Print this page
Saturday, 13 June 2020 13:51

ማዕደ ልሳናት - ለቋንቋ ብልፅግና

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)

    “ማዕደ ልሳናት የቋንቋዎች ገበታ፡- የግእዝ - አማርኛ - እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት” በሚል ርእስ የታተመ መጽሐፍ እጄ ላይ ገብቶ አነበብሁት፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ መምህር እርጥባን ደመወዝ ሞላ ይባላሉ፡፡ ብዙ የተለፋበትና የተደከመበት መጽሐፍ መሆኑን ከይዘቱ መረዳት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ ሦስቱም (ግእዝ፤ አማርኛ፤ እንግሊዝኛ) ቋንቋዎች አንድን አቻ ቃል በቅብብሎሽ እንዴት እንደሚፈቱትና በድልድይነት እንዴት እንደሚያገለግሉ ያሳያል፡፡
መጽሐፉ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለውጭ አንባቢዎች ለአጠቃቀም በተመቸ ሁኔታ መዘጋጀቱ  ልዩ ትኩረት የተደረገበት ሥራ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከሽፋን ሥዕሉ ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው፤ ሦስት ሰዎች በአንድ ገበታ (መሶብ) በጋራ ሲመገቡ ይታያሉ፡፡ የሚመገቡት በአማርኛ ዳቦ፤ በግእዝ ኅብስት፤ በእንግሊዝኛ ብሬድ (Bread) ነው፡፡ ከመሃል ያለው ባለ ኅብስቱ  የግእዝን ቋንቋ የሚያውቁ ሰዎች ምሳሌ  ናቸው፤ በቀኝ በኩል የተቀመጡት ባለ ዳቦው አማርኛ የሚያውቁ የጨዋ ኢትዮጵያዊ ተምሳሌት ሲሆኑ በግራ በኩል የሚታየው ባለ ብሬዱ ደግሞ አለባበሱ ጭምር እንደሚያመለክተው የፈረንጅ አፍ ወይም እንግሊዝኛን የሚያውቁ ሰዎች አምሳል ነው፡፡
ገበታው (መሶቡ) በሦስት ቋንቋዎች የተገለጠ፤ ተመሳሳይ ነገርን በአንድ ላይ እንደያዘ ሁሉ ይህም መጽሐፍ  ሦስቱንም ቋንቋዎች በአንድ ላይ ፊት ለፊት የመያዙ ምሳሌ ነው:: መጽሐፉ በ18 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው:: በምዕራፍ አንድ፡- የሰው አካል ክፍሎችና ተዛማጅ ጉዳዮች  የተገለጹ ሲሆን ለምሳሌም በግእዝ ላሕይ ብሎ በአማርኛ ደም ግባት፤ መልክ፤ ፊት ብሎ ካመለከተ በኋላ በእንግሊዝኛ ደግሞ beauty, attractiveness, face... ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በግዕዝ-ልሳን፣ በአማርኛ ምላስ፣ በእንግሊዝኛ-tongue በሚል ሰፍሯል፡፡  
ይህም አሠራር በአንድ ወንጭፍ ሦስት አዕዋፋት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በምዕራፍ ሁለት ሹመትና ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱ ሲሆኑ ለአብነትም፡- በግእዝ ሊቀሐራ፤ በአማርኛ የሠራዊት አለቃ፤ የጭፍራ አለቃ፤ የጦር አበጋዝ፤ በእንግሊዝኛ general, capitain of the army, military commander, chief of a body of troops, military leader. በግእዝ ፈታሒ፤ በአማርኛ  ዳኛ፤ በእንግሊዝኛ judge, በሚል ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ምዕራፍ ሦስት ስለ ምግብ፤ መጠጥና ተዛማጅ ጉዳዮች፤ ምዕራፍ ዐራት ስለ ቤትና፤ የቤት ክፍሎች፤ ምዕራፍ አምስት ስለ መልክዐ ምድርና ተዛማጅ ነገሮች፤ ምእራፍ ስድስት ስለ ቤተሰብ፤ ምዕራፍ ሰባት ስለ ልዩ ልዩ እንስሳት ስሞች፤ ምዕራፍ ስምንት ስለ እንስሳት የአካል ክፍሎች፤ ምዕራፍ ዘጠኝ ስለ ቤት ቁሳቁስ፤ ምዕራፍ ዐሥር ስለ ልብስና ተዛማጅ ጉዳዮች፤ ምዕራፍ አሥራ አንድ ስለ ጌጣጌጦች ስም፤ ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት ስለ ዕፀዋትና ተክሎች ስያሜ፤ ምዕራፍ ዐሥራ ሦስት ስለ ነዋያ ቅድሳት፤ ስለ ተቀደሱ ዕቃዎች፤ ምዕራፍ ዐሥራ ዐራት ስለ ሰው ስሞች፤ ምዕራፍ ዐሥራ አምስት ስለ ብርሃንና ጨለማ ስያሜ፤ ምዕራፍ ዐሥራ ስድስት ስለ ሙያና ሙያተኛ ስያሜ፤ ምዕራፍ ዐሥራ ሰባት ስለ ማዕድናት ስያሜ፤ ምዕራፍ ዐሥራ ስምንት ስለ ሽቱዎ ስያሜ በሦስቱም ቋንቋዎች ያትታሉ፡፡
ይህ ዓይነቱ  በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ የቋንቋ ስነዳ (ተግባር) የአንዲት ሀገር  የባህልና የተፈጥሮ ሀብቷ ተጠብቆ እንዲኖር፤ እንዲያድግና ለትውልድ እንዲተላለፍ ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡ ይህም መምህር እርጥባን እንደሚለው ባህል፤ ታሪክና ቅርስ እንዲጠና፤ እንዲመዘገብ፤ እንዲጠበቅና እውቅና እንዲገኝ ያደርጋል፡፡ ቋንቋ ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማስፋትና ለማጠናከር፤ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ይረዳል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ የበለጸጉ ሀገሮች ለምሳሌ እንግሊዞች፤ ፈረንሳዮች፤ ጀርመኖች፤ ጣሊያኖች፤ ሩስኪዎች፤ ቻይናዎችና ሌሎች ሀገሮች የራሳቸው ቋንቋ በልጽጎ የዓለም መግባቢያ እንዲሆን የረጅም ጊዜ የነጻ ትምህርት እድልና የአጫጭር ጊዜ ሥልጠና በመስጠት ጭምር ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡
የግእዝ ቋንቋ የሀገራችን የሥነ ፊደልና የሥነ ጽሕፈት፤ የእምነት፤ የፖለቲካና የሥነ መንግሥት ታሪክ፤ የቅኔና የፍልስፍና፤ የሥነ ጥበብና የሥነ ምግባር፤ የዕፀዋትና የመድኃኒት፤ የሥነ ከዋክብትና የሥነ ምድር፤ የባሕረ ሐሳብና የካሌንዳር፤ የገዳማትና አድባራት፤ መስጊዳት፤ የኪነ ሕንጻና ሥነ ሙካሽ ታሪካችን ተጽፎ እሚገኝበት የሥነ ጥበብ ግምጃ ቤት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ግእዝ የራሱ ሆኖ የጥንት ፊደላትን ይዞ የተገኘ፤ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት የሴም ቋንቋዎች አንዱ የሆነ ብሔር የለሽና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት ነው:: በኢትዮጵያ ጥንታዊ ድንጋይ ላይ ጭምር ተጽፎ የተገኘውና የኢትዮጵያን የጹሑፍ ጥበብ ባለቤትነት  ያስመሰከረው ግእዝ ከሳባ፤ ከግሪክና ከአረብኛ ቋንቋዎች መካከል ዐቢይ ድርሻ ያለው ሀብታችን በመሆኑ ልንንከባከበውና በበለጠም ልንኮራበት ይገባናል፡፡ መምህር እርጥባን፤ ሥርግው ሐብለ ሥላሴን (1972) እና ታደሰ ታምራትን፤ ዮላንዴን (1972)  ባሕሩ ዘውዴን (2002) ጠቅሶ እንደጻፈው፤ በሀገራችን በቁጥር እጅግ እሚያዳግቱ የባህል የታሪክ፤ የፍልስፍና፤ የሕክምና፤ የሥነ ከዋክብት፤ የሒሳብ፤ የሕግ፤ የዜማ መጻሕፍት፤ የነገሥታት የየዕለት ውሎዎች (ዜና መዋዕሎች) በግእዝ ተጽፈው ይገኛሉ:: በየአድባራቱና በየገዳማቱም የሚገኙት ቅዱሳት ሥዕላት መግለጫ ተጽፎ የሚገኘው በዚሁ በጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ በጥንታዊው የሥዕል ሥልጣኔ ጭምር ሁነኛ ቦታ ያላት ሀገር መሆኗን የሚመሰክር ነው::
በመሠረቱ ቋንቋው ዓለማቀፋዊ፤ ሀገራዊና ሕዝባዊ እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገልገያ ብቻ አለመሆኑን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ክብርና ልዕልና ለጥንት እናቶቻችንና አባቶቻችን ይሁንና ግእዝ ያካበተው አገር በቀል እውቀት ሁሉ የኢትዮጵያውያንና የዓለሙም ሁሉ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለግእዝ ልዩ ፍቅር የነበራቸው ከውጭ አገር እንደነ አውግስጦስ ዲልማንና ዎልፍ ሌዝላው እንዲሁም ኢዮብ ሉዶልፍ የመሳሰሉ ምሁራን፤ ከአገር ውስጥም እንደነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፤ አለቃ ገብረ ማርያም፤ አለቃ ታየና ሌሎች፤ መዝገበ ቃላት እያዘጋጁ፣ መገብተ እውቀት ሆነው የኖሩትና የሚኖሩት፡፡ በአሁኑ ጊዜም ቋንቋውና ልዩ ልዩ የብራና መጻሕፍት ይዘት በአውሮፓ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለምሳሌ በጀርመን፤ ኢጣሊያ፤ ሩሲያና እንግሊዝ እንዲሁም በአሜሪካ፤ ካናዳና ሌሎች ሀገሮች ውስጥ  በሚገኙ ምሁራንና ተማሪዎቻቸው በመጠናት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ በሀገራችንም በሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለግእዝ ትኩረት ተሰጥቶትና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት ተማሪዎች እንዲማሩትና ጥናትና ምርምር እንዲሰራበት መደረጉ የሚያበረታታ ነው፡፡
በዚህ ዓይነት መምህር እርጥባን ደመዎዝም፣ እንደ ታላላቆች አባቶቻችን በጣም ከባድ የሆነውን ይህንን መዝገበ ቃላት አዘጋጅቶና በቀላሉ ለመረዳት እንድንችል ቃላቱን በየወገናቸው ለያይቶና አፍታቶ ማቅረቡ ለአንባቢዎች ምን ያህል ግልጽ ለማድረግ እንዳሰበ ያስረዳል፡፡ መጽሐፉ ለቅኔ ተማሪዎችና መምህራን ጭምር ጠቀሜታው የጎላ ሲሆን በቤተ ክርስቲያን አካባቢ በቱሪስት አስጎብኝነት ለሚያገለግሉ አስጎብኚዎችም ያለው ርባና ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም አስጎብኝዎች ያለ ተፋልሶ የቅዱሳን ሥዕላቱን፤ የነዋየ  ቅድሳቱን፤ የብራና መጻሕፍቱን ታሪክና ይዘት፤ የሰማዕታቱን፤ የቅዱሳኑንና የመላእክቱን መንፈሳዊ ተልእኮ በእንግሊዝኛ በትክክል እየተረጎሙ ለውጭ አገር ቱሪስቶች ለማስረዳት ያግዛቸዋልና ነው፡፡
 “ማዕደ ልሳናት የቋንቋዎች ገበታ፡- የግእዝ - አማርኛ - እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት” በ366 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን በ110 ብር ለገበያ ቀርቧል::


Read 2000 times