Print this page
Tuesday, 30 June 2020 00:00

የበሽታውን መድኃኒት፣ ከበሽታው ማግኘት!?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማስገበር በተነሱ ጊዜ ሶስት ዋናዋና ነገሮችን ጐን ለጐን አጠንክረው በማካሄድ ላይ ነበሩ:: አንደኛው በሀገራቸው የሠሩት ነው:: እንደ ሚኒሽርና አልቤን ያሉ ጠብመንጃዎች ውጤታማ እንዲሆኑ፣ የተኩስ ርቀታቸውና ጥራታቸው እንዲሻሻል አድርገዋል፡፡ በቢሊየን የሚቆጠር ጥይት፣ በብዙ መቶ ሺህ ቶን የሚገመት ልዩ ልዩ ቦምብና የመርዝ ጋዝ፣ የጦር አይሮፕላን፣ መድፍና ታንክ እንዲሁም ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችም በገፍ አምርተዋል፡፡
ሁለተኛው፤ በአፄ ዮሐንስ ዘመን የተጀመረውን የራዛ ዘመቻ ተጠቅመው ያደረጉት ጥናት ነው፡፡ ደገኛው፤ የአፋር አካባቢ ለምሳሌ ዋጅራትና ራያ፣ ወደ አፋር እየወረደ ከብት ይዘርፋል፤ ሰው ይገድላል፡፡ ሰለባም ያካሂዳል፡፡ ይህን ባህል የተገነዘበው በአስመራ አገረ ገዥ የነበረው ካራ ዞሊ አንድ ጥናት ማድረግ ጀመረ፡፡
በአፋርና በአካባቢው ሕዝብ መካከል ተከታታይ ግጭት እየተካሄደ መሆኑን በማውራትና በማስወራት እራሱን የአፋር ሕዝብ ተቆርቋሪ አድርጐ አቀረበ፡፡ አልፎ አልፎ እውነት ባይታጣባቸውም፣ በነዚህ ወሬዎች የተደናገጠው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በየአካባቢው ጦር እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ችግሩን ለመቆጣጠር ሞከረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማስገበር ብትነሳ እስከ አምስት መቶ ሺህ ጦር እንደሚያስፈልጋት ኮራ ዞሊ መገንዘቡን  ዶ/ር ተወልደ ተኩ፤ "የኢትዮጵያ አንድነትና ኢጣሊያ" በተባለው መጽሐፋቸው ጠቁመዋል፡፡  
ሶስተኛው፤በኢትዮጵያ ውስጥ የሠሩት የፕሮፓጋንዳና የፖለቲካ ሥራ ነው፡፡ በጅማ፣ በሶዶና ሀገረ ሰላም፣ በነቀምት፣ ጐሬ፣ ነገሌ፣ ጐባ፣ ጋርዱላ፣ ባካና እንዲሁም በደንቢ ዶሎና በሌሎችም የፕሮፓጋንዳ ጣቢያ አቋቁመው እንደ ጐንደርና ጅማ ባሉ ከተሞች የቆንስላ ቢሮ ከፍተው፣ ከሞላ ጐደል ሁሉም በኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኙ ብሔረሰቦች፣ በአማራው ላይ እንዲነሱ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በአማራው ላይ የተከፈተውን ዘመቻ እንደ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ አባት አባዲዩ አይነት ሰዎች፣ ጥቁርና ነጭ ጤፍ ደባልቀው እስቲ ለዩ በማለት እንዲከሸፍ አድርገዋል፡፡ "እምነትህ ተጨቁኗል" በሚል ዘዴ ሙስሊሙን በክርስቲያን ወንድሙ ላይ እንዲዘምት ያደረጉት ጥረትም የጠበቁትን ያህል ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘርና በሃይማኖት ሳይለያይ ባደረገው ትግል፤ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነፃነቱን መልሶ ለማስጠበቅና  ለማስከበር ችሏል፡፡ ለጣሊያን ቅኝ አገዛዝ በመሣሪያነት እንዲያገለግል የተፈለገው የዘር ልዩነት፤ ራሳቸውን በነጭነትና በወራሪነት እንዲፈረጁ ያደረጉ ሲሆን ሌላውን ወደ አንድነት በማምጣት ጣሊያኖችን ለማባረር ማገልገሉን ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ በአንድ መጽሐፋቸው ላይ  መግለጻቸውን አስታውሳለሁ፡፡
በ1960ዎቹ “ኢትዮጵያ የማናት፤ ማነው ኢትዮጵያዊ?” የሚሉ ጥያቄዎች በተማረው ትውልድ መካከል ይነሳና ይወድቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚያን ጊዜ ሰው ሲጠየቅ "ጐንደሬ ነኝ፣ አሩሲ ነኝ፣ ጅማ ነኝ መንዜ ነኝ፣ ተጉለቴ ነኝ" ወዘተ እያለ ይመልስ ስለነበር፣ ኢትዮጵያ እንዴት ያለ ባለቤት ትቅር የሚል ጥያቄ ቀስቅሶ  ነበር፡፡ ጐንደሬውም አርሲውም መንዜው ወዘተ-- ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም፣ በተጠየቁ ጊዜ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” አለማለታቸው አገሪቱን ባለቤት እንደሌላት አድርጐ ያስገመተ ኹነት ነበር፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ጥያቄዎች የተቀነቀነው ሃሳብ፤ አንዳንድ ጊዜ አንዱን ወገን ዜግነት ሰጭ ሌላውን ወገን ተቀባይ ሲያደርገውም ታይቷል፡፡ በተለይ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ እንዳባባሰው የማምነው፣ "የአስተዳደር በደል ደረሰብን" ብለው የአመጽ እንቅስቃሴ የጀመሩ ወገኖች በድርጅቶቻቸው ስም ላይ ያከሉት “ነፃ አውጪ” የሚል ቃል መኖር ነው፡፡ ይህን ነፃ አውጭነትና ነፃ ወጪነት መንፈስ፣ የደርግ መንግሥትን በመሣሪያ ትግል አሸንፎ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣንን የያዘው ሕወሓት/ኢሕአዴግ፤ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት ውስጥ አንቀጽ ይዞ እንዲቆም አደረገው:: ሕገ መንግሥቱ አንድነትን በሚፈልገውና በብሔርተኝነት መንፈስ መመራት በሚፈልገው መካከል የክርክር አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በዘመነ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በነበረው የፌደራል መንግሥቱ፤ አባል ክልሎች ከትግራይ በስተቀር አንዳቸውም እንደተባለው ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ እንዳልነበረ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ቃል በቃል የተናገሩት አስተዳደራቸው “የሞግዚት አስተዳደር” እንደነበረ ነው፡፡ የሞግዚት አስተዳደሩ ፈረሰ፤ የክልሉ ሕዝብ ራሱን በራሱ እየመራ ነው በተባለበት ጊዜ፤ በተለይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ የክልልነት ጥያቄ ከየአቅጣጫው እየተነሳ ይገኛል:: በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ሃምሳ ስድስት ብሔረሰቦች ውስጥ አስራ አንዱ የክልልነት ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ከእነሱ አንዱ የሲዳማ ብሔረሰብ፣ የሕዝብ ድምፀ ውሳኔ  አካሂዶ የራሱን ክልል ለመመሥረት በቅቷል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጁ ይመስላሉ፡፡ ከሰሞኑ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት፣ አባል የነበሩ የወላይታ ተወላጆች፣ በራሳቸው ፈቃድ ምክር ቤቱን ለቀው ወጥተዋል፡፡
የዞኑ አመራር፣ የደቡብ ምክር ቤት የሚያሳልፈው ውሳኔ አይመለከተኝም የሚል መግለጫም ማውጣቱን ከማኅበራዊ ሚዲያዎች መመልከት ይቻላል፡፡ የክልሉ መንግሥት ያደረገው ጥናትና ማዕከላዊ መንግሥት እንደያዘው የሚነገርለት መንገድ የታሰበውን ውጤት የሚያመጡ መስለው አልታዩኝም፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ለእኔ እየገነነ ወይም እየጠነከረ የመጣው ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ በየራስ መቆም ነው ማለት እችላለሁ:: ይህ በየራስ የመቆም ፍላጐት በአንፃሩ እንደሚያስፈልግ የሚታመንበትን አንድ አገር አጽንቶ የማቆየት ጉዳይ ለአደጋ እንዳያጋልጠው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አንድ ኢትዮጵያ ሲባል የተወሰነ አካባቢ ፍላጐት አድርገው የሚያዩ ወገኖች፤ ከጥላቻና ከጥርጣሬ ወጥተው፣ ነገሩን በሙሉ ይዘቱ መመዘን ይኖርባቸዋል፡፡
በአንፃሩ በየጊዜው የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን፣ አገርን የማፍረስ ተግባር አድርገው የሚቆጥሩ ወገኖችም እንዲሁ ሁኔታውን በረጋ መንፈስ ሊመለከቱት ይገባል፡፡ ከእርሱ ይልቅ በክልልም ሆነ በፌዴራል የመንግሥት ሥልጣን የያዙትና ከሞላ ጐደል ኢኮኖሚውንና ማኅበራዊ ሁኔታውን እየተቆጣጠሩ ያሉት ተቀናቃኞቹ (ብሔርተኞች) መሆናቸውን ስለ አንድነት የሚቆረቆረው አካል መገንዘብ ይኖርበታል፡፡
በመጨረሻም  ማለት የምፈልገው፤ ነገ ኢትዮጵያ በአገርነት እንድትቀጥል የምንሻ ከሆነ፣ የችግሯ መፍትሄ መገኘት ያለበት ከሌላ ሳይሆን ከራሱ ከበሽታዋ ነው - ከብሔርተኝነትና ከኅብረ ብሔራዊነት፡፡

Read 22328 times