Saturday, 20 June 2020 11:51

አለም ከወራት የኮሮና ጭንቀት በኋላ በጎ ሰማች - ዴክሳሜታሶን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ8.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ከ453 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን፤ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ብዛት ደግሞ 4.5 ሚሊዮን ያህል መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ከ2.24 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተጠቁባት አሜሪካ፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ120 ሺህ በላይ መድረሱን የዎርልዶሜትር ድረገጽ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በብራዚል ከ960 ሺህ፣ በሩስያ ከ562 ሺህ፣ በህንድ ከ373 ሺህ፣ በእንግሊዝ ከ300 ሺህ በላይ መድረሱን የጠቆመው ድረገጹ፤ የሟቾች ቁጥር ደግሞ በብራዚል 47 ሺህ፣ በእንግሊዝ 42 ሺህ፣ በጣሊያን 34 ሺህ በስፔን 27 ሺህ መድረሱን አመልክቷል፡፡
መላው አለም ለኮሮና መፍትሄ የሚሆን መድሃኒት ወይም ክትባት ለማግኘት ደፋ ቀና በማለት ላይ ከሚገኙ 120 በላይ ኩባንያዎችና የምርምር ተቋማት አንዳች የምስራች እንሰማ ይሆናል በሚል ተስፋ ቀናትን መቁጠር ከጀመረ ከወራት በኋላ፤ ባለፈው ሰኞ ከወደ እንግሊዝ አንድ በጎ ነገር ተሰማ:: የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ዴክሳሜታሶን የተባለው መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ በጽኑ ከታመሙ ሰዎች የአንድ ሦስተኛውን፣  ኦክስጂን ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች የአንድ አምስተኛውን ሞት ሊቀንስ እንደሚችል በምርምር ማረጋገጣቸውን ለአለም ይፋ በማድረግ፣ የምርምር ውጤታቸውን ለአለም የጤና ድርጅት አቀረቡ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምም፤ ዴክሳሜታሶን ኦክስጂንና የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ በሚያስፈልጋቸው የኮሮና ቫይረስ ህሙማን ላይ የሚያጋጥምን ሞት የሚቀንስ የመጀመሪያው መድሃኒት መሆኑን በመግለጽ፣ ለዚህ ታላቅ ግኝት አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ለሆስፒታሎችና ለህሙማን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።  ያም ሆኖ ግን ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፤ መድሃኒቱ በጸና ለታመሙ ሰዎች እንጂ ቀለል ያለ ህመም ላለባቸው ሰዎች የሚጠቅም አይደለም፤ የአለም የጤና ድርጅትም አደራችሁን በጽኑ ያልታመማችሁ ሰዎች መድሃኒቱን ወስዳችሁ ለከፋ አደጋ እንዳትዳረጉ ሲል አስጠንቅቋል፡፡
ዴክሳሜታሶን ላለፉት 60 ያህል አመታት በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የሚያጋጥሙ እብጠቶችን ለመቀነስና የተወሰኑ አይነት የካንሰር ህመሞችን ለማከም ጥቅም ላይ ሲውል መቆየቱን ያስታወሰው ሮይተርስ፤ ዋጋው ርካሽ ከመሆኑ በተጨማሪ በብዛት እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡ ነገርዬው በጭንቅ ለተያዘች አለም ተስፋ ሰጪ መልካም ዜና መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ መድሃኒት ተገኝቷል ብለው የሚዘናጉ ሰዎችን ለከፋ አደጋ እንዳይዳርግ መሰጋቱንም ዘገባዎች እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡

ያልተነገሩ 130 ሺህ ሞቶች
ዎርልዶሜትር ድረገጽ እና ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ፤ መንግስታትና ተቋማት የሚሰጡትን የአገራት የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር እየደመሩ እስካሁን በመላው አለም ከ440 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት እንደተዳረጉ ቢነግሩንም፣ ቢቢሲ ግን ቁጥሩ ከዚህም ይልቃል፤ ተጨማሪ 130 ሺህ ያህል ሰዎች ከኮሮና ጋር በተያያዘ ለሞት መዳረጋቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በአለም ዙሪያ ከሚገኙ 27 አገራት የሰበሰብኳቸውን ይፋዊ የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር በማጥናት ያገኘሁት ውጤት፣ አገራቱ ካመኗቸውና መገናኛ ብዙሃን ከዘገቧቸው በእጅጉ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸውን የሚያረጋግጥ ነው ብሏል ቢቢሲ፡፡ የቫይረሱ ስርጭት በላቲን አሜሪካ፣ ሕንድና አፍሪካ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ በመንግሥታት ሪፖርት የማይደረጉ የሟቾች ቁጥር መጨመሩን እንደሚቀጥል መገመቱንም ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

አፍሪካ
ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አፍሪካ ወደ 270 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ ከ7 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ደግሞ ለሞት መዳረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኮሮና የሚጠቁ ዜጎቿ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እያደገ ወደ 12 ሺህ የደረሰባት ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና፣ ከሰሞኑ ጭምብል ማድረግን ግዴታ የሚያደርግ መመሪያ ማውጣቷ ተዘግቧል፡፡
ቻይናዊው ቢልየነር ጃክ ማ፤ ለኬንያውያን በእርዳታ መልክ የላኳቸው የተለያዩ የኮሮና ህክምና ቁሳቁሶች ድንገት የውሃ ሽታ መሆናቸውን በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረገው የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር፣ ጉዳዩን በመመርመር ቀናትን ቢያሳልፍም ይህ ነው የሚባል ውጤት አለማግኘቱን ከትናንት በስቲያ ገልጧል፡፡ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን ጨምሮ ከጃክ ማ የተላኩትና  መጋቢት 24 ቀን በመዲናዋ ናይሮቢ የደረሱትን ቁሳቁሶች የመነተፉትን ሰዎች የማፈላለጉ ጥረት ግን ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነግሯል፡፡
ኬንያ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች በሞቱ በ48 ሰዓታት ውስጥ እንዲቀበሩ አውጥታ የነበረውን አወዛጋቢ ደንብ ከሰሞኑ ማላላቷ የተነገረ ሲሆን፣ የሟቾች አስከሬን በጥንቃቄ እስከተያዘ ድረስ በፈለጋችሁ ጊዜ መቅበር ትችላላችሁ የሚል መልዕክት ለዜጎቿ አስተላልፋለች ተብሏል፡፡
የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ፤ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ተዘግተው የነበሩ የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ እንዲከፈቱ እና ዜጎች አቋርጠውት የነበረውን የማህበራዊ ሕይወታቸውንም ሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸውን እንዲቀጥሉ ማሳሰባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

የክትባቱ ነገር…
የአለም የጤና ድርጅት 10 ያህል ተስፋ ሰጪ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች በሰዎች ላይ በመሞከር ላይ እንደሚገኙና በመጪዎቹ 6 ወራት ጊዜ ውስጥ በመላው አለም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የኮሮና ክትባቶች ይመረታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ በድርጅቱ ዋና ተመራማሪ የሆኑት ሱምያ ስዋሚናታንን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ አገራት የክትባቶች ፍቱንነት ሳይረጋገጥ ገና ከአሁኑ ከመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር የግዢ ስምምነት መፈጸም የጀመሩ ሲሆን እስከ መጪው አመት 2021 መጨረሻም 2 ቢሊዮን ያህል ክትባቶች ሊመረቱ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
ድርጅቱ እውቅና የተሰጣቸውን ክትባቶች በቅድሚያ ማግኘት ያለበት ማን ነው በሚለው ጉዳይ ዙሪያ እቅድ እያወጣ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በኮሮና ህክምና ላይ ለተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎች፣ በዕድሜና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የቫይረሱ ስርጭት ሰፊ በሆኑባቸው እስር ቤቶችን የመሳሰሉ ቦታዎች ለሚኖሩና ለሚሰሩ ሰዎች ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚችልም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎችን ለማከም ይረዳል ተብሎ የተነገረለት ሃይድሮክሎሮኪን የተባለው የወባ መድሃኒት፣ ለኮሮና ታማሚዎች ፍቱን አለመሆኑን ማረጋገጡን ተከትሎ፣ በመድሃኒቱ ላይ ሲያደርግ የቆየውን ጥናት ማቋረጡን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ40% በመቶ ይቀንሳል
የአለማችን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በ2020 የፈረንጆች አመት የ40 በመቶ ቅናሽ እንደሚያሳይና እ.ኤ.አ ከ2005 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በታች ይወርዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመድ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባኤ ባወጣው የ2020 ሪፖርቱ እንዳለው፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት 1.54 ትሪሊዮን ዶላር የነበረው አለማቀፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘንድሮ ከ1 ትሪሊዮን በታች ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣዩ  አመት ደግሞ እስከ 10 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ይገመታል፡፡

489 የሩስያ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ሞተዋል
የሆንዱራሱ መሪ
ከነባለቤታቸው በቫይረሱ ተይዘዋል
በሩስያ በአንድ ወር ብቻ ከ300 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውንና በአገሪቱ እስካሁን በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ባለሙያዎች አጠቃላይ ቁጥር 489 መድረሱን ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡
በሌላ ዘገባ ደግሞ የሆንዱራንስ ፕሬዚዳንት ዩዋን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ፣ ባለቤታቸው እንዲሁም ሁለት ረዳቶቻቸው በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

90% የአለማችን ሙዚየሞች ተዘግተዋል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱንና መስፋፋቱን ተከትሎ በመላው አለም ከሚገኙት ሙዚየሞች መካከል 90 በመቶ ያህሉ አገልግሎታቸውን አቋርጠው ተዘግተዋል ተብሎ እንደሚገመት ተመድ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል:: በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በአለማችን ከሚገኙት 95 ሺህ ሙዚየሞች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በኮሮና ሳቢያ ጎብኚ በማጣታቸውና ገቢያቸው እጅጉ በመቀነሱ በሮቻቸውን ዘግተዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከተዘጉት ሙዚየሞች መካከል 13 በመቶ የሚሆኑት ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ዳግም ወደ ስራ ይመለሳሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ የጠቆመው ተቋሙ፤ 33 በመቶ ያህሉ ደግሞ ስራ ቢጀምሩ እንኳን ከቀድሞው አቅማቸው በእጅጉ ቀንሰው እንደሚሆን አመልክቷል፡፡
በወረርሽኙ ሳቢያ አገልግሎታቸውን ካቋረጡና ለወደፊትም ዳግም ወደ ስራ ይመለሳሉ ተብለው ከማይጠበቁ ተዘግተው የሚቀሩ ሙዚየሞች መካከል አብዛኞቹ በአፍሪካ፣ በአረብና በፓሲፊክ አገራት እንደሚገኙ የጠቆመው ተቋሙ፤ ይህም የአገራቱ ባህል፣ ታሪክና ሳይንስ እንዲጠፋ በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡

በህንድ በ1 ቀን 13 ሺህ ተጠቂዎች ሲገኙ፣ በጀርመን 7 ሺህ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል
በህንድ ባለፈው ረቡዕ ብቻ 13 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና ይህም በአገሪቱ ከፍተኛው ዕለታዊ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መሆኑን ሂንዱስታን ታይምስ ዘግቧል፡፡
በዕለቱ በመላ አገሪቱ 12 ሺህ 881 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ የጤና ተቋማት ማስተናገድ ከሚችሉት በላይ ቁጥር ባላቸው ታማሚዎች መጨናነቃቸውንና ደልሂ እና ሙምባይን በመሳሰሉ የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ሆስፒታሎች ታማሚዎችን ላለመቀበል መወሰናቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በጀርመን ከሰሞኑ 650 የቄራ ሰራተኞች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ፣ ከ7 ሺህ በላይ ተጠርጣሪ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
 
ቤጂንግ እንደገና…
ወረርሽኙን ተቆጣጥሬዋለሁ ብላ እገዳና ክልከላዎችን ባነሳችው የቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ፣ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከሰሞኑ እንደገና ጭማሪ ማሳየት የጀመረ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም ተነስተው የነበሩ አስገዳጅ መመሪያዎች እንደገና እንዲጣሉ የከተማዋ አስተዳደር መወሰኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ለ57 ቀናት ያህል በማህበረሰቡ ውስጥ ምንም አይነት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ባልተመዘገበባት ቤጂንግ፣ ከሰኞ እስከ ረቡዕ ብቻ 17 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡


Read 12049 times