Monday, 22 June 2020 00:00

ነገን ዛሬ መስራት

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

  “ዓላማችን በሃሳብ ብልጫ የሚያምን ትውልድን ማፍራት ነው”
                         
              ታዳጊዎች ራሳቸው፣ ሃሳባቸውንና ህልማቸውን በጽሑፍ ለመግለጽ የሚችሉበትን መንገድ ለማሳደግ የሚያስችል እንዲሁም በሃሳብና በምክንያት የሚያምን ትውልድ ለመቅረጽ ያለመ የሥነጽሑፍ ውድድር በየኔታ አካዳሚ አዘጋጅነት ተካሂዶ ነበር፡፡  
“የኔታ ራይተርስ ኦፍ ዘ ፊዩቸር” የሚል ስያሜ የተሰጠውን  የሥነጽሑፍ ውድድር ያዘጋጀው የኔታ አካዳሚ ሲሆን ውድድሩ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተካሄደና ከ400 በላይ የመንግስትና የግል ት/ቤቶች ተማሪዎች የተሳተፉበት ውድድር እንደነበር ታውቋል፡፡ የየኔታ አካዳሚ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጥሩወርቅ አየለ እንደሚናገሩት፤ የውድድሩ ዓላማ በሃሳብና በምክንያት የሚያምኑ፣ ለሃሳብ ብልጫ የሚገዙ፣ ሃሳባቸውንም በጽሑፍ መሰደር የሚችሉ ተማሪዎችን ለማፍራትና ልጆች የጽሑፍ ፍቅርና ፍላጐት እንዲያድርባቸው ማድረግ ነው፡፡
ታዳጊዎች ከጨለምተኝነት አስተሳሰብ ነፃ ወጥተው ራሳቸውን ፍላጐታቸውንና ምኞታቸውን በአግባቡ ለመግለጽ እንዲችሉ ማድረግና ብሩህ የሆነ ነጋቸውን ዛሬ በትጋት እንዲሰሩት ማነሳሳትም የውድድሩ ዓላማ እንደሆነ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ይናገራሉ፡፡
ከ14 እስከ 20 ዓመት እድሜ ላይ በሚገኙ ታዳጊዎች መካከል የተካሄደው ይኸው ውድድር፤ ታዳጊዎቹ አንድነት፣ ሰብአዊነት፣ መቻቻልና የአየር ንብረት ለውጥ በሚሉ እሣቤዎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤና አስተሳሰብ በጽሑፍ እንዲያንፀባርቁ የተደረገበት እንደነበርም ገልፀዋል፡፡
በውድድሩ ሁሉም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲሳተፉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ጥሪ መቅረቡን የተናገሩት የየኔታ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ከ400 በላይ ት/ቤቶች መሳተፋቸውንና የውድድሩ ዳኝነትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋና ስነጽሑፍ ዲፓርትመንት ምሁራን መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡ “ነገር ሁሉ የሚጀምረው ከሃሳብ ነው” የሚሉት ወ/ሮ ጥሩወርቅ፤ ታዳጊዎች በአገራቸው ብሎም በአለማችን ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሃሳብ በነፃነት ማውጣት የሚችሉበትን ዕድል መፍጠርም የፕሮግራሙ አላማ ነበር ብለዋል፡፡
የውድድሩ ዳኝነት ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲታይ ለማድረግ ታስቦ ኃላፊነቱ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ ጽሑፍ ዲፓርትመንት ምሁራን መሰጠቱን የጠቆሙት ወ/ሮ ጥሩወርቅ፤ ምሁራኑ ዳኝነቱን ሙያዊ በሆነ መንገድ አይተው ውጤቱን አሳውቀውናል። በዚህ መሰረትም በአማርኛ ዘርፍ አንደኛና ሁለተኛ ለወጡ ሁለት ታዳጊዎች፣ በእንግሊዝኛውም ዘርፍ አንደኛና ሁለተኛ ለወጡ ሁለት ታዳጊዎች፣ በድምሩ ለአራት ታዳጊዎች እያንዳንዱ 100 ሺ ብር የሚያወጣና የዘመኑ አዲስ ቴክኖሎጂ የሆነውን ማክሩቭ ኮምፒዩተር ሸልመናቸዋል ብለዋል።
የውድድሩ ዳኝነት እጅግ ከባድ እንደነበር የተናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጪ ቋንቋዎች ዲፓርትመንት መምህር ዶ/ር አንማው አንተነህ፤ ለመጨረሻ ውድድር ከደረሱት 106 ጹሑፎች አሸናፊዎቹን ለመለየት ቀናትን የፈጀ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
“ታዳጊዎች እጅግ የሚያስገርም ብቃት አላቸው፤ አንዳንዶቹ ጹሑፎች እኔ ብጽፈው ይህን ያህል አድርጌ መጻፍ እችላለሁ ወይ ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ አድርገውናል። ጹሁፎቹን ለመገምገም የሃሳቡን ኦርጅናልነት፣ የአጻጻፉን መንገድና የሀሳብ ቅደም ተከተል አጠባበቁን ተመልክተናል። ያየነው ነገር እጅግ አስገራሚ ነው። ልጆቹ ለውድድሩ የመረጧቸው በአብዛኛው በአገር አንድነት፣ በልዩነትና መቻቻሎቻችንና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮሩ ርዕሰ ጉዳዮችን ነው፡፡ ይህም እኒህ ጉዳዮች ልጆቹን ምን ያህል እንደሚያሳስባቸው አመላካች ነው“ ብለዋል፤ዶ/ር አንማው አንተነህ፡፡
መድረኩ በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ራሳቸውን እንዲያዩበትና እንዲፈትሹበት በማድረግ የተሻለ አቅም ያላቸውን ልጆች ለማውጣት የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም ያሉት ዶክተር አንማው፤ እንዲህ አይነት ውድድሮች ታዳጊዎችን በማነሳሳትና በማበረታታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በውድድሩ በአማርኛው ዘርፍ አንደኛና ሁለተኛ የወጡት ታዳጊዎች፡- ተማሪ ጅብሪል ኮናቴ እና ተማሪ መክሊት አበባው ሲሆኑ በእንግሊዝኛው ዘርፍ አንደኛና ሁለተኛ የወጡት፡- ተማሪ ናትናኤል ለገሰ እና ተማሪ አቢጌል ኤርሚያስ ናቸው ተብሏል፡፡  
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሥነጽሁፍ ውድድር አንደኛ የወጣው ተማሪ ናትናኤል ለገሰ በሰጠው አስተያየት፤ ሰዎች በተለያዩ አመለካከቶቻቸው በዘር፣ በቀለምና በሃይማኖት ልዩነታቸው ብቻ ኢላማ እየተደረጉ ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ ማየቱ እጅግ እንደሚያሳስበውና ይህን ስሜቱንም በጹሑፍ ለመግለጽ ሞክሮ አሸናፊ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ወደፊት ለአገሬ ውጤት ያለውና በወገኖቼ ላይ ቀጥተኛ ለውጥ የሚያመጣ ተግባር ማከናወን እፈልጋለሁ ያለው ናትናኤል፤ ለዚህ ደግሞ ከፖለቲካ የተሻለ መንገድ አለመኖሩንና ወደፊት በፖለቲካ ውስጥ በመግባት ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን እቅድ እንዳለው ገልጾልናል፡፤ በአማርኛ ዘርፍ ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል በአንደኛነት አሸናፊ የሆነው ተማሪ ጅብሪል ኪናቴ በበኩሉ፤ ውድድሩ ሃሳቡን በነፃነት ለመግለጽ የሚችልበትን መንገድ ያመላከተው መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህም በሃሳብ የበላይነትና በምክንያት ለማመን የሚችልበትን ሁኔታ አመላክቶናል ብሏል። “ለውጥ የሚመጣው ከውስጥ ነውለ፤ሰው ውስጡን መለወጥ ከቻለ አካባቢውን ብሎም አገሩን ከመለወጥ የሚያግደው ነገር የለም፤ ስለዚህም ሁላችንም በመጀመሪያ ውስጣችንን ለመለወጥ መትጋት አለብን“ ብሏል፤ ጅብሪል።
“የኔታ ራይተርስ ኦፍ ዘ ፊዩቸር” በቀጣይነት በየዓመቱ የሚካሄድ ቋሚ ፕሮግራም እንደሚሆንና አድማሱን በማስፋትም በአገር አቀፍ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ እንደሚሰሩም የየኔታ አካዳሚ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጥሩወርቅ አየለ ተናግረዋል።  


Read 409 times