Tuesday, 16 June 2020 00:00

አፍሪካ ወደ ከፋው ጉዞ ጀ ምራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     • በኬንያ 72 የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል
                  • በመላው ዓለም 50 ሚ. ህዝብ ወደ ከፋ ድህነት ሊገባ ይችላል

             ወደ አፍሪካ ለመግባት በመዘግየቱና ገብቶም ሲለሳለስ በመሰንበቱ ብዙዎችን ግራ ሲያጋባ የቆየው ኮሮና፤ አሁን ደግሞ በአስደንጋጭ ፍጥነት በአህጉሪቱ በየአቅጣጫው መሰራጨትና የከፋ ጥፋት ለማድረስ መንደርደር መጀመሩን የአለም የጤና ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ በድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺሶ ሞቲ እንደሚሉት፤ ኮሮና ከአፍሪካ አገራት ርዕሰ መዲናዎች አልፎ ወደ ሌሎች ከተሞችና ራቅ ያሉ አካባቢዎች መዛመቱን የቀጠለ ሲሆን፣ በቂ የምርመራ መሳሪያዎችና ሌሎች ግብዓቶች አለመኖራቸው ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እያሰናከለው ይገኛል፡፡ ቫይረሱ እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ በመላ አፍሪካ ወደ 210 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ የሟቾች ቁጥርም ወደ 6 ሺህ መቃረቡን አፍሪካን ኒውስ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 56 ሺህ ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ደቡብ አፍሪካ፤ በአህጉሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ግብጽ በ38 ሺህ፣ ናይጀሪያ በ14 ሺህ፣ አልጀሪያ በ11 ሺህ እንዲሁም ጋና በ10 ሺህ 500 ተጠቂዎች እንደሚከተሉም ገልጧል፡፡ በኬንያ በኮሮና ቫይረስ ህክምና ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ 72 የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የሀገሪቱን የጤና ሚኒስቴር ጠቅሶ የዘገበው ሲጂቲኤን፣ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 19ኙ በተለያዩ የህክምና መስጫ ተቋማት ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙም ገልጧል፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ በልብ ህመም ከዚህ አለም የተለዩት የብሩንዲው ፕሬዚደንት ፒዬሬ ንኩሩንዚዛ፣ ለሞት የተዳረጉት መንግስታቸው እንዳለው በልብ ህመም ሳይሆን በኮሮና ምክንያት መሆኑን አረጋግጫለሁ ሲል ከትናንት በስቲያ የዘገበው የኬንያው ዘ ስታር ድረገጽ፤ የፕሬዚዳንቱ ባለቤትም በኮሮና በፀና ታመው ናይሮቢ በህክምና ላይ እንደሚገኙ መረጃ ደርሶኛል ብሏል፡፡ በማላዊ በድጋሚ እንዲካሄድ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለሰጠበት ቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩ ፖለቲከኞች የኮሮና ቫይረስን ችላ ብለው ህዝቡን አደባባይ እየጠሩ መቀስቀሳቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳም፣ ከሰሞኑ ደጋፊዎቻቸውን ሰብስበው ባደረጉት ንግግር “ተረጋጉ!... በማላዊ ኮሮና የሚባል ነገር የለም!...” ሲሉ በድፍረት መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት 455 ያህል ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውና 4 ሰዎችም ለሞት መዳረጋቸውን ይፋ ቢያደርግም፣ ለድጋሚ ስልጣን የቋመጡት ጆይስ ባንዳ ግን መንግስት ይህን ያህል ሰዎች በኮሮና ተያዙ፣ ይህን ያህሉ ደግሞ ሞቱ እያለ በሃሰተኛ ቁጥሮች ህዝቡን ማደናገሩን ማቆም አለበት ብለዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአፍሪካ አየር መንገዶች፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በፈረንጆች አመት 2020 ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ እንደሚያጋጥማቸውና በአህጉሩ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የሚሰሩ 3 ሚሊዮን ሰራተኞች የስራ ዕድል አደጋ ውስጥ መውደቁን አለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የከፋ ቀውስ የሚጠብቀው የአለም ኢኮኖሚ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ እያደረሰበት የሚገኘው የአለማችን ኢኮኖሚ ባለፉት 100 አመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ክፉኛ ቀውስ ውስጥ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተነገረ ነው:: አለማቀፉ ኢኮኖሚ በ2020 የፈረንጆች አመት ዕድገቱ በ7.6 በመቶ ያህል ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኦርጋናይዜሽን ፎር ኢኮኖሚክ ኮፐሬሽን ኤንድ ዲቨሎፕመንት የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ወረርሽኙ የኢኮኖሚ ዕድገታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንስባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ የአለማችን አገራት መካከል የ15 በመቶ ቅናሽ የሚጠበቅባት እንግሊዝ በቀዳሚነት ስትቀመጥ፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ ይከተላሉ፡፡ በመላው አለም ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከስራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን የጠቆመው ተቋሙ፣ በቀጣይም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ይሄው ክፉ እጣ ይደርሳቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስጠንቅቋል፡፡
በፈረንሳይ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች ከስራ ገበታቸው ይፈናቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን የዘገበው ደግሞ አልጀዚራ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ፤ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ አለማችን ባለፉት 50 አመታት ታይቶ የማይታወቅ እጅግ የከፋ የምግብ እጥረት ቀውስ እንዳንዣበበባት አስጠንቅቋል::
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በተለይ ለድሃ አገራት ዜጎች የምግብ ፍላጎትን ማሟላት እጅግ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችልና ከ50 ሚሊዮን በላይ የአለማችን ዜጎች ወደከፋ ድህነት ሊገቡ እንደሚችሉ ያስጠነቀቁት የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ መንግስታት ይህንን ቀውስ ለማስቀረት በአፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድና መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል ሲል ዘ ጋርዲያን ዘግቧል:: ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያጋጥማቸው ታላላቅ የአለማችን የንግድ ተቋማትና ኩባንያዎች ቁጥር አሁንም እያሻቀበ ሲሆን፣ ታዋቂው ስታርባክስ ኩባንያ ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ3.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን ከሰሞኑ ማስታወቁን ሲኤንቢሲ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በአመቱ የመጀመሪያው ሩብ አመት 2.35 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማጣቱን ይፋ አድርጎ የነበረው የጀርመኑ ግዙፍ አየር መንገድ ሉፍታንዛ፤ ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ 22 ሺህ ያህል ሰራተኞቹን ለመቀነስ ማቀዱን አስታውቋል፡፡ በመላው አለም ከ135 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሉፍታንዛ በቀጣይ ከሚቀንሳቸው ሰራተኞቹ መካከል ግማሽ ያህሉ በጀርመን የሚገኙ መሆናቸውን የጠቆመ ሲሆን፣ የአውሮፕላኖቹን ቁጥርም በአንድ መቶ እንደሚቀንስ መናገሩንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የስራ መቀዛቀዝና የገቢ መቀነስ አጋጥሟቸው ከዚህ ቀደም ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ የወሰኑ አየር መንገዶች በርካታ መሆናቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ከእነዚህም መካከል ብሪቲሽ ኤርዌይስ 12ሺህ፣ ሪያንኤይር 3ሺህ፣ ኢዚጄት 4ሺህ500፣ ቨርጂን አትላንቲክ 3 ሺህ ሰራተኞችን ለመቀነስ መወሰናቸውን አመልክቷል፡፡
ኒውዚላንድ እና ታይላንድ ሆኖላቸዋል
ኮሮና ቫይረስን በተሳካ መልኩ በመቆጣጠር ረገድ ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት በምትጠቀሰው ኒውዚላንድ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ከተገኘ ከሃያ ቀናት በላይ እንደሆነው ተነግሯል፡፡ በአገሪቱ በሆስፒታል ውስጥ ህክምናዋን በመከታተል ላይ የነበረችው የመጨረሻዋ የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ባለፈው ሰኞ ማገገሟን የዘገበው ቢቢሲ፣ ኒውዚላንድ ቫይረሱን መቆጣጠሯን ተከትሎ ተግባራዊ አድርጋቸው የነበሩ ገደብና ክልከላዎችን ሙሉ በሙሉ ማንሳቷንም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ኮሮና 3 ሺህ 125 ሰዎችን አጥቅቶ 58 ሰዎችን ለሞት በዳረገባት ታይላንድ፤ ባለፈው ረቡዕ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂም ሆነ ሞት አለመከሰቱን ተከትሎ፣ አገሪቱ ከቫይረሱ ነጻ ነኝ ብላ ማወጇን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ በማህበረሰቡ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የቆመው ከሁለት ሳምንታት በፊት መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ በአገሪቱ በቅርብ ጊዜያት ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡት ሰዎች በሙሉ ከውጭ አገራት የገቡ መንገደኞች እንደሆኑም አክሎ ገልጧል፡፡
በብራዚል 2 አገረ ገዢዎች በኮሮና ሙስና ተከስሰዋል
ኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋባት በሚገኝባትና በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከአለማችን አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ብራዚል፣ ሁለት የግዛት አገረ ገዢዎች ለኮሮና ህክምና የሚውሉ መሳሪያዎችን በመግዛት ሂደት ውስጥ ሙስና ፈጽመዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ሮይተርስ ዘግቧል:: ሲዘናጉ ብራዚልን ለኮሮና አሳልፈው ሰጥተዋታል ተብለው ከሚወነጀሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጄር ቦልሶናሮ ጋር ኮሮናን ለመቆጣጠር የሄዱበት መንገድ ትክክል አይደለም በሚል በግልጽ ይሟገቱ እንደነበር የሚነገርላቸው ሁለቱ አገረ ገዢዎች፣ ምንም አይነት ሙስና እንዳልፈጸሙ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኳስ እና ኮሮና
ዴሎይት የተባለው አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋም ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃ፣ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ክለቦች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከዘንድሮው የፈረንጆች አመት ገቢያቸው 1 ቢሊየን ፓውንድ እንደሚያጡ አስታውቋል፡፡
የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ካለፈው ከመጋቢት ወር ጀምሮ መቋረጣቸውንና ቀሪ ጨዋታዎች ያለ ደጋፊ በዝግ ስታዲየሞች  እንዲካሄዱ መወሰኑን ያስታወሰው መረጃው፣ የአውሮፓ የእግር ኳስ ክለቦች ከፍተኛ የገቢ መቀነስና የወጪ ጭማሪ እንደሚያጋጥማቸውም አመልክቷል::

Read 6737 times