Sunday, 21 June 2020 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

  ሰውየው ነጋዴ ነው። በልጅነቱ ስለ ቆሪጥ የሚተረከውን ሲሰማ ያደገ… የደብረ ዘይት ልጅ። ጨዋታችን ዛሬን ወደ ትናንትና፣ ትናንትን ወደ ዛሬ የገለበጠ ነው። ኮሮና የነገሰው ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት እንደነበረ እናስብ። በወቅቱ በሽታውን ለመከላከል የፊት መሸፈኛ ማስክ ማድረግና ንፅህናን መጠበቅ የዜጎች ሁሉ ግዴታ እንደነበር ይታወቃል።
አሸናፊ የሚባለው ከላይ የጠቀስነው ነጋዴ፤ ማስክ ያላደረገ ደንበኛን በፍፁም አያስተናግድም። ነባሮቹም ሆኑ ተላላፊ ደንበኞች መኪና መለዋወጫ ዕቃ ለመግዛት ወደ ሱቁ ሲመጡ በር ላይ ባዘጋጀው ቦታ እጃቸውን ይታጠባሉ። ግብይቱን ሲጨርሱ ደግሞ በፀረ ሀዋሲ መድኃኒት እጃቸውን እንዲያፀዱ ያደርጋል። ጎረቤቶቹ “ጠንቃቃው አሼ” እያሉ ይጠሩታል።
አንድ ቀን ጓንት ያጠለቀ ተላላፊ ደንበኛ ድንገት ዘው አለበት። የብዙ ሺ ብር ዕቃ ለመግዛት እንደመጣና ለሌላ ሥራ ስለቸኮለ በቶሎ እንዲሸኘው ቢጠይቀው፡-
“መጀመሪያ ውጣና እጅህን ታጠብ። አለበለዚያ አልሸጥልህም” ነበር ያለው አሼ። ሰውየውም እየተነጫነጨ ጓንቱን አውጥቶ እጁን ታጠበና ተመለሰ። አሼ ሰውየውን ከሸኘ በኋላ፡-
“በጣም ከቸኮለ ጓንቱን ከሚያወልቅ ለምን ከጎረቤቶቼ አልገዛም?” ሲል ራሱን ቢጠይቅም፤ መልሱን የተረዳው ከዓመታት በኋላ ነበር።
በዛን ቀን ማግስት፣ ወትሮ እንደሚያደርገው፣ ያለፈውን ዕለት ሽያጭ ይዞ ወደ ባንክ ሄደ። ገንዘቡ በማሽን ሲቆጠር አምስትና ስድስት ያህል ሀሰተኛ የመቶ ብር ኖቶች ተገኙ።
ጉዳዩ ለፖሊስ ደርሶ አሼ በቁጥጥር ስር ዋለ። ሆኖም ከጥቂት ቀናት እስር በኋላ ሲፈለግ እንደሚጠሩት አስታውቀውት በዋስ ተለቀቀ።
ተከታታይ ፖሊሶቹ በሀሰት ገንዘቦቹ ላይ የተገኘውን የጣት አሻራ ባለቤት ለማወቅ ያደረጉት ጥረት አታካች ሆኖ ጉዳዩ በእንጥልጥል (Pending) ከረመ። ጊዜው ደርሶ ከሁለት ዓመታት በኋላ የወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ የተባለው መንግሥታዊ ተቋም፤ የመላው አገሪቱን ዜጎች ማንንት የሚገልጽ መረጃ ሰብስቦና አደራጅቶ መጨረሱን አስታወቀ። ይህም የሀሰት ገንዘቦች ዝውውርን፣ የተጭበረበሩ የትምህርት ማስረጃዎችና መሰል ሰነዶችን ለሚያጣሩ የፍትህ ሰራተኞች የሚታገዙበት ዕድል ፈጠረ።
ከሀሰት ገንዘቦቹ ላይ የተለቀመው የጣት አሻራ ወደዚህ ድርጅት ተልኮ የማን እንደሆነ ሲረጋገጥ አፍታም አልፈጀም። ጥፋተኛው ተይዞ ሲመረመር፣ በከተማው ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እያተመ የሚያዘዋውረው የወንጀለኞች ቡድን አባል መሆኑ ተደረሰበት። ምርመራው ተጠናቆ ፋይሉ ለፍ/ቤት ሲቀርብ አሼ ለምስክርነት ተጠራ። በመጀመሪያ ሶስት ጭንብል ካደረጉ ሰዎች ተከሳሹን እንዲለይ ተጠየቀ።
“ይሄ ነው” አለ ወዲያውኑ፤ ወደ አንደኛው እየጠቆመ።
“ጭንብል ብቻ ሳይሆን ኮፍያም አድርጎ ነበር”  በማለት አከለበት።
“እንዴት እርግጠኛ ሆንክ?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ ማስረጃዎቹን ደረደረ።…ወደኋላ ላይ እንመለስበታለን።
*    *   *
ወዳጄ፡- አኗኗራችንና አስተሳሰባችን በልከኛ መስመር ላይ የሚጓዙት ውስጣዊ መንፈሳችን ከውጫዊው ዓለም  ጋር ያለው ቁርኝት የተጣጣመ ሲሆን ወይም ያለ ማቋረጥ እየተናበበ መሄድ ሲችል ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ድብቅ ማንነቱን የሚያኖርበት ውስጣዊ ዓለም ቢኖረውም ሌሎች ሰዎች የሚያውቁት በጋራ በሚኖሩበት ገሃድ ዓለም በሚያሳያቸው ወይም በሚገምቱት “እሱነት” ነው፡፡ ሁለቱ ዓለማት እርስ በራሱ የሚመጋገብ መስተጋብር (functionalism) አላቸው፡፡
አንዱ ያለሌላኛው፤ ሌላኛው ያላንዱ ህይወት የላቸውም፡፡
ወዳጄ፡- ውስጣችንን ካልተመቸን ወደ ውጭ የምናይበት ዓይናችን ይንሸዋረራል:: የውጭውም ዓለም የኛ ውስጣዊ አለመመቻቸትና ጉስቁልና ሲበረታበት ፈዛዛ ነው፡፡ የሁለቱ ዓለማት ምቾትና አንድነት አካልና አእምሯችንን በማነቃቃት፣ ፈጠራና ሰብዓዊ አስተሳሰብን እንድናዳብር ያደርጋል::
በያንዳንዱ ሰው ኑሮ ውስጥ የሚታየው የመሆንና የመፈለግ ግብግብ፤ ከነዚሁ ሁለት ክስተቶች ጋር የተዛመደ ሲሆን፤ ውሁድነት (Integration) የሚፈጠረው ገሃዱ ወይም ኑባሬያዊው ዓለምና ድብቁ ወይም ኑባሬያዊው መንፈስ ዕኩል በሚናበቡበት ወቅት ነው፡፡
ውሁድነት በተገራ ፍላጐትና ዕውቀት የታነፀ በመሆኑ ራስንም ሌላውንም ያጠቃለለ ወይም በአብዛኛው አብሮነትን ማዕከል ያደረገ የአስተሳሰብ ስርዓት ለማደርጀት ያስችላል፡፡ የሁለቱ ዓለማት አለመቻቻል ወይም አለመመጣጠን (Improper መሆን) ግን ወደ ራስ ያደላ የአስተሳሰብ ስርዓት እንድንገባ ይጫነናል፡፡ ይህም በአንዳንድ ሰዎች ላይ እንደሚታየው የስሜት ህዋሳት መወዛገብ ዓይነት (ለምሳሌ በዓይን የመመልከትና በጆሮ የመስማት ችሎታ ከፍታና ዝቅታ መጠን) ማለት ነው፡፡ አእምሮም ላይ ጅላ ጅልነት ወይም በእጅጉ የላቀ የማሰብ ዓቅም (ESP) እንደ ምልክት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ዕብደት፣ ቅዠት፣ ቁጡነት አንዳንዴም ምርምርና ፍልስፍና የመሳሰሉት ንቃተ ጥበባት የባህሪው መገለጫ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡
ወዳጄ፡- መሆንና መፈለግ እንደ ቃላት ጐን ለጐን ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ በግብር ግን በእጅጉ ይራራቃሉ፡፡ ጨርሶ ሳይገናኙና ሳይተዋወቁ የሚተላለፉበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ሁለቱን ለማቀራረብ ካልተሞከረ ደግሞ የራስን ዋጋ ማወቅ አዳጋች ነው፡፡ ብዙ ሊቃውንት ውህድነት ራስን የመሆን ኦቶኖሚና “አሁን”ን ለመኖር የሚያስችል ብቃት እንደሚያጐናጽፍ ይናገራሉ:: ሁለቱን ዓለማት አጠጋግቶ መሆን የሚችሉትን መሆን እንጂ መሆን እየፈለጉ ለመሆን ያልቻሉትን መሆን መሞከር ጥፋት ነው፡፡
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አሼ አቃቤ ህጉ፣ ዳኛው የተከሳሹ ጠበቃ በየተራ ለጠየቁት ጥያቄ የመለሰው እየተዝናና ነበር፡፡
“ይሄ ሰው ያኔ ያየኸው “እሱ” ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለህ?”
“ቅንድቡ የተጋጠመ ስለሆነ”
“ምን ማለት ነው?” የራሱን የገጠመ ቅንድብ እያሳየ፣ በልጅነቱ ሆራ ሀይቅ ውስጥ የሚኖር ቆሪጥ የተባለ ሰይጣን ቅንድቡ የገጠመ ይከለክሉት እንደነበር አስረዳና፣ ደንበኛውን ሲመለከት ልጅነቱን በማስታወሱ እንደሆነ ተናገረ፡፡ ቀጥሎም ደንበኛው ገንዘቡን ቆጥሮ እንዳስረከበው ለእጆቹ ንጽህና ፀረ ህዋስ መድሃኒት ሲያደርግለት፣ ነጥብ የምታክል ጥቁር ምልክት ማየቱን፣ በተጨማሪም ተጠርጣሪው ወደ ሱቁ ሲመጣ ቲ - ሸርት እንደለበሰና በቀኝ ክንዱ ላይ የመስቀል ምስል ያለው ንቅሳት መመልከቱን እንደሚያስታውስ አስረዳ፡፡ ተጠርጣሪው ጃኬቱን እንዲያወልቅ ታዞ ክንዱ ሲታይ የተባለው ንቅሳት፣ በመዳፉም ላይ ጥቁር ምልክት በመኖሩ አሼ ተጨበጨበለት፡፡
ዳኛው በሆዳቸው “መስቀል የሌባ መጫወቻ ሆኖ ይቅር” በማለት እያሰቡ፡-
“ጨርሰሃል” አሉት፡- “The rest is silence” እንዳለው ልዑል ሃምሌት፡፡
ታላቁ ስፔንሰር ደግሞ፡-
“Life is the continuous adjustment of internal relations to external relations” በማለት ያሰናብተናል፡፡
ሰላም!!

Read 1002 times