Print this page
Saturday, 13 June 2020 13:37

ከኮሮና ያገገመችው ወጣት የለይቶ ማቆያ ተሞክሮዋን ትናገራለች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

                - ባለሁበት ክፍል ውስጥ ብቻዬን ነኝ፣ የሚነበብ የለም፤ ቲቪ የለም ምንም የለም… ይጨንቃል
                - አንዳንድ ለይቶ ማቆያ ያሉ ሰዎች ያልተገባ ቅርርብ በመፍጠር ራሳቸውን ለቫይረሱ ያጋልጣሉ
                - የምለቀው ቪዲዮ ወደዚህ ቦታ ለሚመጡ ሰዎች ትልቅ የሥነልቦና ጉልበት ይሆናቸዋል

            ሰሞኑን ዩቲዩብ ላይ አንዲት በኮሮና ቫይረስ የተያዘችና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የገባች ወጣት የለቀቀችውን ቪዲዮ ተመለከትኩ:: እንዳጋጣሚ ደግሞ ወጣቷን አውቃታለሁ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሥራ ባልደረባዬ ነበረች:: እቺ ወጣት ሃይማኖት ተስፋዬ ትባላለች፡፡ ዛሬ ኢትኤል ኮሚዩኒኬሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናት። ኩባንያዋ ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት ከቱርክ የቢዝነስ አጋሮች ጋር በመጣመር ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ስሙ የናኘ ነው፡፡
ይህቺ ጐበዝ ሥራ ፈጣሪ ናት በኮሮና ተይዛ ለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባቷን ራሷ ከለቀቀችው ቪዲዮ የተረዳሁት፡፡ አድራሻዋን አፈላልጌም ደወልኩላት፡፡ ያነጋገርኳት በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆና ነው፡፡ በቅርቡ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ -19 ምርመራ አድርጋ፣ ውጤቷን እየተጠባበቀች መሆኑን ገለፀችልኝ፡፡ ውጤቷ ኔጌቲቭ ከሆነም በሁለት ቀናት ውስጥ ከለይቶ ማቆያው ወጥታ ከቤተሰቦቿ (በተለይም ከህፃን ልጇ) ጋር ትቀላቀላለች፡፡ ይሄ ቃለ ምልልስ ወጣቷ እንዴት በቫይረሱ እንደተያዘችና አሁን ስለምትገኝበት የጤና ሁኔታ ብቻ የሚያትት አይደለም፡፡ ይልቁንም ብዙዎች የሚፈሩት ለይቶ ማቆያ የሚባለው ሥፍራ ምን እንደሚመስል በዝርዝር መረጃ የሚሰጥና ሌሎችን በሥነልቦና ዝግጁ የሚያደርግ ነው:: በቆይታዋ ከታዘበችው ተነስታ የለይቶ ማቆያውን ጥንካሬና ድክመት በመገምገምም መሻሻል አለባቸው የምትለውንም ትጠቁማለች፡፡ ከኮሮና በማገገም ሂደት ላይ የምትገኘውን ወ/ሮ ሃይማኖት ተስፋዬን የአዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እንደሚከተለው አነጋግራታለች፡፡  


              አሁን ጤናሽ እንዴት ነው? እየበረታሽ ነው?
አዎ በጣም ደህና ነኝ፤ እግዚአብሄር ይመስገን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት፤ በጣም ተሽሎኛል። አሁን አንድ የመጨረሻ ምርመራ አድርጌ ውጤቱን እየጠበቅሁ ነው፤ ውጤቱ ነጌቲቭ ከሆነ በሁለት ቀን ውስጥ ወጥቼ ከቤተሰቤ እቀላቀላለሁ፤ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ።
መቼ ነው ወደ ማዕከሉ የገባሽው?
እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ነው የገባሁት።
በምን አጋጣሚ በቫይረሱ እንደተያዝሽ የምትገምቺው ነገር አለ?
እውነት ለመናገር የት እንደያዘኝ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ቫይረሱ እዚህ አገር ገባ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ እቤት ውስጥ ነበርኩኝ፤ ግዴታ ለሆኑ ነገሮች ብቻ ነበር አልፎ አልፎ የምወጣው። እንደዛም ሆኖ አስፈላጊ የሚባሉ ጥንቃቄዎችን አደርግ ነበር። ሳኒታይዘርም በአግባቡ እጠቀማለሁ። የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልም አደርግ ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በጣም የምጠራጠረው ገንዘብ ነው፡፡ በፊት በፊት ገንዘብ አውጥቼ ስከፍል ሳኒታይዘር አድርጌ መልሼ ቦርሳዬን ከፍቼ ነበር የማስገባው። አንዳንዴ ሱፐር ማርኬት ወይም ሌላ ገበያ ቦታ ስትሆኚና ስትቸኩይ ሳንቲይዘር ሳትጠቀሚ ብሩን ቦርሳሽ ውስጥ ልትከቺ፣ መልስ ልትቀበይ ትችያለሽ። ወይ ቆይቶ ትዝ ይልሽና ልታፀጂ ስትይ፣ ሳኒታይዘሩን ራሱ ነክቶት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንዱ በጣም የምጠራጠረው በገንዘብ ንክኪ ይዞኛል ብዬ ነው። ሁለተኛው፤ አርብ ቀን ለልጄ የወተት ኩፖን ለመግዛት ሰላም የህፃናት መንደር የሚባል ወተት የሚሸጥበት ቦታ ሄጄ ነበር፡፡ በዕለቱ በጣም ብዙ ወረፋና ሰልፍ ነበር፤ ብዙ ሰው ማስክ ቢያደርግም አካላዊ ርቀት አልነበረም። ሁለተኛው የምጠራጠረው ይህንን ቦታ ነው።
የወረፋውን መብዛትና የሰውን አለመራራቅ ስትመለከቺ ነጠል ብለሽ ለመቆም አልሞከርሽም?
በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ወረፋሽን መጠበቅ አለብሽ፤ ራቅ ስትይ ሌላ ሰው መጥቶ ይገባብሻል። እርግጥ ወጣ ብዬ ለመቆም ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰው በአጠገብሽ ገፍቶሽ ያልፋል፤ ብቻ በጣም አስቸጋሪ ነበር።
በቫይረሱ እንደተያዝሽ ያወቅሽው እንዴት ነው?
ከዚህ በፊት አለርጂ ነበረኝ፤ በተደጋጋሚ ብን ብን የሚል ሳል ይይዘኛል፤ አርብ ግንቦት 21  ቀዝቃዛ ነገር በልቼበት ይህ ሳል ተባባሰ:: በቃ ቀዝቃዛ ነገር ስለበላሁ ራሱ አለርጂው ተባብሶ ነው ብዬ ትቼው ነበር፡፡ በነጋታው ቅዳሜ ግን የድካም ስሜትና ብርድ ብርድ ማለት ጀመረኝ፡፡ እሁድ ዕለት ደግሞ ራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ ድክምክም አለኝ፡፡ ያ ብን ብን የሚል ሳል ደግሞ ወደ ደረቅ ሳልነት ተቀየረ፡፡ ደረቴንም መፋቅ ጀመረኝ፡፡ ብዙ ልብስ ስለብስም ሙቀት አይሰማኝም፡፡ ደረቴን ይፍቀኛል፤ ጀርባዬን በሀይል ይቀዘቅዘኛል፡፡ በጣም የጠረጠርኩትም ደረቴን ሲፍቀኝና ጀርባዬን ሲቀዘቅዘኝ ነው፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ከዚያ ሀኪሞች ጓደኞቼ ጋር ደውዬ ስለ ሁኔታው ነገርኳቸው፡፡ ሰኞ ሂጅና ናሙና ስጬ አሉኝ፡፡ ወዲያውኑ ራሴን ማግለል ጀመርኩኝ፡፡ ለምን? በተለይ ህፃን ልጅ ሲኖርሽ በብዛት ወደ አንቺ ይመጣል፤ ልጄ ማስኬን ሊያወልቅ ሲታገል ለማንኛውም ብዬ አካባቢዬ ወደሚገኝ የግል ሆስፒታል ሄድኩኝ:: ምልክቶቼን ነገርኳቸው፤ ሳሌም ተከታታይ ነበር፤ ሀኪሞቹ ዛሬ ተለይተሽ እዚሁ ቆይና ነገ እንመርምርሽ አሉኝ፡፡ ይመስለኛል እንደዚህ አይነት ምልክት ያለው ሰው ሲመጣ፣ ለጤና ሚኒስቴር ማሳወቅ አለባቸው፡፡
ስለዚህ የጤና ሚኒስቴር ሀኪሞች መጥተው፣ ቃለምልልስ አደረጉልኝ፤ ያለኝን ሁኔታ አዩና ብዙ ተመሳሳይ ምልክት ስላለ አሁኑኑ መመርመር አለብን ብለው ወደ እነሱ ማዕከል ይዘውኝ ሄዱ:: እሁድ ማታ ሁለት ሰዓት አካባቢ ላይ ናሙና ሰጠሁ፤ እስከ ሐሙስ ድረስ ውጤቱ አልመጣም ነበር፡፡ ለብቻዬ ተለይቼ አንድ ክፍል ውስጥ ነበር የቆየሁት፡፡ ረቡዕ ሌሊት 8 ሰዓት ላይ ውጤቴ ፖዘቲቭ እንደሆነ ደውለው ነገሩኝ፡፡
ተደውሎ ነው ውጤት የሚነገረው?
አዎ ተደውሎ ነው የሚነገረው፤ ነገር ግን በለይቶ ማቆያ ውስጥ በእነሱ ማዕከል እስካለሽ ድረስ በውድቅት ሌሊት ደውለው ከሚናገሩ ሀኪሞቻቸው ቢናገሩ ነበር የሚሻለው፡፡ ነገር ግን የዶክሜንቴሽን አሰራር ጉድለት አለ፡፡
እንዴት ማለት?
መጀመሪያ የአንቺን መረጃ የሚወስደው ሰው ትክክለኛ ፎርም ይዞ አይመጣም፡፡ ለምሳሌ የእኔን በኖርማል ወረቀት ጽፎ ነበር የሄደው፡፡ ስለዚህ እዚህ ቦታ እንዳለሁ ሁሉ ያላወቁ የሚመለከታቸው አካላት ነበሩ፤ ከጤና ሚኒስቴርም ሆነ ከሌላው ክፍል:: እናም ሲደውሉልኝ ከውጭ አገር የመጣሁ የመሰላቸውም አሉ፤ ቤቴም ውስጥ ያለሁ የመሰላቸውም ነበሩ፡፡ የት ነው ያለሽውም ብለውኛል፤ ብቻ የሆነ ሆኖ እኔ ረቡዕ ሌሊት በስልክ ውጤቴን ሰምቼ፣ እዚህ ያሉት ሀኪሞቼ ውጤቴ የደረሳቸው ሐሙስ 7፡00 ነበር፡፡
ውጤትሽን ስትሰሚ ምን ተሰማሽ? ጠብቀሽ ነበር?
ያው ከነበሩኝ ምልክቶች ልያዝ እችላለሁ ብዬ ስለነበር ብደነግጥም ሃሳቤን መለስኩት:: ምን ማድረግ አለብኝ ወደሚለው ነው ቶሎ ይህ በሽታ ከበሽታው ይልቅ ጭንቀቱ ነው የሚገድለው ስለዚህ ራሴን ማበረታታት ነበረብኝ፡፡ ራሴን ወደ ማጠንከሩ ወደ መጋፈጡ ነው ሃሳቤን ያዞርኩት፡፡
አንድ ታካሚ ለይቶ ማቆያ ሲገባ ያለውን ሁኔታ እስቲ በዝርዝር ንገሪን
ጥሩ፡፡ መሠረታዊ ፍላጐቶች ይሟላሉ:: ምግብ በቀን ሶስት ጊዜ ይቀርብልሻል፤ በቂ ውሃ ታገኛለሽ፤ ውሃ በፈለግሽ ጊዜ ጠይቀሽ መውሰድ ትችያለሽ፡፡ ምግብም ከተሰጠሽ በላይ ድጋሚ መውሰድ ትችያለሽ፡፡ ውስጥ ስትገቢ እነ ሳሙና፣ ሳኒታይዘር ብርድልብስ አለ፡፡ አልጋሽ የተስተካከለ ነው፡፡ ንጽህናሽን ልትጠብቂ የምትችይባቸው ቁሳቁሶች በሚገባ ይሰጡሻል፡፡ ያው ከጥሩ መጀመር ጥሩ ስለሆነ ብዬ ነው፡፡ መጥፎ ነገሩ ምንድን ነው ካልሽኝ? የበሽተኛው የስነ ልቦና ዝግጁነት እዚህ ሲመጣ ከሚያገኘው ነገር አንፃር ጥሩ አይደለም:: ማንም የሚያናግረው የለም፡፡ መቼ ነው ውጤት የሚመጣው? አሁንስ ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለውን ነገር ማንም አይነግርሽም፡፡ በተለይ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነሽ ገና ውጤት እየተጠባበቅሽ ከሆነ፣ በዚህ አይነት የብቸኝነት ጭንቀት ውስጥ ነው የምታሳልፊው፡፡ ፖዘቲቭ ሆነሽ መታመምሽ ከታወቀ ሀኪሞች ጧትና ማታ መጥተው ያዩሻል፤ ግን በለይቶ ማቆያ ምንም የለም:: ሌላው መጥፎ ነገር እስከ ዛሬው ቀን ድረስ (ሐሙስ ነው ቃለ ምልልሱ የተደረገው) ምግብ ለመውሰድ እኛ ነበርን የምንሄደው:: እኔ ለምሳሌ አንደኛ ፎቅ ላይ ነው ያለሁት፤ ታች መሬት በሩ ጋ መውረድና ምግብ መውሰድ አለብኝ፡፡ በዚያ ሰዓት ሁሉም ሰው ነፃ ነኝ ብሎ ነው ራሱን የሚያሳምነው፤ ማንም ሰው ግን ፖዘቲቭ ይሁን ነጌቲቭ ስለማያውቅ ኮሪደር ላይ ይመላለሳል:: በእርግጥ “ብረት አትንኪ ግድግዳ አትንኪ” ትባያለሽ፤ ግን ያም ሆኖ ከቤቴ በሰላም መጥቼ እዚህ ቢይዘኝስ፣ ከአንዱ ቢተላለፍብኝስ በሚል ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭንቀትሽ ይጨምራል፡፡ ሁሉም ሰው ፌስ ማስክ ያደርጋል፤ የእንቅስቃሴው ሁኔታ ግን ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ክፍላችን ውስጥ ተቀምጠን ምግባችንም ውሃችንም በራችን ድረስ ቢመጣ፣ ለእኛ የበለጠ የተሻለ ነው፡፡ እናም ይህንን ጠይቀን ዛሬ ተስተካክሏል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እኛ ሳንወጣ ምግቡ በራችን ድረስ እንደሚመጣ ነግረውናል፡፡
ሌላው ከንጽህና ጋር በተያያዘ፣ አራት ቀን በለይቶ ማቆያ በአንድ ክፍል ውስጥ ስቆይ አንድ ቀን ብቻ ነው ጽዳት ሰራተኛ የመጣልኝ:: “በርና መስኮት አትንኪ፤ የትኛውም ነገር ተነካክቶ ሊሆን ይችላል ተጠንቀቂ” ስለምትባይ፣ በስነልቦና ጭንቀት ውስጥ ሆነሽ ነው የምትቆይው፡፡ ክፍልሽን ለማጽዳትም እጅሽን ለመታጠብም ስለምትሳቀቂ፣ አልጋሽ ላይ ብቻ ነው ቁጭ የምትይው፡፡ እኔ እንደ ዕድል ሆኖ የሰጡኝ ክፍል የራሱ መፀዳጃ አለው:: ሌሎቹ ክፍሎች ግን የጋራ መፀዳጃ ነው ያላቸው፡፡ ውሃ ለመቅዳት ስሄድ በማይበት ጊዜ ማን ተጠቅሞበት ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ ስለዚህ እዚያ ቦታ ላይ ከምንም በላይ የስነልቦና ድጋፍ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ውጤቱ ፖዘቲቭ ለሆነውም ገና በለይቶ ማቆያ ሆኖ ውጤት ለሚጠብቀውም ቢሆን ከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አርባ ምንጭ በለይቶ ማቆያ ገብታ ራሷን አንቃ የገደለችውን ልጅ ታሪክ ሰምተናል፡፡ ይሄ የችግሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የመጀመሪያውን አራት ቀን፣ እኔ ባልሆንና ብዙ የማወራው ሰው ባይኖረኝ፣ ምን አይነት ድባቴ ውስጥ ልገባ እንደምችል አላውቅም፡፡ እኔ ግን ብዙ ሰው ይደውልልኛል:: እኔም የማውቃቸው ሀኪሞች ጋር እየደወልኩ ስሜቴን እነግራቸዋለሁ፡፡ እነሱ ምክር ይለግሱኛል፡፡ በዚህ መልኩ ነው ያለፍኩት፡፡
አንቺ ራስሽ በራስሽ ነው ስነ ልቦናሽን ለመገንባት ትግል ያደረግሽው?
አዎ በራሴ ትግል ነው፡፡ ለምሳሌ መጀመሪያ የገባሁ ቀን ጠዋት፣ ማለትም እሁድ ማታ ገብቼ ሰኞ ጠዋት ሀኪም መጣ ጓንትና ጭምብል እንዴት እንደማደረግ፣ በርና መስኮት መንካት እንደሌለብኝና ከክፍሌ እንዳልወጣ ነገረኝ:: ሁሉም ሰው ይሄ ነገር ይነገረዋል፤ ነገር ግን እኔ አካባቢ ያሉ ሰዎች ከክፍላቸው ወጥተው አብረው ያወሩ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ አንድ ክፍል ውስጥ ገብተው አብረው ምሳ ይበሉ ነበር። አንድ ቀን ሁለት ወንዶች ድንገት እኔ የነበርኩበት ክፍል ውስጥ ገብተው፣ እኔ የምጠቀምበትን መፀዳጃ ተጠቀሙ። ከዚያ በቀጣዩ ቀን ሀኪሞቹ ሲመጡ ነገርኳቸው፡፡ “እኔ የምጠቀምበት ከሆነ ለምን ሌላ ሰው ከውጭ ይገባብኛል” አልኳቸው። ሀኪሞቹ ደግሞ “እዚህ ያለው ሁሉም አዋቂ ስለሆነ ፖሊስ ማቆምም ሆነ እንዲህ አድርጉ አታድርጉ ማለት አንችልም” ነው ያሉኝ።
ክፍልሽ ቁልፍ የለውም እንዴ?
ቁልፍ የለውም። የኔ በር ቁልፉ ተበላሽቶ አይዘጋም። ከውጭ ያለው በር ይዘጋል፤ እኔ ያለሁበት ክፍል ግን አይዘጋም። በሩ አይሰራም። መጀመሪያ ቀን ስትገቢ “በር አትንኪ መስኮት አትንኪ” ስለሚሉሽ፣ እኔም በዕለቱ ተጨናንቄ ስለነበር፤ የሰጡኝ ክፍልም ልክ አንድ መኝታ ቤት እንዳለው የጋራ መኖሪያ ቤት አይነት ስለነበር፣ በመጀመሪያው ቀን በርም መስኮትም ሳልነካ፣ በርም ሳልዘጋ ክፍት አድርጌ ቁጭ ብዬ ነበር ያደርኩት። በአጠቃላይ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም። ሴት ትኖራለች፤ ሕጻን ልጅ የያዘች ሴት ትኖራለች፤ በየወለሉ ጥበቃም ሆነ ልትጠሪው የምትችይው ዶ/ር የለም፤ በየወለሉ ላይ ያስቀመጡልን ስልኮች አይሰሩም። ሰው ከየት ከየት ተሰብስቦ አንድ ቦታ እንደሚመጣ አታውቂም። ብቻ በለይቶ ማቆያ እንደገባሽ ሁለቱን ቀን ሰው ቢመጣብኝስ፣ የሚለው ነገር፣ ሌላ ተጨማሪ ጭንቀት ነው። ደውለሽ በዚህ ዙሪያ ሀኪሞቹን ልትጠይቂ ስትይ ስልኩ አይሰራም። እንደምንም ልዝጋ ብለሽ እንዳትታገይ፣ መነካካቱና ፍርሃቱ ይይዝሻል፤ ብቻ አያድርስ ነው።
አንቺ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነሽ ያየሽውን፣ ሰዎች ሊያደርጉ የሚገባቸውን ነገር ለማስተማር የሰራሻቸው ቪዲዮዎች ሰሞኑን በዩቲዩብ መነጋገሪያ ሆነዋል…
አዎ እኔ ከሁለት ሶስት ቀን በኋላ ማንም እንደማይመጣልኝ ሳውቅ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ራሴን በራሴ ወደ ማከም፣ ስነ ልቦናዬን ወደ ማጠንከር ነው የገባሁት:: ከሰዎች ጋር በስልክ ማውራት፣ ሀኪሞችን ማናገር ጀመርኩኝ፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ብትጮሂ የሚመጣልሽ የለም፤ ቢመጣም በየክፍሉ እንደኔው ለብቻው ያለ ሰው ነው፤ ከሰው ጋር መገናኘት አይቻልም ተብለሻል፤ ግራ ነው የሚገባሽ:: የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሶስት ቀናት ከባድ ነበሩ። አንዳንድ እዛው ተገናኝተው ጓደኝነት የመሰረቱ አሉ፡፡ ለምን? በጣም ድባቴ ውስጥ ትገቢያለሽ፤ የምታነቢው የለም፤ ቴሌቪዥን የለም፤ ምንም የለም። ክፍልሽ ውስጥ ሶኬት ብቻ ነው ያለሽ። ስልክ የማግኘት ዕድል የሌለው አለ፡፡ ስለዚህ ጓደኝነት ይመሰርቱና አብረው ይበላሉ፤ አብረው ያወራሉ፤ ይሄ ደግሞ ራሱን የቻለ ችግር አለው፤ ምክንያቱም አንዱ በቫይረሱ ተይዞ ሌላው ነፃ ሆኖ ግን ተጠርጥሮ ነው የሚመጣው:: ያ ነፃ የሆነ ሰው ሕጉን አክብሮ፣ ተመርምሮ ነፃ መውጣትና መሄድ ሲችል፣ ከዚያ ሰው ጋር በፈጠረው አካላዊ ቅርርብ፣ ቫይረሱ ሊተላለፍበት ይችላል። በዚህ አጋጣሚ የምነግርሽ አንድ እዚህ ያገኘሁት ሰው 12 ቀን ነው የቆየው።
ለምን ይህን ሁሉ ቀን ቆየ?
አስቢው… በለይቶ ማቆያ የምትቆይው ቢበዛ አራት ቀን ነው፡፡ ለምን መሰለሽ” የዚህ ሰው የመጀመሪያ የምርመራ ውጤት ኔጌቲቪ ነበር፤ ነገር ግን አብሮት ሲበላ አብሮት ሲያወራ የነበረው ሌላው ሰው፣ ፖዘቲቭ ሆነ፤ ስለዚህ ይሄ ሰው ድጋሚ መመርመር አለበት፡፡ ይህ ቦታ ለሌላ ተረኛ መለቀቅ እድሉን ላላገኘ መሰጠት ሲኖርበት እዚሁ በተፈጠረ ችግር ይህ ሰው የሌላ ሁለት ሰዎችን ቦታ ነው እየተጠቀመ ያለው:: መንግሥት ለሌላ ሊያውለው የሚገባውን ሃብት  ይሄ ሰው እየተጠቀመ ነው፤ ይሄ ደግሞ የሚመጣው ከግንዛቤ ጉድለት ነው ወይም ከግዴለሽነትም ሊሆን ይችላል ስለዚህ ሌላው መማር አለበት በሚል ነው ቪዲዮዎቹን የሰራሁት። እኛ ሰዎች ፖሊስ ሲጠብቀን በባህሪያችን አይመቸንም፤ ለምንድን ነው የሚጠብቀን? እንላለን፡፡ ነገር ግን እዚህ ቦታ ላይ ሆኜ ሳየው ፖሊስ ያስፈልጋል፡፡ ሰው የሚነገረውን ተግባራዊ ካላደረገ መጠበቅ መከልከል አለበት።  ምክንያቱም ሁላችንም አንድ አይነት አመለካከት የለንም። እኔ በበኩሌ፤ እዚህ አካባቢ ፖሊስ ባለመኖሩ ቅር ብሎኛል፤ ቢኖር ደህንነት ይሰማኛል። ሌሊት አንድ ሰው ወደ ክፍሌ ቢመጣ የምጠራው ሰው አለ፡፡ ሴት ሆነሽ እዚህ ቦታ ላይ ስታስቢው ከፖሊስ ጥበቃ ውጭ መሆን ያስፈራል። ሳልገልፅልሽ የማላልፈው ዶክተሮች በጣም ጥሩዎች፣ ትሁቶች ናቸው:: አብዛኞቹ ማለት ይቻላል። አንድ ሁለት ብቻ ናቸው ከበድ የሚሉ የገጠሙን፡፡ እነሱም ያን ያህል የሚጋነን አይደለም፤ ስለዚህ ሀኪሞቹን ማመስገን ተገቢ ነው።
ሌላውና በጣም ማድነቅ የምፈልገው ከውጭ ምግብ ማስገባት ይቻላል። እንደነገርኩሽ  ለይቶ ማቆያ ስትሆኚ ምግብ በደንብ ይሰጡሻል፤ ነገር ግን እንደኔ በጣም ለመጠንቀቅ ስትሞክሪ ብዙ ነገር ያስፈራል። ምግቡን እፈራው ነበር። ማን ነው የሰራው? ከየት ነው የመጣው? በምን ሁኔታ ታሽጎ ነው እዚህ የደረሰው? በምን አይነት ንጽህና ነው የተዘጋጀው? የሚለው ስለሚያሳስበኝ ምግብ ከዚህ አልበላም ነበር፤ ከቤቴ ነበር የማስመጣው። ይህን ማድረግ በመቻሌ ደስ ብሎኛል። ኔጌቲቭ እስክባል ድረስ ጥሩ ምግብ እያስመጣሁ ራሴን መጠበቅ መቻሌ ምቾት ሰጥቶኛል። በለይቶ ማቆያ ስትሆኚ በአብዛኛው ጭንቀትሽ በሽታው ከዚህ ቢይዘኝስ ነው። ፖዘቲቭ ከሆንሽ በኋላ ደግሞ እዚህ የሚሰጡሽ ምግብ በቂ አይደለም፤ በቂ አይደለም ስልሽ ከብዛት አንፃር ሳይሆን በቃ ለበሽታው የሚሆን ተጨማሪ ምግብ ያስፈልጋል ማለቴ ነው። እዛ ሆነሽ ራስሽን ተንከባከቢ ስትባይ ሙቅ ነገር ጠጪ፤ ቀዝቃዛ ነገር አትጠቀሚ፣ ውኃሽን እያሞቅሽ ጠጪ ትባያለሽ። ህመሙ እንደ ጉንፋን ከሆነ አጥሚት፣ ሾርባ፣ ቅቅልና መሰል ነገሮችን መጠቀም አለብሽ። ሌላው ግን ሁላችንም እዚህ ስንመጣ ተይዘናል የሚል ጥርጣሬ ስለሌለን የሚያስፈልገንን ይዘን አንመጣም፤ ቤትም ውስጥ የተዘጋጀ አይኖረንም። ቤተሰቦችሽም ለማዘጋጀት ትንሽ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ሌላው አንቺ ፖዘቲቭ መሆንሽ ሲሰማ ቤተሰብሽ በያለበት ድንጋጤ ስታክ አድርጎ ነው የሚቀረው። ብቻ አስቸጋሪ ነው።
አሁን ቤተሰብሽ በተለይ ሕጻን ልጅሽ፣ እናት አባትሽ እንዴት ናቸው? ምንም ችግር አላጋጠማቸውም?
እስካሁን ማንም የተያዘ ሰው የለም:: እንዳልኩልሽ የተቻለኝን ጥንቃቄ አደርግ ነበር:: ከቤተሰብ ጋር ስመጣም ስሄድም በጣም በጥንቃቄ ነበር፤ አባቴ ነው ትንሽ ተያያዥ ህመሞች ያሉበት፡፡ እሱ ከተማ ውስጥ አልነበረም፤ ለስራ ወደ ክ/ሀገር ወጥቷል። አርብ ዕለት እናቴንና ወንድሜን ብቻ ነው ያገኘኋቸው። እኔ እዚህ ስገባ እናቴ ልጄን ለመንከባከብ እኔ ቤት መጣች፤ ወንድሞቼ ባሉበት ቆዩ፡፡ እናቴ፣ ባለቤቴ ልጄና ሰራተኛችን ባሉበት ቆዩ፡፡ አባቴ ከክፍለ አገር ሐሙስ ሲመለስ ሆቴል አስገባነው:: ሁላችንም በያለንበት ሆንን ማለት ነው። እስካሁን በቫይረሱ የተያዘም ምልክት ያሳየም ሰው የለም። ምናልባት በቶሎ ስለሄድኩም፣ ሀኪሞቹም እንዳሉኝ “አለርጂ ባይኖርብሽ ኖሮ ሳታውቂውና ምልክትም ሳያሳይ ሊያልፍ ይችል ነበረ፤ ምክንያቱም 70 እና 80 በመቶ የሚሆነው ሰው ያለምንም ምልክት ነው የሚድነው:: እዚህም መጥተው ሳይታመሙ ከቫይረሱ ኔጌቲቭ ሆነው የወጡ አሉ” ነው ያሉኝ፡፡ እስካሁን ያለው ይህን ይመስላል።
እስኪ ስለህመሙ ንገሪኝ… ለመተንፈስ ተቸግረሽ፣ መተንፈሻ አጋዥ መሳሪያ አስፈልጎሽ ነበር?
እኔ እግዚአብሄር ይመስገን… በዚህ አይነት ስቃይ ውስጥ አላለፍኩም። እስካሁን በሚዲያ ከምትሰሚው በተቃራኒ ነው ያሳለፍኩት። በቃ የማያቋርጥ ሳል ብቻ ነው የነበረኝ። ከዚያ ውጪ ትኩሳትም ራስ ምታትም ሆነ ትንፋሽ ማጠር አላጋጠመኝም። ተከታታይ ሳልና የሰውነት ድካምና መድቀቅ ብቻ ነው የነበረኝ፡፡ እሱም እሁድና ሰኞ ነው በጣም ያመመኝ። ለአምስት ቀናት የሳል ሽሮፕ ስወስድ እየቀነሰ መጣ። ነገር ግን በጣም ብርድ ብርድ ይለኝ ነበር፤ በጣም ብዙ ልብስ ነበር የምለብሰው፡፡ አምስት ሹራብ ለብሼ በላዬ ላይ ጋቢ ደርቤ አይሞቀኝም:: ከታች ሁለት ሱሪ፣ ሁለት ካልሲ ደርቤ ነበር የማደርገው:: በዚህ ምክንያት የሻይ ማፍያ እንዳስገባ ፈቅደውልኝ ስለነበር የምጠጣውን ውሃ በሙሉ እያሞቅሁኝ ነው የምጠጣው። በብዛት ቤት ውስጥ የሚሰሩ ባህላዊ መድሃኒቶችን ነው የተጠቀምኩት። ዝንጅብል፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ፌጦ … በማሞቀው ውሃ ውስጥ በመጨመር እጠጣለሁ:: እነሱ ከሚሰጡኝ ምግብ በተጨማሪ ከቤቴ ሾርባና አጥሚት ይልኩልኝ ስለነበር ራሴን ለማከም ጥሬያለሁ፡፡ ለምን ብትይ… በሽታውን የምትዋጊው በመድሃኒት ሳይሆን በምግብ ነው። ስለዚህ ምግብ እንዳስገባ በመፍቀዳቸው ትልቅ ምስጋና አለኝ፡፡ አሁን እንደውም ሪፖርተር ላይ እንዳነበበኩት፤ ኤካ ኮተቤ ያሉ ታማሚዎች ከውጭ ምግብ ማስገባት አትችሉም ተብለዋል። ይሄ በጣም አግባብ ያልሆነ ነገር ነው፤ ሊፈቀድላቸው ይገባል፡፤ እኔ በምግብ ነው የተቋቋምኩት፤ እዚህ ከመጣሁ አንድም ቀን መድሃኒት ወስጄ አላውቅም፤ ከሳል ሽሮፕ ውጪ። እዚህ እያለሁ ክሎሪን ተረጭቶ አለርጂዬ ተነስቶብኝ፣ ሁለት ቀን በጣም ታምሜ ነበር፡፡ ራስ ምታት ያዘኝ ሳሉም እንደ አዲስ ተቀሰቀሰብኝ፤ እሱን ትሪት ለማድረግ በፊት የምወስደውን መድሃኒት ለመውሰድ ፈልጌ፣ “ከዚህ ቫይረስ ጋር የሚያመጣውን ውስብስብ ነገር ስለማናውቅ መውሰድ አትችይም” ብለውኝ ፓራሲታሞል ብቻ ነው የወሰድኩት። ስለዚህ ለበሽታው መድሃኒት ስለሌለ በሽታውን የምትከላከይው፣ በሽታን የመቋቋም ሥርዓትሽን ተጠቅመሽ በመሆኑ በሽታ የመቋቋም አቅምሽን ለማዳበር ብዙና ተመጣጣኝ ምግቦችን ማግኘት ግዴታሽ ነው። እሱን ለማድረግ ደግሞ በቀን 3 ጊዜ መብላት ብቻ አይደለም፤ ቀኑን ሙሉ ትኩስ ነገር መጠጣት፣ ጉንፋንን የምናድንበትን ነገር በሙሉ ማግኘትም አለብን። ስለዚህ ከውጭ የሚገባ ምግብ መከልከል፣ ከቤተሰብ የሚመጣን ዕቃ አለመፍቀድ በፍፁም ትክክል አይደለም።
አሁን አንቺ እንደምትነግሪኝ በብዙ መልኩ ዕድለኛ ነሽ ማለት ይቻላል?
በጣም ዕድለኛ ነኝ፤ በብዙ መልኩ። እኔ እንደውም እዚህ የመጣሁት በምክንያት ነው እያልኩኝ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ። አንደኛ በሕመም በጣም አልተሰቃየሁም፤ ሁለተኛ አጋጣሚ ሆኖ የራሴ መፀዳጃ ክፍል ነበረኝ። ሶስተኛ የነበርኩበት ቦታም (ቦሌ ጨፌ) ዶክተሮቹም ጥሩ ናቸው። ምድጃና ብረት ድስት ገብቶልኝ፣ ባህር ዛፍ እያፈላሁ እሞቅ ነበር፤ ስለዚህ አፍንጫዬም ስለማይታፈን ጥሩ እተነፍስ ነበር፡፡ አራተኛ ምግብ ከቤት ይላክልኝ ነበር። ለዚህ ነው እኔ በምክንያት ነው የመጣሁት የምለው፡፡ ለዚህም ነው ሰው ከእኔ ተሞክሮ እንዲማር ብዬ ቪዲዬ እየሰራሁ  እየለቀኩ ያለሁት፡፡
በቪዲዮው እዚህ ገብቼ ለሶስት ቀናት እንዴት ግራ ገብቶኝ እንደነበር እንዴትስ ራሴን እንዳበረታሁ ነው የሰራሁት፡፡ በአጠቃላይ እዚህ ቦታ የሆንኩትንና ያደረግኩትን፣ የሚያሳይና የሚያስተምር ነው:: ይሄ ወደዚህ ቦታ ለሚመጡ ትልቅ የስነ ልቦና ጉልበት ይሆናቸዋል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። አየሽ አምቡላንስ ውስጥ ከመግባት ጀምሮ አንቡላንስ በአካባቢው ሲጮህ ሽብር ነው፤ ሕዝቡ የሚሰማው። ብዙ ሰው አምቡላንስ ውስጥ ገብቶ የሚሄድ ሰው ሞቶ የሚመለስ ነው የሚመስለው። ኮሮናን ከመታፈንና ከመሞት ጋር ብቻ ነው የምናያይዘው። ስለዚህ ማናችንም በሆነ አጋጣሚ እዚህ ገብተን ልንወጣ ስለምንችል፣ ይህንን ጉዞ ማሳየት ያስፈልጋል። እኔ ከየትኛውም ሚዲያም ሆነ ከየትኛውም የመንግሥት አካል ስለሁኔታው የማውቀው የለም። ናሙና እንዴት እንደሚወሰድ፣ ህመም አለው፣ ከየት ነው የሚወሰደው፣ መቼ ነው የሚወሰደው፣ በስንት ቀን ነው ውጤቱ የሚደርሰው፣ ለስንት ቀን ነው ራስሽን አዘጋጅተሽ እዚህ ቦታ መቆየት ያለብሽ? የሚያቀርቡልሽ ምንድን ነው? አንቺስ ከቤትሽ ምን ይዘሽ መውጣት አለብሽ? የሚለውን አላውቅም፤ አልሰማሁም። እኔ ልጄን እንኳን ቻው ሳልል ወጥቼ ነው፣ በ10 እና 15 ደቂቃ  አምቡላንስ ውስጥ ገብቼ ሆስፒታል የደረስኩት። ለምንም ነገር ዝግጁ አልነበርኩም። ስለዚህ ይህንን የስነ ልቦና ዝግጁነት ማህበረሰቡ ውስጥ መፍጠር በጣም ጠቃሚ ነው ብዬ በማሰብ ነው ቪዲዮዎቹን የለቀቅኩት። ስለዚህ እግዚአብሄር ሁሉንም ሲያደርግ ለበጎ ነውና አመሰግነዋለሁ። እኔ የተጋፈጥኩትን ፈተና ሰዎች በየቤታቸው ሆነው ሲያዩት፣ እኔም ነገ ቢያጋጥመኝ ይህን አደርጋለሁ ብለው ይማራሉ። እኔ እንዳየሁት በሽታው ከአካልሽ ይልቅ ስነ ልቦናሽን ነው የሚጎዳው። ስለዚህ ልብና ጭንቅላታችን ጠንከር ማለት አለበት፡፡ ስለ መሞት ሳይሆን ስለ መዳን ማሰብ አለብን፤ ይህን ለማሰብ እውነታውን ማወቅ አለብሽ። የምትመጪው እስር ቤት አይደለም፤ ከቤተሰብ ጋር በሩቅ ነው መተያየት የምትችይው፤ ውጭ ያለው ቤተሰብሽ ስለሚጨነቅ እነሱን ያረጋጋል ብዬ በማሰብም ነው ቪዲዮዎቹን የሰራሁት።
ለሰጠሽን አስተማሪ የሆነ ቃለምልልስ በአንባቢያን ስም አመሰግንሻለሁ፡፡ ሙሉ በሙሉ አገግመሽ ከቤተሰብሽ እንድትቀላቀይም እመኝልሻለሁ …
እኔም አመሰግናለሁ፡፡ ደውላችሁ እንዴት ሆንሽ? ምን ደረሰብሽ? ስላላችሁኝ እግዜር ይስጥልኝ።


Read 6641 times