Print this page
Saturday, 20 June 2020 12:15

አፍም መናገሪያ፣ ጆሮም ‘መናገሪያ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡— ዛሬ ደግሞ ምነው ጩኸት፣ ጩኸት አለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ላድርግ ብለህ ነው አንድዬ! ምን ላድርግ ብለህ ነው! ጮሄም አልሆነልኝም፡፡
አንድዬ፡— ደግሞ ዛሬ ምንድነው የማየው! አንደኛህን የሰፈርህን ሰው በሙሉ አስከትለህ መጣህ! ይሄ ሁሉ ሰው ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— በምን አቅሜ ላቁማቸው! አንድዬ፣ ዘንድሮ እንደሁ ትልቁም፣ ትንሹም ጉልበተኛ ሆኗል፡፡ እንደውም ጉልበት በሌለው ጉልበተኛ ብዛት ከዓለም አንደኛ ነን፡፡
አንድዬ፡— አብረን እንሂድ ሳትላቸው ነው የተከተሉህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ግማሽ መንገድ ከደረስኩ በኋላ እኮ ነው፣ ዘወር ስል ድፍን ስታዲየም ሲከተለኝ ያየሁት፡፡
አንድዬ፡— እኔ እኮ ድንገት ሳያችሁ እነኚህ ሰዎች የምድሩን ጨረሱና ነው እንዴ እኔ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡት ነው ያልኩት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…እንደሱ አትበል፡፡ እንደሱ ስትል ክፍት ነው የሚለኝ::
አንድዬ፡— እኮ የምትሄድበትን ሳያውቁ ዝም ብለው ተከተሉኝ ነው የምትለው?
ምስኪን ሀበሻ፡—  አንድዬ፣ አብዛኞቹ ወደ ገደል ልሂድ፣ ወደ ገዳም  ምኑንም አያውቁት:: ብቻ የሆኑ ሰዎች “ሆ” በሉ ሲሏቸው፣ “ሆ” ብለው የተከተሉ ናቸው፡፡ አንድዬ የደበ “ሆ” በዝቶ እኮ ነው የተቸገርነው፡፡
አንድዬ፡— እሱን እንደ ፍጥርጥራችሁ:: እና ያለ መሪ ተግተልትለው መጡ ነው የምትለኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ መሪ ነን የሚሉት ከሁለትና ሦስት የማይበልጡ ናቸው፤ ይሄ ሰውዬ እዛ የሚመላላሰው የሆነ ጥቅም ቢኖረው ነው ብለው አካፍለን ሊሉ ነው የመጡት፡፡
አንድዬ፡— ከምኑ ነው የምታካፍላቸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑን አውቄ አንድዬ፣ ምኑን አውቄ! ዘንድሮ አኮ ሌላው ሰው በረኪና እንኳን ሲጠጣ ቢያዩት ጥቅም ቢኖረው ነው ብለው ነገ በረኪና ለመግዛት ግፊያ ነው የሚሆነው፡፡
(ከሰዎች ሁካታ ይሰማል)
አንድዬ፡— አንድ ለአንድ አላቻልኳችሁ፣ ጭራሽ በደቦ ልትነተርኩኝ ነው የመጣችሁት::
ተሰላፊ አንድ፡— እንደሱ አይደለም፣ አንድዬ! እሱ የሚልህን አንድም ነገር እንዳትሰማው፡፡ የሚነግርህ ሁሉ ውሸቱን ነው፡፡ ምድር ላይ የታወቀ ውሸታም ነው፡፡
ተሰላፊ ሁለት፡— አንድዬ፣ ስለ እኛ የሚነግርህን አትመነው፡፡ እኛ አንተ ላይ ጀርባችንን አላዞርንም፡፡ ያለ ሀጢአታችን ነው ስማችንን የሚያጠፋው፡፡
አንድዬ፡— ቆይ ተረጋጉ… (ሁካታው ይጨምራል፡፡) የምታዳምጡኝ ካልሆነ መሄዴ ነው፡፡
(ጸጥታ ይሰፍናል፡፡)
አንድዬ፡— እሱ እኔ ዘንድ ሲመጣ ስለ ሀገርና ስለ ህዝብ ነው እንጂ የሚያወራው የማንንም ስም በክፉ አያነሳም፡፡ አንድም ቀን የማናችሁንም ስም አጥፍቶ አያውቅም፡፡
ተሰላፊ አንድ፡— አንድዬ፣ ሰውዬውን በደንብ ስለማታውቀው ነው፡፡
ተሰላፊ ሁለት፡— የለየለት ማሽንክ ነው…ጥሩ የተናገረ መስሎ በሆዱ ግን እሾህ ነው፡፡ በአስመሳይነት የሚችለው የለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንድም ነገር እንዳትሰማቸው፡፡ እኔ…
አንድዬ፡— ቆይ እስቲ፣ ዛሬ እነሱን ልስማቸው፡፡ እንግዲህ እኔ ነገርኳችሁ…አንድም ቀን ስለ ሌላው ሰው ክፉ ተናግሮ አያውቅም፡፡
ተሰላፊ አንድ፡— አንድዬ፣ አንተ የምትሰጠውን ነገር አንድም ቀን አካፍሎን አያውቅም፡፡
ተሰላፊ ሁለት፡— አዎ፣ ተደብቆ ብቻውን ነው የሚጠቀመው፡፡ አንዲትም ነገር አካፍሎን አያውቅም፡፡
አንድዬ፡— ስሙኝ፣ አንድ ጊዜ ስሙኝ…እሱ እዚህ መጥቶ የሚለምነው ሀገር ሰላም እንድትሆን፣ ህዝቡም እንዲፋቀር ነው፡፡ ይልቅ አሁን እናንተ ናችሁ ስሙን እያጠፋችሁ ያላችሁት፡፡
ተሰላፊ ሦስት፡— የምሰጥህን አካፍላቸው በልልን፡፡
አንድዬ፡— አድምጡኝ አንጂ፣ እዛ ምድር ላይ ያለውን ያለ መደማመጥ ባህሪያችሁን እዚህ አታምጡብኛ! ምንም ነገር ሳልሰጠው ምኑን ነው አካፍላቸው የምለው! ነገርኳችሁ፣ ከዚህ አንድም ነገር አግኝቶ አያውቅም፡፡
ተሰላፊ ሁለት፡— ታዲያ እዚህ ደርሶ ሲመለስ ፊቱ ቅቤ የጠጣ ማሰሮ የሚመስለው ለምንድነው! ወዙ እንዲህ እኮ ነው ጠብ፣ ጠብ የሚለው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ተስፋ ነዋ! እዚህ መጥቼ ስመለስ ተስፋ በኩንታል እየጫንኩ…
ተሰላፊ ሦስት፡— ይኸው ይኸዋ! በኩንታል እየጫንኩ እያለ ነው!
(የስምምነት ሁካታ)
ምስኪን ሀበሻ፡— አየህልኝ አይደል አንድዬ፣ አየህልኝ አይደል! ጉዳዬን ተናግሬ እስክጨርስ እንኳን አልጠበቁኝም፡፡
ተሰላፊ ሁለት፡— ምኑን ነው የምንጠብቀህ…
ተሰላፊ አንድ፡— ኩንታል ብሎ ቶን እስኪል እንድንጠብቀው ነዋ! አንድዬ፣ ይሄን ስግብግብነት አየህልኝ አይደል!
አንድዬ፡— እስቲ ረጋ በሉ፣ በትንሽ በትልቁ እርስ በእርሳችሁ እየተናከሳችሁ እንዴት ይሆናል! ቢያንስ ከእኔ ዘንድ ጨርሳችሁ እስከትሄዱ ድረስ እንኳን ብትደማመጡ ምን እንዳይቀርባችሁ ነው! እኔንም እኮ ግራ አጋባችሁኝ!
(“ይጨርስ፣ ይጨርስ፣” ይባላል፡፡)
ምስኪን ሀበሻ፡— እኔ ልል የፈለግሁት ከዚህ ስመለስ ፊቴ የሚበራው ተስፋ በኩንታል እየጫንኩ ስለምመለስ ነው፡፡ አሁን ገባችሁ፡፡
ተሰላፊ ሦስት፡— (በሹክሹክታ) ተልባ በኩንታል ነው ያለው?
ተሰላፊ አንድ፡— (በሹክሹክታ) እሱ ያው ተስፋ ነው፡፡ ተልባ ያለው ትናንት ስትጠጣ ያደርከው ጠጅ ነው፡፡
አንድዬ፡— ይኸው ሰማችሁት አይደል! ተስፋን አይደለም በኩንታል፣ መርከብ ሙሉ ጭኖ ቢመለስ ለእናንተም ይተርፋል እንጂ የማናችሁ ቤት እንዳይፈርስ ነው!
ተሰላፊ አራት፡— አንድዬ፣ አንድዬ…አንድ የምታደርግልን አጣዳፊ ነገር አለ…
አንድዬ፡— (በመሰላቸት) እሺ…ደግሞ ምንድነው?
ተሰላፊ አራት፡— አንድዬ፣. ሁላችንንም እንዲህ በመደዳ ደርድረንና ፋቀን…
አንድዬ፡— ምን! ምን አድርገን ነው ያልከው!
ተሰላፊ አራት፡— ፋቀን አንድዬ፣ ሁላችንንም ተራ በተራ ፋቀንና ይለይለን፡፡ አጭበርባሪ በዝቷል…
ተሰላፊ ሦስት፡— አንዱ አጭበርባሪ አንተ ራስሀ አይደለህም!
ተሰላፊ አምስት፡— አንተኛው ደግሞ አፍ አለኝ ብለህ ታወራለህ! አናውቅህምና ነው!
ተሰላፊ አራት፡— ዛፍ በሌለበት እንቧጮ አድባር ይሆናል አሉ፡፡ ሁልሽም የጠላት ተልዕኮ ይዘሽ የተሰባሰብሽ ነሽ…
(ይተረማመሳል)
አንድዬ፡— (ቆጣ ብሎ) በቃ!  በቃ! አሁንስ አበዛችሁት፡፡ ምን እንሁን ነው የምትሉት:: ዘላለማችሁን ጣት እየተቀሳሰራችሁ ክንዳችሁንስ አይደክመውም!
ተሰላፊ አምስት፡— አንድዬ፣ በሀገሩ እኮ ምንም ሰው የለበትም..
ተሰላፊ አንድ፡— አንተ ብቻ ነሃ ሰው! የእኛ ምሁር፣ የእኛ አዋቂ!…
አንድዬ፡— ጣጣ! ምስኪን ሀበሻ፤ ሌላ ጊዜ ወደ እኔ ለመምጣት ስታስብ ገና ከቤትህ ስትነሳ ጀምረህ ጀርባህን ገልመጥ እያልክ እያየህ፡፡ አይደለም እንዲህ ሺህ ሰው፣ አንዲት ትንኝ ተከትላህ ብትመጣ የሚያናግርህ አይኖርም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ እሺ፡፡
ተሰላፊ አምስት፡— አንድዬ፣ ይልቅ ዋናው ጥያቄ አለ፡፡ ይቺን ግብጽን አንድ በልልን፡፡ አስቸገረችን እኮ!
ተሰላፊ ሦስት፡— ምን ግብጽ አስቸገረችን ትላለህ…እናንተ አይደላችሁም እንዴ የውስጥ አርበኞች!
(ሁካታው ይባባሳል፡፡)
አንድዬ፡— ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፤ እነኚህ ሰዎች ምን የሚያካክል አፍ ስፈጥርላቸው ትንሽዬ እንኳን ጆሮ ሳልፈጥርላቸው ረስቼ ይሆን እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ ምን በወጣህ አንድዬ፣ አሳምረህ ነው የፈጠርክልን፡፡ እኛው ነን ጆሯችንንም አፍ ካላደረግነው እያልን ያለነው!
አንድዬ፡— (በሹክሹክታ) ብቻ እኔን ማማረሩን በተዋችሁኝና እፎይ ባልኩ፡፡ ሌላ ጊዜ ግን ራስህን ችለህ ና እንጂ በቡድን አትምጣብኝ፡፡ እኔ በቡድን አልፈጠርኳችሁምና በቡድን አላውቃችሁም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ እሺ!
አንድዬ፡— አንተ ምስኪኑም በደህና ግባ::
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
(ሁሉም የየራሱን እያወራ፣ እራሱን እያዳመጠ ትርምሱ ቀጥሏል፡፡)
አፍም መናገሪያ፣ ጆሮም ‘መናገሪያ’…በምን እንደማመጥ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1988 times