Print this page
Saturday, 20 June 2020 11:03

ዎላይታ ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆንና ጥያቄው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጠው የሀገር ሽማግሌዎች ም/ቤት ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   ዎላይታ ከማንም ጋር ሳይዳበል ራሱን የቻለ ክልል ሆኖ በአፋጣኝ እንዲቋቋም የዎላይታ ብሔር የሀገር ሽማግሌዎች (ጉተራ) ም/ቤት ጠየቀ፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች ም/ቤቱ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ ከትናንት በስቲያ በዎላይታ የክልልነት ጥያቄና ከፌደራል መንግስት እየተሰጡ ባሉ ምላሾች ዙሪያ በጥልቀት መምከሩን ጠቁሞ፤ በአሁኑ ወቅትም የዎላይታ ክልልነት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሻ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
የዎላይታ ህዝብ ጥያቄ በደቡብ ክልል ም/ቤት በሰበብ አስባብ እየታፈነ መሆኑን ያስታወቀው ም/ቤቱ፤ የፌደራል መንግስትም ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ አይደለም ሲል ወቅሷል፡፡
ም/ቤቱ ባወጣው ባለ 7 ነጥብ መግለጫው፣ የዎላይታ ህዝብ ክልል እንሁን ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄ ከሚመለከተው አካል አስቸኳይ ህጋዊ ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
የዎላይታ የክልልነት ጥያቄን ከህዝቡ ስምምነትና ፍላጐት ውጪ ከሌሎች አጐራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር ለማዳበል መታቀዱንም የሀገር ሽማግሌዎች ም/ቤቱ በጥብቅ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡ የዎላይታ ብሔር ራሱን ችሎ ለብቻው ክልል ሆኖ መዋቀር እንዳለበትም ም/ቤቱ ጠቁሟል፡፡
የሚመለከተው አካል ተገቢውን ምላሽ እስኪሰጥ ድረስም የዎላይታ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የላጋዎች (ወጣቶች)፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የመንግስት ሰራተኞችና ህብረተሰቡ ጉዳዩን በአንክሮ እንዲከታተሉ፤ ሌሎች የዎላይታ ህዝብን ጥያቄ የሚደግፉ አካላትም ተጽእኖ እንዲፈጥሩ ም/ቤቱ ጠይቋል፡፡  


Read 1386 times