Saturday, 20 June 2020 12:50

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ድኽነት
ቢርበው ቢታረዝ
የሚላስ ‘ሚቀመስ
ባይኖረው የደስደስ
ከሕይወት ሲካሰስ - የኾነው ተረጂ
እሱ ድኻ አይደለም፤ ሀብት የለውም
እንጂ፤
ምሬት የመረዘው
ኑሮ የጎመዘዘው
ማጣጣም ያቃተው፤ የዚች ዓለም ቃና
እሱ ድኻ አይደለም
ተነፍጎ እንጂ ኢማን፤ ተነፍጎ እንጂ
ጤና፤
ካ‘ጣው የሚያተርፍ
ያተረፈው ያጣ
ኹሉ ነገር ኖሮት፣ ከኹሉ የነጣ
ፍጡርን ‘ሚለካ በ‘ሱ እህል ውኃ
‘ማስበውን ዐስብ
ብሎ የሚያስገድድ፣ ይሄኛው ነው
ድኻ።
          
                           *   *   *  
ወይን ጠጁ ሐሙስ
አመሻሽ ላይ መጥተሽ
ወይን ጠጅ ከንፈርሽ፤ ከወይን ጠጅ
ሐሙስ
ዐርብን አስገደፉኝ
ቅዳሜን አስረሱኝ
እሑድ‘ም እንዲሁ - አስይዘውኛል
ሱስ፤
ሰኞን አጥቁረሽው፤ ሥራ ፈትቻለሁ
ጽድቅሽን ስለምሻ፣ ግን እመክርሻለሁ፤
ማክሰኞ በጠዋት፤ ከቤትሽ ስትወጪ
ዝርዝሩን አንድ ብር
ድጋሚ ዘርዝረሽ፤ ለተመጽዋች ስጪ፤
 ሮብም ተነሥተሽ…
ያዲሳባን መንገድ
በመስጠት ብለሽ ገድ
ለኔ ቢጤ ዝርዝር
ለትውልድሽ ምክር - ለግሰሽ ዕለፊ
ቀኑን በጾም ውለሽ፤ በጸሎት ግደፊ፤
እቴ እንድትጸድቂ፤ የምልሽን ሥሪ
ከኹሉም ከኹሉም፤ ሐሙስ
እንዳትቀሪ።
ዩሱፍ ግዛው ዓለምጉድ - (ናፍቆት፤2012)

Read 2489 times