Print this page
Saturday, 27 June 2020 12:01

በትግራይ የክልሉ ም/ቤት አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ተገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


             የትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ በሁለት ወር ከሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የክልል ም/ቤት ምርጫን እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ም/ቤት ምርጫ እንዲያደራጅ የቀረበለትን ጥያቄ ህጋዊ ያላቸውን ምክንያቶችን ጠቅሶ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ የትግራይ ክልል የራሱን የምርጫ ኮሚሽን አደራጅቶ በሁለት ወር ከ15 ቀናት ውስጥ ምርጫ እንደሚያደርግ የህወኃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ለአሜሪካ ድምጽ አስታውቀዋል፡፡
“እኛ የምናካሂደው የፌደራል ፓርላማ ተወካዮች ምርጫ ሳይሆን የክልል ምክር ቤት ምርጫ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ይሄን ለማካሄድ ደግሞ ህገ መንግስቱ ይፈቅድልናል ብለዋል፡፡
ምርጫው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ የክልሉ ህዝብና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፍላጐት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ምርጫውን ውጤታማ የሚያደርገውም የህዝቡና የተቃዋሚዎች ፍላጐትና ተሳትፎ እንጂ በጊዜ እጥረት ውጤታማነቱ ሊመዘን አይችልም ብለዋል፡፡
ምርጫውን ለማካሄድ የክልሉ መንግስትና ተቋማት የተደራጀ አቅም አላቸው ብለዋል - አቶ ጌታቸው፡፡
ምርጫውን ማካሄድ ያስፈልገውም በዋናነት የክልሉን መንግስት ህልውና ለማጽናት መሆኑን የገለፁት አቶ ጌታቸው፤ ኮሮና በክልሉ ስጋት ቢሆንም አስፈላጊው ሁሉ ጥንቃቄ ተደርጐ ምርጫውን ማከናወን ይቻላል ብለዋል፡፡
ከመስከረም 25 ቀን 2012 በኋላ የትግራይ ክልል የፓርላማ ተወካዮችም ውክልና እንደሚያበቃና የፌደራል መንግስትም ህጋዊ ሰውነት እንደማይኖረው የጠቆሙት ኃላፊው፤ ትግራይ በፌደራል መንግስቱ የሚኖረው ውክልና የሚወሰነው በፌደራል መንግስቱ በቀጣይ በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ነው ብለዋል፡፡
ህወኃት ነፃ ሀገር የማቋቋም አላማ የለውም ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የክልሉን መንግስት ህልውና ግን በሚካሄደው ምርጫ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ህወኃት ከመሠረተው የፌደራሊስት ሃይሎች ጥምረት መታገዱን በተመለከተ ሲመልሱም፤ እዚህ ግባ የሚባል ቁም ነገር የሌለው ውሣኔ መሆኑን ጠቁመው ጉዳዩ ህወኃትን እንደማያሳስበው አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ምረጫውን ማካሄድ እንደማይቻል ምክንያቶችን ጠቅሶ ባወጣው ምላሹና መግለጫ በመላ ሀገሪቱ ምርጫን የማካሄድ እና የማስፈፀም ብቸኛ ስልጣን የተሠጠው መሆኑን ህግን ጠቅሶ አስረግጦ ገልጿል፡፡
ቦርድ በመግለጫው የኮቪድ 19 ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ ቦርዱ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ምርጫ አይካሄድም ብሏል፡፡
በተጨማሪም “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት የምርጫውን ከተጽእኖ ነፃ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስፈፀም ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ነው ያለው” መግለጫው በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈፃፀምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የመወሰን ስልጣንም ለተቋሙ ብቻ በህግ የተሰጠ ነው ብሏል፡፡
በመሆኑም የትግራይ ክልል ም/ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሣኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሣኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ህጋዊ መሠረት የለውም ብሏል፡፡
የክልሉ መንግስት ምርጫውን ለማካሄድ የምርጫ ቦርድን ስልጣን ተጋፍቶ ኮሚሽን ቢያቋቁም ምን አይነት የህግ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ እንዲሁም የክልሉ መንግስት ምርጫውን በህግ ማካሄድ ይችላል አይችልም በሚለው ጉዳይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ መግለጫው ላይ ከተመለከተው ውጪ የምንሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ አይኖርም ብለውናል፡፡


Read 1215 times