Saturday, 20 June 2020 10:59

ኮሮና ቫይረስ ያለባቸው በቤታቸው እንዲያገግሙ ሊፈቀድ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  -  ከውጪ ለሚገቡ የተጣለው የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ገደብ፣ወደ 7 ቀን ተቀንሷል
         - በቀብር ስነ ስርዓት ላይ ተጥሎ የቆየው እግድ ማሻሻያ ተደርጎበታል
                    


          በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንደየ ኑሮ ሁኔታቸው እየታየ፣ በቤታቸው ውስጥ እንዲያገግሙ ለማድረግ የሚያስችል ፈቃድ እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ትላንት ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባሉ አንዳንድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። በዚሁ ማሻሻያ መሰረትም፤ ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ ቢያዙ የሚያገለግሏቸውን የቤተሰብ አባላትና የራሳቸውን ፍላጎት ከግምት በማስገባትና የግሰቦቹ የአኗኗር ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት መሆኑን በማረጋገጥ፣ በቤታቸው እንዲቆዩ ፈቃድ ይሰጣል ብለዋል።
ከውጪ አገር የሚመጡ ሰዎች ለአስራ አራት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ መቆየት እንደሚኖርባቸው የሚያስገድደው መመሪያም፣ ወደ ሰባት ቀናት መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ ገቢ መንገደኞቹ ከሚመጡበት አገር ባለፉት 3 ቀናት ውስጥ ተመርምረው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ካቀረቡ፣ ናሙና ብቻ ሰጥተው እንዲገቡ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በወጡ መመሪያዎች ላይ የተገለፀውና በተለያዩ ምክንያቶች የሚሞቱ ሰዎች፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከመምጣቱ በፊት የቀብር ስነ ሥርዓታቸው እንዳይፈፀም የሚከለክለው መመሪያም መሰረዙን ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል። በሌላ በኩል፤በቀብር ስነ ሥርዓቶች ላይ በብዛት መገኘትን የሚከለክለውና በ50 ሰዎች ብቻ እንዲከናወን የሚያስገድደው መመሪያ አለመሻሻሉ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4070 የደረሰ ሲሆን ሕይወታቸውን ያጡት ደግሞ 72 መድረሱ ታውቋል፡፡  

Read 1307 times