዳያሳጡን መሪዎቻችን አጥብቀው ያስቡበት። በተለይም ሙያተኞችን ማሳመን ሲያቅታቸው መሪዎች ይፈርሙ አካሄድ ግልጽ አልሆነልንም?
There is also fire in the other house. Do not forget that the country which is pushing against the rock is the down stream country. Please do not push us to do wrong. If you try to beat our dam, we will beat the Aswan Dam. We will also use every drop of water and tributary rivers as we like if you are not going to be ruled by international water laws. We Ethiopians in all field of life are proud of our national defence force. And, every of us are soldiers to our country.
They said “Egypt is gift of Nile” and now we are saying “Nile is gift of Ethiopia; therefore, Egypt is gift of Ethiopia”. Thus, we have the right to do anything on our gifts. አባይ ግብጽን አስገኘ እንጂ፣ ግብጽ አባይን አላስገኘችም። አረቦች ከግብጽ ጋር እንቆማለን ካሉ፣ ከነዳጅ ከሰበሰቡት ሃብት ኢትዮጵያ ለጊዜው ለምታጣው ጥቅም ለግብጽ ሊከፍሉላት እንደሚገባ ይወቁ።
እኛ እርስ በርስ ስንባላ የአለም የበታች ናችሁ፣ የታዘዛችሁትን አድርጉ እየተባልን በሌሎች መንግስታት ትዕዛዝ እየወጣልን ነው። አብረን ስንቆም አሸናፊ እንሆናለን። ከተለያየን ግን 110 ሚሊዮናችንም ተሸናፊዎች ነን። ለአለፈ መቆጨት አይጠቅመንም። አሁን በአሜሪካ የሚደገፈውን የግብጽን ትንኮሳ በሕብረት ልናከሽፈው ይገባል።
የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአገራችንን ጥቅም ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም መደራደረያ ሊያደርገው በሚፈልገው ትራምፕ አደራዳሪነት ከሚደረገው ድርድር መግባቱ ትክክል ባይሆንም፣ መውጣቱ ግን ትክክልና አስፈላጊም ነው። እኔ አገሬንና መሪዬን ከሚነካ ጋር አይደለሁም። ከተሳሳተ የምተቸው እኔ ዜጋው እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም፣ አይገባምም። ሌላ ጣልቃ ከገባ ግን እኔ ከመሪዬ ጋር ነኝ። እሱ ለኔ ከማንም ይቀርበኛልና። እናም ከአገራችን ጉዳይ እጃችሁን አንሱ እንላለን። Yes, Abiy did some diplomatic missteps and open the way to these international partners to think in a wrong way. However, I am with him in this crisis. Plus, he should reconsider privatization of public properties supported by World Bank and IMF in order to help our poor and develop our infrastructures.
“...final testing and filling should not take place without an agreement. We also note the concern of downstream populations in Sudan and Egypt due to unfinished work on the safe operation of the GERD, and the need to implement all necessary dam safety measures in accordance with international standards before filling begins.”
The Trump Administration is crossing the line to evade the sovereignty of our country, Ethiopia, with regard to the Grand Renaissance Dam. The negotiating team from Treasury and World Bank were trying to have the signed agreement with Egypt through their negative maneuvering of the Ethiopian negotiating team. We are also observing a letter from this team skewed to advantages of Egypt. We hope that US government will play its usual positive role.
የአባይ ጉዳይ የሕብረትን አስፈላጊነት እያሳየን ስለሆነ፣ መነታረካችንን አቁመን፣ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው። ለዚህም ለማንም ብሄር ያልወገነ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መመስረቻው ጊዜ አሁን ነው። አብረን ስንቆም አሸናፊ እንሆናለን። ከተለያየን ግን 110 ሚሊዮናችንም ተሸናፊዎች ነን። ለአለፈ መቆጨት አይጠቅመንም። አሁን በአሜሪካ የሚደገፈውን የግብጽን ትንኮሳ በሕብረት ልናከሽፈው ይገባል። ስለዚህም የውስጥ ችግራችንን ተነጋግረን መፍታትና የሷን ተጽእኖ ግን መከላከልና መቋቋም የኛው ሃላፊነት ነው። መሪዎችም የአባይን አጠቃቀም አስመልክቶ የምንፈርመው ሁሉ የዛሬና የነገን ጥቅማችንን ያስጠበቀ እንዲሆን ይሁን እንላለን። ያለዚያ ግን ነገ ላይ ሆነን፣ ትናንት እንዲህ-እንዲያ ብናደርግ ብለን መቆጨታችን የማይቀር ነው።
(ከመላኩ አዳል ፌስቡክ)


Read 7316 times