Saturday, 27 June 2020 12:06

በሊባኖስ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በከፋ ስቃይ ላይ ይገኛሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   መንግሥት እንዲደርስላቸው እየተማጸኑ ነው

            በቤሩት ሊባኖስ በቤት ሰራተኛነት ስራ ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከኮሮና ጋር በተያያዘ ቀጣሪዎቻቸው ደሞዝ ሳይከፍሏቸው እያባረሯቸው በመሆኑ ለችግር መዳረጋቸውን እየገለፁ  ነው።
“አረብ ኒውስ” በአሰሪዎቻቸው በደል የተፈፀመባቸው ኢትዮጵያውያንን አነጋግሮ በሰራው ሰፊ ዘገባ፤ አብዛኞቹ ፓስፖርታቸውን ተነጥቀውና የሰሩበትን ደመወዝ ተከልክለው በመባረራቸው  ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ጠቁሟል። የ30 ዓመቷ ወጣት ትርሲት ላለፉት 12 አመታት በሊባኖስ በሰው ቤት ተቀጥራ ስትሰራ የኖረች ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሰሪዋ  ምግብ እንደምትከለክላት፣ በየቀኑ አካላዊ ጥቃት ስትፈፅምባት እንደቆየች ገልጻ፤ በመጨረሻም ፓስፖርቷን ተነጥቃና የሰራችበትን ደመወዝ ተከልክላ ከቤት በሀይል መባረሯን አስረድታለች።
ደመወዟን እንድትሰጣት አሰሪዋን ስትጠይቅ “2 ሺህ ዶላር ከፍዬ ነው ያመጣሁሽ፤ በመጀመሪያ እሱን መልሽልኝ” ስትል እንደመለሰችላት ተናግራለች።
አብዛኛዎቹ ከስራቸው ተባርረው በሊባኖስ ጎዳና ላይ ወድቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የትርሲት ተመሳሳይ እጣ የደረሰባቸው መሆኑን ያመለከተው የአረብ ኒውስ ዘገባ፤ ዘገባው ኢትዮጵያውያኑ የመንግሥታቸውን ድጋፍ ይማጠናሉ ብሏል።
ከ100 በላይ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ተሰባስበው በመሄድ መንግሥታቸው ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው መጠየቅ ከጀመሩ ሰነባብተዋል ብሏል - ዘገባው። ኢትዮጵያውያኑ በጎዳና ላይና በቆንጽላ ጽ/ቤቱ ያለ መጠለያና በቂ ምግብ ወድቀው መቆየታቸው ለተለያየ የጤና እክሎች እያጋለጣቸው ነው ብሏል - አረብ ኒውስ በዘገባው። በቪዲዮ ተቀርፆ የተሰራጨው የኢትዮጵያውያኑ የደረሱልን ጥሪም ይህንኑ ያረጋግጣል።
ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያንም በጭንቀትና በተለያዩ የሥነ ልቦና ጫናዎች ራሳቸውን እያጠፉ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን በቅርቡ አንዲት ኢትዮጵያዊት ታንቃ ራሷን ማጥፋቷ  ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ ታዳጊ አገራት የሄዱ ከ250ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴት ወጣቶች በሊባኖስ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው እንደሚሰሩ ያመላከተው ዘገባው፤ ከእነዚህ ውስጥ የሚልቀውን ቁጥር የሚይዙትም ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሏል።
ኢትዮጵያውያኑ በሊባኖስ በወር 150 ዶላር ብቻ እየተከፈላቸው በቤት ሰራተኛነት እንደሚያገለግሉና ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
በስደት የሚገኙት እኒህ ኢትዮጵያውያን እያቀረቡ ያለውን የድረሱልን ጥሪ በተመለከተ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚያውቀው ጉዳይ ስለመኖሩ አዲስ አድማስ ላቀረበው ጥያቄ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሊባኖስ ካለው ቆንጽላ ጽ/ቤት ጋር ተነጋግረን በጉዳዩ ላይም ዘርዘር ያለ መረጃ እንደደረሰን መግለጫ እንሰጣለን ብለዋል።

Read 2020 times