Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 July 2012 07:00

ልጅ እንዳልካቸው መኮንን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለተመድ ዋና ጸሐፊነት የተወዳደሩት የመጀመሪያው አፍሪካዊ

በአስራ ሰባቱ የደርግ ዘመናት የኢትዮጵያ ሥም በረሐብና በእርስ በእርስ ጦርነት ከመጉደፉ በፊት፤ አገሪቱ የምትታወቀው በጥንት ስልጣኔዋ፣ በነጻነቷና እርሱን ባስገኙላት ጀግኖቿ ነበር፡፡ በተለይ በአድዋ የተጎናጸፈችው አንጸባራቂ ድል የኮሎኒያሊስቶችን ቅስም የሰበረ ምት ከመሆኑም ሌላ በአስከፊ ቅኝ አገዛዝ ሥር ወድቀው ሲማቅቁ ለነበሩት ሕዝቦች የነጻነት ተስፋን ጎህ የፈነጠቀ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የአድዋ ድል ያስገኘላትን ክብር በማስቀጠል ከመንግሥታቱ ማህበር (League of Nations) አባል አገራት አንዱ በመሆን ጊዜው በፈቀደው መጠን በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የሚገባትን ስፍራ ለማግኘት ተሽቀዳድማለች፡ ማህበሩ አገሪቱን ከተሰነዘረባት ፋሺስታዊ ወረራ ያለመታደጉ  ጦስ መልሶ ለማህበሩ መፍረስ ምክንያት ሲሆን ደግሞ ይህቺ አፍሪካዊት አገር የዓለምን ትኩረት እንደገና ሳበች፡፡ ንጉሠ ነገሥቷም “አውሮፓ ዛሬ በኛ ላይ የደረሰውን ፋሺስታዊ ወረራ ችላ ብሎ ቢያልፈው ነገ በራሱ ይደርስበታል” ሲሉ ያደረጉት ዲስኩርም ሕያው ትንቢት ሆኖ እንደነቢይ ሊያስቆጥራቸው በቃ፡፡

ከፋሺስት ኢጣሊያ መባረር ወዲህም ቢሆን አገሪቷ ክብሯን ሳትጥል የታገለች ሲሆን ነጻ የሆነ የጥቁር ሕዝብ ወኪል ሆናም ተቆጠረች፡፡ ኢትዮጵያ የአዲሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል በመሆን ቃልኪዳኑን ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ስትፈርም በርካታ አፍሪካውያን አገራት ገና በቅኝ አገዛዝ ጨለማ ውስጥ ይዳክሩ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቅኝ አገዛዝን በማውገዝ ድምጿን ለዓለም ማህበረሰብ ያሰማች ሲሆን አቅሟ በፈቀደው መጠንም ጸረ- ኮሎኒያሊዝም እና ጸረ አፓርታይድ ትግሎችን ደግፋለች፡፡ ከዚያም ወዲህ ኢትዮጵያ በአጼ ኃይለሥላሴ እና በዲፕሎማቶቿ ብርቱ ትግል የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ስትመሰርትና ዋና መሥሪያ ቤቱም በአዲስ አበባ ሲቋቋም አገሪቱ የአፍሪካ መሪ ኮከብ ሆና በመላው ዓለም ታየች፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ የሆኑትን አቶ ክፍሌ ወዳጆን ያበረከተችው ኢትዮጵያ፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊነት የሚወዳደር አዲስ እጩ ማዘጋጀቷ የተሰማው በዚሁ ዘመን ነበር፡፡ ጊዜው 1963 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ሶስተኛው ዋና ጸሀፊ በመሆን ተ.መ.ድን ሁለት ጊዜ በመመረጥ ያገለገሉት የበርማው ተወላጅ ዩታንት ለተጨማሪ ጊዜ ለመወዳደር ፍላጎት እንደሌላቸው ስላሳወቁ ቦታቸው ለብቁ እጩዎች ውድድር ክፍት ነበር፡፡

ዘመኑ “ቀዝቃዛ ጦርነት” ያየለበት እንደመሆኑ የዓለም ፖለቲካ የሚዘወረው በሁለቱ ኃያላን (ሞስኮና ዋሺንግተን) ፍላጎትና ጥቅም ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ስለሆነም የተ.መ.ድ ዕጩ ገለልተኛ ከሚባል አገር ይመጣል የሚል ግምት አለ፡፡ የዋና ጸሀፊነቱን እድል አውሮፓ ሁለት ጊዜ፣ እስያ አንድ ጊዜ ስላገኙ ተራውን ለሌላው ይለቃሉ ተብሏል፡፡

በዚህ ስሌት መሰረት ከሄድን ዋና ጸሀፊው የሚመረጠው ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከደቡብ አሜሪካና ከአፍሪካ አገራት መካከል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ መካከለኛው ምሥራቅ በአረብ እሥራኤል ፍጥጫ ዘወትር የተወጠረ እንደመሆኑ ከዚያ አካባቢ የሚመጣ ዕጩ ለማሸነፍ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ያገኛል ተብሎ ተስፋ አይጣልበትም፡፡

ከደቡብና ከመካከለኛው አሜሪካ አገራት የሚመጣ እጩ ከኩባ ካልሆነ በስተቀር ለመቀበል አሜሪካ ችግር የለባትም፤ ሩስያኖቹ በበኩላቸው ግን ደቡብ አሜሪካ አገራትን በሙሉ የአሜሪካ ጋሻ ጃግሬ አድርገው ስለሚቆጥሩ ከዚያ አካባቢ ለሚመጣ እጩ ድጋፋቸውን ይከለክላሉ የሚል የተንታኞች ስሌት አለ፡፡

በዚህ ጊዜ የተሻለ ግምት የሚሰጠው ለአፍሪካ ይሆናል፤ ብቃት ያለው ዕጩ እስከተጠቆመ ድረስ ሶቭየቶቹም ሆነ አሜሪካኖቹ በአንድ አፍሪካዊ ዕጩ ላይ ሊስማሙ ይችላሉ፤ ምክንያቱም በምሥራቅ ምዕራብ ፍጥጫው አፍሪካ ገለልተኛ ሆኖ የመቆጠር ተስፋ አለው ተብሎ በወቅቱ ፎርሙላ ሂሳቡ ተሰርቶ ነበር፡፡

የፖለቲካ አሰላለፉ ከዚህ በላይ በቀረበው የወቅቱ ትንተና መሠረት ከሆነ፤ በተለምዶ የአፍሪካ ወኪል ተደርጋ ለምትቆጠረው ለኢትዮጵያ ዕጩዋን ለማቅረብ በእርግጥም ከዚህ የተሻለ ጊዜ አልነበረም፡፡ ለዚህ ሥራ የታጩት ኢትዮጵያዊ የ43 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን በተ.መ.ድ የሀገሪቱ ዋና መልዕክተኛ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል፡፡

የዘመኑ መገናኛ ብዙሀን ‹‹አገሩ በኦፊሴል ድጋፍ የሰጠችው የመጀመሪያው አፍሪካዊ ዕጩ የተ.መ.ድ ዋና ጸሀፊ›› ሲሉ የገለጧቸው እኚህ ሰው፤ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው ከመኳንንት ወገን ሲሆን አባታቸው በነጻነት ማግስት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ናቸው፡፡

ልጅ እንዳልካቸው የተወለዱት ጳጉሜ 3 ቀን 1920 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ውስጥ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በእንግሊዝ አገር በሚገኘው ኤክስተር ኮሌጅ እና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው፣ በፖለቲካል ኢኮኖሚ በማስተርስ ዲግሪ በ1943 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡

ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ መንግስታዊ አገልግሎታቸው የጀመረው በ1944 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአታሼ የሥራ መደብ ላይ ሆኖ፤ ደረጃ በደረጃ የፕሮቶኮል ሹም፣ የፖለቲካ ጉዳዮች ዳይሬክተር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እስከመሆን ደርሰዋል፡፡

በመቀጠል በሕዝባዊ ኑሮ እድገትና በትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በእንግሊዝ አምባሳደር፣ በተ.መ.ድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሰፊ አገልግሎታቸውን ያበረከቱ ሲሆን ለመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊነት በተወዳደሩበት ወቅት የፖስታ፣ የመገናኛና የቴሌኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ነበሩ፡፡

ልጅ እንዳልካቸው አገራቸውን በመወከል በበርካታ ዓለም ዓቀፍ ስብሰባዎች ላይ ተካፍለዋል፣ ከነዚህም መካከል በ1945 ዓ.ም የጦር ካሳ ኮንፈረንስ የኢትዮጵያ ተወካይ (ሮም)፣ በ1948 ዓ.ም የገለልተኛ አገሮች ጉባኤ ራፖርተር (ባንዱንግ)፣ በ1952 ዓ.ም የዩኔስኮ ኤሲቢ ኮንፈረንስ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች መሪ (ጄኔቭ)፣ አአድ ሲመሰረት የኢትዮጵያ መልዕክተኞች ፤የተመድ የሱዌዝ ቦይ ጉባኤ  የኢትዮጵያ መልዕክተኞች መሪ (ለንደን)፤ ይገኙበታል፡፡

ልጅ እንዳልካቸው የአዲስ አበባ ሮታሪ ክለብ ፕሬዚደንት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) አመራር አባል ሆነው ሲያገለግሉ፤ እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም ቶኪዮ ላይ የተደረገው የወወክማ ዓለም ዓቀፍ ሕብረት (World Alliance of YMCA) የሕብረቱ ምክትል ፕሬዚደንት አድርጎ የመረጣቸው ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የሕብረቱ ፕሬዚደንት አደረጋቸው፡፡

ልጅ እንዳልካቸው በዕጩነት የቀረቡበትን የተመድ ዋና ጸሀፊነት ስራ በቅርብ የተመለከቱት በድርጅቱ የሀገራቸው ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው በተመደቡበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ከ1959 ዓ.ም እስከ 1961 ዓ.ም በነበረው የሶስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የጸጥታው ምክር ቤት ጊዜያዊ አባል ስለነበረች፤ ልጅ እንዳልካቸው ሁለት ጊዜ ተመርጠው የጸጥታውን ምክር ቤት በፕሬዚደንትነት መርተዋል፡፡

በዚሁ የጸጥታው ምክር ቤት የፕሬዚደንትነታቸው ዘመን በመካከለኛው ምስራቅ፣ በቆጵሮስ፣ በሮዴሽያ፣ በናሚቢያና በቼኮስሎቫኪያ የደረሱ ቀውሶችን አስመልክቶ የተጠሩ ስብሰባዎችን መርተዋል፡፡ እንዲሁም በእስራኤልና በግብጽ መካከል ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ አስታራቂ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉትን ሚስተር ጉናር ጃሪንግን የሰየሙት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ነበሩ፡፡

በአፍሪካ ጆርናል እየተዘጋጀ በየወሩ ለንደን ላይ ይወጣ የነበረው አፍሪካ መጽሔት እ.ኤ.አ በየካቲት 1971 ዓ.ም እትሙ ላይ ልጅ እንዳልካቸውን አፍሪካዊው የዩታንት ተተኪ በማለት ሰፊ ዘገባ እና ቃለ ምልልስ ይዞ የወጣ ሲሆን ‹‹ንጉሥ ኃይለሥላሴ በዓለም ላይ ያላቸው ሥምና ዝና ለእንዳልካቸው የምርጫ ዘመቻ ትልቅ ጉልበት ሊሆናቸው ይችላል›› ሲል ተንብዮ ነበር፡፡

የዚህ መጽሔት ዋና አዘጋጅ፤ ልጅ እንዳልካቸውን ለተመድ ዋና ጸሀፊነት ሥራ ለመወዳደር ምን እንዳነሳሳቸው ሲጠይቃቸው ‹‹የቤተሰቤን ያለፈ ታሪክ ብትመለከት ከአገራዊ ወይም ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ርቆ እንደማያውቅ ትመለከታለህ፤ አባቴ የተመድ ቻርተር ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ላይ ሲፈረም የኢትዮጵያ መልዕክተኞች መሪ ነበር፡፡ ሌላው የግል ትምህርቴ ታሪክ ነው፤ የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቅ እንደመሆኔ ፖለቲካ ይስበኛል - በተለይ ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ›› በማለት መልስ ሰጥተው ነበር፡፡

ልጅ እንዳልካቸው በመቀጠልም ‹‹በተመድ የነበረኝ አገልግሎትና በብሪታኒያ አምባሳደር ሆኜ መስራቴ በዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ለመሳተፍ እንድተጋ አድርገውኛል፤ በተለይ በዚህ ጊዜ ደግሞ አፍሪካ ዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ለማገልገል የራሷን ሚና የምትጫወትበት ጊዜ የደረሰ መስሎ ታይቶኛል፡፡ በተጨማሪም ለዚህ ስራ እንድወዳደር በመላው ዓለም ያሉ ወዳጆች አበረታተውኛል›› ብለው ነበር፡፡

ልጅ እንዳልካቸው ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊነት በእጩነት ራሳቸውን ማቅረባቸውን በይፋ ያስታወቁት ጥር 14 ቀን 1963 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር፡፡ በዚሁ መግለጫቸው፤ እጩ ሆነው እንዲወዳደሩ በንጉሠ ነገሥቱና በመንግሥታቸው እንደተፈቀደላቸው ጠቁመው፤ እጩ ሆነው የሚቀርቡት ግን ዩታንት የሥራ ጊዜያቸውን ለማብቃት ያላቸውን ፍላጎት ያልቀየሩ እንደሆነ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ልጅ እንዳልካቸው መግለጫቸውን በመቀጠል ‹‹ዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ይህንን ታላቅ የኃላፊነት ሥፍራ ለአፍሪካዊ ለመስጠት ከወሰነ እና እኔም ይህንን ታሪካዊ ሥራ እንድፈጽም ከተመረጥኩ የሰው ልጆች ሁሉ ይጠቀሙ ዘንድ የተመድን ተልዕኮ ለማሳካት በሙሉ ልቤ እሰራለሁ›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡

ልጅ እንዳልካቸው የካቲት 4 ቀን 1963 ዓ.ም በተደረገው የውጭ ጋዜጠኞች ማህበር የወሩ የምሳ ግብዣ ላይ ለተሰበሰቡት ጋዜጠኞች፤ ዓለም ዓቀፉን የምረጡኝ ዘመቻቸውን በመጪው ሳምንት የወቅቱ የአአድ ዋና ጸሀፊ የሆኑትን ኬኒት ካውንዳን ሉሳካ ውስጥ በማነጋገር እንደሚጀምሩና ጉዞውም የተለያዩ ቁልፍ አገራትን በመጎብኘት እስከ ሕዝባዊ ቻይና ድረስ እንደሚዘልቅ ገልጸው ነበር፡፡ ልጅ እንዳልካቸው በመግለጫቸው፤ ‹‹በመጪዎቹ ወራት በተለያዩ አገራት የማደርገው ጉብኝት ዓይነተኛ ዓላማ በዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለኝን ምልከታ እና አቋም ለማስረዳት፤ በዚህም የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራትን አመኔታና ድጋፍን ማግኘት ነው›› ብለዋል፡፡

ሰኔ 16 ቀን 1963 ዓ.ም ስምንተኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ ላይ ሲደረግ፣ አባል አገራት ለተመድ ዋና ጸሀፊነት የኢትዮጵያ እጩ የሆኑት ልጅ እንዳልካቸው መኮንንን እንዲደግፉ የሚጠይቅ ሰነድ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተሰራጭቷል፡፡ ሰነዱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአቶ ከተማ ይፍሩን፣ የአአድ ዋና ጸሀፊ የዲያሎ ቴሊን ደብዳቤዎች እና የልጅ እንዳልካቸው መኮንንን የትምህርትና የአገልግሎት ታሪክ (Curriculum Vitae) የያዘ ነበር፡፡በጉባኤው መዝጊያ ላይ የቻድ ፕሬዚደንትና የአአድ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሬዚዳንት ሞክታር ኦልዳዳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ‹‹አባል አገራት በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ተመርተው ጊዜው ሲደርስ ለኢትዮጵያ እጩ ተገቢውን የድጋፍ ድምጽ እንደሚሰጡ እርግጠኛ ነኝ›› ብለው ነበር፡፡የተመድ ዋና ጸሀፊነት የምርጫ ዘመቻ አዲሱ የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት 1972 ዓ.ም ከመግባቱ በፊት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጥር 1964 ዓ.ም አስቀድሞ) መጠናቀቅ አለበት፡፡ ከምርጫው ሶስት ወራት ቀደም ብሎ ሮይተርስ፤ ዲፕሎማቶች የመመረጥ ተስፋ አላቸው ብለዋል ያላቸውን አምስት እጩዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን ከነዚህ መካከል ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ይገኙበታል፡፡

እነዚህም ተስፋ አላቸው የተባሉት እጩዎች (1ኛ) ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ከኢትዮጵያ (2ኛ) ማክስ ጃኮብሰን ከፊንላንድ (3ኛ) ሺርሊ አሜራሲንግ ከሲሎን (4ኛ) ዶ/ር ኩርት ቫልዳሂም ከኦስትርያ (5ኛ) ዶ/ር ፊሊሻ ሄራ ከቺሊ ነበሩ፡፡

መስከረም 20 ቀን 1964 ዓ.ም ሮይተርስ ከኒውዮርክ በላከው ዘገባ፤ ከአምስቱ ኃያላን አገራት አንዱ የሆነችው የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሞሪስ ሹማን አዲሱ የተመድ ተመራጭ ዋና ጸሀፊ፤ ከእንግሊዝኛ ሌላ ፈረንሳይኛም የሚናገር መሆን አለበት ማለታቸውን ጠቅሶ በዚሁ መሰረት ውሳኔው ፈረንሳይኛ የማይናገሩ የሁለት እጩዎችን የመመረጥ ተስፋ ሲያጨልም የሶስቱን ደግሞ የሚያለመልም ሆኖ ተገኝቷል ብሏል፡፡

ሮይተርስ በዚሁ ዘገባው፤ የፊንላንዱ ማክስ ጃኮብሰንም ሆኑ የሲሎኑ ሺርሊ አሜራሲንግ ፈረንሳይኛ የማይናገሩ ሲሆን ኢትዮጵያዊው እንዳልካቸው መኮንን፣ ኦስትሪያዊው ኩርት ቫልዳሂም እና የቺሊው ተወላጅ ዶ/ር ፊልሻ ሄራ እንግሊዝኛም ፈረንሳይኛም ተናጋሪ መሆናቸውን ገልጦ ለመመረጥ ብሩህ ተስፋ አላቸው ብሎ ነበር፡፡ታህሳስ 9 ቀን 1964 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊን ለመምረጥ የጸጥታው ምክር ቤት መሰብሰቡን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከኒውዮርክ አሰማ፡፡ ይሁን እንጂ በምስጢር በተደረገው ምርጫ ሂደት በድምጽ ብልጫ ተፈላጊውን እጩ ለማስገኘት ሳይችል በመቅረቱ ምክር ቤቱ ያለውጤት ተበትኗል፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት በተከታታይ ካካሄደው ሁለት ተጨማሪ ያልተሳኩ የምርጫ ሙከራዎች በኋላ፤ ታህሳስ 13 ቀን 1964 ዓ.ም ባካሄደው ምርጫ ኦስትሪያዊውን ዶክተር ኩርት ቫልዳሂምን 4ኛው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አድርጎ የመረጣቸው ሲሆን በማግስቱ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤም ምርጫውን አጽድቆታል፡፡

ልጅ እንዳልካቸው እንደተመኙት፤ የፖለቲካ ተንታኞችም እንደተነበዩት ከአፍሪካ ሳይሆን ከአውሮፓ ለሶስተኛ ጊዜ የተመድ ዋና ጸሀፊ ተመረጠ፡፡ ዶክተር ቫልዳሂም ሁለት ጊዜ ተመርጠው እ.ኤ.አ እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ ተመድን አገልግለዋል፡፡

የተመድ ዋና ጸሀፊነት ስራ ከአውሮፓ ቀጥሎ የተጓዘው ወደ አፍሪካ ሳይሆን ወደ ደቡብ አሜሪካ ነበር፡፡ የደቡብ አሜሪካዋ አገር የፔሩ ተወላጅ የሆኑት ሀቪየር ፔሬዝ ዴኩየር 5ኛው የተመድ ዋና ጸሀፊ ሆነው እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም የተመረጡ ሲሆን ድርጅቱንም እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ መርተውታል፡፡ከልጅ እንዳልካቸው መኮንን የምርጫ ዘመቻ ልክ ከ20 ዓመት በኋላ ግብጻዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም 6ኛው የተመድ ዋና ጸሀፊ በመሆን ሲመረጡ አፍሪካ የመጀመሪያውን ውክልና አገኘች፡፡ ከ5 ዓመታት በኋላ ደግሞ ኮፊ አናን ሁለተኛው አፍሪካዊ የተ.መ.ድ ዋና ጸሀፊ ሆነው ተመረጡ፡፡እንግዲህ የልጅ እንዳልካቸው የተመድ እጩ ሆኖ መቅረብ ጊዜው ያልደረሰ አሳብ ነበር ወይም ጊዜውን በ20 ዓመት የቀደመ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡

የእንዳልካቸው ዘመቻ ያልተሳካው በዘመኑ ይካሄድ በነበረው የቀዝቃዛ ጦርነት ምክንያት አፍሪካ በኃያላኑ ስሌት ውስጥ ልትገባ ባለመቻሏ ነው እንጂ የእንዳልካቸው ልምድና ችሎታ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አልነበረም፡፡

ልጅ እንዳልካቸው የጓጉለት የተመድ ዋና ጸሀፊ እጩነት ያልተሳካላቸው ቢሆንም ከሶስት ዓመታት በኋላ የካቲት 21 ቀን 1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፡፡ ይህ ሹመት የመጣው የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሁሉም አቅጣጫ በተቃውሞ ማዕበል በሚናጥበት ዘመን በመሆኑ የእንዳልካቸውን የሥራ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ አድርጎት ነበር፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሕዝባዊ ተቃውሞ ሳቢያ ከስር መሰረቱ በመናጋቱ፤ ወታደራዊ መኮንኖችም ቀስ በቀስ መንግሥቱን እየቦረቦሩ በመሄዳቸው እንዲሁም ሕዝባዊው ተቃውሞም ባለመለዘቡ ምክንያት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ሥልጣን ላይ ከወጡ ከ144 ቀናት በኋላ ሐምሌ 15 ቀን 1966 ዓ.ም ከሥልጣን ተሰናበቱ፡፡

ልጅ እንዳልካቸው ከሥልጣን ከወረዱበት ጊዜ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በመኖሪያ ቤታቸው በጥበቃ ሥር ሆነው ከቆዩ በኋላ፤ ከሐምሌ 24 ቀን 1966 ዓ.ም ጀምሮ ቀደም ብሎ በአራተኛ ክፍለ ጦር ቅጥር ግቢ ውስጥ ታስረው ከነበሩት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባለሥልጣናት ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ፡፡

ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ደርግ ያለፍርድ ለብዙ ወራት አስሮ፤ በመጨረሻም ሕዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ማታ በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት በጥይት ተደብድበው በግፍ እንዲገደሉ ካደረጋቸው ስልሳ ንጹሀን ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡

ልጅ እንዳልካቸው በትርፍ ጊዜያቸው ግለ ታሪኮችን፣ መጣጥፎችንና ግጥሞችን  ይሰበስቡ የነበረ ሲሆን የሚወዱት ስፖርት ደግሞ የውሃ ዋና መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ልጅ እንዳልካቸው በ1939 ዓ.ም ከወይዘሮ እንከንየለሽ ሽፈራሁ ጋር በህግ ተጋብተው ሶስት ወንዶችና አራት ሴት ልጆች ማፍራታቸው ታውቋል፡፡

እኒህ ኢትዮጵያዊ በደርግ ጥይት ተደብድበው በጅምላ መቃብር ሲጣሉ ገና 47 ዓመታቸው ነበር፡፡ ሥራቸውንና አገልግሎታቸውን ግን ተገድሎ የማይጣል ስለሆነ ከመቃብር በላይ ህያው ሆኖ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ሴረን ኪርክጋርድ የተሰኘ ጸሀፊ እንዳለው፤ የአምባገነኖች አገዛዝ ሲያከትም የሠማዕታት የሥልጣን ዘመን ይጀምራል፡፡

 

 

Read 5477 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 07:13