Print this page
Saturday, 20 June 2020 12:26

የቀበሮ ባህታዊ፣ የቆቅም ለማዳ የለውም!

Written by 
Rate this item
(11 votes)

  በአብዛኛው፤ የኢትዮጵያ ተረቶች ወጎችና ትርክቶች መነሻቸው አንዳች ዕውነታ ነው። ስለሆነም ታሪካዊ አመጣጡን አንወቅ እንጂ መነሻ ሥረ መሰረት አለው። እነሆ ለአስረጂነት፡-
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ አንቱ የተባሉ የቅኔ መምህር፣ ጎጃም ውስጥ ይኖሩ ነበር። በዚያ የቅኔ ቤት ባህል፣ የቆሎ ተማሪዎች ሲመረቁ በአካባቢው ያሉ የቅኔ መምህራን ይጠሩና ለተመራቂዎቹ ጥያቄ ያቀርባሉ። ተማሪዎቹም እንደየ ብቃታቸው መልስ ይሰጣሉ - ቅኔ ይዘርፋሉ፣ ይፈታሉ። ይሄ ሥነ ሥርዓት ከመካሄዱ አስቀድሞ ግን ዋናው የቅኔ ቤቱ መምህር ቅኔ ይዘርፋሉ። በዚያም በዚህ ደረጃ የምገኝ ባለቅኔ ነኝ ዛሬ ልጆቼን የማስመርቀው እንደ ማለት ያህል ክህሎታቸውን ያሳያሉ።
በዚህ መካከል እኒያ መምህር “ታምሪሃ ለቤዛ” የሚል ቃል ሲያወጡ፤ “ታምሪሃ”ን አላልተው ማለት ሲገባቸው እርግጥ አድርገው “ሪ”ን በጣም አጥብቀው አነበቡ።
ይሄኔ ከሚመረቁት ተማሪዎች አንዱ፤ “የኔታ ልመልስዎት?” አለና ጠየቀ።
“ታምሪሃን አላልተው ማለት ሲገባዎት አጥብቀውታል” አላቸው።
የኔታ አፈሩ። ምነው ቢሉ የሚያስመርቁት ልጅ፣ ገና መጤ ተማሪ ነዋ! ግድ ነውና የኔታ አላልተው ደገሙት።  
የዛሬው ቅኔ በዚሁ ተጠናቆ እንግዶቹ ተመለሱ፤ የጎንደሮቹም ወደ ጎንደር፣ የሸዋዎቹም ወደ ሸዋ… ወደ የቅኔ ቤታቸው ሄዱ። የየኔታ ቤት ከፍታ ቦታ ላይ ነው።
በነገታው የኔታ ግቢያቸው ካለ የወይራ ዛፍ ላይ የወይራ አርጩሜ ይመለምሉና ጋቢያቸው ውስጥ ይደብቃሉ። ይህንን ሲያደርጉ ያ የቆሎ ተማሪያቸው፣ ታች ነውና ቤቱ፣ ሽቅብ ሲመለከት የኔታ የሚያደርጉት ሁሉ ፍንትው ብሎ ይታየዋል።
የኔታ ወደ ቅኔ ትምህርት ቤት መጡ። ያም ተማሪ መጥቷል። ትምህርቱ ተጀመረ። የኔታ ቅኔ ሲጀምሩ “ለማስታወስ ያህል ትላንት የቅኔ መምህራኑ ፊት የዘረፍኩትን ቅኔ ልድገምላችሁ”፤ አሉና ቅኔውን ጀመሩ። ከዚያም “ታምሪሃ” ጋ ደረሱ። ልክ እንደ ትላንቱ፤
“ታምሪሃ ለቤዛ” ብለው፣ ጠበቅ አድርገው ተናገሩት።
ተሜ፤ ዝም!
አሁንም ደግመው ማላላት ሲገባቸው አጥብቀው፤
“ታምሪሃ!” አሉ።
ተሜ፤ አሁም ዝም።
በሦስተኛው ተናደውና ጮክ ብለው፤
“ኧረ ታምሪሃ!” አሉ፤ እጅግ አጥብቀው። ተሜ ዝም፤ አለ።
የኔታ በንዴት፡-
“አንተ፤ አትመልሰኝም እንዴ?” ብለው ጠየቁት።
ተሜም፤
“አይ የኔታ፤ ይህቺማ ውስጠ - ወይራ ናት!” አለ!
*   *    *
መምህር ተማሪው ሲጎብዝለት ሊደሰት ይገባዋል። እንዲያውም እንዲበረታታ፤ “በዚሁ ቀጥል!” ማለት ሲገባ አርጩሜ ቀጥፎ ለመግረፍ መዘጋጀት ከመልካም መምህር የሚጠበቅ አይደለም፡፤ በእርግጥ አበው እንደሚሉት፤
“አዬ! አስተማሪ፣ ያለበት አባዜ
አስተዋይ ተማሪ፣ የጠየቀው ጊዜ”
ተብሎ መጠቀሱ፣ አንድም የአስተማሪውን አለመዘጋጀትና ሥጋት፤ አንድ ከተማሪዎቹ መካከል የተባ አዕምሮ ያለው ንቁ ተማሪ ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁመን ነው።
ለወትሮው ተማሪና አስተማሪ፣ ግብረ ገብን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ነበር የሚያስተሳስራቸው።
- አስተማሪ፤ የእውቀት የበላይ ነው።
- አስተማሪ፤ የሥነ ምግባር አርአያ ነው።
- አስተማሪ፤ ከወላጆች ቀጥሎ እናት አባትን የሚተካና የህይወትን አቅጣጫ አስተካክሎ የሚጠቁም ተወርዋሪ ኮከብ ነው!
- አስተማሪ የልብን የሚያይ ነው።
- አስተማሪ የወላጆች ምትክ ነውና ቢቀጣ ያምርበታል። ቢቆጣ ይሰማለታል።
- አስተማሪ የመማር ማስተማርን ሂደት ከሚያቀላጥፉ ሀይሎች አንዱ ነው፡፡
በህብረተሰብ ዕድገት ውስጥ ሞተር ስለሆነ ነው ስለ ወጣት ስናነሳ፤
- “ወላጁ ማነው?” ብሎ መጠየቅ ደግ የሚሆነው።
- “መምህሩ ማነው?” ቀጣዩ ጥያቄ ይሆናል።
- “ጓደኛው ማነው?” የዛን ያህል ተገቢ ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል።
- “የት አካባቢ ነው ት/ቤቱ?” ወዘተ. ማለትም አይቀሬ ነው፡፡
ችግኝ ስንተክል ልጅ የማሳደግን ፋይዳ አብረን እሳቤ ውስጥ እየከተትን ቢሆን፣ ዕፅዋት ወ እንስሳት እንዲሉ ምሉዕነት ይኖረናል (Flora and Fauna እንዲሉ፤ ከልጅ እስከ አዋቂ ለአገር ዕድገት አሰለፍን እንደ ማለት ነው።)
ከቶውንም አገርን ስናለማ በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ ሆነን እንዳልሆነ ልባችን ሊያውቀው ይገባል፡-
“እንደ እባብ መሰሪ፣ እንደ እባብ ጠቢብ፤
ሆነህ አገልግላት የዋሂቱን ርግብ”
የሚባለው በዚህ ጊዜ ነው። ከመንገዳችን ላይ እንቅፋት መቼም ቢሆን እንደሚኖር አስተውለን ለዚያም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዝግጁነት ሊኖረን የግድ ነው። እንደ አንዳንድ ፀሐፍት አስተምህሮ፤ “ገንዘብ የሚገኘው አንድም አገር ስትለማ፣ አንድም አገር ስትጠፋ ነው። አገር ስትጠፋ ቶሎ መበልፀግ ይቻላል። አገር ስትለማ ግን ብልፅግናው የሚገኘው ቀስ በቀስ ነው” ይባላል። በሙስናዊ መንገድ ቶሎ ባለሀብት እሆናለሁ ብሎ ማቀድ የሙሰኞች ሁሉ ምኞት ነው። በላቡ፣ በወዙ አገር አለማለሁ ብሎ ደፋ ቀና የሚል ታታሪ የመኖሩን ያህል፤ “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ብለው የሚያደቡ እኩይ ጮሌዎችም መኖራቸውን አንዘንጋ፡፡
“በሀዘን ቤት ደረት መቺ አልቃሽ፤ በሰርግ ቤት አፋሽ አጎንባሽ” መቼም ቢሆን ጠፍቶ አያውቅም። እንዲህ ያሉት ደግሞ መቼም ቢሆን መቼም የታረሙ፣ የተቀጡ ይመስለናል እንጂ “ዞሮ ዞሮ አካፋ አካፋ” ነው። ስለሆነም እርምጃ መውሰድ፣ ለመቅደምም መፍጠን፣ ግዴታና ዋና ነገር ነው። ከሰው ቀድመው ለአገር አሳቢ ለመምሰል ተፍ ተፍ፤ ቀደም ቀደም ለሚሉ “ሐሳዊ መሲሆች” በግልፅ ቋንቋ  “የቆቅ ለማዳ የለውም” ብሎ እቅጩን መንገር ያስፈልጋል።
“በአሮጌ ጋን አዲስ ጠላ እንጥመቅ” በሚሉን መሸንገልም ሆነ፣ መጭበርበር የለብንም። ይልቁንም “አባይን የማውቀው ዱሮ ጭብጦዬን የወሰደብኝ ጊዜ ነው”፤ ‘በዱሮ በሬ ደግሞ ያረሰ የለም’ ብሎ አይንን መግለጥ የአባት ነው።
የቀበሮ ባህታዊ፣ የቆቅም ለማዳ የለውም!!   


Read 14071 times
Administrator

Latest from Administrator