Saturday, 27 June 2020 13:14

‹‹…መልካም ስራ ለክፉ ቀን ስንቅ ነው…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  ለዚህ እትም ርእስነት የተጠቀምነውን አባባል ያገኘነው  ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር…መግቢያ በር ላይ ከተሰቀለው መግለጫ ነው፡፡    
የኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ገና አድማሱን እያሰፋ ነው ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን በየ24 ሰአቱ ከሚገኘው የምርመራ ውጤት መረዳት ይቻላል፡፡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን እድሜ ስንመለከትም በወራት እድሜ ካሉ ህጻናት ጀምሮ እድሜ የጠገቡ አረጋውያን ድረስ ያሉ ሰዎችን ሳይመርጥ እንደሚያጠቃልል ከመረጃዎች እንረዳለን፡፡ ይህ አምድ የሚያተኩረው በስነተዋልዶ ጤና ላይ እንደመሆኑ ማንም ከማንም ሳይለይ እናቶ ችንና አባቶችን እንዲሁም የሚወልዱ ዋቸውን ጨቅላዎች እና መላ ቤተሰባቸውን ሲሆን እራስን ከቫይረሱ ለመከላል መፍትሔው ከጤና ባለሙያዎች በሚመከረው መሰረት ጥንቃቄ ማድረግ ቁልፍ ተግባር ነው፡፡
እጅን በሳሙና በደንብ አድርጎ ለ20 ሴኮንድ መታጠብ
ቁልፍ…የበር መዝጊያ እጀታ…ሊፍት…የመኪና በር …ወዘተ የመሳሰሉትን ከመንካት በፊት ቢቻል በአልኮሆል መጠራረግ…ካልተቻለም የነኩበትን እጅ በአልኮሆል ወይንም በሳኒታይዘር መጠራረግ…
ከሰዎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት እርቀትን መጠበቅ
ከሰዎች ጋር አለመጨባበጥ…አለመተቃቀፍ…በርቀት ሰላምታ መለዋወጥ
አፍንጫንና አፍን መሸፈን….ወዘተ የመሳሰሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ ተገቢ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
COVID - 19 ን መከላከል ማለት ሌሎች ሰዎችን ከቫይረሱ ከማዳን በላይ የእራስንም ሕይወት ከህልፈት መከላከል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የሚወዱዋቸውን የቤተሰብ አባላት…ልጅ…የት ዳር ጉዋደኛ…እናትና አባትን ጨምሮ ከምንም በላይ የሚወዱትን የእራስን ህይወት መጠበቅ በመሆኑም በጭራሽ ችላ ሊባል የማይገባው ቅስፈት መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባ ይ አምድ በድጋሚ ያስገነዝባል፡፡ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር በተለይም እናቶች እራሳቸውንና ልጆቻቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም እርጉዝ ሴቶች በተቻለ መጠን እራሳቸ ውን ከቫይረሱ እንዲከላከሉ ባለማሰለስ ማሳሰብ ይወዳል፡፡  
ባለፈው እትም ለንባብ ያልነው የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር በተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰብን በተለያዩ መንገዶች በመርዳት ላይ ላሉ ድርጅቶች የፊት መሸፈኛ ጭንብል ማለትም የFace Mask ድጋፍ ማድረጉን ገልጸን ድጋፍ ከተደረገባቸው ቦታዎች አንዱን የማዘር ቴሬዛን ሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ ያለውን ተግባር አስነብበናችሁ ነበር፡፡ ድጋፍ ከተደረገላቸው ተቋማት ውስጥ ፤ጎጆ የህሙማን ማረፊያ፤ የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር ይገኙበታል፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ በወቅቱ ከተናገሩት ውስጥ ‹‹… ብዙ ጊዜ የፊት መሸፈኛ በቀጥታ የህክምና ተቋማቱ ብቻ እንደሚያስፈልጋቸው አድርጎ ማሰብ ይኖራል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ህብረተሰቡን የሚያግዙ ወይንም እርዳታ የሚያደርጉ ድርጅቶችም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ስለሚያምን  የሙያ አጋሮችን በማስተባበር ከቻይና ማስመጣት የቻለውን የFace Mask እገዛ ማድረግ ችሎአል…›› የሚል ይገኝበታል፡፡
ዶ/ር ቤተልሄም ይስሀቅ እንደገለጹት ጎጆ የህሙማን ማረፊያ እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2007ዓ/ም የተመሰረተ የአገር ውስጥ የእርዳታ ድርጅት ነው፡፡ ጎጆ የህሙማን ማረፊያ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለሕክምና መጥተው ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ላሉ ሕሙ ማን ማረፊያ እና የምግብ አገልግሎትን እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያዎችን የሚሰጥ ሲሆን ሕክምናቸውን ጨርሰው ወደመ ጡበት ሲመለሱም የመጉዋጉዋዣ አገልግሎት የሚያደርግ ነው:: በህሙማን መረፊያው ቆይታ የሚያደርጉ ታካሚዎች ህመማቸው የተለያየ ሲሆን በተለይም ቶሎ መልስ የማያገኙና ክትትል ማድ ረግ የሚገባቸው የካንሰር ሕመም ታካሚዎች ይበልጥ ይገኙበታል፡፡ በእርግጥ ሌሎችም የረጅም ጊዜ ቀጠሮ የሚሰጥባቸው ህመሞች ያሉባ ቸውን ህሙማንም ማእከሉ የሚቀበል ሲሆን ከአስራ ሁለቱ የሪፈራል ሆስፒታሎችና በተለይም ከጥቁር አንበሳና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች ህሙማንን በመቀበል እንዲያርፉ ያደርጋል፡፡ የህሙማን ማረፊያው ሀምሳ ሁለት አልጋዎች ያሉት ነው፡፡  አንድ ታካሚ በጎጆ የህሙማን ማረፊያ እስከ ሁለት ሳምንት መቆየት የሚችል ሲሆን ከዚያ በላይ ቆይታ ማድረግ ካለበት ከሚመለከተው ክፍል መቆያውን በማራዘም የህክምናው ቀጠሮ እስኪደርስ ማረፍ ይችላል፡፡  ዶ/ር ቤተልሄም ይስሀቅ የጎጆ የህሙማን ማረፊያ ምክትል ፕሬዝዳንትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰርጀሪ ዲፓርትመንት ሌክቸረር ናቸው፡፡
የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር የFace Mask ድጋፍ ካደረገላቸው ድርጅቶች መካከል የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር ይገኝበታል፡፡
የማህበሩ መስራች አቶ ስንታየሁ አበጀ በስነስርአቱ ላይ የሚከተለውን ነበር የተናገሩት፡፡
‹‹…ቅንነት ከሌለ ሁሉም ነገር ባዶ ነው፡፡ ቅንነትን የመሰለ ሀብት የለም፡፡ ሀብት ቢኖር ወይንም ምንም ያህል ትምህርት ወይንም እውቀት ቢኖር ሰዎች በአንድ አጋጣሚ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ ሰዎች በጤንነታቸው ወቅት በርካታ እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ የነበሩና ብዙ ተከታይ የነበራቸው ቢሆኑም ቀን ሲያልፍ ወይንም በጤና መጉዋደል ሲወድቁ ግን የነበረው ክብርና ዝና አብሮ እንደሚወድቅ አስቀድሞ ማወቅ ይገባል፡፡ …እኔ ስንታየሁ የዚህ የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር መስራች በአንድ ወቅት በህመም ወድቄ …ጀርባዬ ተልጦ…. ቆስዬ… እራሴን መርዳት አቅቶች በወደቅሁበት አይጥ እስኪበላኝ ደርሼ ነበር፡፡ በጊዜው ለእራሴ ያነሳሁት ጥያቄ ነበረኝ:: ከወደቅሁበት እንደዚያ ተልቼ ውሀ እንኩዋን የሚያጠ ጣኝ እስካጣ ስደርስ …የሰው ልጅ ማለት እንደዚህ ያለ ነው እንዴ…. ለካስ እስክንወድቅ ድረስ ነው እንጂ ከወደቅን መላም የለንም ከሚል መደምደሚያ ደረስኩ:: ስለዚህም እራሴን ምሳሌ አድርጌ ተነሳሁ… በዚህን ጊዜ ወደ ፈጣሪዬ ልመናዬን ማቅረብ ብቻ ነበር የነበረኝ አማራጭ፡፡ ….እባክህን ፈጣሪዬ ….እኔ እንደሆንኩት… ልክ እንደእኔ… ወድቀው፤ ሰውነታቸው ሁሉ ተላልጦ፤ ሰውነ ታቸው ተልቶ፤ አይጥ የሚጎታቸውን፤ ጠያቂ ያጡትን ሰዎች …አቅም ኖሮኝ እንድጠይቅ…ባዶ ቤት ተዘግቶባቸው…ውሀ የሚያጠጣቸው አጥተው …ደርቀው የሚሞቱትን እንድረዳ… እንዳስ ታምም…ከወደቁበት እንዳነሳ የተወሰኑ ቀናትን እድሜ ስጠኝ….ከበሽታዬም ምህረቱን እንዳገኝ እርዳኝ ብዬ ለመንኩት…እሱም ሰምቶኛል…›› ብለዋል፡፡
አቶ ስንታየሁ አበጀ ከህመማቸው ከተፈወሱ በሁዋላ የወደቁትን ለማንሳት የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ጀመሩ፡፡ እርዳታ ፈልገው ወደሳቸው ከመጡት ውስጥ የአንዲት ሴት ታሪክን አይረሱም፡፡
‹‹…ጥሩ ሀብት የነበራቸው የራስ ማእረግ የነበራቸው ሰው ልጅ ናት፡፡ ቤተሰብዋም በስልጣንና በሀብት የከበሩ ነበሩ፡፡ ወደ የወደቁትን አንሱ መርጃ ማህበር ግን የመጣችው በሚገፋ ወንበር እየተገፋች ማረፊያና መታከሚያ የሚሆን እርዳታ ፈልጋ ነበር፡፡ ያ ሁሉ የቤተሰብ ሀብት ምን ሆኖ ወደ እርዳታ ድርጅት እንደመጣች ብጠይቃት…..‹‹በእርግጥ ሀብታሞች ነበርን፡፡ አሁን ግን ምም የለንም፡፡ ስለዚህ እርዳታህን ፈልጌ መጥቻለሁ…›› የሚል ነበር መልስዋ…መንገድ ላይ የሚወድቁት ደሆች ብቻ አይደሉም፡፡ ቀን ሲያዘነብል ለሁሉም ሰው ፈተና ይናል፡፡ ስለዚህ እኔም ለፈጣሪ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም በመብቃቴ እድለኛ ነኝ:: ብለዋል አቶ ስንታየሁ፡፡
ወ/ሮ አይናለም ኃይሌ የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ እንደገለጹት ማህበሩ ከተመሰረተ ወደ ሀያ ሶስት አመት ሆኖታል፡፡ ማእከሉ የአረጋውያን መጦሪያና ክሊኒክ ነው፡፡ በማእከሉ ሁለት መቶ የሚሆኑ አረጋውያን አልጋ ይዘው ሙሉ በሙሉ የሚጦሩ ሲሆን አንድ መቶ የሚሆኑት ደግሞ በውጭ ሆነው እየተመላለሱ ይገለገላሉ፡፡ ማህበሩ ስራውን የሚሰራው እርዳታ በሚያደርጉ ሰዎች እና በሙያቸው በክሊኒኩ ድጋፍ በሚያደርጉ የህክምና ባለሙያዎች አማካኝነት ነው:: ማህበሩ ተረጂዎቹን የሚያገኘው  ከሆስፒታል፤ ከእድር፤ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ወይንም በሰዎች ጥቆማ አማካኝነት መሆኑን ወ/ሮ አይናለም ገልጸዋል፡፡   


Read 27690 times