Print this page
Saturday, 14 July 2012 07:14

ድምጺቱ

Written by  ዶ/ር ፍቃዱ አየለ feke40ayema@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ለእነ ..እንዴት እንመን

Aያንዳንዱ ሰው ወደ ምድረ አዳምነት ሲፈልስ እሱ ባልተገኘበት ጊዜና ወቅት በሌሎች የተጠናም ያልተጠናም ውሳኔ አስገዳጅነት ነበረ፡፡ ማንም “ልወለድ የተገባኝ ነኝ» ብሎ ከመወለድ በፊት ይገኝ የነበረን የምንምነት ጉልበትና ጥበብ ጠረማምሶ ይሕችን ፕላኔት የተቀላቀለ የለም ወይም ሲወለድ ስቆ ታሪክን ያስፈገገ አልተገኘም፡፡ ይህ ጉዳይ ብዙ ገራሚ ባይሆንም  እውነትነቱ ግን ያን ያህል አራኳች አይመስለኝም፡፡ ይህን ስል ፕሌቶ ያስብ እንደነበረው ከመወለድ በፊት ነፍስ ያለ ስጋ እራቁቷን ስትኖር ከርማ በመወለድ ጊዜ በስጋ ተጠቅልላ እርቃንነቷ “ሰውነትን ይጎናፀፋል” ብሎ “ሃሳባዊ” መሆን መቻሉን ዘንግቼ አይደለም፡፡

ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሳይወለድ በፊት የት እንደነበረ፣ እንዴት እንደኖረ ያረጋገጠልን ስላልተገኘ እንዲህ አይነቱ እሳቤ ብዙም የሚያወላዳ አይደለም፡፡ ሳልወለድ በፊት ኖሬ ቢሆን ኖሮ የነፍስ ዋንኛ መገለጫ በሆነው የመወሰን ልዩ መብቴ ተጠቅሜ መወለድን እምቢ ባልኩ ወይም የምወለድበትን ጊዜና ሁኔታ በወሰንኩኝና ከዛም እዚህ አለም ላይ ተከስቼ ስለውሳኔዬ ታላቅነት ወይም ደቃቃነት በፋነንኩ አሊያም ደግሞ በተሸማቀቅሁ ነበር፡፡ ይህን ያደረኩበት ጊዜና ወቅት ይቅርና በእናቴ ማህፀን ውስጥ ያሳልፈኳቸው ጥቂት ወራቶች “በድሎት የተሞሉ” እንደነበሩ በስሚ ስሚ የቃረምኩት ነፍስ ካወቅኩኝ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ የሰው ልጅ ከኋላውም (ከመወለዱ በፊት) ከፊቱም (ከሞቱ በኋላ) “ስላለው እና ስለሚኖረው” ነገር የማወቅ አቅም ያጠረው ግን ደግሞ ስለእነዚህ ነገሮች መጠየቅን ሊያቆም የማይችል ገራሚ ፍጥረት ነው፡፡

 

ስለ እነዚህ ሁለት “የኋላና የፊት” የጊዜ አጥናፎች ምንነት  እርግጠኛውን መልስ የሚያስቀምጥ “ሰው ብቻ የሆነ” ሰው (ተፈላሳፊ ቢሆን፣ ተመራማሪ ቢሆን፣ ከያኒ ቢሆን፣ ሃይማኖተኛ ቢሆን፣ ወዘተርፈ ቢሆን) እስከዛሬ አለመከሰቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡ እንግዲህ የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ የመገኘቱ ምክንያት “በመወለድና በመሞት መካከል ተቀስፋ በምትታትር እዚህ ግቢ ልትባል በማትችል እድሜ የሚጠቃለል ብቻ ነው” ብሎ መደምደም አዳጋች ይሆናል፡፡ ለምን? ምክንያቱም በህይወት እንቅስቃሴው ላይ ትርጉም ሊያመጣ በሚችል መልኩ ወደኋላም ወደፊትም በቅጡ ሊያውጠነጥን የሚችለው የዚህ ፕላኔት ፍጥረት ሰው ብቻ ነውና፡፡ ይኸ ውጥንጥኖሽ ደግሞ ሰው ለምድር በተሰራ ድንኳኑ ውስጥ ለምድር ያልሆነ ማንነትን ለማሳደሩ  ማስረጃ ነው፡፡

አሁን የምንገኝበት ቅጽበት ኋላችንን እውቀት ፣ ፈተታችንን እምነት ያደረገ ስብጥር መጋጠሚያ ነው፡፡ የትኛውም ሰው አለኝ የሚለው እውቀት ምንጩ የትናንትናና የዛሬ ቅንብር ውጤት   ቢሆንም እንኳ የሚያነጣጥረው ግን ነገ ላይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ብልጡ የሰው ልጅ “ጊዜ ምንድን ነው?» ብሎ ጠይቋል ስለጊዜ ብዙ ብሏል፡፡ ተፍጨርጭሯል፡፡ ጠብ ያለው ነገር ግን “ትላንት መወለዱ ዛሬ መኖሩ ነገ መሞቱ ብቻ ነው” የትኛውንም ያህል አስፍቶ ስለጊዜ ቢመረምር ቅሉ ጊዜ በሰው ላይ እየፈጠረ ስላለው ተጽእኖ»  ስለጊዜ የተገነዘበው ሃቅ ኢምንት ነው፡፡ የሰው ልጅ በትክክል ሊገነዘበው ያዳገተውን ፊትለፊቱን ለመቋቋም ትላንትንና ዛሬን መሳሪያው አድርጐ ዘወትር በዝግጅት መንፈስ መኖሩ ኋላውና ፊቱ ከዛሬነቱ ባይልቁም እጅግ ወሳኝ ስለሆኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የፈላስፋና የሌሎቻችን ኑሮ ልዩነት ይሄ ነው “ፈላስፋ ወደ ኋላ ይኖራል እኛ ወደ ፊት” ሁላችንም ግን ዛሬ ላይ ሆነን ተፋጠናል፡፡ “ዛሬአችን” “ትላንታችንን” ሊያርም “ነጋችንን” ሊያሳምር የሚችል በእጃችን ያለ መሳሪያ ነው፡፡ ጊዜው ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ መልስ ፍለጋው መጧጧፍ አለበት፡፡ መልስ ያገኘ የመሰለው ደግሞ ልቡን ማደንደን ያቁም፡፡ ዛሬ እየሆነ ያለው ወይም ያካበትነው ነገር ጥራትና ምጥቀት ወይም ነገን የተነበይንበት ግምትና ረቂቅነት ከብልጥነታችን የመነጨ ስኬት አይደለም፡፡ ይልቁንስ የትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር የፈጠራ መብት ሊጠይቅበት የማይችለው የመወሰን ልዩ መብታችን ውጤት እንጂ፡፡ የትኛውንም ያህል የትንታኔ ጎርፍ ቢጎርፍ፣ እውቀት ቢንዠቀዠቅና ቢንሰራፋ ለውሳኔ ከመጥቀሙ ውጭ የሰውን ብርቅየነት (ኦርጅናሌነት) ሊያጠፋ እስኪችል ድረስ የሚዘልቅ ሃይል የለውም፡፡ ምክንያቱም ሰው ብቻውን ሰው የመሆንና የመመርመር፣ ነገሮችን የማብጠርጠር ልዩ ባህሪ አለውና ነው፡፡ ይህ ሰውን ለየት የሚያደርገው የመወሰን ክህሎት ረቂቅነት ባይሰመርበት ነው የሚገርመው፡፡ ለምን ቢባል ሰው ሳይወስን መኖር አይችልምና፡፡ ማመንም ውሳኔ ነው፤ አለማመንም እንዲሁ፡፡

ሽንጠ ረዥሙን መንደርደሪያዬን ገታ አድርጌ የኑሮ ዘይቤአችንን የሚቃኙት የአስተሳሰብ አይነቶች በአጠቃላይ ምን እንደሆኑ ጠቆም ማድረግ መልካም መስሎ ይታየኛል፡፡ እነዚህ አለምን የምንገነዘብባቸው መመልከቻዎቻችን ብዙ ተደርገው ቢታሰቡም በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ልንጠቀልላቸው እንችላለን - እምነት (theism) , ክህደት (atheism), ኢ-እውቀት (agnosticism) ፡፡ ታዲያ “እንዴት ልመን?” ብሎ የሚጠይቅ ማንም ሰው ህይወትን እየመረመረ ያለበት መመልከቻው ወይ ክህደት ወይም ኢ- እውቀት መሆኑ ግልጥ ነው፡፡ በአጭሩ ያስቀመጥኳቸው እኝህ እይታዎች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም ሰው እንዴት ሊያምን እንደሚችል እኔ ካለሁበት ከእምነት ጎራ አንጻር ሆኜ ለማሳየት እጥራለሁ፡፡

በእኔ እምነት ሚዛን የጠበቀ ሰብአዊነት ያየለበት ሰው የሚጠይቅና ጥያቄውን ለመመለስ ወይም የጥያቄዎቹን ምላሽ ለማብራራት የሚኖር  ፍጥረት ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ላለፉት አራትና አምስት ሺህ አመታት ሲጠየቁ የኖሩ ቢሆንም ቅሉ እሰከዛሬ ይጠየቃሉ፡፡ ምንም እንኳ ለጥያቄዎቹ የምንሰጠው ትኩረትና ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለማግኘት የምናደርገው መኳተን በመጠን ቢለያይም ሰው ሁሉ ይጠይቃል ከየት መጣሁ? ለምን ለእኖራለሁ? ለምን እሞታለሁ? ሳልወለድ ነበርኩኝ ወይ? ለምን ተወለድኩኝ? ከሞት በኋላ እኖራለሁኝ ወይ? ፍጥረት ሁሉ ትርጉም አለው ወይ? ወይስ ከንቱነትን የግድ ትርጉም ያለው ለማስመሰል የምንፍጨረጨር ኢምንት ጠብታዎች ነን? ከህዋው የትየለሌነትና ምጥቀት አንጻር ስንገመገም ለመታሰብ እንኳ ስፍራ የማይገኝልን ግን ስፍራ ለማግኘት የምንፍዋችር፤ ያለቦታችን የተከሰት አግንኑን ባይ ፍጥረቶች ነን ወይ? ምንድን ነን? የሚሉትና ሌሎችም ጥያቄዎች በየሰው ውስጥ የሚሰጣቸው ትኩረት የተለያየ ቢሆንም ሰው ግን የሚጠይቃቸው ናቸው፡፡ ሰው እነዚህን ጥያቄዎች በአንክሮ ባይጠይቅና መልስ ባይሻላቸውም እንኳ እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቀው መልስ አገኘን ለሚሉ “ጮሌ አሳቢዎች” የ”ልክ ናችሁን” እልልታ አቅልጦ፣ ጥያቄዎቹ እንደተመለሱ አስመስሎ ሊኖር ይችላል ወይም ደግሞ የጥያቄዎቹ መልሶች ሁሉ አላጠግብ ብለውት በቁዘማ ህይወትን ሊጋፈጥ ይችላል ወይም የምን “መፈላሰፍ” ነው ብሎ ራሱን ገስፆ ነፍሱን ጭጭ ካሰኛት በኋላ በ”እንብላ-እንጠጣ” ሂሳብ ነገሮችን ሁሉ አወራርዶ ወደ ምድር ፍፃሜው ሊተም ይችላል፡፡ የእውቀት ፍላጎት ብልጭልጭታው እየጎላ ቢሆንም ከ”መልስ ጠያቂው” ተማሚው መብዛቱ ግን መጠርጠር የለበትም፡፡

የጥያቄዎቹ ስፋትና ጥልቀት ከእያንዳንዱ ሰው “መልስ- መላሽነት” አቅም በላይ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በስሌት ሊቀነባበሩ አለመቻላቸውና እንደ “አንድ ሲደመር አንድ ይሆናል ሁለት” የመሰለ ቅልብጭ ያለ ቀመር የሚቀመጥለት ጉዳይ አለመሆኑ ነው እንቆቅልሹ፡፡ በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መጻህፍት ተፃፉ፤ ስእሎች ተሳሉ፤ ኪነቶች ተከነቱ፤ ነገር ግን “ምላሹ” እንደ ሂሳብ ቀመር ቁጭ ቅልብጭ አለማለቱ አነታረከ፡፡ ምክንያትና አመክንዮ በእነዚህ ጥያቄዎች ፊት እንደ ቁንጫ ትንንሽ ሆኑ፡፡ ሳይንስ ሚጢጢዬ የጥቢ ጥቢ ኳስ አክላ ቀሸረረች፡፡ እናም ጥያቄው የሁሉ “መልሱ” ግን የጥቂቶች እንደሆነ ታሪክ መገባደድ ያዘ፡፡ ለባለ መልሶቹም የመልሱ “ልክነት” የጎራ ምንጭነት ሰበብነቱን ቀጥሏል፡፡

“የተጀመረ ሁሉ ማለቁ አይቀሬ ነው” የምንል እኛ፤ ጥያቄዎቹ በጀማሪው ፈጻሚነት ያለእንከን እንደሚመለሱ እንጠብቃለን፡፡ ሆኖም “ጥበበኛ የት አለ? ፀሃፊስ የት አለ? የዚህች አለም መርማሪስ የት አለ?» ተብሎ መጠየቁ ክፍለ ዘመኑ 21ኛ ቢባልም እንኳ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥያቄዎቹ ዛሬም አሉና ጠያቂዎቹና መላሾቹ ግን በታሪክ ጅረት ውስጥ ከመፍሰስ ያለፈ ተጽእኖ በጥያቄዎቹ ላይ ከመፍጠራቸው በፊት በጊዜ ክንድ ተደቁሰው በነዋል፡፡ ሞት እስካልተሸነፈ ድረስ ከሰው የሚሰነዘረው መልስ ሁል ጊዜ … ”የት አለ?”ን ማስጠየቁ አስደማሚ ሊሆን አይችልም፡፡

የአዳም ዘር ሁሉ ትክክለኛውን መልስ የሚጨብጥበት የምንጠብቀው “ጊዜ አልባ” ህይወት የሌለ ከሆነማ በእርግጥ ከመፈጠር አለመፈጠር ባማረብን ነበር፡፡

እንግዲህ የጥያቄዎቹ አለመመለስ ነው እምነትን ወደ ህይወት ገበታ የሚጋብዘው፡፡ መልስ ካልተገኘ  የእያንዳንዱን ጥያቄ መልስ የያዘውን ህላዌ በ”ባለ መልሱ” መንገድ መፈለግ ግድ ይላላ ፡፡ “የዚህችን አለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አደረገ” የተባለለት ራሱ መጥቶ “እኔ ነኝ” (I AM) ካላለ በቀር የዘመናቱ ጥያቄዎች ጥያቄነት አያበቃም፡፡ የጥያቄዎቹ መልስ በ”ባለ መልሱ” አስተማሪነት  ይገኛል፡፡ ትምህርት ደግሞ ያለ አስተማሪ በጭፍን መባዘንን ያስከትላል፤ ለዚህም ነው “ረቢ ሆይ ወዴት ትኖራለህ?” መባሉ፡፡ የሁሉም ጥያቄዎች መልስ ባለቤት የሆነውን መምህር ማግኘት አዋጭ መንገድ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ያ መንገድ የእምነት ጎዳና ነው፡፡ “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ጸንተው ይኖራሉ” ተብሏል ነገር ግን በዛሬው አግባብ በእምነት የሚገኘው የጥያቄዎቹ መልስ የመመለሳቸው ተስፋ ይሆናል፡፡

እንግዲህ የሁሉም ነገር መልስነት የሆነው ያ “ህላዌ” በእምነት ካልሆነ በቀር ላለመገኘት መወሰኑ እንቆቅልሽነት ቢከጅለውም ሃቁ ግን እሱ ሆነ፡፡ እሱን ማወቅ የጥያቄዎቹ ሁሉ መልስ መጀመሪያ ነው፡፡ የእኔን እሳቤ እና እምነት ለሌሎች አብራርቼ ራሴን ለሰዎች መግለጥ የ”እኔ ጉዳይ”ነቱ ምንም አይገርምም፡፡ ልክ እንዲሁ የሁሉም ጥያቄዎች መልስ ያለው ህላዌ እሱ ራሱን ካልገለጠ በቀር ሰብአዊው ፍጥረት “አሰላሳይ” ከሆነ በጥያቄዎቹ እንደተወጠረና እንደተወራጨ “ሃሳበ-ቢስ” ከሆነ ደግሞ ያገኘውን አይነት ኑሮ ኖሮ እንደ “ከብት” በመሰለ ህይወት የምድር ኑሮውን ይቋጫል፡፡

ነገር ግን በመጠበብ አባዜም የምትትከነከን ነፍስ ትሁን በደነዘዘ ስብእና የሚክለፈለፈው ጥቁሩን ነጩንም ሃይማኖተኛውን ከሃዲውን፣ ጠርጣሪውንና ወዘተውንም እኩል የምታደርግ አንድ መውጫ አለች - እሷም እምነት ትባላለች፡ የእምነት ምስጢሯ ተስፋዋ ነው፤ ፍጻሜዋ ደግሞ ፍቅሯ፡፡ በነገራችን ላይ በፍቅር የማይጠናቀቅ እምነት ተስማምቶ ማበድ ይባላል፡፡ የእምነት መስፈሪያው ፍቅር ነውና፡፡

እምነትን “አላምንም” ብሎ ልቡን ለከረቸመ ማብራራት እጅግ አዳጋች ቢመስልም እንኳ አምኖ መገኘት ግን ሰው ቅድሚያ ግምት ሊሰጠው ወደ ማይችለው የህይወት ከፍታ ውስጥ የሚወነጨፍበት ቅፅበታዊ ሂደት ነው፡፡ ልክ ከእናትና አባቴ ባልወለድ ኖሮ ዛሬ ይህን የምፅፈውን እንደማልችል ሁሉ ባላምን ኖሮ የእርግጠኝነትን መወለድ ከየትም ባላመጣሁት ነበር፡፡ በእምነት የተብራራልኝ ያ ነገር የእምነት ልምምዴ ነው፡፡ የእምነት ልምምዶሽ ሲደጋገምና ወደዚያ ልምምድ ብዙዎች ሲመጡ፣ ያ ልምምድ ሃይማኖት ተብሎ ስም ሊወጣለት ይችል ይሆናል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የመንፈሳዊውና የተጨባጫዊው ሃቅ ፍትጊያ፡፡ እነዚህ ሁለቱም በተመሳሳይ ሰዓትና ጊዜ እውነት ሊሆኑ አይችሉም፤ አንዱ ከውጭ ነው ሌላው ከውስጥ ነው፡፡ አንዱ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚፈነዳ ነው፤ ሌላው ከውጭ ወደ ውስጥ የሚሸማቀቅ ነው፡፡ አንዱ በመልስ ይኖራል፤ ሌላው ከጥንት እስከዛሬ ይጠይቃል፡፡

እንዲያም ተባለ እንዲህ የምድር ህይወት መልስ ሆኖ ራሱን በሚገልጠው ታላቅ ህላዌ መሪነት ስትመራ ሰው አመነ ይባላል፡፡ እሱ ነው መንፈሳዊነት፡፡ ይህ ምክንያትን ብቻ ሳይሆን ህይወትን የመረዳት ከፍታና አቅም ነው፡፡ ለእኔ ህይወትን ጣፋጭም መራራም የሚያደርጋት ከምክንያት ያለፈ ምስጢር መቋጠሯ ነው፡፡ የእነዚያ ሁሉ ጥያቄዎች ጋጋታ መልሱ ምስጢር የሆነው ህላዌ ራሱ ይሆናል፡፡ እንግዲህ የህይወት ምስጢርና ትርጉም የተቋጠረው እምነት በሚባል ቅኔ ውስጥ የሚሆንበትም ምህኛት ይሄ ነው፡፡ ታዲያ ይሄን በቃላት ለማብራራት መጭነቁ ምን ይደንቃል፡፡ ምክንያቱም ስለእርሱ እንመሰክራለን እንጂ እሱነቱን የሚያብራራውን እምነትን ለሌላው ማመን አንችልም፡፡ ጥያቄው ተመለሰም አልተመለሰ ሊታወቅ የሚገባውን ህላዌ በእምነት በኩል ባወቁትና ባላወቁት መካከል የመለያየት ሰበብ ሆኗል፡፡ እርግጥ የሆነው ነገር ግን እምነት ለሰው ዘር ሁሉ “ሊደረስበት የሚችል” ተደርጎ መቀመሩ ነው፡፡ እምነት ዋጋ የተከፈለበት ወደ ሌላ አውታር የመግቢያ ትኬት ነው፡፡ ጥያቄ ሳይሆን መልስ ብቻ ያለበት አውታር፡፡

ሆኖም ሰዎች “እንዴት እንመን?” ብለው ቢጠይቁ ወሳኝ ጥያቄ መጠየቃቸው እሙን ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ ማቅረብ ባይቻልም ማመን እኔ በህይወቴ እንደተለማመድኩት  የማሰላሰል ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳ ውሳኔና እምነት በጣም የተቆራኙ ጉዳዮች ቢሆኑም ውሳኔ የምክንያታዊነት ቅንጣቢ አለው፤ እምነት ግን የመንፈስ እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ እምነት በሰው ውስጥ እንዲፈጠር የሁሉም ነገር ምክንያት የሆነው እግዚአብሄር በአማኙ ህይወት የሚሰራው ተአምራዊ ነገር ይኖራል፡፡ ያ ተአምራዊ የሆነ ነገር እንዲፈፀምና የሰው ፈቃደኝነትና ነፃ መራጭነቱ ይረጋገጥ ዘንድ “መስማት” የእምነት በር ተደረገ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር እምነት በሰው ውስጥ ይፈጠር ዘንድ እምነትን የሚያስተላልፉ ተናጋሪዎችን ይጠቀማል፡፡ ከዚህም የተነሳ እምነት በመስማት ሆነ “ካልሰ እንዴት ያምናሉ?” መባሉም ለዛ ነው፡፡ ማንን መስማት? በትክክል ያመኑትን መስማት፣ እምነትን በሰው ውስጥ ይፈጥራል፡፡ በነገራችን ላይ እምነት የጥበበኝነት ጉዳይ አይደለም፡፡ እምነት የመሸነፍ ጉዳይ ነው፡፡ “በማን የመሸነፍ” የተባለ እንደሆነ የሁሉም ነገር መልስ በሆነው በእግዚአብሄር መሸነፍ ነው፡፡ ስለዚህ እምነት በሁሉም ፍጥረት ላይ የፈጠራ መብት ያለውን እሱን መገናኘት እስካልሆነ ድረስ የእምነትነት ሙላት ይጎለዋል፡፡ መሰማት ያለበትን ችላ ብሎ እንከን እንዳይገኝበት ዙሪያ ገባውን እያማተረ ውልብ ውልብ በምትል ትንታኔ የሚብጠለጠል ስብእና እምነትን ውጤቱ ሊያደርግ አይችልም፡፡ እምነት በመቀበል ይጀምራል እንጂ በመስጠት አይደለም፡፡ “በተነ ለምስኪኖች ሰጠ” መባሉ ከእርሱ ያልተቀበለ ሁሉ ለመመስከኑ ማረጋገጫ ነው፡፡

የብዙ እምነት አልባውያን እምነተ ቢስነት መሰረት ሁሉን የፈጠረ፣ የሁሉም ነገር ምንጭ አለመኖሩን አለማመን ሳይሆን “ኖሮ ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ ውጥንቅጥና ፍርደ ገምድልነት፤ ልክ የለሽ አበሳና ጭንቅ፤ ግፍና አድልዎ” ወዘተ የመሳሰሉትን ሃቆች የፈጣሪ አለመኖር ምልክት አድርገው መደምደማቸው ነው፡፡ ማንም ቢሆን አንድ ታላቅና ሁሉ በሁሉ የሆነ ጉልበታም ፈጣሪን ሳያምን በፊት፣ ፈጣሪው በፍጥረቱ ውስጥ እየሆነ ስላለው እንቅስቃሴ ያለውን ሃሳብና ፍርድ መረዳት አይችልም፡ የክፋትና በጎነት ትንቅንቅና ፍትጊያ መኖሩ ሁሉን ቻይ አምላክ «አለ? የለም? ወደሚል ጥያቄ ሰውን ሊገፈትረው እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ ቢሆንም ግን የዚህች ኢምንት ፕላኔት ነገረ ጉዳይ፣ የነገረ ጉዳዩ ምንጭ የሆነው የሰው ዘር በፈለገው አይነት የፍልስፍና፣ የምርምርና የምትሃት ናዳ ሊያዳፍናት ቢጥርም “አምላክ አለ” የምትለዋ ረቂቅ ድምጽ ከእያንዳንዱ የምክንያት ማዕበል መረጋጋት በኋላ፣ በየሰው ልብ በለሆሳስ መሰማቷ አይቀሬ ነው፡፡ የዚህች ድምፅ መጉላትና መመንመን እለት እለት በምንመገበው የእውቀት አይነት ላይ  የተመሰረተ ቢሆንም ድምጺቱ ግን በሰብአዊነት ጥልቀት ውስጥ ተሰንቅራ መሹለኩለኳ ግድ ነው፡ የጥያቄዎቹ መመንጨት ምክንያት “ያለ እና የሚኖረው” አለ የምትለው ያች ድምጽ፤ እራሷ ናት፡፡ ዘመን ሲጠቃለል ደግሞ እንደ ፍርድ መዝገብ የምታገለግል ወሳኝ ማመሳከሪያ መሆኗ አይቀሬ ነው፡ የድምጺቱ ማጉያዎች ደግሞ ያልተበጠበጠ ህሊናና ያልተንጋደደ ህውሰት ናቸው፡፡ለዚህ ነው “አናምንም” “እሱ የለም” የሚሉ ሰብዓዊ ፍጥረታት ከሃዲያን የሚባሉት፡፡ የካዱት ለእምነት የምትጋብዘውን “አለ” ብላ የምታውጀው በሁሉም ሰዎች ውስጥ በስራ ላይ የምትገኘውን ድምጺቱን ጭምር እንጂ እግዚአብሄርን ራሱን ብቻ አይደለም፡፡

ክህደትን አውግዘው ወደ ቅድመ ማንነታቸው የተመለሱ የብዙ ከሃዲያን ምስክርነት የሚያስረዳው ይህንን ነው፡፡ በትልቁ መካድ ትንፋሽ በሚያሳጣና በአደንቋሪ የክህደት ዳንኪራ ውስጥ ያለማቋረጥ ማረጥረጥን ይጠይቃል፤ ምክንያቱም የክህደት ውዝዋዜው ነፍስን ዝም ሊያሰኛት የሚችለው የመንፈስን ድምፅ  በእልፍ አእላፋት አሼሼ ገዳሜ ካዋከባት ብቻ ነው፡፡ ከክህደት የተመለሰ አንድ ሰው «As I challenged those who believe in God, I was deeply curious to see if they could convince me otherwise. Part of my quest was to become free from the question of God.» ማለቱ ጥሩ ማጣቀሻ ነው፡፡ ”በእግዚአብሄር የሚያምኑትን በምፈታተናቸው ጊዜ የውስጥ ጉጉቴ በተቃራኒው ያሳምኑኝ እንደሆን ማየት ነው፡ ግማሽ ጥማቴ ስለ እግዚአብሄር ከመጠየቅ መገላገል ነበር” ማለቱ መሰለኝ፡፡  የአብዛኞቹ ጥማት ይሄ ነው “ከጥያቄዎቹና ከእግዚአብሔር መገላገል”፡፡ እንግዲህ ለእነ”እንዴት እንመን?” እንዲህ እላለሁ፡ እኔን ያሳመነበት አካሄድ ምንአልባት ለሌላው የማያዋጣ ሊሆን ቢችል አይደንቅም፤ ምክንያቱም ልዩ ልዩ ነንና፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ  በውስጡ ዘወትር የምታነበንበው ወደ እምነት የምትጣራ “ተአምራታዊ” ድምፅ “ድምጺቱን” በተለያዩ ስነ አእምሮአዊና ስነ ሰብዓዊ ተልኮስኳሽ ማፈኛዎች እያፈነ በእምነት የመዳንን እድል ማሽቀንጠሩ አዋጭ አለመሆኑን በማወጅ የጊዜ ሁሉ ጌታ ጊዜያችንን ይባርክልን እያልኩኝ አንድ ሃይለ ቃል መዝዤ የዛሬን  ልጨርስ፡ “እምነት በመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል”፡፡

 

 

Read 3551 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 07:23