Saturday, 20 June 2020 11:13

ጉባኤውና የአገር ሽማግሌዎች መማክርት የፖለቲካ ሀይሎችን የሚያቀራርብ መድረክ እያዘጋጁ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 መቀሌ የሄድነው በራሳችን ተነሳሽነት እንጂ ተልከን አይደለም”

             የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤና የአገር ሽማግሌዎች መማክርት በአገሪቱ የፖለቲካ ተቃርኖና ቁርሾ ውስጥ ያሉ ሁሉም ሀይሎች ተሰባስበው የሚነጋገሩበት መድረክ ለማዘጋጀት ማቀዱን የገለፀ ሲሆን፤ በዚህ ረገድም የፌደራል መንግሥቱን ከሚመራው ብልፅግና ፓርቲ በኩል በጎ ምላሽ መገኘቱን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል።
ከሰሞኑ የሀይማኖት ተቋማት አባቶችና ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት አባላት ወደ መቀሌ አቅንተው ህወኃትን ያነጋገሩት ማንም ልኳቸው ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት እንደነበር አስረግጠው የተናገሩት ቀሲስ ታጋይ፤ የሽማግሌዎቹ የጉዞ ወጪም ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነው በሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
“ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ በራሱ ወጪ ቻርተር አውሮፕላን ተከራይቶ ነው ወደ መቀሌ የተጓዝነው፤ ይህም የሆነው ሂደቱ ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ እንዲሆን በማሰብ ነው” ብለዋል ቀሲስ ታጋይ ታደለ።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤውም ሆነ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት የሽምግልና አላማ በህወኃትና በብልፅግና ወይም በሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች መካከል እርቅ ለመፈፀም ሳይሆን ተቀራርበው ለመነጋገር እንዲችሉ ለማግባባት ብቻ መሆኑንም ቀሲስ ታጋይ አስረድተዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የፖለቲካ ሀይሎች የውስጥ አንድነት አሳሳቢ በመሆኑ ለውጭ ሀይሎች ጥቃት እንዳያጋልጠን በመስጋት ነው የሽምግልና ሂደቱ የተጀመረው፤ ለዚህ ሂደት ሁሉም ወገን የድርሻውን ማበርከት አለበት” ብለዋል።
የሽምግልናው አላማ የሁለቱንም ወገኖች ቅሬታና አቤቱታ ሰምቶ ማሸማገል ሳይሆን የየራሳቸውን አጀንዳ ይዘው ተቀራርበው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ስለ አገራቸው ጉዳይ በጥልቀት የሚመክሩበትን ሂደት ማመቻቸት ብቻ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በአገሪቱ አሉ የተባሉ ተቃርኖዎች በሙሉ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ነው ዋናው አላማችን ያሉት ቀሲስ ታጋይ፤ ከመቀሌ መልስ ብልፅግና ፓርቲን ማነጋገራቸውንና ከፓርቲው አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች መፍትሄ የሚሹ ተቃርኖዎች መኖራቸውን የገለፁት ዋና ፀሐፊው፤ አጠቃላይ አገራዊ ሰላምና አንድነት ለማምጣት ሁሉም ሀይሎች አዲስ አበባ ተገናኝተው መምከር አለባቸው ብለዋል።
የአገሪቱን ብሄራዊ አንድነት ለማስጠበቅ በእጅጉ ጠቃሚ ነው የተባለውን የፖለቲካ ሀይሎች የምክክር መድረክ ዝግጅት ሁሉም የህብረተሰብ አካል በበጎ ተመልክቶ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።   

Read 1711 times